መንግሥት እንደ አገር ወደ ብሄራዊ ባንክ ለሚገባው የወርቅ መጠን እየቀነሰ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በጥናት በመለየት ለመፍትሄው እየሰራ ይገኛል። በወርቅ ግብይት ላይ ለተፈጠረው ችግር ዋናው ምክንያት በወርቅ ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይቱ በህገወጦች ክፉኛ መያዙ መሆኑን በመረዳት ህገወጥ ድርጊቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። እርምጃው እየተወሰደባቸው ከሚገኙ ክልሎች መካከል በወርቅ ማእድንና ምርቱ በእጅጉ የሚታወቀው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዱ ነው።
በክልሉ በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ በርካታ የውጭ ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያን በወርቅ ማእድን ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጸጥታና ደህንነት ግብረ ኃይል ከወራት በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ግብረ ኃይሉ እንዳለው፤ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ አገር ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተመሳሳይም በክልሉ በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ አገራት ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በቅርቡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በወጣ መረጃ መንግሥት በክልሉ በወርቅ ማእድን ህገወጥ ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይት ላይ በተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ተከትሎ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን እየጨመረ መጥቷል። የክልሉ ማእድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀሚድ በተለይ ለኢፕድ ሰሞኑን የሰጡት መረጃም ይህንኑ ያረጋግጣል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ በአንደኛና በሁለተኛ ሩብ ዓመት የወርቅ ምርትና ግብይት አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነበር፤ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በወርቅ ምርትና ግብይት ላይ በተደረገው ከፍተኛ ቁጥጥር መሻሻሎች እየታዩ መጥተዋል።
ከክልሉ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ ክልሉ በ2014 በጀት ዓመት 2ሺ300 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል። ይህንን መነሻ በማድረግ በ2015 በጀት ዓመት ሦስት ሺ ዘጠኝ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ አቅዶ ወደ ስራ ገብቶም ነበር። እስካሁን ባለው ሂደትም 482 ኪሎ ግራም የሚገመት ወርቅ ተገኝቷል፤ አፈጻጸሙ ግን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው።
የክልሉ ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ ለወርቅ ምርትና ግብይት አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ዋነኛው ምክንያት ሕገወጥ የወርቅ ግብይት መበራከት መሆኑን ይገልፃሉ። በተለይ በርካታ የሰው ኃይል በሚሰራባቸው አንዳንድ ካምፖች አካባቢ የወርቅ ምርት ቅነሳ መታየቱ በጥናት መረጋገጡንም ይጠቁማሉ።
ኃላፊው እንዳሉት፤ በቅርቡ በፌዴራል ደረጃ በተቋቋመ ግብረ ኃይል በክልሉ በወርቅ ምርትና ግብይት ላይ በተሰማሩ ሕገወጥ የውጭ ዜጎች ላይ የተወሰደው አይነት እርምጃ ቀደም ሲልም በክልል ደረጃም ሲወሰድ ቆይቷል፤ ክልሉ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በእነዚህ የውጭ ዜጎች ላይ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት የውጭ አገር ዜጎች ናቸው በሚል የሚሰሙ በርከት ያሉ ጩኸቶች ነበሩ። እነዚህ የውጭ አገር ዜጎች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባ ምንም አይነት ወርቅ አነልነበረም። በዚህ ምክንያት የውጭ አገር ዜጎቹ ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ እየታየ ይገኛል። በሌሎች ባልተያዙ ሕገወጦች የሚወሰደው እርምጃዎቹ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ክልሉ ቀደም ሲልም ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ በወርቅ ምርትና ግብይት ላይ የተሰማሩ አካላትን እየተከታተሉ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደነበር የጠቆሙት ኃላፊው፤ ጠንከር ያሉ እርምጃዎች በመውሰድ ረገድ ግን ክፍተቶች እንደነበሩም ተናግረዋል። በወቅቱ እንደ አሁኑ ዓይነት ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳልነበሩም አስታውሰው፣ አሁን በፌዴራል ደረጃ ከተቋቋመ ግብረ ኃይል ጋር አቋም በመያዝ የማያዳግም እርምጃ እየወሰድን እንገኛለን ብለዋል።
በክልሉ ወርቅ ለማምረት የሚያስችል አቅም የሌላቸው አንዳንድ በወርቅሥራ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው አካላት እንዳሉ ኃላፊው ጠቁመው፣ እነዚህ አካላት ወርቅ ለማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂም ሆነ የተማረ የሰው ኃይል እንደሌላቸው ተናግረዋል። በዚህ መሀል የሚፈጠሩ ክፍተቶች ወርቅ በሕገወጥ መንገድ እንዲመረት በር መክፈታቸውንም ጠቅሰው፣ እነዚህ ማህበራት በወርቅ ስራ ላይ መሰማራታቸው እንጂ እምብዛም እውቀቱ እንደሌላቸውም አስታውቀዋል።
