የፕየሞንቴው መስፍን የጣሊያን መንግሥት አልጋ ወራሽ ባለቤት በመውለዷ በአዲስ አበባ ገነተ ልዑል ግቢ ውስጥ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ድግስ ተደግሷል። ሕዝቡም በቦታወ ተሰብስቧል። ግራዚያኒ ሰገነቱ ላይ ንግግር እያደረገ በነበረበት ወቅት ሞገስ አስገዶም እና አብርሀ ደቦጭ አከታትለው የእጅ ቦምብ ወረወሩ። ከግራዚያኒ በተጨማሪ ሌሎች ሹማምንት ሁሉ ቆሰሉ። ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ከጣሉት ሰዎች ጀርባ እጁ አለበት በሚል ፋሺስት ጣሊያኖች ይዘው ሊሰቅሉት በእግር በፈረስ ያፈላልጉት ጀመር።
ይህንን ግለሰብ የገባበት ሁሉ ገብተው ለመያዝ ጣሊያኖች አደናቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በመጨረሻም በጥብቅ የሚፈልጉት ግለሰብ በእጃቸው ቢገባም ማንነቱን ግን አላወቁትም ነበር። እርሱም ጣሊያኖችን አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ “ማንን ነው የፈለጋችሁት”? አላቸው። እነርሱም፣ የእርሱን ስም ጠርተው “እገሌ የሚባል ሰው” አሉት። እርሱም “የምትፈልጉትን ሰው ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፤ አብሬያችሁ በከተማው ዘወር ዘወር ብል እናገኘዋለን” አላቸው። ጣሊያኖቹም እውነት መስሏቸው የሚፈልጉትን ሰው በእጃቸው ይዘው እራሱን መፈለግ ጀመሩ። እርሱም በዛ አጋጣሚ በሥርቤት ከተመለከተው የፋሺስቶች በደል ባለፈ በከተማዋ የተፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በአይኑ ተመለከተ። በኋላም የሚፈልጉት ሰው እንደነበር ሳያውቁት ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሮ እንዲረሸን እጣው ደረሰ።
እርሱም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጸው “ጣልያኖች እየጠሩ ከሚወስዷቸዉ ሰዎች መካከል ሆኘ ተወሰድኩ። ከሰው መሀል ጠርተው ወስደው መረሸን ልማዳቸው ስለነበረ ወደ ሞት እየሄድን እንደሁ ታውቆኛል። የተቆፈረ ጉድጓድ አፋፍ ስር ቁመናል። ከጀርባችን ደግሞ አናታችን ላይ ተነጣጥረው የተደቀኑ መድፎች አሉ። እስከዛሬ ሰዎች ሲገደሉ አይቻለሁ። አሁን ተራው የእኔ ነው። ሞት ምን ይመስል ይሆን? መድፎች ተናገሩ፤ ተተኮሰ። ወደ ጉድጓዱ ወደቅን። መድፉ ብዙዎችን የገደለ ቢሆንም እኔ ግን አልተመታሁም። እንደ ሞተ ሰው ከሟቾች ጋር ተኛሁ። ሲጨላልም ከወደቅኩበት ጉድጓድ ወጥቼ አመለጥኩ” በዚህ ቅፅበት ከመረሸን የተረፈው አርበኛ፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ ጠበቃ እና ባለቅኔው ተመስገን ገብሬ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ላይ የፈፀመውን የግፍ ጭፍጨፋ በአይኑ አይቶ ሕይወቴ በሚለው በግል ታሪኩ ላይ በሚያጠነጥነው መጽሃፉ ላይ ያሰፈረው ነው።
በየአመቱ የካቲት 12 ቀን ሲታወስ በቀዳሚነት ከሚዘከሩ አርበኞችና የሀገር ባለውለተኞች ውስጥ አንዱ ታላቁ አርበኛና ደራሲ ተመስገን ገብሬ፤ ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ ግንቦት 15 ቀን 1901 ዓ.ም ተወለደ። ቤተሰቦቹ ካህን ስለነበሩ ተመስገን አራት ዓመት፣ ከአራት ወርና በአራተኛው ቀን ከቤታቸው አጠገብ ከሚገኘው ቤተክርስቲያን ከነ የኔታ (መርጌታ) እግር ስር ቁጭ ብሎ የፊደል ገበታን ቀስሟል።
