በቅርቡ ማሻሻያ ተደርጎ የቤት ባለይዞታዎች እንዲከፍሉ የተደረገውን ግብር የማኅበረሰቡን ኑሮ ያላማከለ፤ ኅብረተሰቡ እንዲወያይ ሳይደረግ በአቅጣጫ በግዳጅ እየተፈፀመ ያለ፤ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቆጥበው ያገኙት ቤት ላይ እንዲከፍሉ መደረጉ፤ ድሃውን የሚጎዳ ነው የሚሉ ሰፋ ያሉ ወቀሳዎች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ። አሠራሩ ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ የተለያየ ነው የሚሉ እና ሌሎችም ተያያዥ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ ናቸው። እነዚህ እና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎችን በመያዝ የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ዘገየ በላይነህን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡-የንብረት ግብር ይከፈል መባሉ በችኮላ የተወሰነ፣ ኅብረተሰቡ ያልተወያየበት እና የኅብረተሰቡን አቅም ያላገናዘበ ነው የሚሉ እና ሌሎችም ቅሬታዎች በመሰማት ላይ ናቸው። እርሶ ምን ይላሉ?
አቶ ዘገየ፡– በቅድሚያ ይህ ግብር አዲስ እንዳልሆነ እና ከ1937 ዓ.ም ከንጉሡ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የነበረ ነው ። በደርግ ጊዜም በ1968 ዓ.ም በአዋጅ ተሻሽሎ አዋጅ ቁጥር 80/1968 በሚል አዋጅ እስከ ዛሬ እየተተገበረ ነው። ወቅታዊ ከማድረግ በስተቀር አዲስ አይደለም።
ከስያሜ አንፃርም መስተካከል ያለበትነገር አለ። አሁን እየተተገበረ ያለው የንብረት ግብር ሳይሆን፤ የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር ነው። ይህ አዋጅ ደንብም አለው። አዋጁን ለማስተግበር ደንብ ቁጥር 36/1968 በዚያው ጊዜ የወጣ ነው። ስለዚህ በጣም የቆየ እንጂ እንደአዲስ የታወጀ አዋጅ አይደለም።
በችኮላ በአቅጣጫ በግዳጅ እንዲፈፀም የተወሰነ ነው በሚል ነገሮችን አጠቃሎ ማስቀመጡ ተገቢ አይደለም። ይህ በጥናት ላይ የተመረኮዘ፤ ግብሩም ወቅታዊ የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ዋጋን መሠረት ያደረገ ነው።
በካሬ ስንት እንደሆነ ጥናት ላይ በመመሥረት የተዘጋጀ ነው። ቀድሞ ግን እንደገለፅኩት አዋጁ በ1968 የተዘጋጀ እና የቆየ ነው ፤ አከፋፈሉ ላይ ግን ትልቅ ችግር ነበር። ለምሳሌ የ2014 ዓ.ምን አከፋፈል ማየት ይቻላል።
በ2014 ዓ.ም 182 ሺህ ሰዎች ይህን ግብር የከፈሉ ነበር፤ ይህን ግብር ከከፈሉ ሰዎች መካከል 2ሺህ 578 ሰዎች የሚከፍሉት አንድ ብር አካባቢ ብቻ ነበር። 23 ሺ ሰው ከ10 ብር ያነሰ የሚከፍል ነው፤ ወደ 84ሺህ ሰው ከ11 ብር እስከ 100 ብር ከፍሏል።
በአዋጁ በግልፅ እንደተመላከተው በየጊዜው ወቅታዊ ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ነገር ግን በአንድም ሆነ በሌላ ወቅታዊ ሳይደረግ ቆይቷል። አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ እያቀረበ ካለው የመሠረተ ልማት እና በከተማ ውስጥ ቤቶች በካሬ የሚከራዩበትን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥናት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል።
