የተወለዱት በቀድሞ አጠራሩ ጎጃም ክፍለ ሀገር አዲስ ቅዳም በምትባል ከተማ ሲሆን፣ ያደጉት ደግሞ የታላቁ አባይ ወንዝ መፍለቂያ በሆነችው ግሽ አባይ ሰከላ አያታቸው ዘንድ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በዚያው በሰከላ በደጃዝማች ዘለቀ ደስታ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ የተማሩት በዳንግላ ሃይስኩል ነው፡፡
ከሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በኋላ ያመጡት ነጥብ ከፍተኛ በመሆኑ የአለማያ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለው በእርሻ ምህንድስና (በአግሪካልቸራል ኢንጂነሪንግ) በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ፡፡ እንደተመረቁም ሥራ የጀመሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ በመሆን በደብረማርቆስ አውራጃ ስናን በምትባል ደጋማ አካባቢ ነው፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኔዘርላንድስ ዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ በአፈርና በውሃ ማኔጅመንት ሠሩ፡፡ እንዳጠናቀቁም ወደ አገራቸው ተመልሰው የተሰማሩት በተፋሰስ ልማት ላይ ነው፡፡ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩት ደግሞ በስዊዘርላንድ በርን ዩኒቨርሲቲ በሁለት ነጥቦች ላይ ነው፤ አንደኛው በኢትዮጵያ የመልክዓ ምድሩ ትራንስፎርሜሽን ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ምን ይመስላል? የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የመሬት መራቆት መጠንን በተፋሰስ ደረጃ ማወቅና እንዴት መቀነስ ይቻላል? በሚል ነው፡፡
በእርግጥ አስቀድመው በሠሩት ሥራም ሆነ በተመረቁበት ዘርፍ ከአገር ውጪ መስራት የሚያስችላቸው እድል ቢኖርም እዛ መቅረትን አልወደዱም፡፡ መሬት መራቆት ላይ ሠርተውና ለውጡን አይተው ስለነበርም ያንን ትተው ምቾት ወደአለው ስፍራ ለመሄድ ለሕሊናቸው ምቾት አልሰጣቸውም፤ በመሆኑም ተመልሰው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ላይ ቀጠሉ፡፡ በሒደትም ፕሮጀክቱን መሰረቱ፡፡
አንድ ሰው ሆነው የጀመሩት ፕሮጀክት በአሁን ሰዓት ከ200 በላይ ባለሙያን ይዞ ወደ ማዕከልነት አድጓል፡፡ ይህ ተቋም ለአገር የሚጠቅም ትልቅ ሥራ እየሰራ ሲሆን፣ ወደ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ልማት መቀየር የሚችል ብዙ የምርምር ውጤቶች ያለው ነው፡፡ አዲስ ዘመንም የዛሬ እንግዳ ያደረገው ማዕከሉን በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩትን ዶክተር ጌቴ ዘለቀን ነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንድ ሰው አንድ ተቋም መሰረተ ሲባል ብዙ የተለመደ አይደለም፤ ተቋሙን ለመመስረት ያነሳሳዎ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ አስቀድመን ውይይቱን እንጀምር?
ዶክተር ጌቴ፡- የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ሥራ ከመጀመሬ በፊት የስዊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሆኖ እኤአ በ1982 ላይ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ፕሮጀክት ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል። የዚህ ፕሮጀክት አመሰራረትም በወቅቱ በ1966 በተለይ የሰሜኑ፣ የምሥራቁና የደቡቡ አካባቢ የተከሰተው ድርቅ ያመጣው ከአካባቢ መራቆት ጋር ቁርኝት አለው የሚል እምነት በመያዙ (በተለይም በአፈር ብክለት) እና በተለይም በቀይ መስቀል የሚመራው ቡድን በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር በሲሪንቃ አካባቢ የአፈርና ውሃ ጥበቃ በመጀመሩ ለዚያ የሚሆን በሳይንስ የተደገፈ መልስ ለመስጠት ነበር።
ምክንያቱም በወቅቱ እኤአ በ1966 አካባቢ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የአፍርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ስለማይታወቅ የተጀመረው በተለመደው የአፍርና ውሃ አጠባበቅ ሥራ ነው፤ የትኛው ለኢትዮጵያ የአየር ጸባይ እንዲሁም የአፈር አይነት ይሆናል በሚል አይደለም። ምክንያቱም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደየስነምህዳሩ አይነት የሚለያይ ነው። ለምሳሌ ዝናብ የሚበዛበት አካባቢና ዝናብ አጠር አካባቢ የሚያስፈልጋቸው የቴክኖሎጂ አይነት አንድ አይነት መሆን አይችልም። በትክክለኛው ቴክኖሎጂ ባለመሰራቱ ያንን የተመለከቱ የሲውዘርላንድ ባለሙያዎች በተለይ ፕሮፌሰር ሃንስ ሁርኒ በወቅቱ ከነበረው የግብርና ሚኒስቴር ጋር እና ሌሎችንም ይዘው የአፈር ጥበቃ ፕሮጀክት መሰረቱ።
