ኪነጥበብ ለአንድ አገር የቱሪዝም እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የቱባ ባህል ባለቤት ለሆኑ አገራት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ ህብረተሰቡ ባህሉ፣ ወጉን፣ እሴቶቹንና ታሪኩን ጠብቆ ለትውልድ እንዲያስተላልፍ ከማድረጉም ባሻገር የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጀው 14ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ለዚሁ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹በሥነ ጥበባት ሕብራዊ መልክ የተዋበች ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት በተካሄደው የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል የተለያዩ የባህልና ኪነጥበብ ክንውኖች ተስተናግደዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ቦታ ላይ ስንደርስ በተዘጋጁ ዱንኳኖች በስተቀኝ በኩል በአራት ማዕዘን በእያንዳንዳቸው ውስጥ በእጅጉ የተዋቡ የኢትዮጵያን ቱባ ባህል የሚያጎሉ ሥራዎች ተሰድረው ተቀም ጠዋል። የተለያዩ በጥንታዊና ዘመናዊ መልኩ የተዘጋጁ ባህላዊ አልበሳት ፣ ልዩ ልዩ ቅርሶች፣ የኪነጥበብ መሳሪያዎች፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች በስፋት ቀርበዋል፡፡ በዚሁ ፌስቲቫል ላይ ሥራቸውን ይዘው ከቀረቡት አንጋፋ የኪነጥበብ ተቋማት ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤቶች ድረስ ያሉ ተማሪዎች የተለያዩ ጥዑመ ዜማዎችን እያሰሙ ዝግጅቱን አጅበውታል፡፡ በተቃራኒው በኩል ባሉት ዱንኳኖች ደግሞ የተለያዩ የመጻህፍት፣ የቅርጻ ቅርጾችና የሥነ ጥበብ ውጤቶች (ስዕል) በስፋት ጎልተው የቀረቡበትን አውደ ርዕይ ተመልክተናል፡፡
በእጅጉ በተዋበ ህብረ ብሔራዊነትን በሚገልጽ መልኩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳትን ለብሰው ያጌጡ፣ በቡድን በቡድን ሆነው ህብረ ዝማሬን የሚያሰሙ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች እንዲሁም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች የፌስቲቫሉ ድምቀት ነበሩ፡፡
ፌስቲቫሉ ሲጀመር በከተማዋ ያሉ የካበተ ልምድ ያላቸው የቴአትር ቤቶች የኢትዮጵያን ባህላዊ እና ዘመናዊ የኪነጥበብ ሥራዎች አቅርበዋል። የዳግማዊ ሚኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ማርሻል ባንድ ለየት ባለ ሁኔታ ልዩ የሆነ ጥዑመ ዜማ ያቀረበበት ያማረ ዝግጅትም ሌላው የዝግጅቱ ድምቀት ሆኗል፡፡
በዕይታዊ ጥበባት፣ በክንውን ጥበባት፣ በሥነ ፅሑፋዊ ጥበባት መስኮች የተለያዩ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የሥነ ጥበብ ተቋማት፣ ቴአትር ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች፣ ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎችም ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ዝግጅታቸውን ካቀረቡት አንጋፋ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ አገር ፍቅር ቴአትር ቤት አንዱ ነው፡፡ ቴአትር ቤቱ በርካታ ባህላዊና ዘመናዊ የሆኑ ኪነጥበባዊ ሥራዎች ይዞ መቅረቡን የሚናገሩት የቴአትር ቤቱ ስቴጅ ማናጀር አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ፤ የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከተቋቋመበት 1934 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የጥበብ ሥራዎች እያበረከተ ይገኛል፡፡ በፌስቲቫሉም ቴአትር ቤቱ እስካሁን ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳዩ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት እንዲሁም ጥንታዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እና በተለያዩ ወቅቶችን የሚያስታውሱ መገልገያ መሳሪያዎች ይዞ ቀርቧል፡፡
በተለይ በ1934 ተሰርቶ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ‹‹እናት መስንቆ›› በመባል የሚታወቀውን ለእይታ አቅርቧል፡፡ ይህ መሰንቆ ከሌሎች ለየት ባለ መልኩ የተሰራና በወቅቱ የማህበረሰቡ የፈጠራ ችሎታ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ በቴአትሩ ረገድ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት የተሰራው እነ ቀኝ ጌታ ዩፍታሄ ንጉሤ የነበሩበት ‹‹አፋጀሽኝ›› የተሰኘ እውቅ ቴአትር እና መሰል በርካታ ቴአትሮች የተዘጋጁባቸውን በአብዛኛው ባሕላዊ የሆኑ አልባሳትና መገልገያ መሳሪያዎች በማስተዋወቅ ትውልድ እንዲያውቃቸው ለማድረግ መቅረባቸውን ይገልጻሉ፡፡
በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መገልገያ መሣሪያዎች በቴአትር ቤቱ እንደሚገኙ የሚናገሩት አርቲስት ዮሐንስ፤ አንጋፋዎቹ ቴአትሮች ከተሰሩባቸው አልባሳት በተጨማሪ አስቴር አወቀን የመሳሰሉ ድምጻውያን ለብሰውት ሲወዛወዙባቸው ከነበሩ አልባሳት እና መገልገያ መሳሪያዎች የተወሰኑት ለማሳያ ያህል በፌስቲቫሉ ላይ ማቅረባቸውንም ነው አርቲስት ዮሐንስ ያብራሩት፡፡
‹‹ይህ ፌስቲቫል በየዓመቱ የሚዘጋጀበትን ዓላማ በሚገልጽ መልኩ የሚዘጋጅ እንደመሆኑ መጠን መሻሻሎችን እያሳየ፣ እየተለወጠና እያደገ የመጣ ነው›› የሚሉት አርቲስት ዮሐንስ፤ ቴአትር ቤቱ በእዚህ ፌስቲቫል ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ እስካሁን ጠብቆ ያቆያቸውን እነዚህን ባህላዊ አልባሳት፣ መገልገያ መሳሪያዎችና የኪነጥበብ መሳሪያዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ህዝባዊ እይታዎች የሚያገኙበትና በኪነጥበብ ዘርፍም ያለውን ድርሻ የሚወጣበት ነው ብለዋል፡፡
አርቲስት ዮሐንስ ቴአትር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ለአገር ፍቅር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ብዙ ሥራዎች መሥራቱን ነው የሚገልጹት። በተለይ በጥበቡ ዘርፍ አገር አንድ እንድትሆንና የከፍታ ማማ ላይ እንድትደርስ ለማድረግ በርካታ የኪነጥበብ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አርቲስቱ ጠቁመዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ተሳታፊ የሆኑት የኪነጥበብ ባለሙያው አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ በበኩላቸው ከዚህ ፌስቲቫል የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ያለበትን ደረጃ ለመገመት የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ የኪነጥበብ ፌስቲቫሎች ዓመት ጠብቀው የሚዘጋጁ መሆን የለባቸውም፡፡ ሌሎች አገራት እንደሚያደርጉት በየወሩ፣ በየሦስት ወሩና በየስድስት ወሩ ሊቀርቡ የሚችሉበት ዝግጅት ቢሆን ይመረጣል፡፡ ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቅሱት እንደዚህ አይነት በተደራጀ መልኩ የሚቀርብ የኪነጥበብ ፌስቲቫል ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ነው፡፡
‹‹በፌስቲቫሉ የቀረቡት ዝግጅቶች የተወሰነ ቦታ ላይ ተገድበው የሚቀሩ ናቸው ብዬ አስባለሁ›› የሚሉት አርቲስት ጥላሁን፤ ዝግጅቶቹ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የሚያበረታቱ ከመሆናቸውም በላይ የውጭ አገር ቱሪስቶችን እንዲስቡና ገቢ እንዲያስገኙ ለማድረግ ድንበር ተሻጋሪ ሆነው ከአገር ውጭ መውጣት አለባቸው ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ውጪ ለመውጣት አቅም እንዳላቸው ዝግጅቱ ጥሩ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡
‹‹በመድረኩ ወጣቶቹ ያሳዩት ሞራል፣ ኃይል፣ ጉልበት፣ አቅም፣ ችሎታ፣ ብቃትና ፍላጎታቸው የሚደነቅ ነው›› ያሉት አርቲስት ጥላሁን፤ እንደዚህ አይነት ፌስቲቫሎች ላይ የሚጨመሩ ነገሮችን በማሳደግ በከተማ ብቻ ተገደቦ ያለውን የኪነጥበብ ፌስቲቫል ለዓለም እንዲደርስ ቢደረግ ኪነጥበብ ራሱን ከማሳደግ አልፎ ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያስችላል በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ሌላኛው የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ደጀኔ እንደሚሉት ፤ ፌስቲቫሉ ኪነጥበብን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በፌስቲቫሉ የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ሥራዎች ቀርበዋል፡፡ እንዲዚህ አይነት ፌስቲቫሎች ባሕል እንዲያድግና እንዲበለጽግ ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ ስለሆነ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየስድስት ወሩ ቢዘጋጁ ጠቀሜታቸው ላቅ ያለ ነው፡፡
‹‹በኪነጥበብ ፌስቲቫሉ በየዓመቱ እካፈላለሁ፤ አሁንም እድሉ እንዳያመልጠኝ ሥራዬን ትቼ ነው የመጣሁት። ዝግጁቱም ከሚጠበቀው በላይ እየጨመረ መምጣቱን ተመልኬቻለሁ›› የሚሉት ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ፤ የኪነ ጥበብ ዝግጅቱ የአገርን ባህል፣ ወግን በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተረሱ የኪነጥበብ መሣሪያዎች፣ ባሕላዊና ዘመናዊ የሆኑ አልባሳትና መገልገያ መሣሪያዎች ለትውልድ እንዲተላለፉ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