‹‹ኅብረተሰቡን ማወያየት ያስፈልግ ነበር›› ለሚለው በየመገናኛ ብዙኃኑ ኅብረተሰቡ ግራ ለሚጋባባቸው ጉዳዮች እና ከሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። በገቢ ቢሮ በኩል መዋቅራችን እስከ ወረዳ ድረስ አለ። ሥራው የመሬት ቢሮን፣ የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣንንም ይጨምራል። እነዚህ ሁሉ ተቋማት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፤ በእነዚህ ሁሉ ተቋማት በኩል ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ እየተሰጠ ነው።
የሌሎች ሀገሮችን የአፍሪካ አገሮችን ልምድ እንኳ ወስደን ስናይ ለምሳሌ የዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ 74 ነጥብ 6 በመቶ የከተማው ገቢ ከዚህ ዓይነት ግብር የሚሰበሰብ ነው። ይህ የ2021 መረጃ ነው። የጎረቤታችን ኬንያ የዋና ከተማ የናይሮቢ ገቢ 20 በመቶ የሚሰበሰበው ከእንደዚህ ዓይነት ግብር ነው።
የእኛ አገር ደግሞ የ2014 ዓ.ም ከላይ እንደጠቀስኩት የተሰበሰበው የከተማዋን በጀት ከአንድ በመቶ ያነሰ እንዲያውም ወደ ዜሮ ነጥብ ዜሮ ስምንት አካባቢ የተጠጋ ነው። ስለዚህ ይህንን በምናይበት ጊዜ ወቅታዊ ማድረጉ የግድ ነው። እስከ አሁን ሳይፈፀም ወደ ኋላ መቅረቱ እንጂ፤ በጊዜ ወቅታዊ እየተደረገ ቢሆን ኖሮ መንግሥት የተሻለ መሠረተ ልማትም እንዲገነባ የሚያስችል ነበር። ስለዚህ ግብሩ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው። በግብታዊነት የተወሰነ አዲስ አዋጅ አይደለም።
የአከፋፈል ሁኔታውን በተመለከተ አሁን እየተከፈለ ነው። ቅርንጫፎች እና ንዑስ ቅርንጫፎች ወይም በወረዳ ደረጃ ያሉ የታክስ ማዕከላት ትንሽ የሰው መብዛት እና መጨናነቆች ቢኖርም እየተሠራ ነው። ስለዚህ ያንን ለማቃለል ሠራተኞቻችን ማልደው በመግባት እና ማታም አምሽቶ በመሥራት አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረግን ነው።
ከሌሎች የሥራ ክፍሎችም ሰዎችን አንቀሳቅሰን የሰው ኃይል በማብዛት አገልግሎቱ እንዲሰጥ ጥረት እያደረግን ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ሰነድ እንኳን ብንጠቀም እስከ አሁን ያልከፈሉ ሰዎች ከፍለው ወደ ሚቀጥለው አመት እንሸጋገራለን። በዚህ ዓመት የሚከፈለው መኖሪያ ቤት ከሆነ 50 በመቶ ብቻ ነው። ድርጅት ከሆነ ደግሞ 75 በመቶ ብቻ ነው። ይህ ከሆነ በአንድ ጊዜ ግብር ከፋዩ ላይ ጫና እንዳይመጣ መንግሥት አስቦ ያደረገው ነው። ይህ ጫናውን ለማቅለል የተወሰደ ከፍተኛ እርምጃ ነው። ስለዚህ ክፍያው በዚህ መልክ እየተሰበሰበ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብሩ አዲስ ባይሆንም ተመኑ ሲወጣ ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ ምን ያህል ወቅቱን ያገናዘበ ነው? ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር አያይዘው ቢነግሩን?