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማው የነበረው አንደኛው በኢትዮጵያ በተለያዩ አግሮ ኢኮሎጂዎች ምን አይነት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ቴክኖሎጂ ነው የሚያስፈልገው? የሚለውን መለየት ነው። ሁለተኛው እንደ ተዳፋቱ አይነት እንዴት ይሰራል? የሚለውን መለየት ነው። ሦስተኛው ደግሞ በዓመት እየታጠበ የሚሄደው የአፈር መጠን በአንድ ተፋሰስ ወይም በሔክታር ምን ያህል ነው የሚለውን መለየት ነው። አራተኛው ደግሞ አቅም ማጎልበት ሲሆን፣ የግብርና ባለሙያውንም ሆነ አርሶ አደሩን ማሰልጠን ነው።
ሥራው የተጀመረው አካባቢው እኤአ በ1982 በደሴ ሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ማይባር በምትባል ተፋሰስ ላይ ነው፤ ሁለተኛው ተፋሰስ ደግሞ የማዕከላዊ ጎጃምን ይወክላል የተባለ አንጄኒ በምትባልባት እኤአ በ1984 ላይ ደምበጫ አካባቢ ተጀመረ። በወቅቱ አካባቢው የተመረጠው እንደሚታወቀው ጎጃም ትርፍ አምራች ነው፤ ግን አካባቢው ከፍተኛ ዝናብ ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቦረቦር የተጠቃ አካባቢ ስለነበር ያንን ለማስተካከል ታስቦ ነው። ቀጥሎም ወደሰሜን ሸዋ አካባቢ በልግ አምራች በሆነው ቦታ ጣርማ በር አንዲት-ጥድ በምትባልበት ዳገታማው አካባቢ ተመሰረተ።
ከዚያ ቀጥሎ ጭሮ አካባቢ የጨርጨር ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ሐረር ሁንዴላፍቶ በሚባል አካባቢ፤ ከዚያም በደቡቡ አካባቢ የሚወክል ወላይታ ውስጥ ጉኑኖ ተፋሰስ በሚባልበት አካባቢ ተመሰረተ። ከዚያም የቀሩት ሁለት ተፋሰሶች የደቡብ ምእራብ አካባቢ ደንና ረግረጋማ አካባቢ ያለበትን ቦታ የሚወክል ኢሉአባቦር ውስጥ ዲዚ በሚባል ቦታ ላይ ሌላ ተመሰረተ። እነዚህ ዋና ዋና የሚባሉ ስነምህዳርን የሚወክሉ ናቸው። በወቅቱ ኤርትራም አንዷ የኢትዮጵያ ግዛት ነበረችና ኤርትራ፣ ትግራይንና ዋግኸምራን በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በወሎና በአፋር መካከል ያለውን ደረቃማ ቦታ የሚወክል ኤርትራ ውስጥ አፈደዩ የምትባል ቦታ ሌላ ተመሰረተ።
አጠቃላይ ሰባት ዋና ዋና የሚባሉ የተለያዩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ስነ ምህዳሮችን የሚወክሉ ተፋሰሶች ተመስርተው ሥራ ተጀመረ። ይህም አስቀድሜ እንደነገርኩሽ በስዊዘርላንድ መንግሥትና በግብርና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ማለት ነው። በእነዚህ የተፋሰስ ጣቢያዎች ውስጥ ወዲያው በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓላማቸው መሰረት የትኛው ቴክኖሎጂ ለየትኛው አካባቢ ይመጥናል የሚለውን መለየት ተቻለ።
በየአግሮኢኮሎጂው በሔክታር እየተጠረገ የሚሄደው የደለል መጠን ምን ያህል ነው? የሚለው መለየት ተቻለ። የወንዞቹን ፍሰትና የአየር ንብረቱን እንዲሁም የዝናብ መጠኑ ምን ያህል ነው? የሚለው ተለየ። እኤአ በ1982 ተጀምሮ 1987 አካባቢ የመጀመሪያው የልማት ጣቢያ ሠራተኞች የአፍርና የውሃ ጥበቃ መመሪያ ተጻፈ። ከዚያም የአፈርና ውሃ ጥበቃ በስፋት መሠራት ተጀመረ። የመጀመሪያው ተፋሰስ ከተመሰረተ በኋላ ሌሎችም ወዲያው ተከታትለው ተመሰረቱ። የማስተዋወቁ ሥራ በስፋት ቀጠለ። በእንዲህ አይነት ሁኔታ እስከ ደርግ መጨረሻ ጊዜ ድረስ ቀጠለ።
በኋላ ላይ የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ፕሮጀክቱ ወጣ። እኔ በወቅቱ ዶክትሬት ዲግሪዬን እየሰራሁ ነበርና ከፕሮፌሰር ሃንስ ጋር ተወያየን፤ እነዚህ ተፋሰሶች እንዲሁ ከምናስቀራቸው ከመንግሥት ተቋማት ጋር እናያይዛቸው ብለን ተማከርን። በመሆኑም እንደያሉበት ቦታ በክልል ደረጃ ካሉ የምርምር ማዕከላት ጋር አያያዝናቸው። በአማራ አካባቢ ያሉትን ከአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ምርምር ማዕከላት ጋር ሌሎችን እንዲሁ ከየክልሎቹ ጋር አስተሳሰርናቸው። እኔ በወቅቱ የአማራ ክልል የግብርና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ጄነራል ነበርኩ። የቀረን አፈደዩ የተባለው በኤርትራ ውስጥ የሚገኘው ሲሆን፣ ኤርትራ እንደ አገር ራሷን ችላ በመውጣቷ እሱ ቀረ።
