
በሕዝቦች ተቃውሞና ግፊት ተቀጣጥሎ ተጠቃሽ ውጤቶችን ካመጣው የአገራችን የለውጥ ሂደት ጎን ለጎን ያጋጠሙን መሰናክሎች በርካታ ናቸው። ሁሉም ግን ማረፊያቸውና ማጠንጠኛቸው ህዝብን ማፈናቀል፣ የግለሰቦችን ህይወት ማጥፋትና ሀብትና ንብረት ማውደም ሆነዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ሆን ተብለው በሰለጠኑና በተደራጁ፣ ባንዱ ባይሳካ ቀጣይ ዕቅድ ወጥነው በሚንቀሳቀሱ አካላት የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ጉዳታቸው የከፋ ሆኖ ታይቷል።
የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ብዙ ርቀት የሚቀረውን ያህል በየነጥቡ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችም የዚያኑ ያህል በርካታ በመሆናቸው ወንጀል ሲሰራና ህግ ሲጣስ ማህበረሰቡ መንግስትን ህግ ማስከበር አለብህ በሚል ጫና መፍጠሩ የግድ ነው። አዎን! ሕዝብ ከፈጣሪው በታች ለህልውናው ዋስትና ትልቁን ድርሻ የሚሰጠው ለመንግስት ነው። በተለይ ደግሞ በምርጫውና በይሁንታው ስልጣኑን የያዘ መንግስት ከሆነ ኃላፊነቱ ከፍተኛ ነው። በእኛም አገር በመንግስት ላይ የሚያርፈው ጫና ከዚሁ ስለሚመነጭ ነው።
ይህ በመሆኑም ወቅትንና ሁኔታን ተንተርሰው በተናጠልም ይሁን በቡድን የሚያውኩ አካላት ሲከሰቱ እንዲያስታግሳቸው አቤት የሚባለው ወደ መንግስት ነው። “መንግስት ሆይ በህግ አምላክ ህግ አስከብር” በማለት! የህግ የበላይነት ተሸርሽሮ አጥፊው ወገን በሚፈጽመው ዕኩይ ተግባርና በሚያደርሰው ጉዳት ሳይጠየቅ የዘገየ ወይም የቀረ እንደሆነ ራሱን በአሸናፊነት ስነልቦና አስቀምጦ ለተጨማሪ ጥፋትና ጉዳት ይዘጋጃል።
ሕዝቡ ወይም ማህበረሰቡ በየጊዜውና በየአካባቢው መልኩንና ይዘቱን እየቀየረ በሚደርሰው ጉዳትና ጥፋት ቀዳሚ ተጎጂ በመሆኑ ህይወቱና ተስፋው በስጋት ተወጥሮ ይያዝበትና “መንግስት ባይችል እንጂ…” የሚል ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ ይገባል። ህግን የሚያስከብረው ዋናው ባለጉዳይ መንግስትም በአንድ በኩል ሆደ ሰፊነቱ ፤ በአንድ በኩል በእያንዳንዱ ምስቅልቅል ውስጥ መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው፤ እያንዳንዷን ርምጃውን አንጥረውና ነቅሰው “የከፋው መጣ” እንዳይባል የሚያደርገው ጥንቃቄና ነገሮችን በብልሀት የመያዝ ጥረቱ የየወገኑን ድምዳሜ ያሰጠዋል።
እናም አጥፊው ሀይ ባይ የለኝም ብሎ በተቀያየረ ስልትና ዘዴ ጥፋቱን ይቀጥላል። ሕዝብም ሰለባ ነውና ምሬቱን ከፈጣሪው በታች “ከማንኛውም አደጋ ትታደገኛለህ” ባለው መንግስት ላይ ያሰማል። መንግስትም“ የለም ዝም አላልኩም …” ይላል። አዎን እንደ ህዝብ መንግስት ዝም ማለት የለበትም። ግን እንደመንግስት በርግጥ መንግስት ዝም ብሏልን? ያም ሆነ ይህ ጥቃቱ፣ ግጭቱና በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ጉዳት መቆም፤ በአጠቃላይ ህግ መከበር አለበት። ህግ ማስከበር ደግሞ ቅድሚያ ግጭቱን የማስቆሙ ጉዳይ ይሆንና በየደረጃው ያሉትን የጥፋቱን ተሳታፊዎች ወደህግ ፊት ማቅረብን ይጨምራል።