አቶ ዘገየ፡– የጋራ መኖሪያ ቤቶች እስከ አሁን ሳይከፍሉ የቆዩት አዋጁ ላይ እንደተመላከተው የአከፋፈሉ ሁኔታ በየጊዜው ወቅታዊ ባለመደረጉ ነው። በተጨማሪም ኅብረተሰቡ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ታሳቢ በማድረግ ነው። በሌላ በኩል ግን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በብዛት አንድ ቦታ የተገነቡ ቢሆንም አንዳንዱ ዕጣ ደርሶት፣ አንዳንዱ ገዝቶ ሌላው ደግሞ ድርጅት ገዝቶለት የሚኖር ነው። ቤቶቹ ካርታ አላቸው የሚጠቀምባቸውም ግለሰብ አለ። ስለዚህ ከተማ ውስጥ ያሉ ቤቶችን ግብር የመሰብሰብ ሥልጣን የከተማ አስተዳደሩ ስለሆነ እስከ ዛሬ አልከፈልንምና ነፃ መሆን አለብን የሚለው አያስኬድም።
ነገር ግን መንግሥታችን አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ ጫና እንዲሁም ያሉትን ነገሮች ይረዳል። በዚህ የተነሳ በዚህ ዓመት እስከ የካቲት 30 ግብር መከፈል ነበረበት። ነገር ግን የአሁኑ ግብር ተግባራዊ የሚደረገው ባልከፈሉት ላይ ብቻ ነው። እስከ አሁን ያልከፈሉትም ቢሆኑ የግብሩን 50 በመቶ ብቻ እንዲከፍሉ ተደርጓል። በመንግሥት ይህ የተደረገው የሕዝብን ጫና ለመቀነስ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የግለሰብ ግብር ከፋዮች መክፈል ያለባቸውን ግብር ይሰበስባል። ቤቱ የግለሰብ ቤት ነው። እንደምሳሌ የጋራ መኖሪያ ቤትን እንጥቀስ ከተባለ፤ የጋራ መኖሪያ ቤት በግል የሚከፈል ሲሆን፤ በልዩ ሁኔታ የተቸገረ ከሆነ እና ቤቱን የሆነ ድርጅት ገዝቶ የሠጠው እንዲሁም ምንም ዓይነት ገቢ ከሌለው ምንም ማድረግ የማይችል ሰው ቅሬታ የሚሰማባቸው ማዕከላት አሉ።
በከተማ ደረጃ የተዋቀረ ቅሬታ ሰሚ አለ። የእኛም የታክስ ማዕከል ላይ ቅሬታ የሚሰበስቡ ባለሞያዎች አሉ። በግሉ የተቸገረ ሰው ችግሩን ተናግሮ ከችግር የመውጫ መንገዶቹን በተመለከተ በተቋም ደረጃ እኛም ስላለን በዚያ መገልገል ይችላል። ነገር ግን እስከ ዛሬ ስላልከፈልን አሁንም መቀጠል አለብን የሚለው አያስኬድም።
ግለሰብ ግብር የሚከፈለው ለራሱ ነው። መንግሥት ወኪል ነው፤ ግብር ሰብስቦ በተገቢው ቦታ ላይ የሚያውል አካል ነው። ከዚህ ውጪ ግብር በመከፈሉ ተጠቃሚው መንግሥት ብቻ አይደለም። ራሱ ግብር ከፋዩም ተጠቃሚ ነው። በተከፈለው ግብር ተጠቃሚ የሚሆነው ራሱ ነው የሚባለው መሠረተ ልማት በየደጃችን እንዲስፋፋ ስለሚያስችል ነው።
የመሠረተ ልማት መስፋፋት የንብረቶቻችንን ዋጋ ይጨምረዋል። ለምሳሌ ሽያጭም ሆነ ኪራይ መሠረተ ልማት ሲስፋፋ መጨመሩ አይቀርም። እንደመሠረተ ልማት ተደራሽነት እና እንደቦታው የከተማ ቅርበት የቤት የሽያጭ ዋጋም ሆነ ኪራይ ከፍ ይላል። ስለዚህ መሠረተ ልማት በተስፋፋ ቁጥር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ግለሰብ ተጠቃሚ ይሆናል። ስለዚህ ግብር መክፈል ጥቅም ያስገኛል።
በግል አሁን ከምንነጋገረው ውጪ ይሔ ችግር አለብኝ የሚል ሰው ከመጣ ልናዳምጠው ዝግጁ ነን። የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ የልኬት ችግር አይኖርም። ነገር ግን ሌሎችም ከልኬትም ሆነ ከአከፋፈል ጋር በምንም መልኩ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ቅሬታ ያላቸው ሰዎች በክፍለከተማም ሆነ በገቢዎች ቢሮ በኩል ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- በአብዛኛው