ካስተሳሰርናቸው በኋላ ተቋማዊ ሥርዓቱ የፖለቲካውን ስልት እየተከተለ ዥዋዥዌ ሲበዛበትና የሰው ኃይልም ሲቀያየር እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረው የየሰው አስተሳሰብም ሲቀያር የነበረው ነገር እየቀነሰ መጣ። ማዕከላቱም የሚያመነጩት መረጃ ጥቅም ላይ መዋሉ ቀረ። በመሆኑም ከፕሮፌሰሩ ጋር ተነጋገርንና ለየት ያለ ተቋማዊ ሥርዓት እናብጅለት በሚል ወሰንን። ምክንያቱም በተፋሰስ ደረጃ ለረጅም ዓመታት በዚህ መልኩ መረጃ የሚሰጥ ተቋም በአፍሪካ ደረጃ የለም። ምክንያቱም በዚህ አሰራራችን የአየር ንብረት ለውጡን፣ የውሃ መጠኑንና የጎርፉን መጠንም ሆነ የአፈር ክለት መጠኑን እንከታተል ነበርና ነው። እንዲህ አይነት የረጅም ጊዜ ክትትል ምናልባት በትንሹ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊኖር ይችል ይሆናል፤ ስለዚህ ይህንን ሥራ ከፕሮጀክት ወደ ማዕከል እንቀይር በሚል ተነጋገርን። ተሟሙቆ የነበረው ተሳትፎአዊ የተፋሰስ ልማትም ወደ የዘመቻ ሥራ ስለተቀየረና ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ ስለገባ ምርምር ብቻ መስራቱ ብዙም አይደለም የሚል እምነት ነበረንና ከምርምሩ በተጨማሪ የተፋሰስ ልማት ሰርተን እናሳይ ወደሚለው መጣን። ለዚህም የሚሆን የሲውዘርላንድ መንግሥት እኤአ 2011 ላይ የተወሰነ ሪሶርስ መደበልን።
በወቅቱ ጀምረናቸው የነበሩትን ስድስቱን የምርምር ተፋሰሶች በማደራጀት ከየክልሉ የምርምር ተቋማት ጋር ሆነን ሥራቸው ተጠናክሮ እንዲሄድ ማድረግ አንዱ ነው። ሁለተኛ እስካሁን ድረስ ያለውን መረጃ በመተንተን እና ትርጉም በመስጠት ለሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ለፖሊሲ አውጪ አካል ለግብዓትነት እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። ሦስተኛውና ዋናው ሠርቶ ማሳያዎችንና ሞዴል የመማሪያ ተፋሰስ መመስረትና ሠርተን ማሳየት የሚል ነው። ለዚህ ሥራችን ስድስት አነስተኛ ተፋሰሶችን በአባይ ተፋሰስ ውስጥ መረጥን። በወቅቱ የመረጥናቸው ተፋሰሶች የየራሳቸው መስፈርት ነበራቸው። አራተኛው ዓላማ አቅም ማጎልበት ነው። በዚሁ መሰረት እኤአ በ2011 በአጭር ጊዜ ውስጥ በእኔ አነሳሽነት በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነቱ ተፈረመ። እኤአ በ2012 ጥር ወር ላይ ሥራ ተጀመረ። ሥራው መሰራት የተጀመረው ነባሮችን መልሶ ማቋቋምና አዲሶችንም በመስራት ነው።
እኔ እንደ ባለሙያ የሚቆረቁረኝ ይህ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ የብዙ ባለሙያ ጉልበትን የሚጠይቅ ነው። ነገር ግን በዘመቻ የሚሰራው ዛሬ ተሰርቶ ነገ ይፈርሳል። ስለዚህ ያደረግነው ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋርም መመካከር ነበር። ስንጠቀም የነበረው በየዓመቱ ለአፈር ጥበቃ የሚወጣውን የሰው ጉልበት ነበር። በዛ ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስገባት ጀመርን። አካባቢያቸውን በደንብ ለጠበቁ ቴክኖሎጂውን በድጉማ እናቀርባለን። የከብቶች መዋያ የሚባለውን የተራቆተ ቦታዎችን ከተጠቃሚው ማህበረሰብ ጋር በመመካከር በመከለል አካባቢው እንዲያገግም በማድረጋችን ስራችንን በመስክ ጉብኚ ማሳየት ቻልን። በዚህ ብቻ ሳያበቃ በየአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የጓሮ ልማቱን፣ ፍራፍሬውንና ለከብቱ መኖውን ማልማት ጀመሩ። በተለይም በጓሮ ልማት ዙሪያ ወደ 11 ፓኬጆችን በማዘጋጀት ማለትም፣ ፍራፍሬ መትከል፣ መኖ ማልማት፣ አትክልት ማምረት፣ ኮምፖስት ማዘጋጀት፣ ንብ ማነብ፣ ዶሮ ማርባት፣ ከብት ማደለብ፣ አነስተኛ የወተት ልማት፣ እንስሳትን አስሮ መቀለብ፣ ውሃ ማዘጋጀት፣ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በማሰራት በጥቅሉ አካባቢያቸውን ወደጥምር ግብርና በመቀየር የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዲለወጡ አደረግን። በስድስቱ ተፋሰስ ሰፊ ለውጥ ማምጣት ቻልን።
እኤአ በ2016 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማእቀፍ ስር በራሳችን የምንተዳደር ተቋም ሁነን፤ ስራችን ከፕሮጀክትነት ወደተቋምነት ተቀየረ። በዚህ ጊዜ ከሌሎችም ድጋፍ ማግኘት ቻልን። የሰው ኃይላችንም ቢሯችንም መለወጥ ጀመረ። በዘርፉ በጣም ሰፊ ሥራ እየሰራን ትኩረታችንን ደግሞ ውሃና መሬት ላይ አደረግን።
አዲስ ዘመን፡- ውሃና መሬት ላይ በዋናነት ስትሰሩ የነበረው ምንድን ነው?
