አገሬው ዘመናትን በተሻገረው አብሮነቱ የሚያጋጥሙትን ማኅበራዊ ችግሮች ሁሉ እየፈታ አገሩን ያጸናበት የራሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች አሉት:: ተረቶቹ፣ ምሳሌዊ ንግግሮቹ ወጎቹ … ወዘተ በዘፈቀደ የሚነገሩ ሳይሆኑ አኗኗሩን እና እሱነቱን በሚገባ የሚገልጹ፤ ማኅበራዊ አወቃቀሩ፣ ስሪቱ ወይም አኗኗሩ ምን መልክ መያዝ እንዳለበት ቅርጽ የሚያስያዙ ናቸው::
ምሳሌዊ ንግግሮቻችን እኛን ይመስላሉ፤ እኛም እነርሱን እንመስላለን:: ከችግሮቻችን የምንወጣባቸውን ቀና መገንገዶች ያመላክቱናል፤ በፍቅር፣ በሰላም እንድንተሳሰር ብርቱ ምክር ይለግሱናል፤ ከላይ ርዕስ አድርገን የተጠቀምነው ‹‹ እርቅ እንባ ያድርቅ›› የሚለው የአበው ብሂል በተለያዩ ጉዳዮች በተለይም በነፍስ መጠፋፋት ምክንያት ዓይንህ ለአፈር የተባባሉና ለበቀል የሚፈላለጉ ሰዎች ቂማቸውን እርግፍ አድርገው ትተው እርቅ እንዲያወርዱ የሚያደርግ፤ ይቅር ባይነትን የሚያስተምር፤ የልብ ስብራትን የሚጠግን ነው::
አባባሉ ተራ ንግግር ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን የግሪክ ፈላስፎች ከሚናገሯቸው አባባሎች ያልተናነሰ በብዙ መልኩ ሊተነተን እና ሊመነዘር ወደሚችል እውነታ የሚወድስ ምጡቅ አስተሳሰብ ነው:: ይቺ አንድ ዘለላ የቃላት ስብስብ ወይም ሐረግ የተሸከመችው መልዕክት ለብዙዎች መድህን የመሆኗ ነገር አያጠራጥርም:: በየአካባቢው በበዳይና በተበዳይ መካከል ያለውን የጥላቻ ግንብ እየደረመሰች በሕዝቦች መካከል ሰላማዊ መስተጋብር እንዲፈጠር የማድረግ ሚናዋ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም::
እነዚህ ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን ማኅበራዊ ቅርጻችንን በተለያየ መንገድ መልክ አስይዘውታል:: ለምሳሌ ‹‹ወፍ እንደአገሯ ትጮሃለች፤ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› የሚሉትን ብንመከት ለአካባቢያዊ ችግራችን እራሳችን አካባቢዊ መፍትሔ መስጠት እንዳለብን የሚያስገነዘቡና የሚመክሩ ናቸው::
ሩቅ ከመመልከት ይልቅ አጠገባችን ያሉትን በርካታ አማራጮች እየተጠቀምን የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን እንድናጠናከር፤ እንደጎረቤቶቻችን ሳይሆን እንደቤታችን ወግና ባሕል እንድንኖር የሚረዱን ናቸው:: የአማርኛ ምሳሌያዊ ንግግሮችን ለማሳያነት ተጠቀምሁ እንጂ በሁሉም ቋንቋዎቻችን ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው አባባሎች አሉ::
ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን እሴቶቻችንም ናቸው፤ እሴቶቻችን ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችንን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ መገለጫዎቻችን ናቸው፤ ሠርተውናል:: ፍቅርን፣ ሰላምን፣ እርቅን፣ መተዛዘንን፣ መደጋገፍን፣ መተማመንን፣ አንድነትን ወዘተ እየሰበኩ ማኅበራዊ ግንኙነታችን በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም አስተዋጽኦ አበርክተውልናል:: ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንም ቢሆኑ እንዲሁ የህሊናችንን ጉድፍ አጽድተው ግላዊ ባህሪያችንም ሆነ ማኅበራዊ ቅርርባችን የተቃና እንዲሆን አስችለውናል::
እኛ ኢትዮጵያውያን ከጎረቤቶቻችንም ሆነ ከተቀረው ዓለም የምንለየው ለሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ዋጋ የምንሰጥ ሕዝቦች በመሆናችን ነው:: ያ ባይሆን ኖሮ ከባዕድ አገር እየተነሳ ሱማሌን፣ የመንን፣ ሱዳንን ፣ ሶሪያን ለእርስ በእርስ ግጭት የዳረጋቸውና ምስቅልቅላቸውን ያወጣቸው አውሎ ነፋስ እኛንም ባፈራረሰን ነበር::
ከዓመታት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረውን ጦርነት መነሻ አድርገው የተዛቡ መረጃዎችን በማስተላለፍ እና የአንድ ወገን ተቆርቋሪ መስለው በመቅረብ አብሮነታችንን ለማፈራረስና ሰላማችንን ለማደፍረስ ምን ያህል እንደደከሙ የታዘብነው ሐቅ ነው::