ቅሬታዎች ተመኑ የወቅቱን የኑሮ ውድነት ያገናዘበ አይደለም የሚል ናቸው። ችግሩ ተከራዮችንም የሚነካ በመሆኑ ፍትሃዊ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ዘገየ፡– ከመሬት በመነሳት የተሰጠ ውሳኔ አይደለም። በተቻለ አቅም ጥናት ላይ ለመመስረት ጥረት ተደርጓል። በከተማ ደረጃ ተጠሪነቱ ለፋይናንስ ቢሮ የሆነ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን፤ የንብረት ታክስ ማስተግበሪያ ጽሕፈት ቤት ነው። እርሱ የንብረት ግብርን ወደፊት ሥራ ላይ ስናውል የዓለም አቀፍ ሕግና ተሞክሮ ምን ይመስላል? የሀገራችን ሕጎችስ ምን ይመስላሉ? የሚለውን እያየ ይህንንም በታሳቢነት ማሻሻል ይገባል የሚለውን ያጠናው ይህ የሥራ ክፍል ነው።
በደንብ በባለሞያዎች የተደራጀ እኔን ጨምሮ በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ እና የምናስተባብረው ነው። አሁን ተገቢ ነው የሚለው በጥናት የተመለሰ ጥያቄ በመሆኑ እዚህ ላይ ምንም ብዥታ የለም። ሕግ ቢወጣም ተግባር ላይ ሲውል አፈፃፀም ላይ ችግር ሊኖር ይችላል። ችግሮች ሲኖሩ በጋራ እየተወያየን በአስተዳደር የሚፈቱ ደግሞ አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን እየሠጠን እንሔዳለን። በዚህ ወቅት መጠናቱ እና መተግበሩ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይህንን ከከተማ አስተዳደሩ ልማቶችን ከመሥራቱ አንፃር መታየት አለበት።
ወደ ኋላ ዞር ብለን ብንመለከት ባለፉት አራት ዓመታት እንኳ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ እና የኅብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል። የካፒታል ፕሮጀክቶችን ብናይ፣ የምገባ ማዕከላት፣ የተማሪ ምገባ፣ ድሃ ተኮር ፕሮጀክቶች ሁሉ በብዛት ከግብር ከፋዩ በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚሠሩ ናቸው። ግብር ስንከፍል ተጠቃሚ የምንሆነው እኛው ነን። ለጊዜው ጫና ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በመጨረሻ በጊዜ ሒደት ተጠቃሚ ኅብረተሰቡ ነው።
አፈፃፀም ላይ ወይም በጥናት ላይ ያልታየ ነገር ካለ የባለሞያን ምክር እየወሰድን እየተሻሻለ ይሔዳል። ከላይ አውሮፓን ሳናነሳ የአፍሪካ አገሮችን ጠቅሰን ምሳሌዎችን አንስተናል። ሌሎች አገሮች የገቢያቸውን ሃምሳ በመቶ እና ከዚያ በላይ ከተመሳሳይ የገበያ ርስት እየሰበሰቡ እኛ ከአንድ በመቶ በታች እየሰበሰብን ነው። ይህንን አልሰበሰብንም ማለት ዕድገት ተጓተተ ማለት ነው። መሠረተ ልማት በአግባቡ አይስፋፋም ማለት ነው። ያ ሲሆን ደግሞ በተዘዋዋሪ በወቅቱ የምንፈልገው አገልግሎት እንዳናገኝ፤ መሠረተ ልማት እንዳይስፋፋ ዞሮም ደግሞ በመሠረተ ልማት ተደራሽነት ሊጨምር የሚችለውን የንብረታችንን ዋጋ የሚቀንስ ስለሆነ ግብር በዚህ ልክ መሰብሰቡ ብዥታ መፍጠር የለበትም።
ይሔን ብቻ ሳይሆን ሌላም ሕግ ሲወጣ መሬት ላይ ወርዶ እንዳይፈፀም የሚያደርግ፤ የሚያስከትለው ችግር ካለ ወይም በጥናት ጊዜ ግንዛቤ ውስጥ ያልገቡ ነገሮች ካሉ በሥራ ሒደት እየተሻሻሉ ይሔዳሉ።
አዲስ ዘመን፡- የጋራ መኖሪያ ቤት የካሬው ልኬት እየታወቀ በድጋሚ መሐንዲስ ይለካል መባሉ በተጨማሪ የመሐንዲስ የአገልግሎት ክፍያ መጠየቁን ተገቢ ነው ?