በመጨረሻም ህግ ፊት አቅርቦ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ ቅጣት ማስጣል የህግ ማስከበር ጥጉ ይሆናል። ጥፋተኞችን በመለየት ተጠያቂ ማድረግ ህዝብ የሚፈልገው፤ መንግስትም የሚጠብቀው ወቅታዊ ሀላፊነት ነው። ለአንድ መንግስት ህልውናና በስልጣን ላይ መቆየት ከምንም በላይ የመረጠው ህዝብ አመኔታና ይሁንታ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። አመኔታና ይሁንታ ደግሞ ሆን ተብሎ አሊያም፤ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር እንዲሸረሸር ቀዳዳ መክፈት ለህዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግስት አይጠበቅም።
በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከዚህ ውጪ አይደለም። መንግስት የህዝብን ይሁንታ ማጣት አይፈልግም። ይልቁንም የበለጠ እንዲጠናከርለትና በሰበብ አስባቡ የተስተጓጎለው ፀጥታ በዘለቄታዊ ሰላም ተተክቶ ሁሉም ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር ፍላጎቱ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በዓይን በሚታይ፤ በጆሮ በሚሰማና በአንደበት በሚቆጠር ተጨባጭ ርምጃ መንግስት ለህግ የበላይነት መቆሙን ማሳየትና ማስመስከር ይገባዋል።
በቅርቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተውጣጣ ቡድን ግጭት በተከሰተባቸውና በተፈናቀሉ ወገኖች ባሉባቸው ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ ከደረሰባቸው ድምዳሜዎች መካከል ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን አካላት እንዲጠየቁ ማድረግ የመንግስት ግዴታ መሆኑን ያመለከተበት አንዱ ነው። እናም አፈናቃዮች ወደ ህግ መቅረብ አለባቸው። በአጠቃላይ የፌዴራል መንግስት የሚያስተዳድረው ህዝብ በእርሱ ላይ ያለው አመኔታ እንዲሸረሸርና አጥፊዎችም ከልካይ የለንም በሚል እሳቤ በጥፋታቸው እንዳይቀጥሉ የተደረሰባቸውንና ዝርዝራቸው በእጁ ላይ ያሉትን አፈናቃዮችና ልዩ ልዩ ጉዳት አድራሾች ህግ ፊት ሊያቀርባቸው፤ ይህንንም ለህዝብ ሊያሳውቅ ይገባዋል።
ህዝቡና የክልል መንግስታትም በተለያዩ ምክንያትና ደረጃ ጥፋት ያጠፉ፤ትዕዛዝ የሰጡ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ አድርገው በአገርና በህዝብ ላይ ጉዳት ያደረሱ፤ እንዲሁም እንዲደርስ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባቸዋል። ሁሉም አጥፊዎች የመጡት ከማህበረሰቡ ነውና የሚደበቁትም በማህበረሰቡ ውስጥ በመሆኑ ለይቶ በማውጣትና ለህግ በማቅረብ ቀዳሚ መሆን ይኖርበታል።
የህግ የበላይነትን ለማስከበርና መንግስት እንደ መንግስት ለመቀጠል የእስካሁኑ አካሄድ አላዋጣም። አያዋጣምም። የህዝብን በሰላም ወጥቶ መግባት በአስተማማኝነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ርምጃ መውሰድ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ኃላፊነት ያለባቸው የፀጥታ ተቋማት ተቋማዊ ተልዕኳቸውንና መንግስታዊም ሆነ ህዝባዊ አደራቸውን ያለአድልኦ በማከናወን የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነታቸውን በመወጣት ዜጎች ያለስጋት የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011