ዶክተር ጌቴ፡- ውሃ ላይ የምንሰራው የውሃ አያያዝና የውሃ ብክለት ላይ ነው። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ወንዞች ሲታዩ ይፈሳሉ እንጂ በውስጣቸው ሕይወት የለም።
ይፈሳሉ እንጂ በውስጣቸው ሕይወት የለም። ይህ በካይ ነገር የመጣው ከየት ነው በሚል ዝርዝር ሥራ እንሰራለን። በሰው ጤና እና በአካባቢ ላይ ያለውን ጉዳት እናጤናለን። በዚህ መልኩ በስፋት ለጊዜው እየሰራን ያለነው የአዋሽ ተፋሰስ ላይ ነው። ይህን ተፋሰስ የመረጥነው አንደኛ የአገሪቱ ዋና ከተማ ያለው አዋሽ ተፋሰስ ውስጥ ሲሆን፣ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብንም የሚያካትት በመሆኑ ነው። ሌላው የአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ ኢንዱስትሪዎችና ትልልቅ የንግድ እርሻዎችም ያሉ ስለሆነም ነው። ስለዚህ ይህን ታሳቢ አድርገን የአዋሽን የውሃ ብክለት ከላይ እስከ ታች መቃኘትና መንስዔውን ማወቁ ተገቢ ነው። ስለዚህ አዋሽ ላይ ትኩረት አድርገን መስራት የጀመርነው እኤአ ከ2015 ጀምሮ ነው።
ሥራውን የበለጠ ሊያጠናክርልን የሚችል እኤአ በ2015 ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የእንግሊዝ መንግሥት የሚያግዘው አንድ ፕሮጀክት አገኘን። ፕሮጀክቱም ‹‹የውሃ ደህንነት ድህነት ለመቀነስ›› በሚል መሪ ሐሳብ የሚንቀሳቀስ ነው። ፕሮጀክቶቹ ኬንያ፣ ባንግላድሽና ኢትዮጵያ የሚተገበር ሲሆን፣ እኛ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሆንን። ዋና አጋራችን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ዩኒሴፍ ናቸው።
ከውሃ ጋር ተያይዞ ሌላ ትልቅ ፕሮጀክት ከእንግሊዝ መንግሥት አገኘን። በአምስት አገሮች ይተገበራል፣ ኢትዮጵያ፣ ኮሎምቢያ፣ ህንድ፣ ማሌዥያና እንግሊዝ፤ የኢትዮጵያን ምርምር የምናስተባብረው እኛ ስንሆን የሁሉንም አገር የሚያስተባብረው ደግሞ ኒውካስትል ዩኒቨርስቲ ነው። በዚህ ፕሮጀክት በሦስት ተፋሰሶች ላይ ማለትም አባይ፣ አዋሽና ስምጥ ሸለቆ ላይ አተኩረን እንሰራለን። የምንሰራቸው ምርምሮችም የውሃ ብክለትና ጉዳት፣ የውሃ አጠቃቀምና ስርጭት፣ የዝናብ ውሃ አጠቃቀም፣ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ግንኙነት በዝርዝር ማጥናት ነው፤ እንዲሁም የውሃ ስርጭት ብዙ ጊዜ የውሃ ፍላጎትና አንድ ተፋሰስ ያለው የውሃ አቅርቦትን በዝርዝር ማጥናትም ሌላው ሥራ ነው። የከተሞች የውሃ አቅርቦት በምን አግባብ መያዝ አለበት የሚለው ሲሆን፣ ውሃ ኦዲት የማድረግ ሥራም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ውሃ ኦዲት የሚደረገው እንዴት ነው?