አቶ ዘገየ፡– በልኬት በኩል ያለውን ዋጋ በመሬት ቢሮ በኩል ስለሆነ ያንን ማለት አልችልም። እኔ በምክትል ቢሮ ኃላፊነት የምመራው የገቢዎችን ቢሮን ነው። ስለዚህ የመሬትን ጉዳይ የመሬት ቢሮ ቢመልስ ይሻላል። አጠቃላይ ልኬትን በተመለከተ ለምሳሌ አንድ ሰው የኔ ቤት ስፋት ይህንን አያክልም ሊል ይችላል። የዚያን ጊዜ ግብሩ ታሳቢ ያደረገው ቤቱ የተሠራበትን ቁሳቁስ የአፈር ወይም የብሎኬት ሊሆን ይችላል። ወይም ስፋቱ እና የቤቱ አገልግሎት ማለትም ቤቱ ለንግድ ነው ወይስ ለመኖሪያ የሚለው እነዚህን ሁሉ ግብሩ ግምት ውስጥ ያስገባል።
ቤቱ ወይም ሕንፃው የሚገኝበት የቦታ ደረጃ እንደሚታወቀው አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ እና ሦስተኛ ደረጃ የሚባል ቦታ አለ። ስለዚህ ግብሩም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው። ለምሳሌ ከእነዚህ በአንዱ ላይ ግብር ከፋዩ የእኔ ቤት ስፋት ይህን አያክልም ቢል፤ ወይም ይህን አገልግሎት እየሠጠ አይደለም ብሎ መጠየቅ እና ምላሽ ማግኘት ይችላል። በሌላ በኩል ሊለካለትም ይችላል።
አሁን ባለኝ ግንዛቤ ከዚያ ቢሮ ጋር ባለኝ ግንኙነት በሁሉም የጋራ መኖሪያ ቤት ልኬት የሚያስፈልግበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን ለአንዱ ቤት የተሟላ መረጃ ተይዞ በሌላ በኩል መረጃ የሌለው የጋራ መኖሪያ ቤት ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ተመሳሳይ ሕንፃ ላይ ሆኖ የተጓደለ መረጃ ካለ የአንደኛው ተለይቶ ሊለካ ይችላል። ስለዚህ በዚህ መልኩ ልኬት የግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ። የማያስፈልግበት ሁኔታም አለ። አከፋፈል ላይም ተጨማሪ ክፍያ የሚያስፈልገው አለ። ለዚህ የመሬት ቢሮ ቢጠየቅ ይሻላል።
አዲስ ዘመን፡- ከግብር አከፋፈሉ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ግንዛቤ ተፈጥሯል? በአስቸኳይ እንድንከፍል መደረጉ ተገቢ አይደለም ከሚለው አስተያየት አንፃር ምን ይላሉ?
አቶ ዘገየ፡- የግንዛቤ ጉዳይ ሲነሳ ከተማው ሰፊ እና ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት በመሆኑ ሁሉም ጋር ግንዛቤው ተፈጥሯል ለማለት አልችልም። ነገር ግን በጥናቱ ጊዜም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሞያዎች፣ የሥራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ ሠራተኞች እንዲሁም በአንድም በሌላ መልኩ የግብር ከፋዩ ተወካዮች ተሳትፈዋል። የጥናቱን ግኝት ወደ ሥራ ይዘነው ስንመጣ እነዚህ አካላት በደንብ ያውቁታል። ዋናው ነገር ከላይ እንደገለፅኩት ግብሩ አሁን የተፈጠረ ርዕስ አይደለም።
የተሠራው የግብሩን ተመን ወቅታዊ ከማድረግ በስተቀር ምጣኔ እንኳን አልተሻሻለም። በጥናት የተሻሻለው ያውም አሁን ከተማዋ ባለችበት ሁኔታ ስንት ሕዝብ እየተከራየ ነው? ኪራይ ደግሞ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ይከራያሉ። እነዚህ ሁሉ የጥናት ግብዓት ሆነዋል። ቃለመጠይቅ ተደርጎ በብዙ ሒደት ውስጥ አልፎ በጥናት የተገኘ ስለሆነ ሁሉም ሰው ጋር በአንድ ጊዜ ግንዛቤው ተፈጥሯል ባይባልም፤ በብዛት ግን የሚመለከታቸው አካላት እንዲሳተፉበት ተደርጓል። ከላይ እንደገለፅኩት እስከ ታች ድረስ መዋቅር ስላለ ግብሩን የመሰብሰብ እና የማሳወቅም ሥራ ይሠራል። ከከተማው ስፋት እና ከግብር ከፋዩ መጠን አንፃር ካየን ግን ሁሉም ሰው ጋር በተመሳሳይ መልኩ መልዕክት ደርሷል የሚል ድምዳሜ የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- የተሰጠው የግብር መክፈያ ጊዜ አጭር ነው መባሉስ ?
