ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? በጣም ጥሩ ነው እንደምትሉ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ጎበዝና ቤተሰቡን የምትሰሙ ልጆች እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ይህንን የሚያደርግ ልጅ ደግሞ በትምህርቱ ውጤታማ እንደሚሆን ማወቅ አለባችሁ፡፡
ልጆች ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ሃሳብ የምታውቁት ቢሆንም በድጋሚ ማንሳትና ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ይዤላችሁ የቀረብኩት ጉዳይ ጠቃሚ ነው፣ ምንድነው እሱ? ካላችሁ ስለሰኔ 5 ነው የምነግራችሁ፡፡ እንደምታውቁት ሰኔ አምስት የዓለም ፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን ነው፡፡ ለምን ይከበራል ካላችሁ ደግሞ ቀጣዮቹን ምክንያቶች አንብቡ፡፡
ልጆች ቀኑ የሚከበርበት ምክንያት አንድ እና አንድ ነው፡፡ ልጆች ከአቅማቸው በላይ ሥራ እንዳይሰሩ ማድረግ፤ ቤተሰባቸው ያላግባብ በስራ ጠምደው ለጭንቀት እንደይዳረጉ መከላከል፤ ልጆችም መብትና ግዴታቸውን አውቀው ቤተሰባቸውን እንዲያገለግሉ ማስቻል ነው፡፡ ቀኑ ሲታሰብ በሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ሁሉም ሰው ማድረግ ያለበትን እንዲያውቅ ይሆናል፡፡ ስለዚህም የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ይቀራል፡፡
ልጆች ሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ ደርሶባቸዋል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? እስቲ ትንሽ ላብራራላችሁ፣ ሕፃናት በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ሲባል በየሳምንቱ ለ21 ሰዓታት ወይም ከዚያ በላይ በቤት ውስጥ ወይም በሌላ የሥራ መስክ ላይ ተጠምደው ውለዋል ማለት ነው፡፡ ይህ የጉልበት ብዝበዛ ደግሞ ሕጻናት ላይ አርፏል የሚባለው የእድሜ ክልሉ ከአምስት እስከ 14 ዓመት ላይ ሲሆን ነው፡፡
የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ሊፈጠር የሚችልባቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው። ዋነኛው ግን የኢኮኖሚ ችግር እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተጨማሪም የኢኮኖሚ መዛባት እና የብሔራዊ በጀቶች መቀነስ የዓለም የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን በእጅጉ ከጨመሩት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ የመከሰቻ አጋጣሚው ደግሞ በተለይም የትምህርት ቤቶች መዘጋት የሥራ ማጣት፣ የኑሮ ሁኔታ እና የማኅበራዊ ደህንነት እና የኢኮኖሚ እጦት ናቸው፡፡ የህዝብ ብዛት መጨመር፣ ተደጋጋሚ ቀውሶች፣ ከፍተኛ ድህነትም እንዲሁ ችግሩን ከሚፈጥሩት መካከል ናቸው፡፡ ለመሆኑ ይህና ይህን መሰል ምክንያቶች ምን ያህል ሕጻናትን ጎድተዋል ካላችሁ ካነበብኩት ያገኘሁትን መረጃ ላካፍላችሁ፡፡
በዓለም ዙሪያ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በቁጥር ወደ 160 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው መግለጫው ያስረዳል፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ በየዓመቱ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳያል፡፡ ይህ ቁጥር በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖዎች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሕጻናት ወደ አስገዳጅ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ የመግባት አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር ያወሳል።
የዓለም ፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀንን አስመልክቶ ይኸው ድርጅት ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ እንዳስቀመጠው፤ የህጻናትን ጉልበት ብዝበዛ ለማስቆም የተጀመረው ሥራ ግቡን ሳይመታ በመቅረቱ የተነሳ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አስገራሚ በሆነ መልኩ ቀደም ሲል እያሽቆለቆለ የነበረው አሃዝ በመቀልበስ ከፍተኛ በሆነ ቁጥር መጨመር አሳይቷል፡ ፡ እኤአ በ2000 እና በ2016 ባሉት ዓመታት መካከል 94 ሚሊዮን ሕጻናት ለአስገዳጅ የጉልበት ብዝበዛ ተዳርገዋል።
በልጆች የጉልበት ሥራ ላይ ያሉ ሕፃናት ረዘም ላለ ሰዓት መሥራት ወይም በከፋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡ ብዙዎች ደግሞ በተጎጂዎች መካከል ሥራ በማጣት እና ገቢ በማጣት ወደ አስከፊ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በወንድ ልጆች ላይ ይከፋል፡፡ በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በጣም የተለመደ ነው።
ይህ ማለት ከከተማ ሕፃናት ጋር ሲነፃፀር በገጠር አካባቢዎች የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ (13 ነጥብ 9 በመቶ) ሲሆን፤ በከተማ ከሚገኘው (4 ነጥብ 7 በመቶ) አሃዝ ይሆናል። ስለዚህ አሃዙ በሦስት እጥፍ ይበልጣል። በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዋነኛው እና ትልቁን ድርሻ የሚወስደው በቤተሰብ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ሲሆን፤ ግብርናው በስፋት ይጠቀሳል።
የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በተደጋጋሚ ሕጻናቱ ከትምህርት ቤት ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን የጉልበት ብዝበዛ ሁሉም ሊታገለው ይገባል፡፡ ምን በመስራት ካላችሁ የመጀመሪያ የሚሆነው ግንዛቤ በመፍጠር አገራት ገቢያቸውን ከፍ የሚያደርጉበትን መንገድ መቀየስ፤ ልጆች ወደነበሩበት ትምህርት ቤት እንዲመለሱ የማህበራዊ ጥበቃ መርሃ ግብሮች ማስፋት፤ ሕጻናት ለመብታቸው እንዲሟገቱ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም መብታችሁን አውቃችሁ የሕጻናት ጸረ ጉልበት ብዝበዛ ትግል ልታደርጉ ይገባችኋል በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን።
ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015