መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቱሪዝም ዘርፍ ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ከሚፈጥሩ ዋና ዋና የምጣኔ ሀብት ዘርፎች አንዱ መሆኑን በመገንዘብ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ይህን ተከትሎም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ ከመሥራት ባለፈ ግዙፍ የመስህብና የመዳረሻ ልማቶችን እያከናወነ ነው።
ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብትና ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ እንዲሁም ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩ እንደ ገበታ ለሸገርና ገበታ ለአገር የሚሉ ማእቀፎች ውስጥ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ እነዚሁ የቱሪስት መዳረሻዎቹ በእርግጥም በስፋት እየተጎበኙ ይገኛሉ፡፡ በግንባታ ላይ የሚገኙት ሌሎች ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ሲገቡ ለዜጎች ተጨማሪ ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠራቸውም ባሻገር እንደ አገር የኢኮኖሚ አቅምን ለማጎልበትና ሃብቶቹን በማስተዋወቅ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያን መልካም ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ መገንባት ይቻላል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስህብ በርካታ ሃብቶች ካላቸው አገራት በተለይም ደግሞ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ተርታ ትሰለፋለች። ይህንን ዘርፍ በላቀ ሁኔታ ለማሳደግና ደረጃውን ጠብቆ የአገር ዋልታ ከሆኑ ዋና ዋና አውታሮች አንዱ እንዲሆን ለማድረግ የመስተንግዶና የሆስፒታሊቲ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ይህም የመስህብ ሃብቶችን ከማልማት፣ ከመጠበቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅ ባለፈ በዋናነት በልዩ ትኩረት ሊታይና ሊያዝ የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ ነው።
የሆስፒታሊቲና መስተንግዶ ጉዳይን ስናነሳ በቀዳሚነት የሚነሳው የትራንስፖርት ጉዳይ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዝ ወዲህ እየተገነቡና ለቱሪዝሙ ተጨማሪ እሴት እየሆኑ ያሉት ታላላቅ የመዳረሻ ልማቶች ይህን መሰል ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሹ ናቸው። ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመንን ይጠይቃል፡፡ ይህ አገልግሎት ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶችና የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ስፍራ መዳረሻቸው ለሚያደርጉ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ምቹ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ስለ መስህብ ስፍራው በቂ መረጃ መስጠት የሚችሉ፣ የአገልጋይነት ስሜትና ሙያዊ ስነ ምግባርን የተላበሱ አገልግሎት ሰጪዎችን የያዘ መሆን ይኖርበታል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ጎብኚዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ (ቱር ኦፕሬተሮችን ሳያካትት) የትራንስፖርት ዘርፍ የለም። በዚህ ምክንያት ጎብኚዎች በቅርብ ርቀት ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆና በቂ መረጃ አግኝተው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ስለሚቸገሩ የቆይታ ጊዜያቸውን አሳጥረው ይዘው የመጡትንም ገንዘብ ይዘው ይመለሳሉ። ይህ ደግሞ ዜጎች በሥራ ፈጠራ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባሻገር የአገርን ጥቅም ይጎዳል። በዚህ ችግር መነሻ ምክንያት መንግሥትም የሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደራጀና ወቅቱን የሚመጥን የጎብኚዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚያቀርቡ ግለሰቦችና ማህበራት ድጋፍ ለመስጠት ትግበራ መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በቱሪዝሙ ዘርፍ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ከተጀመሩ ጥረቶች ውስጥ ይበል የሚያሰኘውና ጥሩ ማሳያ የሚሆነው “የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ሰጪ ማህበራት” ተደራጅተው ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ነው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ጥረቱን እየደገፉትና ለስኬታማነቱ ከማህበራቱ ጋር እየሰሩ ይገኛሉ። ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ሲገባም ኢትዮጵያ በስነ ምግባርና በአገልጋይነት ስሜት ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ጎብኚዎችን በጥራት የሚያስተናግዱ የቱሪስት ትራንስፖርት ሰጪዎች በስፋት እንደሚኖሯት ይገመታል።