አቶ ዘገየ፡– ግብር የመክፈያ ጊዜው እንደሚታወቀው እየተጠናቀቀ ነው። እስከ ሰኔ 30 እንዲከፈል ብለናል። እንዲያውም መከፈል የነበረበት እስከ የካቲት 30 ነበር። የካቲት 30 ባይከፈልም እስከ ሰኔ 30 እንዲከፈል ብለናል። ሰኔን አልፎ ወደሚቀጥለው ዓመት ከሔደ ስለሚደረብ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል። ስለዚህ እስከ ሰኔ 30 እንዲከፈል እናበረታታለን። በእኛ በኩልም ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን። ስለዚህ ጊዜው ያጠረው በበጀት ዓመቱ ውስጥ መሰብሰብ ስላለበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ ክፍያ ለመፈፀም መጨናነቆች እየተፈጠሩ ናቸው። ግብር ከፋዮች በአንድ መስኮት አገልግሎት መሰጠት እያለባቸው የተለያየ ቦታ ላይ እንዲሄዱ እየተገደዱ ስለመሆኑ እየገለፁ ናቸው። ለምሳሌ ልኬትን በተመለከተ ከወረዳ ወደ ክፍለ ከተማ፤ እንዲሁም ወደ ንግድ ባንክ እየተላኩ በወረፋ እየተንገላቱ ስለመሆኑ እየገለፁ ነው። ይህንን በተመለከተ ምን ይላሉ?
አዲስ ዘመን፡- እንግዲህ ሌሎች ግብሮች፤ ለምሳሌ የ2014 ዓ.ም የግብር መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 2014 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 የነበረውን የቴክኖሎጂ ሲስተማችንን በማሻሻል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሥራት ግብር ከፋዩ እንዳይንገላታ አድርገናል። ለምሳሌ ግብር ከፋዩ ወደ እኛ ሳይመጣ በእጅ ስልኩ መልዕክት እንዲደርሰው በማድረግ በቴሌ ብር ግብር እንዲከፍል አድርገናል። በተለይ ደረጃ ‹‹ሐ›› የሚባለው መክፈል የሚገባው ግብር በቴሌ ብር ወይም በባንክ ሔዶ እንዲከፍል ብዙ ሁኔታዎችን አመቻችተናል። ይህ ግን ሳይከፍሉ የዘገዩ ናቸው።
ልኬት የሚመጣው ከመሬት ቢሮ ነው፤ እኛ ቢሮ ተጀምሮ እኛ ቢሮ ላይ የሚጠናቀቅ አይደለም። ስለዚህ ድካም ሊኖረው ይችላል። እኛ ግን በፍፁም የግብር ከፋዩን ድካም ለመቀነስ በአነስተኛ ጊዜ ግዴታውን ተወጥቶ መብቱን አግኝቶ መሔድ እንዳለበት በመንግሥት ታምኖበት እየተሠራ ነው።
በአንዳንድ ቅርንጫፎች በተለይም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አካባቢ ሰው በዝቶ እየተቸገሩ መሆኑን አይተናል። የሰው ኃይል ከሌላ ክፍል በማንቀሳቀስ እንግልቱን ለመቀነስ እንሠራለን፤ ምናልባት ሰኔ ሙሉውን መክፈል ስለሚቻል። ሁሉም ይህቺኑ ጊዜ ተጠቅሞ አጠናቆ ቢሔድ ጥሩ ነው።
ነገር ግን አሁንም ግብር ከፋዮቻችን በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን መቼም ቢሆን ግብር ከፋዮች የሚሔዱት በመጨረሻዎቹ ቀኖች አካባቢ ነው። ከቀን 26 በኋላ ወደ ቅርንጫፎቻችን ሲኬድ በጣም ብዙ ሰው ተሰልፎ ይታያል። ከ10 እስከ 15 ደግሞ ማንም ላይኖር ይችላል፤ ስለዚህ ጫና እያመጣ ያለው የግብር ከፋዩም የሚከፍልበት ጊዜ ነው።
ነገር ግን በምንም ሁኔታ ተጨማሪ የሰው ኃይል በማምጣት እና ተጨማሪ ጊዜ በመስጠት አሁን ያሉትን ጫናዎች ለመቋቋም ጥረት እናደርጋለን። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ እንደሌሎች ግብሮች ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በቀነሰ ድካም እና እንግልት ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን ተወጥተው መብታቸውን እንዲያገኙ እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- የተመኑ ሁኔታ እና አከፋፈሉ ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑን በሚመለከት ቅሬታዎች በመቅረብ ላይ ናቸው። ይህንን በተመለከተ ያለው ነገር ምንድን ነው ?