‹‹አብዛኛዎቹ የውጭ አገር ዜጎች የወርቅ ቀለምን የሚቀይሩ ኬሚካሎችን ይዘው ነው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት›› የሚሉት ኃላፊው፤ ይህ አይነቱ ሕገወጥነት እዚህ ካለው ማህበረሰብ ንቃተ ህሊና አንጻር ሲታይ በእሱ ደረጃ መቆጣጠር የሚቻል አልነበረም ይላሉ። ሕገወጦቹ ቴክኒካል ሥራዎች በመሥራት ህገወጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ መቆየታቸው እንዳልታወቀባቸው ገልጸዋል።
ኃላፊው በሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም በሕገወጥነት ተግባር ላይ ተሰማርተው ስለተደረሰባቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል። በወርቅ ህገወጥ ተግባር እርምጃ የተወሰደበትን ‹‹ እሊኒት›› የተሰኘውን ድርጅት ለአብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም፣ ድርጅቱ ሕጋዊ የወርቅ ማምረት ፈቃድ ያለውና ከፍተኛ የወርቅ አምራች ሆኖ በዚያ ልክ ወርቅ ባንክ ሲያስገባ እንዳልነበረ ተናግረዋል። ድርጀቱ በሕገወጥ የወርቅ ምርት ላይ ተሰማርቶ በመገኘቱ ቀደም ሲል እርምጃ ተወስዶበት የወርቅ ማምረት ሥራውን እንዲያቆም ተደርጎ እንደነበርም አመልክተዋል።
ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ ሕጋዊ ከሆኑ አነስተኛ ማህበራት ጋር ተቀላቀለው የገቡ ሌሎች ሕገወጦች መኖራቸውም ተደርሶበታል። አምራቾቹ በነበሩበት ሳይት ወርቅ አምርቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ እስካልገባ ድረስ የወርቅ ምርቱ የት ገባ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። እነሱ የሚያመርቱት ወርቅ ብሔራዊ ባንክ እስካልገባ ድረስ መድረሻው የት እንደሆነ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ቀደም ሲል አብዛኛው ወርቅ በሕገወጥ መንገድ ወደውጪ ይወጣ ነበር። አሁን ሕገወጥነት እየተስፋፋ መጥቶ በህገወጥ መንገድ ከክልሉ የሚወጣው ወርቅ ወደ መሀል አገር ጭምር እየተወሰደ ይገኛል።
‹‹አሁን በክልሉ በወርቅ ምርት ላይ መሻሻሎች እየመጡ ነው›› የሚሉት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ እስከ 10 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይ ከመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ መሻሻሎች መምጣቸውን ነው የጠቀሱት፤ የወርቅ ምርትና ግብይቱ በመጋቢት ወር 12 ነጥብ 3 ኪሎ ግራም፣ ሚያዚያ ወር 20 ኪሎ ግራም እና በግንቦት ወር ደግሞ 43 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል። ቁጥጥሩ ጥሩ ለውጥ ማምጣት እያስቻለ ነው ብለዋል።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ ብሔራዊ ባንክ በወርቅ ዋጋ ላይ የወሰደው የማሻሻያ እርምጃም በሕገወጦች ምክንያት መቀዛቀዝ ባሳየው የወርቅ ምርትና ግብይት ላይ የተወሰኑ መሻሻሎች ማምጣት እያስቻለ ነው፤ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፤ ለአብነት ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም 5 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱ እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ በየቀኑ ይገባ ከነበረው የወርቅ መጠን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት ሰኞ ሰኞ ቀን በአማካይ 5 ኪሎ ግራም ወርቅ ይገኛል፤ እንደ ክልሉ በተለየ ሁኔታ ቅዳሜና እሁድ ተሰርቶ ሰኞ ላይ የተሻለ መጠን ያለው የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ይደረጋል።
በተለይ በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገብቶ ለአገር የሚሰጠውን ኢኮኖሚያ ፋይዳ እንዲሁም ወርቅን የጋራ ሀብት መሆኑን በማስረዳት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ኃላፊው የሚናገሩት።
እንደ ክልል አሁን ባለው ሁኔታ በአንጻራዊነት ሲታይ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ አካላት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ የሚሉት ኃላፊው፤ አሁን እንደ ክልል ትልቁ ችግር ያለው ኩባንያዎች ጋ መሆኑንም ይገልጻሉ። ኩባንያዎች በወርቅ ማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው የተሻለ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፤ ይሁንና አሁን ያላቸው አቅም ግን በዚህ ልክ አይደለም ብለዋል። ለምሳሌ እንደ ኢሊኔት ያሉ ኩባንያዎች በሕገወጥነት ሥራ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው እርምጃ የተወሰደባቸው።
በሌላ በኩል ሌሎች በወርቅ ማምረት ሥራ ላይ ለመሰማራት ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡ እንዳሉም ኃላፊው ጠቅሰዋል። በሥራውም ላይ ያሉት በሚጠበቀው ልክ ወርቅ አምርተው ማቅረብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በወርቅ ምርቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊፈጥር መቻሉን አመላክተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በክልሉ በባህላዊ የወርቅ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ 370 ማህበራት አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ይነስም ይብዛም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት የጀመሩት 30 የሚያህሉት ብቻ ናቸው።
ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት ያለባቸው አምራቾች፣ አዘዋዋሪዎች እና ኩባንያዎች ሲሆኑ፤ አሁን ላይ በወርቅ አዘዋዋሪዎች በኩል ወደ ብሑራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ እዚህ ገባ የሚባል አይደለም ሲሉ ኃላፊው ይጠቁማሉ። አዘዋዋሪዎች በነፍስ ወከፍ የሚመረተውን ወርቅ ከመግዛት ጀምሮ ለጥቁር ገበያው ተጋላጮች መሆናቸውንም ይገልፃሉ። አዘዋዋሪዎቹ ለሕገወጥነት የተጋለጡ በመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግና መረጃዎች ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በእጀጉ አስቸጋሪ እንዳደረገውም አመልክተዋል።
አቶ ካሚል እንዳሉት፤ በክልሉ በወርቅ ግብይትና ዝውውር ላይ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር 47 በሚሆኑ አዘዋዋሪዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ ፈቃዳቸው ተሰርዟል። ለ12 አዘዋዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ እነዚህ አዘዋዋሪዎች ከሕገወጥ ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ ደግሞ የማያዳግም እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
በክልሉ በወርቅ አምራችነት ሆነ ግብይት ላይ የተሰማሩ አካላት ሕጋዊ ሆኖ መስራት ላይ ችግር እንዳለባቸው ኃላፊው ጠቅሰው፣ ትልቁ ችግር ወርቅ ከተመረተ በኋላ ያለው አሻጥረና የጥቁር ገበያ የዋጋ ጭማሪ ሕገወጥነት እየተሰፋፋ መምጣት መሆኑን አመልክተዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው የውጭ አገር ዜጎች የማዕድን ምርት ላይ ያልተሰማሩ ምንም ሕጋዊነት የሌላቸው እንዴት እንደገቡ እንኳን የማይታወቁ ናቸው የሚሉት ኃላፊው፤ ከአነስተኛ አምራቾች ጋር የሚሰሩ አንዳንድ ሕገወጦች የሉም ማለት አይደለም ይላሉ።
ኃላፊው እንዳሉት፤ በቀጣይም እንደ ክልል በሕጋዊ መንገድ ወርቅ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን በመቆጣጣር አምራቾች በራሳቸው በቀጥታ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚያስገቡበት መንገድ በማመቻቸት ሕገወጥነት እንዳይስፋፋ ለማድረግ ይሰራል። አሁን ላይ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግብይትን የሚፈጽመው በንግድ ባንክ ውክልና ሲሆን፣ ባንኩ በተቻለ መጠን እስከታች ድረስ በመውረድ የግብይት ማዕከል መፍጠር በሚያስችለው ሁኔታ እየሰራ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ወርቅ ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚደረግ ሂደት ወርቁን ለሕገወጥነት ተጋላጭ እንዲሆን ያደርጋል።
በክልሉ በወርቅ ላይ የሚፈጸምን ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠር ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትልቅ ሥራ መስራትም ያስፈልጋል። በሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በሚገኙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል። በክልሉ ከላይ እስከታች ድረስ ያለው የመንግሥት መዋቅር በወርቅ መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ ይገኛል። ባለው ሥራ ጥሩ ለውጦች እየመጡም ናቸው። ችግሩ ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግን ይጠይቃል።
አሁን በክልሉ የወርቅ ግብይትን ለመቆጣጣር በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ የሕገወጥነቱ መንገዶችም በዚያ ልክ ብዙ ናቸው። እንደ ክልል ከማምረቻ ቦታ ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል። በፌዴራል ደረጃ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በጋራ የሚሰሩት ሥራዎችም እንዲሁ ይጠናከራሉ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የሰላም ችግር ክልሉ ያለውን የወርቅ አቅም አሟጦ አልተጠቀመም ያሉት ኃላፊው፤ በክልሉ ወርቅ የሚመረተው በአሶሳ ዞን ብቻ እንደነበር ይጠቁማሉ። አሁን በክልሉ በሰፈነው ሰላም በየቦታው እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ጠቅሰው፣ ክልሉ ያለውን የወርቅ አቅም ሁሉ አሟጦ መጠቀም አለበት በሚል እቅድ መያዙን ይናገራሉ። መተከል እና ከማሼ ዞኖች ወርቅ የማምረት ትልቅ አቅም ያላቸው ቦታዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ እየተሻሻለ የመጣውን የጸጥታ ሁኔታ በመጠቀም መሟላት ያለባቸውን ምቹ ሁኔታዎች በማሟላት የወርቅ አምራቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ወርቅ የማምረት አቅምን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ወደ ሥራ ያልገቡ ኩባንያዎችንም ሆነ አነስተኛ አምራቾች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት። ወርቅን የሚገዛው ብሔራዊ ባንክም ወርቅ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ድረስ መግዛት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል። ይህ ሁሉ ከሆነና በክልሉ በኩል የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተደረገ ወርቅን ትርጉም ባለው መልኩ ለአገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማዋል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2015