ተመስገን ገና አስር ዓመት ሳይደፍን ከወላጆቹ ጠፍቶ በጨቅላ እድሜው ቀየውን ለቆ ሞጣና ቢቡኝ እየተዘዋወረ የቤተ ክህነት ትምህርት እስከ ቅኔ ድረስ ተምሯል። በኋላም በቢቡኝ ውስጥ ረዳት የቅኔ መምህር ሆኖ አስተምሯል። በትምህርቱና ቅኔ አዋቂነቱ የአንቱታን ካባ የደፋ ድንቅ ሰው ነበር። በትምህርቱ እጅግ ጐበዝ የሚባል በመሆኑ ገና በ15 ዓመቱ የቅኔ መምህር ለመሆን በቅቷል፡፡ በቤተ-ክህነት ትምህርት በዚህ እድሜ የቅኔ መምህር የሆነ ሰው ከተመስገን ሌላ አልተገኘም ይባላል፡፡
እርሱም “ሕይወቴ” በሚለው መጽሃፉ “ትምህርት ቅኔ ነው እንጅ”! ይላል፡፡ ከቅኔ በላይ ምን ትምህርት አለ ማለቱ ነው፡፡ በቅኔ ትምህርት የሚመሰጥ ሰው ነበር፡፡ በዚህ መጽሀፍ ገጽ-19 “ቅኔ የኢትዮጵያ ታላቅ የመጨረሻው ትምህርት ነው” ይላል፡፡ እንዲሁም በገጽ-23 “ቅኔ ካወኩ በኋላ ትዕቢተኛ ሆንኩ” ሲል ቅኔ አዋቂ በመሆኑ የሚሰማውን ኩራት ተሜ ይናገራል፡፡
በሞጣና ቢቡኝ እየተዘዋወረ ቅኔውን ፉት ካደረገ በኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ ደብረ ማርቆስ ተመልሶ በራስ ኃይሉ ተክለኃይማኖት ዙፋን ዙሪያ ደንበኛ አቤቱታ ፀሐፊ በመሆን ገና በለጋ እድሜው ህዝብን አገልግሏል። በወቅቱ የነበረውን የእጅ መንሻ (ጉቦ) አጥብቆ ይቃወም ስለነበር ከመኳንንቱ ጋር ባለመስማማቱ ወደ አዲስ አበባ ተሰደደ። በ1918 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አቅንቶም በትርፍ ጊዜው እየሠራ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርቱን ተከታትሎ ጨርሷል።
አርበኛና ደራሲ ተመስገን ገብሬ የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታና የፖለቲካ አሰላለፍ በንቃት የሚያውቅና የሚከታተል ባለብሩህ አእምሮ ስለነበር “አድዋ ላይ የሽንፈትን ካባ የተከናነበችው ኢጣሊያ ዳግም ኢትዮጵያን እንደምትወር ቀድሞ ያወቀና የነቃ ሰው ነበር። በዚህም በ1920ዎቹ ውስጥ ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም ከመውረሯ በፊት በሕዝብ አደባባይ የጣሊያንን የወረራ ዝግጅት እና ዕቅድ ለኢትዮጵያውያን አስገንዝቧል። ወረራው የማይቀር መሆኑንና ህዝቡ አንድ ሆኖ ጠላትን እንዲመክት በየአደባባዩ ያስተምር፣ ያነቃ ነበር፡፡ ህዝቡም ወረራውን ለመመከት ዝግጅት እንዲያደርግና ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ አጥብቆ ወትውቷል። በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ ታዋቂ ንግግር አድራጊ ስለነበረ፤ ‹‹ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር ነው፤ ለጦርነት እንዘጋጅ›› እያለ ዲስኩር የሚያሰማ ንቁ ኢትዮጵያዊ ነበር። በአንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመመስረት ብርቱ ትግልም አድርጓል፡፡
ያ በእንዲህ እንዳለ ጣሊያን አዲስ አበባ ገባች። የተመስገን የአርበኝነት ትግል ከዚህ ይጀምራል። በሞገስ አስገዶም እና አብርሀ ደቦጭ አማካይነት ተወርውራ ግራዚያኒን ካቆሰለችው ቦምብ ጀርባ ተመስገን እጁ አለበት ተብሎ ይታሰብ ስለነበር፤ ጣሊያኖች ያሳድዱት ጀመር። ቆይቶም በጣሊያኖች እጅ ወደቀ። ያኔ ጉድጓድ አፋፍ ላይ ቆመው ከተረሸኑ ዜጎች አንዱ የነበረው ተመስገን፤ “ከንፍሮ መሃል ጥሬ” እንደሚገኘው በጭፍጨፋው ዕለት በተአምር ከሞት ተረፈ። እሱም ከክምር አስከሬን መሀል ተነስቶ ወደ ሱዳን ተሰደደ። ሱዳን ውስጥ ሆኖ ዋነኛው የአርበኞች ትግል አቀጣጣይ ነበር።
ተመስገን፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ፤ ብዙ ተንገላቷል። ወገኖቹ ተማርከው በውሃ ጥም ምክንያት ደም የተቀላቀለበት ውሃ ሲጠጡ አይቷል። በእሱ እና በወገኖቹ ላይ ይደርስ የነበረውን በደል ለጃንሆይ ይጽፍላቸው ነበር። ጃንሆይም በስደት አገር በለንደን ሆነው የፃፈላቸውን ደብዳቤ እያነበቡ ያለቅሱ እንደነበር ተጽፏል። እንዲሁም ጃንሆይ ጄኔቫ ላይ የሊግ ኦፍ ኔሽን ስብሰባ ንግግር ሲያደርጉ የንግግራቸው አብዛኛው ሃሳብ ተመስገን ገብሬ ሱዳን ሆኖ ከፃፈላቸው ደብዳቤ የተወሰደ ነበር።