ዶክተር ጌቴ፡- አንደኛ በዛ ተፋሰስ ውስጥ ምን የውሃ መሰረተ ልማቶች አሉ? ግድብ፣ መስኖ. የከተማና የገጠር አቅርቦት፣ መሰረተ ልማቶች፣ ምን አይነት ደረጃ ላይ ናቸው? የሚይዙት የውሃ መጠን፣ የውሃ ዓመታዊ ፍሰታቸውና የሚሰጡት መጠን፣ ያለባቸው ችግር ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ወይ? ባለቤቱ ማን ነው? የመስኖ መሰረተ ልማት ዲዛይን አላቸው ወይ? የሚለው ሁሉ ዝርዝር ጥናት ሲጠና ኦዲት ተደረገ እንደማለት ነው፤ እኛም ይህን ሁሉ አጠናን። ይህን የሠራነው አዋሽ ተፋሰስ፣ ስምጥ ሸለቆና ዓባይ ተፋሰስ ላይ ነው። ይህ በጣም ሰፊ ጥናት ነው።
እሱ ብቻ ሳይሆን ከስምምነታችን ወጣ ብለን የውሃ ኦዲት መረጃ ሥርዓት ሶፍትዌር አለማን። በሦስተኛ የምንሰራው የውሃ ኦዲት አትላስ ነው። በአትላስ የት ቦታ ምን አለ? አቅሙስ ምን ያህል ነው? የሚለውን እየሠራን ነው። ሥራውን በቅርቡ ይፋ እናደርገዋለን። ለምሳሌ በአንድ ‹‹ክሊክ›› በአቃቂ ተፋሰስ ውስጥ ስንት ጥልቅ ጉድጓድ አለ ተብሎ ቢጠየቅ ከነካርታው ይወጣልናል። እያንዳንዱን ጥልቅ ጉድጓድ ደግሞ ‹‹ክሊክ›› ስናደርግ የጉድጓዱ ጥልቀት፣ ባለቤቱ፣ የውሃ መጠኑ፣ መቼ እንደተቆፈረና አሁን ላይ ያለበት ደረጃ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በአሁኑ ወቅት ውሃን በመቆጣጠር ደረጃ በጣም ብዙ ሥራ መሠራት አለበት። ለምሳሌ አቃቂ ተፋሰስ ውስጥ 913 ጥልቅ ጉድጓዶች አሉ። እነዚህ ጥልቅ ጉድጓዶች የተወሰኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚቆጣጠራቸው ውጪ ብዙዎቹን ሆቴሎች፣ ኢንዱስትሪዎች፤ የንግድ ማዕከላት በግል የቆፈሯቸው ናቸው።
የመቆፈር ፈቃድ ብቻ ነው ያላቸው እንጂ ምን ያህል ውሃ አላቸው? በከርሰ ምድር ላይ ምን ተጽዕኖ ያመጣል? የሚለው ነገር የላቸውም። እሱ ክፍተት ነው። አዲስ አበባ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያለች ከተማ ናት፤ የሕዝብ ብዛቱ እየጨመረ ነው። በገጸ ምድር ላይ ያሉ ግድቦቿ ለገዳዲ፣ ድሬና ገፈርሳ የቆዩ ግድቦች ናቸው። እኛም ከሕዝቡ መጠን ጋር የውሃ ሀብትን የአስተዳደሩ ሁኔታ በምን ያህል የሚጣጣም ነው የሚለውን እያጠናን ነው። የሚቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች በምን ያህል መጠን እየሄዱ ናቸው የሚለውንም እያጠናንና ከሚመለከታቸው ጋር እየተነጋገርን ነው። በአሁኑ ወቅት የውሃን ጉዳይ ስናይ ከብክለት አኳያ፣ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ መጠኑ በጣም እየተመናመነ ነው፤ እኛም ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመሆን በእኛ ጥናት ላይ መሰረት ተደርጎ ዝርዝር የወደፊት የዘላቂ የውሃ አቅርቦትና የአያያዝ ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ መሠራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከመመናመኑ የተነሳ አደጋ ውስጥ ያለውን ውሃ መታደግ የሚቻለው እንዴት ነው?
ዶክተር ጌቴ፡- መታደግ ይቻላል፤ በጣም ቀላል ነው። በጣም ብዙ አማራጮችም አሉ። አንደኛው የለገዳዲና የገፈርሳ ውሃን ማጎልበት ሲሆን፣ ሁለተኛው እንደተፈለገ የሚቆፈረውን የጥልቅ ውሃ ጉድጓድን የቁጥጥር ሥርዓትን ማበጀት ነው። ሦስተኛው ደግሞ የላይኛውን የተፋሰስ አካል ማልማትና ውሃ ወደ ከርሰምድሩ እንዲሰርግ ማድረግ ነው፣ አራተኛው የውሃ ብክነት እንዳይኖር መቆጣጠር ነው። አምስተኛው የውሃ መበከልን መቀነስ ነው። ብዙዎች ጥናት ያካሄድንባቸው ኢንዱስትሪዎች ቆሻሻቸውን የሚለቁት በቀጥታ ወንዞች ላይ ነው። ከዚህ የተነሳ ወንዙ ሙት ውሃ ይሆናል። እሱ ደግሞ ለአትክልት ልማት ይውላል፤ ያ ደግሞ በጤና ላይ ጉዳት ያደርሳል። ስለዚህ ውሃ ላይ ከተሰራ ማዳንና ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል። ቆሻሻ ነው የተባለ ውሃም አስፈላጊው እንክብካቤ ከተደረገለት ለአትክልትና ለመሰል አገልግሎት ማዋል ይቻላል። ከውሃ ጋር ተያይዞ በብዛት የሠራናቸው ሥራዎች እነዚህን ይመስላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከውሃ ጋር ተያይዞ የሰራችኋቸው ሥራዎች አሉ፤ በጥናታችሁ ያገኛችሁት ግኝት በዋናነት የሚደርሰው ለማን ነው? ምንስ እንዲደረግ ነው?
ዶክተር ጌቴ፡- የጥናቱ ግኝት አንዱ ዋና ባለቤቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተፋሰስ አስተዳደር ናቸው። ለጊዜው የሚያስተባብሩትም የዓባይ፣ የአዋሽና የስምጥ ሸለቆ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ናቸው። ሁለተኛው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመስኖና ቆላማ አካባቢ እና የግብርና ሚኒስቴር ናቸው። ሌላው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። ኢንዱስትሪዎች የሚያወጧቸውን ፍሳሾች አጣርተው መስራት እንዳለባቸው እንደግዴታ መቀመጥ አለበት። አራተኛው የከተማ ልማት ሚኒስቴር ነው። የከተሞች ማስተር ፕላን ሲሰራ ውሃን ታሳቢ ያደረገ ነው ወይ? የሚለው ሲታይ የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ አይደለም። ስለዚህ ውሃን ማዕከል ያደረገ የከተሞች ፕላን በሚል አንድ ፕላን ጀምረናል። አዲስ አበባን እንደ ማሳያ ወስደን እየሰራንበት ነው።
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ማስተር ፕላኖች እንዴት አድርገን ውሃን በማእከልነት የሚያዩ ይሁኑ የሚለው ነው። የዚህንም ጥናት እየሰራን ሲሆን፣ እሱ በአጭር ጊዜ ይወጣል። ከዚያ በኋላ እኛ ያሰብነው የከተማ ልማት ፕላን ሚኒስቴር እንደ አንድ የቤት ሥራ ወስዶ ከተሞች ሲሰሩ ውሃን ማዕከል ያደረጉ መሆን እንዲገባቸው ነው። በጥቅሉ ከዚህ በኋላ ያሉት የከተሞች ማስተር ፕላኖች ውሃን ታሳቢ ያደረጉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ነባር ከተሞችስ ምን መሆን አለባቸው?
