አንዳንድ ሰዎች ለሆነ ጉዳይ ምክንያት መፍጠር ሲሹ በዘመንና ጊዜ ያሳብባሉ። ሁሌም እንዲህ ባሰቡ ጊዜ መነሻ መድረሻቸው ያው መከረኛ ጊዜና ዘመን ይሆናል። እነዚህ ሰዎች በየጨዋታቸው መሀል ‹‹አይ ጊዜ ! ›› ማለትን ያበዛሉ። ዘመኑን ኮንነው፣ ጊዜውን ይራገማሉ። እስካሁን ለሆነውና ወደፊት ለሚሆነው አሉታዊ ድርጊት ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉት ያለፉበትንና ወደፊት የሚመጣውን አዲስ ዘመንና ጊዜውን ነው። እንደ እኔ ሀሳብ ግን ለክፉ ጉዳዮች ተጠያቂ መሆን የሚገባው ጊዜና ዘመን ሳይሆን ራሱ የጉዳዩ ባለቤት ነው።
በርከት ያሉ ተሳፋሪዎች ከያዘ የሕዝብ አውቶቡስ ውስጥ እገኛለሁ። አጋጣሚ ሆኖ ወንበር አጥተው ከቆሙት መሀል አልተደመርኩም። አስቀድሜ ከያዝኩት መቀመጫ አረፍ እንዳልኩ ከውጭ ወደውስጥ የሚገቡትን ተሳፋሪዎች እየታዘብኩ ነው። አውቶቡሱ ከሞላ ቢቆይም የያዘው ብቻ የበቃው አይመስልም። ትኬት ቆራጩ አሁንም አንገቱን በመስኮት እንዳሰገገ ነው። እጃቸውን ከዘረጉት ሁሉ ገንዘብ እየተቀበለ ተሳፋሪዎችን ወደ ውስጥ ያሳልፋል። አሁን ሆዱ ያለቅጥ የሞላው አውቶቡስ ሞልቶ ከመፍሰሱ በፊት ‹‹በቃኝ›› ያለ ይመስላል። በሩን እንደምንም ዘግቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ጥቂት እንደተጓዝን ትንፋሽ ያጣሁ ቢመስለኝ መስኮት ፍለጋ ዓይኖቼን አሻገርኩ። በዚህ አፍታ በጭንቅ ከቆሙት ተሳፋሪዎች መሀል ትኩረቴ በአንድ አዛውንት ላይ አረፈ። ዕድሜ ጠገቡ ሰው ብረቱን እንደምንም ይዘው ይንገዳገዳሉ። ድካም ያዛለው አካላቸው በላብ ወርዝቷል። በቁማቸው ዕንቅልፍ የወሰዳቸው መሰለኝ።
ዞር ብዬ ዙሪያ ገባውን ቃኘሁ። ወንበር ከያዙት አብዛኞቹ ወጣቶችና በጉብዝና ዕድሜ ያሉ ጎልማሶች ናቸው። ደነገጥኩ። ከነዚህ መሀል አንዳቸው እንኳን ስለአዛውንቱ ደንታ ማጣታቸው አሳሰበኝ። አብዛኞቹ ‹‹ባላየ›› በሚባል መልኩ መንገዳቸውን ቀጥለዋል። ‹‹አይ ! ጊዜ ወይ ! ዘመን ማለት አልፈለኩም። እንዴ! ወዴት እየሄድን ነው ? ራሴን ጠየኩት። ደግነቱ ከመልሱ በፊት ሽማግሌው ወንበር ይዘው አየኋቸው። የተባረከች አንዲት ልጅ እግር ቢጤ ተነስታላቸው ኖሯል።
ወዳጆቼ ! ይህን ትዝብታዊ ምሳሌ ማንሳቴ ያለ ምክንያት አልሆነም። እርግጥ ነው በመንገዴ ያጋጠመኝ አይነት እውነት ሁሌም እንደማይሆን አውቃለሁ። አብዛኛው ታላላቁንና ሽማግሌዎችን ያከብራል። ይህ የቆየ ማንነት አሁን ላይ እየሳሳ ቢሄድም ለዘመናት በክብር አብሮን ቆይቷል።
‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› እንዲሉ ከዕድሜና አዛውንትነት ጋር ተያይዞ የሚሳስበኝን አንድ እውነታ ልናገር። አሁን ላይ በየቤታችን ብሎም በአካባቢያችን ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች ከጎናችን ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ዛሬ ላይ ደርሰው ‹‹አረጋውያን›› ሲባሉ እንዲሁ በዋዛ አይደለም። ጥቂት የማይባል የኑሮ ውጣውረድን አልፈው፣ ለሀገርና ትውልድ የሚተርፍ ደማቅ አሻራን አሳርፈው ነው።
እንዲህ አይነቶቹ ታላቅ የሀገር ባለውለታዎች ደግሞ ብድራታቸው ይመለሳል። ሳይሞቱ፣ ሳይረሱ በቁመናቸው በጎነት፣ መልካምነታቸው ይዘከራል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ለትውልድ የሚቀመጠው የታሪክ ቅብብሎሽ አይዛነፍም። ሰንሰለታዊው ጉዞ ሳይዘነፍ በጥንካሬው ይቀጥላል።
አሁን ባለንበት ጊዜ ግን ይህ እውነታ በወጉ ቀጥሏል ለማለት አያስደፍርም። ዛሬ ላይ ወላጆቻቸውን ከመጦር ይልቅ እስከለተሞታቸው በእነሱ አቅምና ትከሻ የሚጦሩ ልጆች በርክተዋል። ተወልደው ያደጉበትን ቤት ከመደጎም፣ እድሜ ያጎበጣቸውን አዛውንቶች ከመደገፍ ይልቅ ለራሳቸው ብቻ የሚያድሩ ልጅ ተብዬ ሸክሞች በየቤቱ አይጠፉም።
እንዲህ አይነቶቹ ውል አልባዎች መለስ ብለው የወላጆቻቸውን ድካም አይቃኙም። ዛሬም በእነሱ ጥላ አርፈው የእጃቸውን ፍሬ ይጠብቃሉ። የጡረታቸውን ጥቂት ገንዘብ መንጠቅን ይናፍቃሉ። እንደህ አይነቶቹ ልጅ ተብዬዎች ወልደው አሳድገው፣ ቁምነገር ላበቋቸው ወላጆቻቸው ደንታ የላቸውም። ዛሬም ድረስ የእናቶቻቸውን ቁራሽ በፍቅር ሳይሆን በአስገዳጅነት መጉረስ ይሻሉ። ይህ አይነቱን ስሜት ይዘውት ኖረዋልና ‹‹እንጡር ፣ እንደግፍ፣ በዛውም እንመረቅ፣ እንመስገን›› ይሉትን ወግ አይሞክሩትም ።
በሀገረ ቻይና አንድ ልጅ ዕድሜው በደረሰ ጊዜ የወላጆቹን ታላቅ ውለታ እንዲመልስ ይገደዳል። (በእኛም አገር ስንጠቀምበት አይታይም እንጂ በቤተሰብ ሕግ ውስጥ እንዳለ ሰምቻለሁ። ) ወላጆችም ቢሆኑ በልጆቻቸው የሚደረገላቸውን እንክብካቤ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው። ይህ በሕግ ተደንግጎ በመመሪያ የጸደቀው ደንብ በየትኛውም ሰበብ ተፈጻሚ ከመሆን የታቀበ አይደለም ።
ወደ እኛ አገር ተጨባጭ እውነታ መለስ ስንል ከመከባበር ባለፈ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችን ብቻ ሳይሆን ላልተወለዱን አዛውንቶች ጭምር እጆቻችንን የምንዘረጋበት አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ይህን ለማድረግ ስንውስን ግን በገሀድ የሚታይ ችግር ስላለና እነሱም ችግሩን መቋቋም ስለተሳናቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ወላጆች ዕድሜያቸው በገፋ በደከሙ ጊዜ ለችግር የመጋለጣቸው አጋጣሚ ትኩረት ሰጥቶ የሚረዳቸው ወገን የመጥፋቱ እውነታ ነው። እንዲህ ባይሆንማ እንደውለታቸው ዓይን ጥሎ፣ ጊዜ ወስኖ ‹‹አለሁ›› የሚላቸው ባልጠፋ ነበር።
