አሜሪካ እና ቻይና በመካከላቸው የነበረውን ውጥረት ለማርገብ ተስማሙ። ይህ የሆነው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቻይናን ከጎበኙ በኋላ ነው። ብሊንከን በቻይና የሁለት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል። ሰኞ ዕለት ብሊንከን የቻይናውን ፕሬዚዳንት አግኝተው በልዩነቶቻቸው ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ሁለቱ አገራት በሚከተሉት ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የተነሳ ምናልባት ወደ ግጭት ያመሩ ይሆን የሚል ስጋት ረብቦ እንዳለ አለ። የቻይናው ፕሬዚዳንት ከውይይቱ በኋላ «ይበልጥ ለመነጋገር በር ከፍተናል» ይበሉ እንጂ በንግግራቸው ምን እንዳሳኩ ያሉት ነገር የለም። ውይይቱን የተከታተሉ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ግን በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የነበሩት ሰፊ ልዩነቶች አሁንም እንዳሉ ናቸው ብለዋል።
አሜሪካ ቻይናን ለሩሲያ አደገኛ የጦር መሣሪያ እንዳታቀብል እንዳግባባች ተሰምቷል። «በሁለት አገራት መሀል ያለ ፉክክር ወደ ግጭት እንዳያመራ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ንግግር እንዲኖር ያሻል» ብለዋል ብሊንከን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ። «ይህን መተማመን ከቻይና በኩልም እንዳለ ተረድቻለሁ፤ ውጥረት ለማርገብ ተስማምተናል» ሲሉም ጨምረው ገልጠዋል።
ይሁንና የ61 ዓመቱ ብሊንከን በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ ሰፊ ልዩነቶች እንዳሉ እንደሚቀጥሉ አልሸሸጉም። «በእኛ መካከል ያለው ልዩነት በአንድ ጉብኝት፣ በአንድ ንግግር የሚጠናቀቅ መቼ ሆነና?» ሲሉም ነገሩ ውስብስብ እንደሆነ ለማመላከት ሞክረዋል።
በቤጂንግና በዋሺንግተን መካከል ግንኙነቶች ማሽቆልቆል የጀመሩት ትራምፕ ቻይና ላይ የለየለት የንግድ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ነበር። ከንግድ ጦርነቱ ባሻገር ቤጂንግ ታይዋን የኔ አንድ አካል ናት በማለት ደጋግማ ማስጠንቀቋ፣ ከዚያም ደግሞ አሜሪካ የቻይና የስለላ ፊኛዎች ናቸው ያለቻቸውን በራሪ አካላት መትታ መጣሏ ውጥረቱን ሲያጉነው ሰንብቷል።
ብሊንከን ጉብኝታቸውን ሊያደርጉ በሚሰናዱበት ወቅት ነበር የቻይና ፊኛዎች በአሜሪካ የአየር ክልል ቅኝት ማድረጋቸው የተደረሰበትና ጉብኙቱም የተሰረዘው። የሰኞ ዕለቱ የብሊንከን ጉብኝት ከአምስት ዓመት በኋላ በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ የተደረገ የመጀመሪያ ጉብኝት ሆኖ ተመዝግቧል።
በቻይናው ፕሬዚዳንትና በብሊንከን ውይይት ከተደረገባቸው አበይት ጉዳዮች መካከል የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ የሰሜን ኮሪያ ነገር፣ ቻይናና የሰብአዊ መብት አያያዟ፣ እንዲሁም የታይዋን ዕጣ ፈንታ ይገኙበታል። ምንም እንኳ መሪዎቹ ‘ቁልፍ ጉዳዮችን አንስተን በመግባባት መንፈስ ተወያየን’ ቢሉም ይህ ነው የሚባል ስምምነት አላደረጉም። ከንግግራቸው በጎ ነገር ሆኖ የተሰማው ንግግሩን ለመቀጠል መወሰናቸው ነው። ብሊንከን፣ «አሁን ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘናል» ብለዋል።
ጆ ባይደን ከቻይና ጋር ያላቸው ግንኙነት «የውድድር እንጂ የመጠፋፋት» መሆን የለበትም ሲሉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ይሁንና ሁለቱ ኃያላን በምጣኔ ሀብትና በወታደራዊ አተያያቸው ብዙ የሚጣረሱ ፍላጎቶች ስላሏቸው መስመር ተላልፈው ወደለየለት ግጭት እንዳያመሩ ወትሮም ስጋቱ እንዳለ ነው።
ሁለቱን ኃያላን ከሚያፋጥጧቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የታይዋን ጉዳይ ነው። ቻይና፣ ታይዋን «ከእኔ ለጊዜው ያፈነገጠች፣ ነገር ግን አንድ አካል ግዛቴ ናት፤ ባሻኝ ጊዜም ደግሞ እጠቀልላታለሁ» ስትል አሜሪካ ደግሞ ታይዋን ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ወታደራዊ ትንኮሳ የመከላከል ቃል አለብኝ ትላለች። ብሊንከን፣ አገራቸው ታይዋንን ሉአላዊት አገር እንድትሆን አሜሪካ እንደማትሻ መጠቆማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርት
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015