አቶ መሳፍንት ዘውዱ የቱሪስት ታክሲ ማህበራትን በማደራጀት ወደ ትግበራ ለማስገባት በሂደት ላይ የሚገኘው የ2 ኤም ቲ የንግድ ስራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ 2 ኤም ቲ የኢትዮጵያን የቱሪዝም አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈና ተደራሽነቱ ሰፊ የሆነ ሥራ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየሠራ ነው። በተለይ በትራንስፖርት ዘርፉ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች እንዲኖሩ፣ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን፣ ደህንነቱ የተረጋገጠና ፈጣንና ምቹ የታክሲ አገልግሎት በማቅረብ የጎብኚዎችን ቆይታ ማራዘም እንዲቻል በመስራት ላይ ይገኛል። ለተግባራዊነቱም የቱሪስት ታክሲ ማህበራትን በማደራጀት አገልግሎቱ በአንድ ማእከልና ሰንሰለት የሚሰጥበትን ሂደት እያመቻቸ ይገኛል። የአገሪቱን የመስህብና የመዳረሻ ስፍራዎችን ጠንቅቀው የሚያውቁ የቱሪስት ታክሲ አሽከርካሪዎች በመፍጠር ጎብኚዎች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ተጨማሪ አቅም ለመሆን መስራቱን ተያይዞታል።
“ዲጂታላይዝድ የሆነና ሁሉን አቀፍ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራን እንገኛለን” የሚሉት አቶ መሳፍንት፣ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል እውቅና ካገኘበት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አገራት ሴቶችና ወጣቶችን ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ በማህበር እንዲደራጁ መስራቱን ይናገራሉ። የማህበሩ አባላት የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩና የባንክ ብድር እንዲመቻችላቸው በማስቻልም አስፈላጊውን የፋይናንስ አቅም በየማህበራቱ መፍጠር መቻሉን ይገልፃሉ።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ፤ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴርና የቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን ፕሮጀክት ደግፈው በጋራ እየሰሩ ናቸው፡፡ የቱሪስት ታክሲዎቹን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ጉዳዩ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ተመርቶ በማኔጅመንት የመጨረሻ ደረጃ ግምገማ ላይ ይገኛል። በ 2 ኤም ቲ የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ 55 ማህበራት ተደራጅተዋል፤ 2 ሺህ 700 አባላትንም ይዘዋል፤ በ3000 ዘመናዊ የቱሪስት ታክሲዎች ሥራውን ለመጀመር ታቅዷል። የፋይናንስና የኢንሹራንስ አገልግሎትን በተመለከተም ከአማራ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ዘመን ኢንሹራንስና ሌሎችም መሰል የፋይናንስና የኢንሹራንስ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰሩ ናቸው።
ቱሪዝምና የአካባቢ ጥበቃ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ደግሞ ቴክኖሎጂ ሁነኛ አማራጭ ነው። ዓለም አሁን ላይ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን እያስተዋወቀችና ወደ ሥራ እያሰማራች ነው።
ቱሪዝም ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ዘርፍ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ለሚጀመረው የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት የሚገቡት መኪኖችም ይህንን ታሳቢ ያደረጉና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አማራጮችንም ያካተቱ እንዲሆኑ 2 ኤም ቲ በመስራት ላይ መሆኑን ስራስኪያጅ ይናገራሉ።
ለእዚህም በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪናን በማስመጣት ከሚታወቀውና በኢንጂነር ቅደም ተስፋዬ ባለቤትነት ከሚተዳደረው “ግሪን ቴክ አፍሪካ” ጋር እየተሰራ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል። በቻይና መቀመጫውን ካደረገ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ 51 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው የግሪን ቴክ አፍሪካ ባለቤትም ለዚሁ አገልግሎት እውን መሆን ስምምነታቸውን ሰጥተዋል።
የ2 ኤም ቲ የንግድ ስራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሌላኛው መስራችና የማርኬቲንግ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንደሰን ለገሰ እንደሚሉት፤ በቴክኖሎጂ የተደገፉ፣ ለአረንጓዴ ልማት ምቹ የሆኑና ለቱሪስት ምቹ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ለማስገባት የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ተደርሷል። የቀረው ጉዳይ የገንዘብ ሚኒስቴር የቀረጥ ነፃ ፍቃድ ነው። ለ55ቱ ማህበራትና አመራሮቹም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በቅርቡ ተሰጥቷል።