ዶክተር ጌቴ፡- እነሱ መከለስ መቻል አለባቸው። ለምሳሌ ጎንደር ከተማን ለአብነት ብንወስድ የውሃ አቅርቦቱ 25 በመቶ ብቻ ነው። አዲስ አበባም እንዲሁ አነስተኛ ነው። ባህርዳር ዙሪያው ውሃ ሆኖ ሳለ ተመሳሳይ ችግር ያለበት ነው። ስለዚህ የከተሞች ስፋት ውሃን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ስለማይታቀድ ከተሞች መስፋታቸው አይቀርም፤ መጨረሻ ላይ ግን ውሃ የለም።
በሌላ በኩል የሚመለከተው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ነው። ባለስልጣኑ ለምሳሌ ወንዞችም ሆኑ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳይበከል መቆጣጠር አለበት። ኢንዱስትሪዎችና የተለያዩ የንግድ ማዕከላት ቆሻሻቸውን ወደ ወንዝ እንዳይለቁ በጣም ሰፊ ሥራ መስራት አለበት። በዚህ ላይ ብዙ ሥራ እየተሰራ አይደለም። የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ይህን የመቆጣጠር ስልጣን አለው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የሃይድሮ ፓወርና የመስኖ ትልልቅ ግድቦችን እየሰራች ነው። ወደዚያ የሚገባው ደለል (የዓባይን ግድብ ጨምሮ) ምን ያህል ነው? የሚለውን ለማየት ሞክረናል።
የዓባይ ግድብ ለሕዝቡ ኩራት የሆነ ነው። ነገር ግን ግድቡ ሲጀመር ስለታላቅነቱ እንጂ ወጣ ያለ ነገር እንዲወራበት አይፈለግም። ግድቡ ለትውልድም ለአገርም ትልቅ መልዕክት ያለው ነው። ነገር ግን ግድቡ ዘላቂ መሆን አለበት። ግድቡን ገድበን 75 እና 100 ዓመት ብቻ ብንጠቀምበት ዋጋ የለውም። ስለዚህ ግድቡ እየወጣበት ያለው ትልቅ ሀብት እንደመሆኑ አገልግሎቱም የዚያን ያህል ዘላቂ መሆን አለበት በሚል ዝርዝር ጥናት አጥንተን ለሚመለከተው መናገር ጀመርን።
አንዳንዶቹ በወቅቱ ቅር ቢላቸውም፤ በኋላ መረዳት ጀመሩ። እንደዋና አጀንዳም ሆኖ መሄድ ቀጠለ፤ ይሁንና ብዙ የሚቀረን ነገር አለ። እኛ በዓባይ ግድብ ላይ ተያይዞ ያጠናነው ዝርዝር ጥናት አለ። በዓመት የሚገባው ደለል ምን ያህል ነው? በዚህስ ከቀጠለ እድሜው ምን ያህል? ተፋሰሱን አልምተን ሃምሳ በመቶ ደለሉን ብንቀንሰው አሁን ከሚባለው ከዲዛይኑ እድሜው በተጨማሪ ምን ያህል ዓመት መቆየት ይችላል? የሚለውን አጠናን። 50 በመቶ ወደግድቡ የሚገባውን ደለል መቀነስ ብንችል 246 ዓመት፣ በ70 በመቶ ያህል ደግሞ ብንቀንሰው ኃይል እያመነጨ እስከ 375 ዓመት ድረስ መቆየት እንደሚችል በጥናታችን ማግኘታችንን አሳወቅን። ይህን ወደገንዘብ ቀይረን ለመንግስት አሳይተናል። ነገር ግን በመሃል ለውጡ መጥቶ ለተወሰነ ጊዜ ዝብርቅርቅ ሲል መንግሥትም ትኩረቱ አገር ማረጋጋት ላይ በመሆኑ ያሰብነውን ትልቁን ሥራ ለጊዜ ያዝ አደረግነው።
አዲስ ዘመን፡- ጥናታችሁን ለመንግሥት ማሳወቅ ችላችኋልና የመንግሥት ምላሽ ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር ጌቴ፡- መንግሥት ገና ብዙ ይቀረዋል፤ እኛ ባሰብነው መንገድ እየሄደ አይደለም። በእርግጥ ተቋማትም ሆኑ በወቅቱ የነበሩ ግንዛቤውን ያስጨበጥናቸው ሰዎችም ሲቀያየሩ በታሰበው ልክ ማስኬድ አይቻልምና ሁኔታዎች እስኪረጋጉ እየጠበቅን ነው። በእኛ በኩል የት ቦታ ምን መሰራት እንዳለበት ጥናቱን አጥንተን ጨርሰናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዝርዝሩ በእጃችን አለ።
