መልከ ሙሴ እንደ ሙሴ
ሆነው መሩት ስንቱን ጊዜ
በእጆች እጅ ውዝዋዜ
አበራዩት ያን ትካዜ።
ካስተማሩን ትምህርቶች
ከነገሩንም ተረቶች
ገና ሲሉን ልጆች ልጆች
ወደድናቸው እኚያን እጆች።
ከልጅነት ትዝታ
ከአፍላነት ጨዋታ
ካቋደሱንም ስጦታ
እንዴት ልርሳ ያን ውለታ።
የአባትነት ግሩም ለዛ
በኢትዮጵያዊነት የወዛ
ዘነጋነው በፈዛዛ
ያንቱን ፍቅር እንደዋዛ።
ባስተማሩን ሁሉ ትምህርት
በነገሩን ሁሉ ተረት
ያገር ፍቅር መንታ እውቀት
ጣፋጭ ዘቢብ ቃል አለበት።
እንደ እጣን ሲያውደን
እንደ ከርቤ እየማግን
ያንን ጣፋጭ አጣጥመን
ከልጅነት ተሻገርን።
ከተረቱ ሲተርቱ
አብረው ከእኛው ሲጫወቱ
የፍቅር ልክ ከነእትብቱ
አይተን ነበር እኛስ ባንቱ።
የሕይወት ስንቅ ሲያጎርሱን
ጥኡም ፍቅርን ሲያቀምሱን
እንደ ሙሴ እየመሩን።
በአንቱ ቃል ገነት ገባን።
እኛ ግን
ያን ውለታ እረሳን
የነገሩንን ዘነጋን
ያጎረሰን እጅ ነክሰን
ይሄው አለን እንደነበርን።
………
ስለ አባባ የተስፋዬ
ከንቱ እንዳይሆን ውዳሴዬ
ለኢትዮጵያዊው ለኛ ሙሴ
አባ አባ ትበል ነብሴ።
ባለፈው ሳምንት የአባቶች ቀን መከበሩን ተከትሎ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት የሆኑትን አባባ ተስፋዬን አለማሰብ ከባድ ነውና በዛሬው የዝነኞች ገፃችን ስለእሳቸው እንደ ነገሩ በቋጠርኳቸው ስንኞች ለመጀመር ተነሳሳሁ። ስለ እኚህ ታላቅ አባት በቃላት ጀምሮ በቃላት ለመጨረስ ከንቱ ድካም ቢሆንም ከሕይወታቸው ምንጭ የተቀዱ አንዳንድ ነገሮችን ከብዙ በጥቂቱ እንቃኝ።
አባባ ተስፋዬ በምድር ላይ እንደ ሙሴ አንድ ጊዜ ብቻ ብቅ ብለው ዳግም በማንም ያልታዩ የትውልድ አሻጋሪ እውነተኛ ፋና ወጊ አባት ናቸው። አባባ ተስፋዬን የመሰለ የኢትዮጵያ ልጆች ድልድይ ከእሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ እስከዛሬም ድረስ አልታየም። እንደ ዛሬ ሚዲያዎች ባልበዙበት ዘመን ከአንዲት የቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው በመላው ኢትዮጵያ ከገጠር እስከ ከተማ በሁሉም ልጆች ልብ ውስጥ ነግሰዋል። ዛሬም ድረስ በሁሉም አዋቂዎች ዘንድ ስማቸው የናኘ እንደ አባባ ተስፋዬ ማን አለ?