ዛሬ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ቀውስ ወጥታ ወደ ቀደመው ሰላሟ ለመመለስ አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች:: ‹‹ወፍ እንደአገሯ…. እንጂ›› እንደ ሂውማን ራይት ዋች ስለማትጮህ የጀመርነውን የሰላም ንግግር እንደአገራችን የሽምግልና ባህል እያስኬድን ለችግራችን መፍትሔ እናስቀምጣለን እንጂ ባዕዳን በሚቀዱልን ቦይ አንፈስም፤ ሰላማችንም ወደ ኋላ አይመለስም::
እርግጥነው ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚኖሩና በዚህም በዚያም ወገን ያሉ በርካታ ንጹኃን ዜጎቻችን ጉዳት ደርሶባቸዋል:: በትግራይ፣ በአፋር በአማራ ክልል ዜጎች በግፍ ተገድለዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ ተፈናቅለዋል:: ለጠፋው ጥፋት አንዱ አንዱን ይወቅሳል፣ አንዱ ሌላውን ይከሳል:: ግን በሁሉም ወገን ቆሞ ያጠፋውም ሆነ የጠፋው የእኛው ናቸው::
‹የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ›› እንደተባለው ዓይነት ነው:: የቤታችንን ችግር መፍታት ያለብን እኛው ቤተኞቹ እንጂ እንደሂውማን ራይት ዎች ዓይነቶቹ የሩቅ ተመልካቾች አይደሉም:: ‹‹ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንዲሉ በቅርብ ስላሉ ቤተሰቦቻችን ጉዳት ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ሂውማን ራይት ዎች ሊነግረን ባልተገባ ነበር::
የት ምን ተከሰተ? ምን ያህል ሰው ሞተ? ምን ያህል ንብረት ወደመ? የሚለውን ዛሬም ከእኛው ከኢትዮጵያውያንና ከአካባቢው ነዋሪዎች በላይ የዓይን እማኝ ሆኖ ሊናገር የሚችል የለም:: የሁሉም ዜጎቻችን ጉዳት ጉዳታችን ነው:: የሂውማን ራይት ዎች ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ ሪፖርት እና ‹‹አዛኝ ቅቤ አንጓችነት›› የጀመርነውን ሰላማዊ ንግግር ለማደናቀፍ የታሰበ ሴራ እንጂ ከእኛ በላይ ለእኛ በማሰብ አይደለም::
አሁን ኢትዮጵያውያን በደልን ከመቁጠር ወጥተን እንደወግ ባሕላቸው ይቅር እየተባባልን ያለንበት ሰዓት ነው:: በቅርቡ በትግራይ ክልል ጊዜዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ልዑክ ወደ አመራ ክልል በመሄድ የተጀመረውን የሰላም ንግግር ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና ከኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር መምከሩ የሚታወስ ነው::
በውይይቱም ዋጋ የማይጠይቅ ሰላማዊ ንግግር እያለ በተፈጠረው ጦርነት ብዙዎች ዋጋ መክፈላቸው የሚያስቆጭ እንደሆነ ተነስቷል:: በፖለቲካ አመራሮች በኩል ያሉ ልዩነቶች ከሕዝቡ በታች እንደሆኑም ተጠቅሷል:: አሁን የጦርነት ምዕራፍ ተዘግቶ የሰላም አማራጭ እየታየ ያለበት ወቅት በመሆኑ ገርበብ ብሎ የተከፈተው በር በደንብ ተከፍቶ በሁለቱም ክልሎች የሰላም አየር እንዲናኝ ተመክሯል::
ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ልዩነቶችን በሰላማዊ ንግግርና በሕግ አግባብ መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ፤ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውና የንግድ ትስስሩ እንዲጀመር፤ በፖለቲካ አመራሩ የተጀመረውን የሰላም ግንኙነት የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች በተለይም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ያሉ ሕዝቦች አጠናክረው ሊቀጥሉት እንደሚገባ ተመክሯል::
እንግዲህ ችግሮችን እንዲህ ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ እርቅማውረድና ሰላም መፍጠር ነባር እሴታችን ነው:: አባቶቻችን በዚህ መልክ ሠርተው ያስረከቡንን አገር እኛም የእነርሱን አደራ ተቀብለን ለልጆቻችን ማስተላለፍ ይገባናል:: እንነጋገር! እንተራረም! እንታረቅ!
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015