እኛ እያልን ያለነው ወደግድቡ የሚገባውን ደለል መቀነስ ከፈለጋችሁ ስራው መሰራት ያለበት የእኛ የመማሪያ ተፋሰሶችን በሚመስል መንገድ ነው። እሱ ሁለት ጥቅም አለው፤ አንዱ በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን የአርሶ አደር ኑሮ ሙሉ በሙሉ ይቀይረዋል። ሁለተኛ ደግሞ ወደተፋሰሱ የሚገባውን ደለል እስከ 70 እና 80 በመቶ ድረስ ያስቀራል። ስለዚህ የግድቡን እድሜ ያራዝማል። ይህ ደግሞ ተጨማሪ የኃይል ምንጭ ወደ መቶ እና ከዛ በላይ እንዲያመነጭ ስለሚያደርግ በኢኮኖሚውም የሚገኘው ብዙ ትሪሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኃይል መኖር ብዙ የኢኮኖሚ መንገዶች እንዲከፈቱ ያደርጋል። ለምሳሌ እኛ በምንሰራቸው በአነስተኛ ተፋሰሶች ላይ በ2 እና 3 ዓመት የአርሶ አደሩ ገቢ በዓመት ሦስት እጥፍ ድረስ ሲጨምር አስተውለናልና ስር ነቀል ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የዚህን ያህል ፋይዳ ያለው ጥናት እስከሆነ ድረስ መንግሥት ተቀብሎት ወደትግበራው የማይገባው ስለምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ጌቴ፡- የሆነው ነገር እኛ ሙሉ ጥናቱን ጨርሰን ባለንበት ወቅት ለውጡ መምጣቱ ነው። ዲዛይን ያደረግነው ስትራቴጂ አለ፤ አንዳንዱን ወዲያው ብናቀርበው ነገሮች ባልተመቻቹበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለጩሉሌዎች ሲሳይ እንደማድረግ ነው። ስጋታችን ጩልሌዎች ፍላጎታቸው ገንዘብ ብቻ ስለሚሆን ዘለው ገብተው እንዳያበላሹት ነው።
ሰላም ሆነ በሚል ልንጀምር ስንል ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው የሕልውና ዘመቻ ለጊዜው ቆመ። እኛ አሁን ያደረግነው ነገር ተጨማሪ ጥናት እንቀጥላለን። የመማሪያ ተፋሰሶችን ደግሞ እያሰፋን ነው። ከነበሩት ስድስት ተፋሰሶች ላይ በኒዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ በላቀ ደረጃ የሚተገበሩ 18 ተፋሰሶችን ጨምረናል። በየአካባቢው ይህን ተሞክሮ እንዲያሰፉትም በማድረግ ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር ያለው የተፋሰስ ቁጥር ምን ያህል ነው? እየለማ ያለውስ?
ዶክተር ጌቴ፡- እንደ አገር ከሦስት ሺ በላይ ተፋሰሶች አሉ። ይሁንና እነዚህ ሁሉ የእኛን አካሄድ እየተከተሉ አይደለም። ነገር ግን ያንን እንዲከተሉ ለማድረግ እየሞከርን ነው። ምክንያቱም ለግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ የተፋሰስ ልማት፣ የክህሎትና የመረጃ ሥርዓቱን ዲዛይን አድርገንላቸዋል። በዛ ውስጥ የእኛ የመማሪያ ተፋሰሶች ተሞክሮ ሶፍትዌር ውስጥ እንዲገባ አድርገነዋል። ፍላጎታችንም ቀስ በቀስም ቢሆን ወደዚህ ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ነው። እኛ የመማሪያ ተፋሰሶችን ከስድስት ወደ 24 አሳድገናል፤ ከተሳካልን ደግሞ ተጨማሪ አስር የመማሪያ ተፋሰሶችን በእምነት ቤዝኖች ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ለመስራት ተዘጋጅተናል። መንግሥት ደግሞ በተረጋጋ ሁኔታ ከቀጠለ ያልኩሽን ጥናት ይፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ከመሬት ጋር ተያይዞ ወደምትሰሩት ሥራ እንምጣ ዶክተር?
ዶክተር ጌቴ፡- ከመሬት ጋር ተያይዞ የምንሰራው ሁለት መሰረታዊ ሥራዎችን ነው። አንደኛው የመሬት አጠቃቀም ለውጡ ምን ይመስላል? የሚለውን መፈተሽ ነው። አንዱ የሦስተኛ ዲግሪዬ አካል እሱ ነው። በዚህም ጥናቴ አሁን ያለው የመሬት አጠቃቀም ሁኔታ በጣም ያስፈራል። ምክንያቱም ደኖች በከፍተኛ ሁኔታ እየተመነጠሩ ነው፤ በኢንቨስትመንት ስምም ሆነ ከተሞችን ለማስፋፋት በሚል እየተመነጠረ ነው። ረግረጋማ ስፍራ አሁን አሁን በነዋሪው መስፈር የተነሳ እየተወገደ ነው። ረግረጋማ ስፍራዎች ግን በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው እንደመሆናቸው መጥፋት የለባቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች ረግረጋማ ቦታን የመሬት ኩላሊት ነው እስከማለት ይደርሳሉና ስለዚህ ቦታ ይንገሩን እስኪ?