አቶ ዘገየ፡- ከላይ እንደገለፅኩት ነው። ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት እና ደረጃ ሦስት የሚባሉ ቦታዎች አሉ። ካሬው ተመሳሳይ ቢሆንም ደረጃው የተለያየ ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- እርሱ ትክክል ነው። ነገር ግን አከፋፈሉ ላይ በአንድ ይዞታ ላይ የቤቱ ግንባታ የተለያየ ሲሆን ፤ ማለትም አንድ ሰው 50 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የጭቃ ቤት እና 100 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የድንጋይ ቤት ቢኖረው ሙሉ ለሙሉ የድንጋይ ቤት እንደሆነ ተቆጥሮ፤ በድንጋይ ቤት ተሰልቶ ይከፈላል።
አቶ ዘገየ፡- የድንጋዩ ቤት ከበዛ መመሪያው እንደሚለው እንደ ድንጋይ ወይም 150ውም እንደብሎኬት ቤት ይወሰዳል።
አዲስ ዘመን፡- ይሔ ሁሉም ክፍለ ከተማ ላይ አሠራሩ አንድ ነው ?
አቶ ዘገየ፡– ከክፍለ ከተማ ክፍለከተማ የተለያየ አሠራር አይኖርም። አንድ ግለሰብ የአሠራር ልዩነት አለ የሚል ከሆነ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል። ልኬትም ላይ ችግር ሊኖር ይችላል። 150 ካሬ ሜትር ቤት 250 ነው ከተባለ ግለሰቡ ቅሬታ አስገብቶ እንደገና እንዲገመትለት ማድረግ ይቻላል። የእያንዳንዱን ግለሰብ ጉዳይ እያነሳን አጋነን ማቅረብ የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- አንደኛው አሠራሩ ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ የተለያየ ነው የሚባለው አንዳንዱ ቦታውን ለክቶ ሲያስከፍል፤ አንዳንዱ ደግሞ ካርታን መሠረት አድርጎ ብቻ ያስከፍላል የሚል ነው?
አቶ ዘገየ፡– ልኬት የሚኖረው የተደራጀ መረጃ ሳይኖር ሲቀር ነው። እንዲያውም እኛ መለካት አንፈልግም። ነገር ግን መረጃ ከሌለ ሊለካ ይችላል። ነገር ግን እንደአቅጣጫ ልኬት አይኑር ብለናል። ይሔ ከብዙ ሰው ውስጥ የአንድ ሰው ፋይል ላይኖር ይችላል። ይህ ከብዙ አንድ ቢያጋጥም ነው። ድርጅት ወይም የግለሰብ ቤት፤ ወይም ፎቅ ሊሆን ይችላል። መረጃ ባይኖርም ግብሩ መከፈል ስላለበት በራሱ በግብር ከፋዩም ጥያቄ ሊለካ ይችላል። በቂ መረጃ ከሌለ ሰውየው ላይ ጫና እንዳይፈጠር ወይም የመንግሥትም ጥቅም እንዳይጎድል ልኬት ሊከናወን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ ለሚያቀርበው ቅሬታ ምላሽ መሰጠት እና ግልፅነት መፍጠር አለበት?