ያኔ በሲልቪያ ፓንክረስት አማካኝነት በለንደን በሚታተመው “new times and Ethiopia news” በሚል በሚታወቅ ጋዜጣ ላይ ተመስገን የፃፋቸው ፅሁፎች ይወጡ ነበር። “The Addis Ababa Massacre Italy’s National Shame” የሚል መፅሃፍ ላይ የተመስገንን የአይን እማኝነት እና ጋዜጣው ላይ የወጡ ፅሁፎቹን በዋቢነት ተጠቅሷል። ከዚህ ባሻገር ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በመላላክ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትሰለፍ የዲፕሎማሲ ሥራ ሰርቷል። “ሀገራችን ነፃ መሆኗ አይቀርምና ሀገር የሚረከብ ትውልድ በትምህርት መቅረፅ አለብን” በሚል በሀገረ ሱዳን በስደት በነበረበት ወቅት ጋዳሪፍ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በተለይ ህፃናትን ያስተምር ነበር።
በጥቅሉ 30 ሺህ የአዲስ አበባ ኗሪዎችን ጭፍጨፋ በአይኑ በብረቱ ተመልክቶ የጣሊያንን ነውረኝነት በዓለም አደባባይ በማስጣት ታሪክ ከማጋራቱ ባለፈ የፋሽስቶችን ግብአተ-መሬት ካፋጠኑ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን መካከል ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነበር።
የየካቲቱ ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ የገፈቱ ቀማሽ የሆኑት አርበኛው ደራሲ ‹‹ዓለም በድንገት ተለውጣ፣ አዲስ አበባም ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያውያንን የሚያርዱበት ቄራ ሆና ነበር›› ሲሉ ገልጸውታል። ይህንን ወደር የለሽ ጭፍጨፋም “የካቲት 12” በሚል ርዕስ እና “ሊቀ-ጠበብት እውነቱ” የተሰኙ ሁለት አጫጭር ልብወለዶችን ጽፎ ለትውልድ ታሪኩን ከትቦ አስተላልፏል። በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ወረራ ጊዜም በደረሱት ‹‹በለው በለው አትለውም ወይ፤ የጥቁር አንበሳ አይደለህም ወይ›› በሚለው መዝሙሩም ይታወሳል፡፡
ከዚህም ሌላ የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የተደረገውን ጭፍጨፋ እና በአጠቃላይ በርሱ ሕይወት ዙሪያ ያለውን ውጣ ውረድ “ሕይወቴ” በሚል ርዕስ ፅፎታል፡፡ ይህ መፅሐፍ እርሱ ከሞተ ከ60 ዓመታት በኋላ የታተመ ሲሆን፤ የእርሱን የሕይወት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ የያዘ ነው። ምን ይሄ ብቻ በ1941 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሥነ ፅሁፍ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን አጭር ልቦለድ “የጉለሌው ሰካራም” በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅቷል።
እዲሁም አርበኛው ተመስገን ገብሬ ከነፃነት ማግስት ወደ ሀገሩ ገብቶ የኤርትራ ድምጽ የተሰኘችው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን አገልግሏል። ፋሺስት ኢጣሊያ ከለቀቀች በኋላ በሀገሪቱ ዘመናዊ አስተሳሰብና ዕድገት ዕውን እንዲሆንም ፍፁም የለውጥ አርበኛ በመሆን ሠርቷል።
