ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ከጦርነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከ‹‹አጎዋ›› (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና የኢንቨስትመንት ዘርፉን ከፈተኑት ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
‹‹አጎዋ›› አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የሰጠችው ነፃ የንግድ እድል መርሃ ግብር ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች። ይሁን እንጂ የአሜሪካ መንግሥት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ባሳደረው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ኢትዮጵያ ከዚህ ነፃ የንግድ እድል ተጠቃሚነቷ ታግዳለች።
አለመረጋጋቱን ተከትሎ የመጣው የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሰሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር። በተጨማሪም የውጭ ሃገራት ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በኤምባሲዎቻቸው በኩል ከፍተኛ ግፊት ይደረግ ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመስራት ተገደው እንደነበርም ይታወሳል። በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት የምርት አገልግሎትና አቅርቦት መቋረጥ፣ የምርት ሽያጭ ገቢ መቀነስ፣ የስነ ልቦና ጫናዎችንና ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱም ይታወቃል።
ጦርነቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድሎችን በፈጠሩና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳካት እገዛ እያደረጉ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ አስገብቷቸውም ነበር። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩና ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በረጅም ጊዜ የግዥ ውል ለገዢዎች ስለሚያቀርቡ ምርቶቻቸውን በሌሎች ሀገራት ወደሚገኙ ቅርንጫፍ ማምረቻዎች እንዲያዞሩ ጫናዎች ነበሩባቸው፤ ግዢዎችም ይሰርዙባቸው ነበር።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙና በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያበረከቱ ካሉ 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮችና አንድ ነጻ የንግድ ቀጣና መካከል ሦስቱ (የመቀሌ፣ ሰመራ እና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች) የጦርነቱ ቀጣና በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው። በዚህም ምክንያት እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጦርነቱ ያስከተላቸው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተጽእኖዎች ሰለባ ሆነዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የመቀሌ እና የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በጦርነቱ ዘረፋና ውድመት አልተፈፀመባቸውም። በ90 ሚሊዮን ዶላር የተገነባውና በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ባለዘጠኝ ሼዱ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግን ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት እንደተፈፀመበት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን አምርተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አራት የደቡብ ኮሪያ፣ የጣልያን፣ የአሜሪካና የቻይና አምራች ኩባንያዎች የገቡበት ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ፤ የፓርኩ የቢሮ እቃዎችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ሲስተሞች፣ የአምራች ኩባንያዎች ቢሮዎችና ቁሳቁስ፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ተዘርፈዋል። ወደ ፓርኩ ገብተው በምርት ስራ ላይ ያሉ ድርጅቶች አምርተዋቸው የነበሩና ወደ ውጪ ሊላኩ የነበሩ የተለያዩ ምርቶች ተሰርቀዋል።
ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ለማምረት ጥቅም ላይ የሚያውሏቸው ጥሬ እቃዎችም ተዘርፈዋል። በድርጅቶቹ ቢሮዎች ውስጥ የነበሩ መገልገያዎች፣ በቀላሉ ሊተኩ የማይችሉ መሳሪያዎችና የምርት ሥርዓቶች፣ አገልግሎት መስጫዎች፣ የደኅንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች፣ የኤሌክትሪክ እና ሌሎች ገመዶች፣ ለፓርኩ ተጨማሪ ግንባታ ለማድረግ እንደመጋዘን ሲያገለግሉ የነበሩ ኮንቴይነሮች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያሉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁስም ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። አምራች ኩባንያዎቹ ለሥራዎቻቸው ያስገቧቸው መለዋወጫ እቃዎችና ሌሎች ጥሬ እቃዎች ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ ተፈፅሞባቸዋል።
የፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች፣ የማምረቻ ቦታዎች፣ የኬሚካል ማጣሪያ እና ሌሎች በፓርኩ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ክፍሎች ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል። በባለሀብቶች ተመራጭ የሆነው ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲመለስ የተለያዩ ተግባራት በመከናወናቸው፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በፍጥነት ወደ ስራ ሊመለስ ችሏል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጆነዲ፣ በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመቀሌ፣ የሰመራና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ስለደረሰባቸው የጉዳት (ውድመትና ዝርፊያ) ዓይነትና መጠን ሲያስረዱ ‹‹ጦርነት በባህሪው አውዳሚና ጎጂ መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም በፓርኮቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ጉዳቱን በገንዘብ ለመተመንና እስካሁን መገኘት ከነበረበት ጥቅም አኳያ የደረሰውን ኪሳራ ለማወቅ ዝርዝር ጥናት የሚያስፈልግ በመሆኑ በቀጣይ ጥናት ይደረጋል››ሲሉ አስታውቀዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ትኩረት ፓርኮቹን ወደ ስራ መመለስ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዘመን፣ በዚህ ረገድ ባለሃብቶቹና ሰራተኞቹን ወደ ስራ መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነም ያስረዳሉ። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ወደ ስራ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ዓመታት ያህል ስለመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምንም መረጃ ሳይኖረው ቆይቷል። የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኮርፖሬሽኑ የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን ወደ መቀሌ አምርቶ ፓርኩ ስለሚገኝበት ሁኔታ ምልከታ አድርጓል። በዚህም ፓርኩ ምንም አይነት ዘረፋም ሆነ ውድመት እንዳልደረሰበት ታውቋል። ስለሆነም ፓርኩን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
ኮርፖሬሽኑ ለረጅም ጊዜ ከስራ ውጭ የነበረውን የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለመመለስ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማግስት በርካታ ተግባራት ያከናወንን ሲሆን፤ ለአብነት ያህልም ቡድን በማዋቀር በፓርኩ ምልከታ የማድረግ፣ በፓርኩ ውስጥ ከነበሩ ባለሀብቶች ጋር የመወያየት እንዲሁም የአመራር ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት፣ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ስራ አቁመው የቆዩ ባለሃብቶችን ከሼድ ኪራይ ነጻ በማድረግ ወደ ስራ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል። በፓርኩ ውስጥ ከነበሩት ስምንት ባለሀብቶች ጋር በስልክና በኢ-ሜይል (e-mail) መነጋገር ተችሏል፤ በቅርቡም የጋራ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ተጨማሪ ውይይቶች ይደረጋሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ርብርብ ዘረፋና ውድመት አጋጥሞት የነበረው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአጭር ጊዜ ተመልሶ ወደ ስራ እንዲገባ ስለመደረጉና በሰመራ እና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየታየ እንደሚገኝ አቶ ዘመን ያስረዳሉ።
በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ ጫና እያሳደሩ ያሉ ተግዳሮቶች እንዳሉ የገለፁት አቶ ዘመን፤ ባለሃብቶችን አሳምኖ ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተበተኑ ሰራተኞችን ወደ ቀድሞ ስራቸው መመለስ፣ የሰራተኞች ሰርቪስ የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ በአንድ ማዕከል ውስጥ የሚቀርቡ አገልግሎቶች በተሟላ ሁኔታ አለመጀመር እና የውሃ አቅርቦት ችግር ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደሆኑም ያስረዳሉ።
እነዚህን ችግሮች ለማቃለል በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስለተወሰዱትና በሂደት ላይ ስላሉት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሲያብራሩ እንዳሉት፤ በፓርኩ የነበሩ ባለሃብቶች ወደ ስራ እንዲገቡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሚመሩት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፤ ባለሃብቶችን የማግኘትና ወደ ስራ እንዲገቡ የማሳመን ስራ ተሰርቷል። በፓርኩ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅና ባለሃብቶቹ ወደ ስራ ሲገቡ የሰራተኛ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ ጋር ውይይት በማድረግ የትራንስፖርቱ ችግር የሚፈታበት ሂደትም ተመቻችቷል። የመብራትና የዳታ እንዲሁም የድምጽ መቆራረጦችን ለማስወገድ የሚያስችል ውይይት ተደርጎ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ የሚያሥችሉ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ። የውሃ አቅርቦትን በተመለከተ ደግሞ በአካባቢው ያለው ውሃ ከማህበረሰቡ አልፎ ለፓርኩ በትንሽ መጠን የሚደርስ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋገርና የጉድጓድ ውሃ ለማውጣት የሚያስችል የፓንፕ ግዥ ለመፈጸም እየተሰራ ነው።
በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ አምራቾች ዘርፈ ብዙ ችግሮች የደረሱባቸው በመሆናቸው ልዩ የማበረታቻ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይታመናል። በዚህ ረገድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ ባለሀብቶች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ለማገዝ ለባለሀብቶቹ የተለያዩ ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግ አቶ ዘመን ይናገራሉ። ከመደበኛ የድጋፍና ክትትል ስራዎች በተጨማሪ ባለሀብቶቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረባቸው የሼድ ኪራይ ነጻ የማድረግ እና ከፓርኩ የስራ ኃላፊዎችና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ውይይት በማድረግ ቀደም ሲል በፓርኩ የነበሩ የተለያዩ አገልግሎቶችን በፍጥነት ወደ ስራ የመመለስ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል። የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው።
ስለሆነም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታትና አፈፃፀማቸውን በማሻሻል መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ማሳካት ይገባል። ለዚህም በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት ስራቸው እንዲመለሱ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማቃቂያ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና በብቃት መተግበር ያስፈልጋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2015