አቶ ዘገየ፡– ግልፅ ሊሆን የሚገባው ልኬቱ መሠረት የሚያደርገው ቤቱ የተሠራበት ግብአት እና ቤቱ የሚሰጠው አገልግሎት ነው። መኖሪያ ነው ወይስ የንግድ፤ የቤቱ ስፋት እንዲሁም ቤቱ የሚገኝበት የከተማ ደረጃ ነው። እንዲያውም በመሬት ማኔጅመንት እስከ ደረጃ 18 ነው። እኛ ግን ከሦስት በኋላ ያሉት ስለሚቀራረቡ ደረጃ ሦስት ብለን ይዘናል። ይሔ መመሪያው ላይ በትክክል ስለተቀመጠ ችግር የለውም። አፈፃፀሙ ላይ ችግር የገጠመው ሰው ማለትም በቦታው ስፋት መጠኑ ከተለያየ፤ ቤቱ መኖሪያ ሆኖ የንግድ ከተባለበት ወይም ደረጃ አንድ ሆኖ ደረጃ ሦስት ከሆነ ይህ ሰው ቅሬታ ማቅረብ ይችላል።
እስከ አሁን ስንሠራም በአፈፃፀም ላይ በቸልተኝነት ወይም በተለያየ ምክንያት ስህተት ሊፈጠር ይችላል። ስህተት ሲሠራ ደግሞ ይህ ሊፈጠር እንደሚችል በመገመት መንግሥት ማረሚያ መንገድ አለው። የታክስ ሕጉ ላይ ራሱ ቅሬታ የሚሠማበት አሠራር አለ። ከቅርንጫፍ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ቅሬታ ማቅረብ ይቻላል። ስለዚህ ይህም ተመሳሳይ ነው። ቅሬታ ማቅረብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ግብር ላይ ከተፈጠረው ብዥታ መካከል አንዱ ግብሩ የንብረት ነው ወይም ፕሮፐርቲ ታክስ ነው ይባላል። እርሶም ሆኑ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሉት ይህ የንብረት ግብር አይደለም እያላችሁ ነው። ወደፊት የንብረት ግብር አለ ማለት ነው?
አቶ ዘገየ፡- አዎ የንብረት ግብር ገና ሕግ አልወጣለትም። ረቂቁ እየተዘጋጀ ሃሳብ እየተሰጠበት ነው። ስለዚህ ስለሱ ማውራት የሚቻለው ገና ሕጉ ሲወጣ ነው። ምን ምን ነገሮች ታሳቢ ይደረጋሉ፤ ምን ተጨማሪ ነገሮችን ያመጣል የሚለውን ማውራት የሚቻለው ወደ ፊት ነው። የአሁኑ አዋጅ 80 1968 ነው። ደንቡም 30 1968 ነው። የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር ነው። አሁን ቦታው ላይ ትኩረት ስላላደረግን ከአዋጁ ጋር እንዲጣጣም የቤት ግብር ብለን ወስደነዋል።
አዲስ ዘመን፡-ሌላ መናገር የሚፈልጉት ነገር ካለ?
አቶ ዘገየ፡– በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን እንደተነገረው አዲስ ነገር አልመጣም። ወሬው ትክክል አይደለም፤ ከላይ እንደገለፅኩት ነባር የግብር ዓይነት እየተሰበሰበ ነው። ኪራዩን ወቅታዊ ማድረግ በጣም ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌላ ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ሊያመነጩ እና መልሰው ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ የአገልግሎት ተመኖችን ወይም የገቢ ሁኔታዎችንም በተጨማሪነት ማየት ሊያስፈልገን ይችላል።
ኅብረተሰቡ ዞሮ ዞሮ ከራስ ለራስ የሚከፍል ስለሆነ ለራሱ መሠረተ ልማት ተደራሽ ለማድረግ የሚሰበሰብ በመሆኑ፤ ቀደም ሲል ከአንድ ብር ጀምሮ ሲከፈል ነበር። አሁን ግን እንኳን በአንድ ብር በአስር ብርም የሚገዛ ምርትም ሆነ የሚገኝ አገልግሎት የለም።
አሁን ከአንድ ብር ጋር በማነፃፀር ዛሬ ከቁጥር አንፃር ሦስት እና አራት ሺህ ብር ክፈል ሲባል፤ ተገቢ አይደለም ሊል ይችላል። ነገር ግን እኛ እንደመንግሥት በየጊዜው እያሻሻልን ማስከፈል ሲኖርብን አለማስከፈላችን እንጂ፤ አሁን ክፈሉ የተባለው ተገቢ ክፍያ ነው። ስለዚህ በዚሁ መሠረት ሕዝቡ ግብሩን እየከፈለ መብቱን እንዲጠይቅ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄ ካለ ግን በማንኛውም መልኩ ለማስተካከል ዝግጁ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠትዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
አቶ ዘገየ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2015