በአማርኛ ቋንቋ ችሎታውና በአፃፃፍ ቴክኒኩ እጅግ የተዋጣለት ደራሲ መሆኑን የሀገሪቱ ጉንቱ ሃያሲያን መስክረውለታል። ለአብነት ሀዲስ አለማየሁ “ትዝታ” በሚለው መጽሃፋቸው በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ወረራ ወቅት ወደ ሱዳን ተሰደው ለሀገራቸው ብዙ ሥራ ከሠሩ ሰዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ አርበኛው ደራሲ ተመስገን ገብሬ እንደነበር ጠቅሰው፤ “መቼም በድርሰት ዓለም ተወዳዳሪ የለውም” ብለው በእርሳቸው ብዕር ወደር የለሽ ደራሲ እንደነበር ተገልጿል።
ፀሃፊ እንዳለጌታ ከበደ በበኩሉ ሕይወቴ” የተሰኘው የአርበኛው ደራሲ መጽሀፍ እሱን ብቻ ሳይሆን፤ የዘመኑን መንፈስ ቃኘንበት፤ የአተራረክ ብቃቱን ብቻ ሳይሆን እሱና ሌሎች አርበኞች፤ በየካቲት 12/1929 ዓ.ም ስለተጎነጩት የመስዋዕትነት ፅዋ ያወቅንበት፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ የዚያን ዘመን ትውልድ አባላት፤ ሀገር እና ባንዲራ የሚባል መስቀል ተሸክመው፤ ምን ያህል ጊዜ እንደተገረፉ፤ ምን ያህል ጊዜ እንደተወገዙ፤ ምን ያህል ጊዜ ቀራኒዮ ተራራ ላይ ወጥተው ለነፃነት ብለው በፋሽስት ምስማር እንደተቸነከሩ ያየንበት ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሰዎች፤ በቁጥር ጥቂቶች ናቸው። አስፈላጊነታቸው የሚገባን ዘግይቶ ነው። ለመታየት በሚጓጉ እና ሌላውን ዝቅ አድርገው ከፍታ ቦታ ላይ ለመቆም በሚታትሩ ሰዎች ይሸፈናሉ። አርበኝነታቸው ጦር ሜዳ ሄዶ ተጋድሎ ለመፈፀም ብቻ የሚዘከር አይደለም። አንደበታቸውም፤ ብዕራቸውም ለሃቅ የቆመ እና ለእውነት የተገራ ነው፡፡ እንዲህ ናቸው ተመስገን ገብሬዎች” ሲሉ ፀሀፊው መስክረውለታል።
ሌላው ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ተመስገንን በአይነ ሥጋ ለማየት ባይታደልም አርበኛው ደራሲ በተለይ በኢትዮጵያ የሥነ- ጽሁፍ ታሪክ ያበረከተውን አስተዋጽዖ እየፈለፈሉ ለህዝብ እንዲደርስና ተመስገን ማን እንደነበር ትውልድ እንዲያውቀው የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል። ደራሲ ጥበቡም፤ “በ1930ዎቹ ኮሚኒዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝም ወዘተ. የመሳሰሉ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ጽንስ ሃሳቦችን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ የብዙ ነገሮች ፈር ቀዳጅ ነበር። የዓለምን እድገት፣ ግስጋሴ የሚያውቅና የሚከታተል ባለምጡቅ አዕምሮ ሰው ነበር። የተለያዩ አንቱታን ያተረፉ ደራሲያን የተሜን ድርሰት በሥነ-ጽሁፍ አላባውያን መዝነው፤ ሥራዎቹ ዘመናዊ፣ በሥነ-ጽሁፍ ብቃቱ ወደር የለሽ፤ ከዘመኑ የቀደመ ሰው እንደነበር መጻፋቸውን” ይናገራል።
…ተመስገን ገብሬ ከርቀት ይኼ ነው፤ በቅርበት ለማወቅ ‹ሕይወቴ›ን ማንበብ ግድ ነው፡፡ በመጨረሻም ይህ የቅኔ ጠበብት፣ አርበኛ፣ መምህር፣ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማንነታቸው ያልታወቁ እኩይ ግለሰቦች የተመረዘ ምግብ አብልተውት በ1941 ዓ.ም በተወለደ በ40 ዓመቱ ይህን የድካም ዓለም ተሰናብቷል። የሁለት ሴት ልጆች እና የአንድ ወንድልጅ አባት ነበረ። ታዲያ ለዚህ እውቅ ባለቅኔ፣ ደራሲ እና የነፃነት ታጋይ አርበኛ እንዴት እኛ ኢትዮጵያውያን ለባለውለታችን አንድ የመታሰቢያ ሐውልት ማቆም ከበደን? ቢቻል በመዲናዋ ካልሆነ ደግሞ በትውልድ ቦታው ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ ሥሙን፣ ዝናውንና ሥራውን የሚያወሳ የመታሰቢያ ሐውልት ቢተከልለት ስንል የሚመለከታቸው አካላትንና የኢትዮጵያ ሕዝብን በዝግጅት ክፍሉ ስም እንጠይቃለን።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2015