“ማህበራቱ የተደራጁት በዋናነት ዘመናዊ የቱሪስት ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ነው” የሚሉት የማርኬቲንግ ቢሮው ኃላፊው፣ ማህበራቱ ለጎብኚዎች ትክክለኛና በቂ መረጃ የሚሰጥና በፍፁም ስነምግባር የሚያስተናግድ የቱሪስት ታክሲና አሽከርካሪ እንዲኖር በማሰብ መነሻ ፕሮጀክቱን ለ2 ኤም ቲ የንግድ ስራዎች አቅርቦና ማህበራቱን የማደራጀት ኃላፊነት ወስዶ ስምምነት ላይ በመድረስ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ በዚህ መሰረትም በክልሎች ባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ የመስህብ ስፍራዎች፣ ኤርፖርቶችና መሰል ስፍራዎች ማህበራቱ ተደራጅተዋል። በማህበራት የተደራጁት አባላቱም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በባንኮች እየቆጠቡ ሲዘጋጁ ቆይተዋል።
የ2 ኤም ቲ የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አመራሮች እንዳብራሩት፤ አስፈላጊዎቹ ሂደቶች ተጠናቀው መኪኖቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው አስቀድሞ አባላቱ አገልግሎት የሚሰጡባቸውን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ጠንቅቀው እንዲያውቁ፣ ስለ ሃብቶቹ በቂ ግንዛቤና መረጃ እንዲኖራቸው ተከታታይ የጉብኝትና የስልጠና መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ። አገልግሎቱ በመጀመሪያው ዙር 3000 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል በሁለተኛው ዙር እስከ 4000 የሚጠጉ አባላትን የያዙ ማህበራትን በማደራጀት በሥራ እድል ፈጠራው ላይ የበኩሉን ሚና ይወጣል፡፡
አቶ አለማየሁ ጌታቸው የቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው። ከላይ ያነሳነውን ጉዳይ አስመልክቶ ለማህበሩ አባላት በተሰጠ የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ነበር። እርሳቸው ቱሪዝምም ሆነ ቱሪስት በባህሪያቸው ምቾትን እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ። የቱሪስቱን ምቾት ከሚጠብቁና የመዳረሻ ስፍራዎች ቆይታውን እንዲያራዝም ከሚያደርጉ መንገዶች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት አንዱ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ምቾት ማለት የመኪናው ወንበር አሊያም አጠቃላይ ይዞታ ብቻ እንዳልሆነ ተናግረው፣ ተሽከርካሪዎቹ የሚያወጡትም ድምፅ ወሳኝ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ ዘመኑ በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ የሚመረቱና ድምፅ አልባ የሆኑ የኤሌክትሪክ መኪኖች በአሁኑ ወቅት በዓለም ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ነው ተብሎ የሚጎበኝ ስፍራ የለም። ሁሉም ለቱሪስት መዳረሻ ስፍራነት የሚሆንና የሚጎበኝ ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ ፣ ዋናው የማስጎብኘትና ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም ማሳደግ እንደሆነ ይገልፃሉ። ለዚህ ውጤታማ ሥራ ደግሞ በመዳረሻ ስፍራዎች አካባቢ ብቁ፣ ታማኝ፣ የቱሪስቱን ደህንነትና ምቾት የሚጠብቅ አገልግሎት ሰጪ መፍጠር እንደሚገባ ይገልፃሉ። ከዚህ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና ሌሎችም ሃብቶች በሚገባ የተረዳና በቂ እውቀት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አካል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ዳይሬክተሩ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጁ ላሉት በ2 ኤም ቲ የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር ለተደራጁ 55 ማህበራት ተወካዮች ባስተላለፉት መልእክት፤ አንድ ጥሩ ባል ሚስቱን እንደማያማ እንዲሁም አንድ ጥሩ ልጅ እናቱን አጋልጦ እንደማይሰጥ ጠቅሰው፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች የአገራቸውን መልካም ገፅታ በመገንባትና አወንታዊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ለቱሪስቶች በማቅረብ ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መትጋት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
“እየተጠናቀቀ ባለው 2015 በጀት ዓመት 9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከቱሪዝም 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተረጋግጧል” ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይሄ በቀጥታ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለመንግሥት ገቢ የሆነ ሳይሆን ሆቴሎች፣ ትራንስፖርት ሰጪዎች (አየር መንገድን ጨምሮ)፣ ቱር ኦፕሬተሮች መዳረሻ ስፍራ ላይ የቱሪዝም ምርት የሚያቀርቡ ማህበራት እና ሌሎችም ተጠቃሚ የሆኑበት እንደሆነ ጠቅሰዋል። በዚህ ዘርፍ ላይ በቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየት ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸው፣ የ2 ኤም ቲ ንግድ ስራዎችም ሆነ የተደራጁት ማህበራት በልዩ ቁርጠኝነትና የአገልጋይነት ስሜት ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ድጋፉን እንደሚሰጣቸውና ከጎናቸው እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2015