የእሳቸው ምክር ልክ እንደ ሙሴ በትር ነበር። ከቴሌቪዥን መስኮት ሆነው ምክራቸው እለቱን እየሰነጠቀ ተግሳጻቸው ልብን ይከፍላል። ብድግ በሉ ሲሉን ብድግ እያልን ቁጭ በሉ ሲሉን ቁጭ ያልንስ ስንቶቻችን ነን። አጠገባችን ሳይኖሩ አጠገባችን እንዳሉ እያሰብን የሚሰጡንን አባታዊ ፍቅር የተቋደስንስ እልፍ ነን። ገና በቴሌቪዥን መስኮት እጃቸውን እያውለበለቡ ብቅ ሲሉ ‹‹እንደምን አላችሁ ልጆች የዛሬ አበባዎች፣ የነገ ፍሬዎች›› የሚላት የተለመደች መግቢያቸው ዛሬም ድረስ በብዙዎች ጆሮ ታቃጭላለች።
በተረት ተረት ሳህን ምክርን ከፍቅር ጋር እየለወሱ አብልተው አጠጥተውናል። በልጅነታችን፣ ለልጅነታችን የቋጠሯቸው በርካታ ቁምነገሮች ለብዙዎች ዛሬም ድረስ የሕይወት ስንቅ ሆነዋል። ያ ሁሉ ውለታቸው በሕይወት ዘመናቸው መገባደጃ እንደ አመድ ብናኝ ቢሆንም ለብዙዎች ህያው ናቸው። አባባ ተስፋዬ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጆች አባት፣ ሁሉም ደግሞ የእሳቸው ልጅ ነበር። የልጅነት ጊዜያችንን እንደ አበባ አፍክተው እንደ ዘንባባ አለምልመውታል። በምክር እየኮተኮቱ በፍቅር አሳድገውናል። ‘ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ’ እንዲሉ በጊዜው የልጅነት ሕይወቱን በአባባ ተስፋዬ ያጣጠመ ስለእሳቸው በደንብ አድርጎ ይመሰክራል።
አባባ ተስፋዬ ጥለውት ያለፉት ቅርስ ዛሬም በበረከቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ምትክ ያልተገኘለት መማሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። ለዚህም ነው የዚህ ዘመን ልጆች ሳይቀሩ የኚህን ታላቅ አባት ዝና የሚያውቁት።
አባባ ተስፋዬ ሳህሉ ወይም የተረት አባት በወርሃ ሰኔ 1916 ዓ.ም በባሌ ክፍለ ሀገር ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢወርቅ በለጠ ተወለዱ። የአባታቸው መጠሪያ ስም ሳህሉ የሆነው በድንገት ነበር። በአንድ ወቅት ትንሽ ልጅ እያሉ የአባታቸውን ስም ሲጠየቁ ሳህሉ ብለው ይመልሳሉ። ያሉበት ምክንያት ደግሞ አባታቸው ይሰራ የነበረው በራስ እምሩ ስር ምክትል ኃላፊ በነበሩት ፊታውራሪ ሳህሉ ክፍል ስለነበረና ለፊታውራሪው ያላቸው ፍቅር የተለየ ስለነበረ ነው። የልጅነት ሕይወታቸው እጅግ በጣም በፈተና የተሞላና በብቸኝነት አለንጋም የተገረፉበት ነበር። ቀደም ሲል የተደላደለና ጥሩ የልጅነት ሕይወት ነበራቸው። በልጅነታቸው የአባታቸውን ሹመት ተከትሎም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያመሩ ነበር። ሐረር በገቡበት ወቅትም በፈረንሳዮች ትምህርት ቤት በሆነው በጊኒር ትምህርት ቤት እንዲሁም በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከአስኳላው ትምህርት ባሻገርም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችንም በቤተክርስቲያን ውስጥ ተምረዋል። ሕይወትን ጀምረው ገና በማጣጣም ላይ ሳሉ ድንገት ነገሮች ተዘበራረቁ። ወደ ሀገር የገባው ጭለማ ወደ እሳቸው ሕይወትም ዘልቆ ገባ። መድፍና ታንክ ተሸክሞ አዲስ አበባን የወረራት ፋሽስቱ ጣሊያን ቤተሰቦቻቸውን አንድ በአንድ ለሞት ማገዳቸው። አባባ ተስፋዬ ብቻቸውን ቀሩ።
