በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምድ ከበርካታ ዓመታት በፊት በጋዜጣው ለንባብ ከበቁ ዘገባዎ መካከል በብዛት ወንጀል ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩትን መራርጠናል:: ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችም ተካተዋል:: ከእነዚህም መካከል የሰማዕታት ሐውልት ስለ መመረቁ ፣ በወረባቡ አካባቢ ድርቅ በእጅጉ አስግቷል መባሉ፣ ሐሰተኛ ወሬን ሲያሰራጭ የነበረው ግለሰብ ተይዞ ለፍርድ ስለመቅረቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ 110 ታኒካ ማር በቤቱ ደብቆ ስለተገኘው ግለሰብም የወጣ መረጃን መለስ ብለን እናስታውሳለን:: በተጨማሪ ማህበረሰቡ በሳምንቱ ካጋጠማቸው ነገሮች መካከል ለአንባብያን ከሚያቋድሱበት “የሳምንቱ አጋጣሚ” ከተሰኘው ገጽ ላይ ሁለቱን በመቀንጨብ አቅርበናል::
የሰማዕታት ሐውልት ተመረቀ
(ኢ.ዜ.አ)- ለሰላም ለዴሞክራሲና ለፍትህ መከበር ሲታገሉ በደርግ በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች መታሰቢያ ከሃምሳ ሺ አንድ መቶ ሰባ አምስት ብር በላይ ወጪ በጎንደር ከተማ የተሰራው ሐውልት ተመረቀ::
በደርግ አገዛዝ አስራ ሰባት አመታት የተከፈለውን መራራ ትግል የሚያንጸባርቁ ቅርጻ ቅርጾች የሰፈሩበት ይሄው ሐውልት በተመረቀበት ወቅት አቶ ታደሰ ካሳ የክልሉ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ባሰሙት ንግግር የጀግኖች ሰማዕታት በተገኘው የዲሞክራሲ መድረክ ላይ ቆመን መብታችንን በአግባቡ በመጠቀም ዘላቂ ጥቅማችንን ለማስከበር ስንችል ነው ሲሉ አስገንዘበዋል::
……………………
በዚህም ሥነ ሥርዓት ላይ ከሃያ ሺህ በላይ ሕዝብ ተገኝተል::
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 1987 ዓ.ም)
በወረባቡ ወረዳ ድርቅ አስግቷል
ደሴ፣ (ኢ.ዜ.አ)- በአምባሰል አውራጃ በወረባቡ ወረዳ በቆላው ክፍል አምሮና ገበሬዎችን አጓግቶ የነበረው የእህል አዝመራ በዝናብ እጥረት ምክንያት በእንጭጩ ጠውልጎ ከጥቅም ውጪ ወደመሆን ደረጃ መድረሱ ተገለጠ።
የወረዳው አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈልን ሪፖርት እንዳረጋገጡት በተለይ በቆላማው ክፍል በሚገኙት ሐደሬ፣ ኤጀርሳ፣ ጎደታና ዱበታ በተባሉት ቀበሌዎች የተዘሩት ማሽላ፣ ጤፍ፣ሰሊጥ፣ በቆሎ፣ ምስርና አተር በሚያሳዝን ሁኔታ ከመድረቃቸውም የተነሳ ገበሬዎቹ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን የለየላቸውን እየመረጡ ለከብቶች መኖ በማጨድ ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል።
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 1968 ዓ.ም)
ተደብቆ የተገኘ 110 ታኒካ ማር ለመንግሥት ገቢ ሆነ
ጎባ፣(ኢ.ዜ.አ)- በጎባ ከተማ የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን ለማጋለጥ እንዲቻል ፍተሻ በተደረገበት ወቅት ከአንድ ነጋዴ ቤት ተደብቆ የተገኘ 110 ታኒካ ማር ሰሞኑን በጨረታ ተሸ ገንዘቡ ለመንግሥት ገቢ ሆኗል።
…………..
በሌላ በኩል ደግሞ በጊኒር ከተማ ሰሞኑን በተደረገው አሰሳ በ13 አሻጥረኛ ነጋዴዎች ሱቅና መኖሪያ ቤት ውስጥ ግምታቸው $2,291 የሆነ ልዩ ልዩ እቃዎች ተደብቆ ተይዘዋል።
ከእነዚህ አሻጥረኛ ነጋዴዎች ሱቅና መኖሪያ ቤት ተደብቆ የተገኘው በርበሬ፣ ክብሪት፣ ቅቤ፣ ጨው፣ ቀዝቃዛ መጠጥና ማር መሆኑን አንድ የማዘጋጃ ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጧል። (አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 1969 ዓ.ም)
የገበሬዎች ማኅበር የተደበቁ የጦር መሣሪያዎች አገኘ
ነቀምቴ፣(ኢ.ዜ.አ)- በቄለም አውራጃ የጋዋቄዴ ወረዳ ገበሬዎች ማኅበር ሰሞኑን ባደረገው አሰሳ አራት ጠመንጃና 21 ልዩ ልዩ አይነት ጥይቶች ከተደበቁበት ቦታ አግኝቷል። የተያዙት መሣሪያዎችና ጥይቶች በገበሬው ማኅበር ዕቃ ግምጃ ቤት ገቢ ሆነዋል።
(አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 1969 ዓ.ም)
ቪዲዮ ቤቶች ተዘጉ
አሰላ(አ.ዜ.አ)- በአርሲ መስተዳድር ዞን በአሰላ ከተማ በሕገወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤቶች በድብቅ የስርቆትና የብልግና ፊልሞች ያሳዩ ከነበሩ ቪዲዮ ቤቶች መካከል ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆኑት በቁጥጥር ስር መቃላቸውን የአሰላ ሲኒማ ቤት ገለጠ::
ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተቁአቁአሙት እነዚህ የቪዲዮ ፊልም ቤቶች ለመንግሥት መክፈል የሚገባውን ቀረጥ ሳይከፍሉ ፊልሞችን በድብቅ በማስገባትና ወጣቶች ዘግናኝ የሆኑ ፊልሞችን እንዲመለከቱ በማድረግ ሥነልቦናቸውን ከመስረቅ ባሻገር ወርቃማ የትምህርት ጊዜያቶችን በመሻማት ጭምር ችግር ፈጥረው እንደነበር የሲኒማ ቤቱ ገልጦአል:: (አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 1972 ዓ.ም)
የሐሰት ወሬ ያሰራጨው ተቀጣ
አዲስ ዓለም ,(ኢ.ዜ.አ)- የገጠር መሬት የሕዝብ እንዲሆን በወጣው አዋጅ ተደናግጦ የሐሰት ወሬ ሲያሰራጭ የተገኘው ደመቀ ለገሰ በስድስት ወር እስራት እንዲቃጣ ሰሞኑን ተወስኖበታል:: (አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 1968 ዓ.ም)
ተቆጣጣሪ በመምሰል ያጭበረበረው ተቀጣ
ደሴ፣ ኢዜአ በደሴ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት ሥልጣን ሳይኖረው የአሥር አለቃ ነኝ በማለት ከገጠር ወደ ከተማ የሚገባውንና የሚወጣውን እህል፣ ስኳርና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በመፈተሽ ሲያወናብድ የተገኘው ዓሊ መሐመድ በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የ04-01-01 ቀበሌ ማኅበር የፍርድ ሸንጎ ከትናንት በስቲያ ወስኖበታል።
በተከሳሹ ላይ የእስራት ቅጣት ሊወሰንበት የቻለው ባልተሰጠው ሥልጣን በመንገድ ላይ እየጠበቀ ስኳርና ሸቀጥ ጭነው ወደ ገጠር የሚወጡትንና እህል ጭነው ወደ ከተማ የሚገቡትን መኪናዎች እያስቆመ በመፈተሽ የተመቸውን ጥቅም በመቀበል ሲለቅ ያልተመቸውን ደግሞ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በማቅረብ አወናብዶ ለማስቀጣት ሞክሮ እንደነበር በማረጋገጡ ነው:: (አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 1969 ዓ.ም)
የሳምንቱ አጋጣሚ
እሁድ እለት አንባሳደር ቡና ቤት ቁጭ ብለን ሻይ ስንጠጣ አንድ የምናውቀው ሰው በመጠጥ ኃይል ተሸንፎ መዝጊያውን የከፈተ መስሎት ከመስተዋት ጋር ሲታገል በማየታችን በጣም አስቆናል::
ሺመክት አለሙ
ከአዲስ ከተማ
……………
አንድ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጭ ልጅ ለአንድ የውጭ ዜጋ ታይም መጽሔት ለመሸጥ በሚያሳየው ጊዜ የውጭ ሰው ሐውማች ብሎ ሲጠይቀው ልጁ ጣቱን እያሳየ ዋን ብር ዋን ስሙኒ ብሎ መለሰለት:: (አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 1968 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2015