በሕይወት አጋጣሚ እንደሚታየው ወላጆች አያት በሆኑ ጊዜ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ይሆናል። ከልጆቻቸው ይልቅ ለልጅ ልጆቻቸው የሚያሳድሩት ፍቅር በእጅጉ ያይላል። በዚህ መሀል ድካምና ችግር ቢኖር እንኳን ተቋቁመው ያልፉታል እንጂ ፈጽሞ አይከፉም ። አንዳንዴ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የሕይወት አቅጣጫ ይቀየራል። በሚያርፉ፣ በሚጦሩበት ዕድሜ የልጅ ልጆቻቸውን አሳደጊዎች ይሆናሉ።
ወደዚህ መንገድ የመግባታቸው እውነት ምናልባትም የልጆቹን ወላጆች በሞት ማጣታቸው አልያም በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ይችላል። እንዲህ መሆኑ ብቻውን ስለነእነሱ አትኩሮት እንዳይኖር ያደርጋል። በሰለጠኑት ዓለማት የዕድሜ ባለጸጋዎች እንደ ታላቅ ሀብት ይቆጠራሉ። ከእነሱ ጠጋ ያሉም ትርፍ እንጂ ኪሳራ አይገጥማቸውም። እነዚህ አዛውንቶች ልጆች ካላቸው በልጆቻቸው፣ አልያም በቅርብ ዘመዶቻቸው ይደገፋሉ። የአገራቸው መንግስት ፈጽሞ አይተዋቸውም። የዕድሜ ዘመናቸውን አክብሮ የተለየ ቦታ ይቸራቸዋል።
በነዚህ ዓለማት የዕድሜ ባለጸጎቹ በቤታቸው ምቹ ሕይወት ባይኖር እንኳን ለእነሱ ተብሎ በተዘጋጁ ማዕከላት ሙሉ ወጪያቸው ተችሎ ዘላቂ ድጋፍ ይኖራቸዋል። ህክምናን ጨምሮ ውሏቸውን በደስታና ተዝናኖትም ያሳልፉታል። የእነዚህ አገራት የዕድሜ ባለጸጎች እንደ እኛዎቹ ቀሪ ዘመናቸውን በሀዘንና ትካዜ አይገፉትም። በልዩ ትኩረት፣ የተለየ እንክብካቤና ፍቅር እየተመገቡ ያለፉበትን ዘመን በያዙት ዓለም ደስታ ያጣጥማሉ።
ወደ እኛ ሕይወት መለስ ስንል አብዛኞቹ አንጋፋዎቻችን በዕድሜያቸው ማምሻ ለሀዘንና እንግልት የተጋለጡ ናቸው። ጥቂት የማይባሉትም ያለ ጧሪ ቀባሪ ኑሯቸውን ለመግፋት ይገደዳሉ። ይህ ችግር ከሕዝብ ቁጥር መጨመርና ከኑሮ ማሻቀብ ጋር ለአረጋውያኑ ታላቅ ፈተና ይሆናል። የሀገር ባለውለታነታቸውንም ያስረሳል።
ተደጋግሞ እንደሚባለው ‹‹አንድ ትልቅ ሰው ሲሞት አንድ ቤተመጻህፍት እንደተቃጠለ ይቆጠራል›› ብዙ ጊዜ ግን በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብን ታላላቅ ሀብቶቻችን ስናከብር፣ ዕውቀትና ተሞክሮን ስንጋራ አይስተዋልም። አረጋውያን የማንነታችን መነሻ፣ የትውልድ መሰረት ናቸው። ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› እንዲሉ ታላላቆችን በማክበር፣ ውለታቸውን የመመለስ ልምድ ይኑረን። ትናንትን አልፈን፣ ዛሬን ኖረን፣ ነገን ለማየት የእነሱ ታላቅ አሻራ በማንነታችን ስር ታትሟልና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም