(የመጨረሻ ክፍል)
በይደር ወዳቆየሁት የ«ፍቅር እስከ መቃብር» እና የዳይሬክተርና የፕሮዲውሰር የሰውመሆን ጉዳይ ከመመለሴ በፊት «ፍቅር እስከ መቃብር» የተዋጣለት ፊልም እንዲሆን ካለኝ ብርቱ መሻትና ምኞት የተነሳ ከረጅም ልቦለድነት ወደ ፊልም ተቀይረው ከሰመረላቸው ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎች እነ ፦ “The Lord of the Rings” by J.R.R. Tolkien ፣ “Harry Potter” series by J.K. Rowling ፣ “The Hunger Games” series by Suzanne Collins ፣ “The Da Vinci Code” by Dan Brown ፣ እና “Gone with the Wind” by Margaret Mitchell ማስታወስ እፈልጋለሁ። እነ ሰውመሆን እነዚህ ሥራዎች እንዴት የተዋጣለት ፊልም ሊሆኑ እንደቻሉ ቢመረምሩ ብዙ ያተርፋሉ ብዬ አምናለሁ። ለመንደርደሪያ ያህል ይሄን ካልሁ ወደ ዳይሬክተርና ፕሮዲውሰር ሰውመሆን ልመለስ፦
ሰውመሆን ለቀረጻ እንዲያመች አድርጎ የጻፈውን የመጀመሪያ ፊልሙን በወቅቱ ስም ላላቸው ተዋንያን እንዲተውኑለት ሲሰጣቸው በድፍረት ነበር። ጽሑፉን ያነበቡት ግሩም ኤርሚያስ፣ ዕንቁሥላሴ አገኘሁ እና ይገረም ደጀኔን የመሳሰሉ ዕውቅ ተዋንያን በሀሳቡ ተስማምተው በፊልሙ ተሳተፉ። ተዋንያኑ «ሀሳቡን ወደውት፣ አምነውኝ ነው የሠሩት» ይላል ሰውመሆን። ሰማንያ ሺህ ብር ገደማ ከወጣበት ከዚህ ፊልም ግማሹ የተከፈለው ለዋናው ተዋናይ ግሩም ሲሆን ቀሪውን ሌሎቹ ተዋናዮች መከፋፈላቸውን ያስታውሳል። ፊልሙ አብዛኛው ቀረጻው በአንድ ቤት ውስጥ በመከናወኑም ብዙ ወጪ አላስወጣውም። «862» በሚል ርዕስ ለእይታ የበቃው የሰውመሆን ሥራ ሊያሳካ የሚያስበውን ግብም መትቶበታል።
«ምን እላለሁ መሰለህ? የመጀመሪያ ሥራህ ሁልጊዜ ወይ አነጋጋሪ መሆን አለበት ወይም ደግሞ ትልቅ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። ፊልሙ በወጣ ጊዜ ሁለት ዓይነት ተመልካች ነበረው። አንዳንዶቹ ‘ይህን ፊልም ከምናይ ፒዛ ብንበላ ይሻላል’ ብለው ይወጣሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ‘እንዴት ዓይነት የተለየ ፊልም ነው’ ብለው ወጡ። በዚህ ግርግር ውስጥ ይህ የሞከርኩት ነገር ዋጋ አግኝቶ፣ ሰዎችም እውቅና ሰጡት። የፎቶግራፍ እውቀቴም እየቀጠለ ሄዶ በደንብ ወደ ሲኒማው ገባሁ» ይላል በመጀመሪያ ፊልሙ ስላገኘው ምላሽ ሲያስረዳ።
በራሱ ፊልም እጁን ያፍታታው ሰውመሆን በመቀጠል በቶም የፊልም ትምህርት ቤት ባለቤት በተሠራው «ፔንዱለም» በተሰኘ ፊልም በሲኒማቶግራፈርነት ተሳተፈ። አዳዲስ እና ያልተለመዱ ነገሮች ሁሌም መሞከር የሚወደው ሰውመሆን በዚህም ፊልም ከዚያ ቀደም በሌሎች ፊልም ሠሪዎች ያልተደፈረ ነገር አድርጓል። እስከዚያን ጊዜ በነበረው አሠራር ፊልም የሚቀረጸው በቪዲዮ ካሜራ አሊያም ለሲኒማ ተብሎ በተሠራ መቅረጫ ነበር። የዘመኑ ቴክኖሎጂ በእጅ የሚንጠለጠሉትን የፎቶ ካሜራዎች ቪዲዮም እንዲቀርጹ አድርጎ አሻሻላቸው። እንዲህ ዓይነት ካሜራዎች ወደአገራችን ቢዘልቁም ደፍሮ ለፊልም የሚጠቀምባቸው አልነበረም። ተስፋዬ ወንድማገኝ በዚያን ወቅት የነበራቸውን ሙከራ ያስረዳል።
«ፔንዱለም የመጀመሪያው የ7D የፊልም ሥራ ነው። 7D የሚባል ካሜራ ከመምጣቱ በፊት በኒከን D90 በሚባል ካሜራ እኔ እና ሰውመሆን/ሶሚክ/ ከተማ እየዞርን እንቀርጻለን። ‘እንደዓይን የሚያይ ነገር በደንብ እንዴት መሥራት እንችላለን? ሌንስ የመጠቀም አቅማችንን እንዴት ነው [የምናዳብረው]’ እያልን በዚያ D90 ትንንሽ ነገሮች እንቀርጽ ነበር። ከዚያ 7D የሚባል ካሜራ ሲመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ እኛ ነን ያመጣነው። ሶሚክ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ፔንዱለም’ ላይ የቀረጸበት። እና ከብዙ ትግል በኋላ ነው ያመኑን። በትክክል በፎቶ ካሜራ እንደሚቀረጽ ማለት ነው» ይላል ተስፋዬ።
ሰውመሆን በፊልም ሥራ ውስጥ መስመር ያስያዘኝ የሚለውን «የፀሐይ መውጫ ልጆች» ፊልምን ከመስራቱ በፊት ሲኒማቶግራፈርነቱን አጠናክሮ ቀጥሎበት ነበር። «ኦፕሬሽን አክሱም» የተሰኘ የትግርኛ ፊልም፣ ሄርሞን ሃይላይ ያዘጋጀችውን «ባላገሩ» እና እስካሁን ለዕይታ ያልበቃ በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተቀረጸ «ለአንድ ዲግሪ 360 ዲግሪ»ን በተከታታይ ቀረጸ። በመሃል «ይሉኝታ» በተሰኘው የሚካኤል ሚሊዮን ፊልም ላይ በረዳት አዘጋጅነት ተሳትፏል። የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ቀረጻው በተከናወነው «የፀሐይ መውጫ ልጆች በዝግጅት (ዳይሬክቲንግ)፣ በፊልም ጽሑፍ እና የፊልም ቀረጻ ድርሻዎችን ጠቅሏል። ፊልሙን ፕሮዲዩስ ካደረጉ አምስት ሰዎችም አንዱ ነው።
በቢኒያም ወርቁ የተጻፈው ይህ ፊልም ሰውመሆን እጅ ሲገባ በ28 ገጽ ነበር። ይህን አስፋፍቶ፣ ለፊልም በሚሆን መልኩ አደራጅቶ በ70 ገጽ ለመጻፍ አንድ ዓመት ተኩል እንደወሰደበት ይናገራል። በፊልሙ ላይ ዋና ተዋናይ የነበረው ግሩም ኤርሚያስም አግዞታል። ሰውመሆን «በደንብ ተፈትኜበታለሁ» ስለሚለው «የፀሐይ መውጫ ልጆች» ማብራሪያ አለው።
«ይሄ የመንገድ ጉዞ ፊልም ነው። ሁለት ሰዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ስለነበር ጥንቃቄ ይፈልግ ነበር። ‘የፀሐይ መውጫ ልጆች’ የቀረጻ ሂደቱ ከባድ ነበር። ምን መሰለህ? ‘የፀሐይ መውጫ ልጆች’ የወጣበት ገንዘብ እና የፈጀው ጉልበት የሚነጻጸር አይደለም። በገንዘብ ብቻ ለ‘ፀሐይ መውጫ ልጆች’ የወጣው 150 ሺህ ብር ነው። ከዚያ ግን ግሩም ኤርሚያስ፣ ብርቱካን በፍቃዱ፣ ሰለሞን ቦጋለ አልተከፈላቸውም። ማንም ባለሙያ ገንዘብ አልተከፈለውም። እብደት ነበር። ዝም ብለን ወጥተን ነበር ያበድነው።
መንገድ ላይ በጣም ብዙ አስቂኝ፣ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመውናል። አፋር በረሃ ውስጥ ቀርጸናል። አፋር በረሃ ውስጥ ስንቀርፅ አይሱዙ መኪና ነበር ተከራይተን የሄድነው። አይሱዙ ላይ ‘ግሪን ስክሪን’ እያነጠፍን ነበር የምናድረው። ‘እባብ፣ ጊንጥ አለ’ እየተባልን እንደዚህ ነበር የሰራነው ፊልሙን። በጣም ፈታኝ ነበር። ግን ደግሞ ለሁላችንም ትልቅ መሠረት፣ ትልቅ ትምህርት ጥሎ ያለፈ ሲኒማ ነው” ይላል።
ሰውመሆን በዚህ ፊልም የጀመራቸውን አዳዲስ ነገሮችን የመሞከር ሂደት «ዓለሜ» በተባለው ቀጣይ ፊልሙ ላይም አሳይቷል። ስለ ሰውመሆን ሞካሪነት ዳይሬክተሩ ዳዊትም መስካሪ ነው።«ሲኒማቶግራፊ ላይ ስንመጣ ብዙ ጊዜ በአቀራረጽ፣ በተለይ ደግሞ በመብራት እና ብርሃን አጠቃቀም የራሱን ዘይቤ የፈጠረ ሲኒማቶግራፈር ነው ማለት እንችላለን። በዳይሬክተርነት እንደእኔ ሰውመሆን እየተጓዘ ያለ ዳይሬክተር ነው ብዬ ነው የማስበው።
ብዙ ነገሮችን እየሞከረ፣ እርሱ የሚወደውን እና የሚያምንበትን ዓይነት ነገር ላይ ለመድረስ እየሞከረ ያለ ዳይሬክተር ነው። «የፀሐይ መውጫ ልጆች»ን ምሳሌ ብናደርግ፣ ሌሎቹንም ፊልሞቹንም ብናያቸው ተመሳሳይ ሙከራዎች ውስጥ ያልሆኑ በጣም ብዙ ዓይነት ሙከራዎች እና ሙከራ ብቻ ሳይሆን የሲኒማ ስኬቶችን ጭምር የሚያገኝ ዳይሬክተር ነው።
«የፀሐይ መውጫ ልጆች» ፣ «ዓለሜ»ን ካየኸው ሌሎችም ፊልሞቹን የሚወጡትን፣ የወጡትን ፊልሞችም ካየኻቸው አንደኛ ታሪኩ የሚፈልገውን ነገር በመገንዘብ አዲስ ነገርን ለመፍጠር ይሞክራል። ሁለተኛ ደግሞ ከታሪኩም ውጪ እርሱ እንደፊልም ሰሪ የራሱን ቀለም እና አሻራ ያሳርፋል። ምናልባት እርሱ ቀለምእና ዐሻራ ለማሳረፍ የሚያደርገው ሙከራ ላይሆን ይችላል ግን የሚያደርገው ጥረት ዐሻራውን እንዲያሳርፍ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ።
«ዓለሜ»ን ከወሰድነው በጣም ቀዝቀዝ ባለ ፍጥነት፣ በጣም ጥልቅ የሆነ ታሪክን ለመንገር የሚሞከርበት ፊልም ነው።«የፀሐይ መውጫ ልጆች»ን ደግሞ ካየኸው ፈጠን ባለ ፍጥነት፣ በጣም የሚያስገርም፣ በስሜት ልብ የሚያንጠለጥል አድርጎ ለመንገር የሚሞከርበት ነው። ለሁለቱም እንደ ሲኒማቶግራፈርም፣ እንደዳይሬክተርም ሁለቱም ላይ የሞከራቸውን እና ያደረጋቸውን ነገሮች ስታይ የተለያዩ ግን ለየፊልሞቹ በጣም ተገቢ የሆኑ ነገሮችን የሞከረው» ይላል ዳዊት ስለ ሰውመሆን ሙከራዎች እና ጠንካራ ጎኖች ሲተነትን።
«ዓለሜ» ሰውመሆን በአገር አቀፍ የፊልም ውድድሮች ሽልማቶችን የሰበሰበበት ነው። እርሱም ራሱ «የእኔ ምርጥ ፊልም» ነው ይላል። «ደግሜ እሠራው ይሆን ብዬ ሁሉ የምጠራጠረው ነው» ሲልም ለፊልሙ ያለውን መውደድ በፈገግታ ታጅቦ ያስረዳል።«ከሰኒማቶግራፊ አልፌ ማዘጋጀት አካባቢ ስመጣ ከፍተኛ የሆነ መነሳሳት እፈልጋለሁ። ወደዚያ ታሪክ የሚወስደኝ።«ዓለሜ» መጀመሪያ ተጽፎ ሲመጣ ኮሜዲ የሚመስል ዘውግ ነበረው። ፕሮዲዩሰሯ ዳግማዊት ክፍሌ ትባላለች። ይዛልኝ ስትመጣ መጀመሪያ የእኔ ጥያቄ እንደፈለግሁት እንድጽፈው ትፈቅጅልኛለሽ ወይ? የሚል ነበር ከፈቀድሽልኝ ልሥራው አልኳት።
እንደፈልግኹት እንዳደርገው ፈቀደችልኝ። ሰለሞን ቦጋለ ነበር በጊዜው።«ዓለሜ» ላይ ምንድን ነው ያደረግሁት ? «ዓለሜ» እንደሀሳብ ትንሳኤ ላይ ነው የተሠራው። እውነታን ያለመቀበል ሀሳብም አለበት። ግን ዋናው ሃሳቡ ትንሳኤ ነው። የሰው ልጅ በጣም የሚወደውን፣ የሚያፈቅረውን ሰው ድንገት በሞት ሊያጣ ይችላል። ከዚያ ምንድነው የሚሆነው? ምንድነው መሰለህ? ‘በጣም የምትወደውን ሰው ህልም በመኖር ሰውየውን ማኖር ትችላለህ። ዕድሜ ልክ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ሀሳብ ያለው ሀሳብ ስለሆነ ትንሽ ጥልቅ ፊልም ነው። አንድ ሰው ከሁለት አሻንጉሊቶች ጋር የሚጫወተው ፊልም ነው። እና ትልቁ ተግዳሮት የነበረው አንድን ተዋናይ ከሁለት አሻንጉሊት ጋር ሙሉ ሰዓት ከተመልካች ጋር መግባባት ፈጥሮ እንዲቆይ ማድረጉ ነው።
ሌላ«ዓለሜ»ላይ ትልቅ ሙከራ ያደረግኹት የፊልም ሥራውን ነው። ፊልም ሥራው አሁንም በጣም የምኮራበት ነው። በ5D ነው የተቀረጸው፣ ካሜራው ትንሽ ፎርማት ነው ግን በጣም ኃይለኛ Computer Generated Images (CGI) የሚሠራ ዳንኤል ታምራት የሚባል ልጅ እና ሌላኛው Production Designer ተስፋዬ ወንድማገኘሁ የሁለቱ ግብዓት ፊልሙን ለምናቤ የቀረበ አድርጎታል። እኔ በምናቤ የምስለውን ነገር ቀርጬ አላውቅም እላለሁ።«ዓለሜ» ግን ለምናቤ የቀረበ ፊልም ነው። ያሰብኩትን ነገር በትክክል ለማሳካት የተጠጋሁበት ነበር። በእነዚህ ሁለት ልጆች እገዛ ወደዚያ፣ ወደ ህልሜ ቀርቧል ብዬ አምናለሁ ይላል ሰውመሆን።
የወጣቱ ፊልም ሰሪ ሥራ ከአገር ተሻግሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው በቅርቡ በሠራው «እውር አሞራ ቀላቢ» በተሰኘው ፊልሙ ነው። ዘካሪያስ ጥበቡ በተባለ ኢትዮጵያዊ የስደት እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሠራው ይህ ፊልም በፌስቲቫሎች ሽልማቶች እና እውቅናዎች አግኝቷል። ባለፈው ግንቦት በተካሄደው የኒውዮርክ አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የፌስቲቫሉ ዋና ፊልም ሆኖ ተመርጧል። በዳላስ ኢንተርናሽናል አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ደግሞ ሽልማት አግኝቷል።
ከአዲ ዳዕሮ-አዲግራት እስከ ገላባት ሱዳን፣ ከመተማ እስከ ጅቡቲ ድንበር፣ ከአፋር እስከ ትግራይ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር ተዘዋውሮ የተቀረጸው ይህ ፊልም በመጪው መስከረም ወር በኢትዮጵያ መታየት ይጀምራል ተብሏል። ወጣቱ የፊልም ባለሙያ በዚህኛው ፊልም ከሙከራዎች አልተገታም።በ«እውር አሞራ ቀላቢ»ም በተወሰነ መልኩ ሙከራ አድርገናል ብዬ አምናለሁ። የዶክመንተሪ ድራማ ይዘት ያለው ሥራ ነው። ምን ማለት ነው? እውነተኛ ድርጊቶቹን እንደገና መልሰን ሠርተናል። ተዋንያን ስንመርጥም በሕይወት የሌሉትን ሰዎች ብቻ ነው ተተኪ ተዋናይ ያደረግነው።
በሕይወት ያሉትን ራሳቸው ባለታሪኮቹን ታሪኩ የተፈጸመበት ቦታ ድረስ እየሄድን ነው የቀረጽነው። ዋናው ታሪክ ከስደት በኋላ ቤተሰቦቹን፣ አጎቱን እና የአጎቱን ልጆች ለማግኘት ስለሚመጣ ልጅ ነው። ወደ አጎቱ ልጆች ቤት የሚሄደውም በእውን ነው የቀረጽነው። ሲገናኙ፣ እናቱ እና አባቱ መቃብር ሄዶ የሚያይበት፣ ለቅሶ የሚደርስበት ገቢሮች አሉ። እነርሱ የእውነት ነው የተቀረጹት። ከእዚያ ደግሞ ከእርሱ ተነስተን ጉዞውን፣ የተሰደደውን፣ የሄደውን መንገድ፣ የተሰቃየውን ስቃይ እርሱን ደግሞ በድራማ አድርገን ነው የሠራነው። ሁለቱን ቀላቅለን ነው ፊልም ያደረግነው።
«ይሄኛው ሌላ ዓይነት መንገድ ነው» ይላል ሽልማት ስላጎናፈው ፊልም ለየት ያለ ዘውግ ሲያብራራ።«ከፊልም ፊልም እየተማርኩ ነው» የሚለው ሰውመሆን የሁለት ቀጣይ ሥራዎችን ቀረጻ አጠናቅቋል። ባህር ዳር ላይ የተቀረጸው አንደኛው ፊልሙ በተለይ እስከዛሬ ከሠራኋቸው ሁሉ ሃሳቦቼን በደንብ የገለጽኩበት ነው ይላል። በፊልም ሥራ ስለሚከተለው ፍልስፍና ሲጠየቅ በረጅሙ ተነፍሶ፣ የፊልም ባለሙያው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከዚህ ቀደም የተናገሩትን አጣቅሶ ተከታዩን ምላሽ ይሰጣል።
ፍልስፍና ይሁን፣ ምን ይሁን አላውቅም ብቻ ጋሽ ኃይሌ በጣም ደጋግሞ «የሰው ልጅ በጣም የሚውቀውን ነገር መሥራት አለበት»ይላል። እኔም ደጋግሜ ስሰማው በጣም እየገባኝ የመጣው ነገር እርሱ ነው። በጣም የምታውቀውን ነገር ስትሠራ ኃይለኛ ይሆናል። ዓለም ላይ በደንብ መታየት እንችላለን ብዬ አስባለሁ። በደንብም የሰው ልጅ የሚያውቀውን ነገር መሥራት አለበት። በጣም ብዙ ነገር አለን። አንዳንድ ልጆች ይመጣሉ የፊልም ጽሑፍ ይዘው ይመጣሉ። የሆነውን ገቢር ስታነበው የሆነ ፊልም ይመስልሃል፣ ሌላኛውን ገቢር ስታነበው ሌላ ፊልም ይመስልሃል።
ከዚያ እስኪ የእናትህን ታሪክ ንገረኝ፣ እናትህ እንዴት ናቸው?፣ አባትህ እና እናትህ እንዴት ተገናኙ ስትለው ጉደኛ ታሪክ ይነግርሃል። እና ምን ሆነ ነው ከዚህ ጋር የምትላፋው፣ ምን ይሠራልሃል ይሄ፣ የምትነግረኝ ነገር እኮ በጣም የሚገርም ነው ስትለው አፉን ይዞ ልጁ ተመልሶ ይሄዳል። ስለዚህ በትክክል የሰው ልጅ የሚያውቀውን ነገር መሥራት አለበት ብዬ አምናለሁ።
ይሄ ነው ለእኔ ሲኒማ ውስጥ ያለኝ ሀሳብ። እና የእውነት መነሳሳት ያስፈልገዋል። በቃ! ከነፍስህ፣ ከልብህ ጋር ሲገናኝ ታገኘዋለህ። የእውነት ከውስጥህ ሲወጣ ነው በትክክል የሚሠራው ብዬ አምናለሁ ሲል እምነቱን ለጀርመኑ ዶቸ ቬለ ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ እና ሸዋዬ ለገሠ ይገልጻል። እኔም ሰውመሆንንም ሆነ ቡድኑን ወይም ክሩው «ፍቅር እስከ መቃብር»ን ወደ ፊልም ለመቀየር ሥራ ሲጀምር ይህን ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ በደንብ ጥንቅቅና ልቅም አድርጎ አውቆ ይሆናል ብዬ በጽኑ አምናለሁ።
ሻሎም ! አሜን×፫።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015