ዶክተር ጌቴ፡- ረግረጋማ ቦታዎች ትልቁ ጥቅማቸው የከርሰ ምድር ውሃን መልሶ እንዲያገግም ማድረጊያ ስፍራዎች ናቸው። ሌላው ቀርቶ በአንድ ስፍራ ያለው ረግረጋማ ቦታ ለየትኛው ስፍራ የከርሰ ምድር ውሃ እንደሚያጎለብት ራሱ አይታወቅም። ረግረጋማ ቦታን ማጥፋት ማለት የውሃውን ምልልስ እንደማበላሸት ይቆጠራል። በረግረጋማ ቦታ መጥፋት ምክንያት የሚጠፋ ጥልቅ ውሃ ይኖራል። ሁለተኛው ፋይዳው አካባቢውን የመቀየር አቅም አለው። ብዝሃ ሕይወትን የማነቃቃት አቅም አለው። በአግባቡ ራሱን እየተቆጣጠረ የሚሄድ የተፈጥሮ ሥርዓትን ማዛነፍ ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ ለዚህም ቦታ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።
በዚህ ዙሪያ ልክ እንደ ውሃው ሁሉ የመሬት አሁናዊ አቅምንም ጭምር ዝርዝር ጥናት አጥንተን ለመንግስት አቅርበናል። በተለይ ከመናገር ይልቅ ያለውን አስፈሪ አካሄድ እንዲያስተውሉ በሚል በተለያየ አምስት አቅጣጫ ከአዲስ አበባ ጎንደር፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ ነቀምት ሐዋሳና አዳማ በኋላ ላይ ሰመራንም ጨምርንና በእያዳንዱ አቅጣጫ ከመንገዱ 20 ኪሎ ሜትር በግራም በቀኝም 40 ኪሎ ሜትር ዲያሜትር ያለውን ቦታ ወስደን ዝርዝር ጥናት አጠናን። እኤአ ከ1985 ጀምሮ እስከ 2016 ድረስ የመሬት ለውጡ ምን ይመስላል? የሚለውን ዝርዝር ጥናት የያዘ ጥናት ነው። በጥናታችን ደኖች መመንጠራቸውን፣ ረግረጋማ ቦታዎች ወደእርሻነት መቀየራቸውን፣ ከተሞች መስፋታቸውንና ሌላም ዝርዝር ሁኔታ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለክቡር አቶ ኃይለማርያም አቀረብንላቸው። ጥናቱን ማቅረብ እንድንችል የግብርና ሚኒስቴር በጣም አግዞናል።
በወቅቱም በጥናታችንም መፍትሔ የሚሆነውን አመላክተናል። በተለይ ጉዳዩ በዘፈቀደ የሚሄደው አገሪቱ የመሬት ፖሊሲ ስለሌላት ነው። የመሬት አጠቃቀም ፕላንም የላትም። ስለዚህ እርሳቸውም በወቅቱ ፖሊሲውም ፕላኑም እንዲወጣ ሴክሬታሪያት እንዲቋቋም ተደርጎ ስራም ተጀምሮ ነበር። በዚህ መሃል ለውጡ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለ አላውቅም። እኛ በወቅቱ ያጠናነው እኤአ እስከ 2016 ያለውን ነበር፤ አሁንም እስከ 2022 ያለውን ለውጥ እያየነው ነው። አሁን ላይ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሙ በተወሰነ ደረጃ እገዛ ያደረገ ይመስላል።
ሌላው በትኩረት የምንሰራው የመሬት አያያዝ ላይ ነው። የተፋሰስ ልማት ሲባል ዝም ብሎ የአፈርና ጥበቃ ስራ አይደለም። ችግኝ መትከልም ብቻ አይደለም። ቅንጅታዊ ስራ መሆን አለበት። የተፋሰስ ልማት በአጭር ጊዜ የሚያስገኙ ሁለት ጥቅሞች አሉት። አንዱ ሕዝቡ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲይዝ ማድረግ ነው። እንዲያ ሲሆን፣ ምርታማነት ይጨምራል፤ መራቆት አይኖርም፤ የአየር ንብረት የሚያመጣውን ተጽዕኖ መቋቋም ያስችላል።
ሁለተኛው ደግሞ የረጅም ጊዜ ጥቅም ሲሆን፣ የተራቆቱ ቦታዎች እንዲያገግሙ ማድረግና ምርታማ መሬት ማድረግ መቻሉ ነው። በዚህ ስራ ጠፍቶ የነበረው ምንጭ ይጎለብታል፤ ብዝሃ ሕይወት ይመጣል። በዘላቂነት ግን ሶስት ጥቅም አለው፤ አንዱ ጤናማ ኢኮሲሰተም ሰርቪስ እንዲመጣ ያደርጋል፤ ኑሮን ያሻሽላል፤ በአየር ንብረት ጉዳት እጅ የማይሰጥ ሁኔታ ይፈጠራል። አሁን እኛ በምንከተለው ተፋሰሶች ላይ በተግባር እያሳየን ያለነው እሱን ነው። እርከን ብቻ ከምንሰራ ሌሎች ቋሚ የሆኑ ተክሎችንም መትከል አዋጭ ነው። እኛ ተፋሰስ ላይ ይህ ሁሉ አለ። በየተፋሰሱ ካሉ ነዋሪዎች ቢያንስ አብዛኛዎቹ የሚኖሩት በተስተካከለ የአኗኗር ስርዓት ሲሆን፣ ሌሎቹም ወደዚህ ስርዓት እንዲገቡ ተሞክሮዎችን እያጋራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጣም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ጌቴ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015