በዚያው ወቅት እግራቸውን በጣም ያማቸው ስልነበር ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ገብተው ህክምና ተደረገላቸው። ከህመማቸው ካገገሙ በኋላ ቅልጥፍናቸውን የተመለከተ አንድ የፋሽስት ዶክተር በጣም ስለወደዳቸው ከዚያው ከሆስፒታሉ እንዲቀመጡ አደረጋቸው። የሕክምና ቁሳቁሶችን በማጠብና በመላላክም ያገለግሉ ጀመር። የጣሊያንኛ ቋንቋንም የተማሩት እዚሁ ነበር። ነገሮችን የመቀበልና የመከወን ልዩ ችሎታቸውንም በመመልከት በአንድ ሆቴል ውስጥ ምክትል ኃላፊ አድርጓቸው ነበር።
ከእለታት በአንዱ ቀን አጼ ምንሊክን እወደዋለሁ ስላሉ አንዱ የፋሽስት ወታደር እንደገረፋቸው አባባ ተስፋዬ በአንድ አጋጣሚ ተናግረው ነበር። 1957 ዓ.ም የአባባ ተስፋዬ የውለታቸው ግንድ ማቆጥቆጥ የጀመረበትና ለእሳቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ ልጆች ልዩ ዓመት ነበር። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመሰረተ። አባባ ተስፋዬም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በጣቢያው የልጆች ፕሮግራም እንዲኖር የራሳቸውን የፈጠራ ንድፍ በመንደፍ ሃሳቡን አቀረቡ። ፈጠራቸው ተቀባይነትን በማግኘቱ ስራቸውንም አሐዱ ብለው ጀመሩ። ልዩ በሆነው አቀራረባቸውና የልጆች አያያዝ ችሎታቸው እንደተወደዱና እንደጣፈጡ ለ42 ዓመታት ገደማ በጣቢያው የልጆች ፕሮግራም ላይ ሰነበቱ። ነገር ግን በጣቢያው እንደነበራቸው ቆይታና እንደባለውለታነታቸው የመጨረሻው የስንብት ጊዜያቸው ያማረ አልነበረም። በጣቢያው የነበራቸው ቆይታ ያከተመ መሆኑን የሚገልጽ ባለሁለት መስመር ደብዳቤ የስንብታቸው የመጨራሻ እጣ ፈንታ ሆነች።
አባባ ተስፋዬን የምናውቃቸው በተረት ተረት ቢሆንም እሳቸው ግን ዘርፈ ብዙና ተሰጥኦ ሙሉ የነበሩ ሰው ናቸው። ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ደራሲ (የልጆች ተረት)፣ ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የምትሃት (አስማት) ባለሙያም ነበሩ። በዘመነ ጃንሆይ አባባ ተስፋዬ አንድ መድረክ ላይ ትርኢት እንዲያቀርቡ ታጅበዋል። በእለቱ ጃንሆይ ከፊት ለፊት በክብር ተቀምጠዋል። ትርኢቱ ደግሞ የአስማት ወይንም ምትሃት ነው። አስማተኛው አባባ ተስፋዬ ከመድረኩ ላይ ወጡና በእጃቸው የያዟትን አንዲት እንቁላል ካሉበት ሆነው እያዞሩ ለታዳሚው አስመለከቱት። ከዚያም ከመቅጸብት ወደ አፋቸው ሰደው ዋጥ አደረጓትና ሁለቱንም እጃቸውን አንስተው እንቁላሏ ከእጆቻቸው ውስጥ እንደሌለች አረጋገጡላቸው። ነገሩን በአንክሮ ሲከታተሉ የነበሩት ጃንሆይም ስቅጥጥ ቢላቸው ጊዜ “አንተ በል ቶሎ ትፋት” ሲሉ አምባረቁባቸው ይባላል። በወቅቱ አባባ ተስፋዬ በርካታ የአስማት ትርኢቶችን ያሳዩ ነበር። አስማት ይባል እንጂ ነገሩ የውሸት ወይም ‘ትሪክ’ መሆኑን ቆየት ብሎ አባባ ተስፋዬ ይናገሩ ነበር።
አባባ ተስፋዬ የተዋጣላቸው የመድረክ ቲያትር ባለሙያም ናቸው። ከተሳተፉባቸው የመድረክ ቲያትሮች መሃከል ‘ሀ ሁ በስድስት ወር’ ፣ ‘ኤዲፐስ ንጉስ’፣ ‘አሉላ አባነጋ’፣ ‘ዳዊትና ኦርዮን’፣ ‘ኦቴሎ’፣ ‘አስቀያሚዋ ልጃገረድ’ና ‘ስነ ስቅለት’ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በቲያትር መድረክ ላይ መተወን ብቻ ሳይሆን ቲያትርን ጽፎ ማዘጋጀትም ይችሉበታል። ‘ብጥልህሳ’፣ ’ ነው ለካ’ እና ‘ጠላ ሻጯ’ የተሰኙትን ቲያትሮች ደርሰዋል።
