የአሜሪካ ፍርድ ቤት ‘የጥቃት አቀናባሪዎች’ የፍርድ ማቅለያን ውድቅ አደረገ

የአሜሪካ የፌደራል ይግባኝ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ የተፈጸመውን የ9/11 ጥቃት በማቀናበር የተከሰሱት ካሊድ ሼክ መሐመድ እና ሌሎች ተከሳሾች የፍርድ ማቅለያ ስምምነትን ውድቅ አደረገ። ካሊድ ሼክ መሐመድ እና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች የሞት ፍርድ እንዳይፈረድባቸው ለማስቀረት፤ በምትኩ የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች በሙሉ አምነው ለመቀበል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

የይግባኝ ፍርድ ቤቱ ተከፋፍሎ ነበር የተባለ ሲሆን፤ ጥቃቱን ያቀናበሩት ግለሰቦችን በጽኑ የእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣውን ስምምነት የዋሽንግተን ዳኞች 2ለ1 በሆነ ድምፅ ውድቅ አድርገውታል። መሐመድ በአውሮፓውያኑ መስከረም 11 ቀን 2001 የመንገደኞች አውሮፕላን ጠለፋን በማቀነባበር እና በመምራት ተከሷል። የተጠለፈው አውሮፕላን በኒውዮርክ የዓለም ንግድ ማዕከል እና ከዋሽንግተን ወጣ ብሎ በሚገኘው ፔንታጎን ላይ ተከስክሶ 3 ሺህ ያህል ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ሌላኛው አውሮፕላን ውስጥ አንድ መንገደኛ በመታገላቸው በፔንስልቫንያ በሚገኝ ሜዳ ላይ ተከስክሷል። ይህንን ጥቃት በማቀናበር ክስ የተመሠረተባቸው ሦስቱ ግለሰቦች ከ20 ዓመት በላይ በአሜሪካ በእስር ላይ ቆይተዋል። የቅድመ ችሎት ሰሚም ከአስር ዓመት በላይ ቆይቷል። በዚህ ወቅትም ሦስቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ነን ብለው ያመኑት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በሲአይኤ ለረጅም ጊዜ በደረሰባቸው የከፋ ማሰቃየት በኋላ ነው የሚሉ ክርክሮች ተሰምተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2003 በቁጥጥር ስር የዋለው መሐመድ በምስጢራዊ የሲአይቤት ከታሰረ በኋላ 183 ጊዜ ያህል በውሃ እንዲሰጥም እና እንዲታፈን የማድረግ ስቃይ ተፈጽሞበታል። እሱን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ ርቃናቸውን ማጋለጥ ጨምሮ፣ እንቅልፍ ማሳጣት እና ሌሎች “የረቀቁ የምርመራ ዘዴዎች” ተግባራዊ ሆኖባቸዋል ተብሏል። በአሁኑ ወቅት መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች በኩባ፣ ጓንታናሞ ቤት በአሜሪካ እስር ቤት እንደሚገኙ ታውቋል።

በስምምነቱ መሠረት በ9/11 ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦች ለመሐመድ ጥያቄ እንዲያቀርቡ የሚፈቀድላቸው ሲሆን እነሱም “ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ እውነተኛ በሆነ መልኩ እንዲመልስ” ይጠበቅበት እንደነበር ጠበቆች ተናግረዋል። ተጎጂ ቤተሰቦች በስምምነቱ መከፋፈል እንደታየባቸው ተዘግቧል። ስምምነቱን የተቃወሙ ሰዎች የፍርድ ሂደቱ ስለ ጥቃቱ የበለጠ መረጃ ለማግኘት እንዲሁም ለፍትሕ የተሻለ መንገድ እንደሆነ ያምናሉ።

ስምምነቱን የደገፉ በበኩላቸው ይህንን ለረጅም ዘመናት የቆየውን ፈታኝ ምዕራፍ መቋጫ ነው ይላሉ። የፍርድ ማቅለያ ስምምነቱ ሁለት ዓመት በወሰደ ድርድር የተደረሰ ሲሆን ወታደራዊ ዓቃብያነ ሕግ እና በጓንታናሞ ቤይ ከፍተኛ የፔንታጎን ባለሥልጣን የፀደቀ ነው። በቅድመ ችሎት ከአስር ዓመታት በላይ የቆዩት መሐመድ እና ሌሎች ተከሳሾች በአሜሪካ እና በጓንታናሞ ቤይ እንግልት እና ስቅይት በከፍተኛ ሁኔታ የተፈጸመባቸው ከመሆኑ አንጻር ከተከሳሾቹ የተገኙ መረጃዎችን ያወሳሰቡ እና ጥያቄዎች ያጫሩ ሆነዋል።

ባለፈው ዓመት የባይደን አስተዳደር ከመሐመድ እና ሌሎች ሦስት ተከሳሾች ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቆ ነበር። ነገር ግን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ከሁለት ቀናት በኋላ እንዲህ ዓይነት ስምምነት ውስጥ የመግባት ሥልጣን ያላቸው እሳቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ሽረውት ነበር።

ነገር ግን ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሚኒስትሩ ያሳለፉትን ውሳኔ ውድቅ አድርጎ ይህንን የፍርድ ማቃለያ ስምምነት መልሶት ነበር። ነገር ግን ዓርብ ዕለት የፌደራሉ ይግባኝ ፍርድ ቤት ቤተሰቦች እና የአሜሪካ ሕዝብ የወታደራዊ ፍርድ ሂደትን የማየት ዕድል ሊሰጣቸው ይገባቸዋል በሚል ውሳኔ አሳልፈዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You