ወደ ኮሪያ ካቀናው ታሪካዊው የኢትዮጵያ ወታደር ውስጥ አባባ ተስፋዬ አንዱ ነበሩ። እዚያው ኮሪያ ውስጥ እያሉ ጠላ ሻጭዋ የተሰኘውን ቲያትር ለማሳየት በዝግጅት ላይ ሳሉ የጠላ ሻጯን ገጸ ባህሪ ወክላ የምትጫወት ሴት ትጠፋለች። አባላቱ ግራ ገብቷቸው ምን እናድርግ እያሉ ሲወያዩ ሳለ አባባ ተስፋዬ ቀረብ አሉና ጠላ ሻጯን እኔ ወክዬ እጫወተዋለሁ ሲሉ ተናገሩ። ይሄኔ አጠገባቸው የነበረ ቤተሰቦቻቸውን የሚያውቅ አንድ ወታደር ወደ አባባ ተስፋዬ ዞር አለና “አንተ የጀግና ዘር ሆነህ ይህንን እንዴት ታደርጋለህ፣ እንዲህ ብለህ ስትናገር ቤተሰቦችህ ቢሰሙህ ኖሮ ይገሉህ ነበር“ አላቸው። አባባ ተስፋዬ ግን ልባቸውን የነሸጠውን የጠላ ሻጯን ገጸ ባህሪ ወክለው በብቃት ተወኑት።
አባታዊ ለዛ ታጅበው ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ እየቀረቡ ተረት በማውራት ህፃናት ልጆችን ሲያንፁ የኖሩ ታላቅ የሞራል መምህር ነበሩ። አባባ ተስፋዬ ከ1937 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ለ8 ዓመታት፤ በኢትዮጵያ ቲያትር ቤት ደግሞ ከ50 ዓመታት በላይ የተለያዩ ቲያትሮችን በመስራት ለኪነ-ጥበቡ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
የአባባ ተስፋዬ ውለታ በኢትዮጵያ ልጆች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊ የገዘፈ ቢሆንም ለብዙ ዘመናት በሕይወት መኖራቸው እንኳን እስከማይታወቅ ተረስተው ኖረዋል። የጻፉዋቸው አራት የተረት ተረት መጽሃፍትን ጨምሮ ለቁጥር የሚታክቱ ስራዎቻቸው ለትውልዱ በቅጡ ሳይደርሱ ቀርተዋል። እሳቸው ግን በእድሜ አንድ ምእተ ዓመት ሊያስቆጥሩ ጥቂት በቀራቸው ጊዜ እንኳን ፈጽሞ የእርጅና ስሜት አይታይባቸውም ነበር። በቪዲዮ ካሴት የታጨቁትን የዘመናት ስራዎቻቸውንና መጽሃፍቶቻቸውን በየቦታው እየዞሩ ይሸጡ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ተቸግረው አሊያም ገንዘብ ፍለጋ አይደለም። አላማቸው ችላ ተብለው የቀሩትን ትውልድ ገንቢ የነበሩ ስራዎቻቸውን ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ነበር።
አባባ ተስፋዬ ለሰሩት ስራ በጊዜውና በሰዓቱ ተገቢውን እውቅናና ሽልማት ባይበረከትላቸውም ዘግየት ብሎም ቢሆን የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት ችለዋል። በኮሪያው ዘመቻ ስላበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦም ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የኮሪያው አምባሳደር ካሉበት ድረስ ሄዶ እጅ በመንሳት የምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል። በኃይለ ሥላሴ ዘመን ከንጉሱ እጅ ሁለት ጊዜ የወርቅ ሽልማት የተበረከተላቸው ብቸኛው የጥበብ ሰውም አባባ ተስፋዬ ናቸው። በቲያትሩ ዓለም ስላበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ የኪነ ጥበባትና መገናኛ ብዙሃን በ1991 ዓ.ም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጓቸዋል። አባባ ተስፋዬ ሕይወታቸው ከማለፏ ሁለት ቀናትን ቀደም ብሎ የተበረከተላቸው ሌላ አንድ ትልቅ ሽልማት ነበር። ይሄውም ሐምሌ 22 ቀን በ2009 ዓ.ም የዪኒቲ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸው ነበር። ግን ምን ያደርጋል ወትሮም ለምስጋና አልታደሉምና በዚህ ማዕረግ ስናወድሳቸው ሳይሰሙ ስማቸውን አንግሰው በ93 ዓመታቸው ወደ አፈር ወረዱ። ሐምሌ 24/2009 ዓ.ም የኢትዮጵያዊው ሙሴ የታላቁ የክብር ዶክተር አባባ ተስፋዬ ምድራዊ ሕይወት አከተመች።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2015