እንደ ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ገለጻ፤ በየዓመቱ ያለው ዝግጅት እየሰፋ፤ ይዘቱ እየጨመረ እና እየደመቀ መምጣቱ ለኪነ ጥበብ ምንያህል ትኩረት ተሰጥቶ ሥራዎች እንደተሰሩ ዝግጅቱ አንድ ማሳያ ነው፡፡ የኪነጥበብ ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ ብቻ ተወሰኖ መቅረት የለበትም፡፡ አጠናክሮ ማስቀጠል ከከተማ አቀፋዊነት ተሻግሮ አገር አቀፋዊ ሁነት እንዲሆን ከክልሎች ጋር ትስስር በመፍጠር የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ሁሉም በየተራ የሚዘጋጅበት ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል፡፡ በአገር አቀፍ መልኩ ሲዘጋጅ እርስ በእርስ ለማስተዋወቅ፤ ባሕልን ከባሕል ለማስተሳሰርም የሚያስችል በመሆኑ የባለሀብቱም ሆነ የሚመለከተው አካል ሁሉ ድጋፍ ቢያደርጉ ዘርፉን ማሳደግና ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡
ኪነጥበብ ለአገር ባለውለታ ነውና መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ማድረግ አለበት የሚሉት ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ፣ ‹‹የኪነጥበብ ዘርፉ አሁን ላይ የምናያቸው ነገሮች ተሻግረው መጪው ትውልድ ዘንድ እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል›› ሲሉ ይገልጻሉ፤ ይህም ለአገር ፣ለልማት ፣ ባሕልና ወግን ለመጠበቅ ፣ ህብረተሰቡን ለማነቃቃት፣ ለማስተማር ግንዛቤን ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ አለው›› ይላሉ። በዘርፉ ጎልቶ እንዲወጣ ትኩረት ሰጥቶ ብዙ መሰራት አለበት የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንዳሉት፤ የባሕልና የኪነጥበባት ዘርፍ እጅግ በጣም ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ማመንጫ እሴቶች ናቸው፡፡ የቱሪዝም ዘርፍን ለማስተዋወቅና ለቱሪስት መስህብ ከመሆን አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡
የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ የሚቻለው የባህልና የኪነጥበብ ዘርፉ ካደገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የባሕልና የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የባሕልና የኪነ ጥበብ ዘርፉ የአገር ውስጥንም ሆነ የውጭ ቱሪስትን የሚስቡ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠሩ ናቸው፤ ማህበረሰቡ እየተዝናና ለአገሩ ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋፅኦ የሚያደርግበት ነው›› ብለዋል፡፡
በተለይ በባሕልና ኪነጥበባት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፌስቲቫል ማዘጋጀት ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ከማመቻቸት በተጨማሪ የፈጠራ ሥራን እንደሚያበረታታም አስታውቀዋል፡፡ ፌስቲቫሉ ባሕልንና የኪነ-ጥበባት ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ከማሳደጉም በላይ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም የቆየ ባህል፣ ታሪክና ልማድ ለትውልድ ለማሸጋገር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹በኪነጥበብ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፤እነዚህን ሥራዎች ከዚህም ባሻገር ከተማ አቀፍ፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያበረታታቸው፣ሊደግፋቸውና እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ፌስቲቫል የኪነ ጥበቡ ማህበረሰብ ሥራዎቹን የሚቀርብበት አቅሙን የሚያሳይበት፣ የአገሪቱን ፣ የከተማዋን ገጽታ የሚገነባበት ለቱሪዝም ሀብት ማመንጫነት ሰፊ እድል የሚፈጥርበት ነው፡፡ ስለዚህ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የኪነጥበብ ዘርፉን በማበረታታት ሊደግፉ ይገባል፡፡
‹‹ባህል፣ ኪነ ጥበባዊ ተግባራት እንዲሁም ታሪክ ለአገራችን ብርቅዬ ሀብቶች ናቸው›› ያሉት አቶ ስለሺ፤ በቀጣይም ባህልን፣ ታሪክንና ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን መጠበቅና መንከባከብ ላይ መስራት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ኪነጥበቡ አንዱ የቱሪዝም ሀብት ሆኖ ወደ ገበያ እንዲቀርብ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሐት በበኩላቸው ፤ፌስቲቫሉ በከተማዋ ያሉትን የኪነ ጥበብ ሀብቶች አጉልቶ ለማሳየት የሚረዳ መሆኑን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የኪነ ጥበብ ወይም የሥነ ጥበብ ሥራዎች የእይታና የክዋኔ መድረክ ከማግኘት በላይ ቀዳሚ ጥያቄ የላቸውም፡፡ የሥነ ጥበብ ፈጠራ ትልቁ አንቀሳቃሽ ኃይል የህዝብ እይታ፣ አድናቆትና እውቂያ ማግኘት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እነዚህ ዘርፉች ጎልተው የሚታዩባቸውን መድረኮች ማዘጋጀት በብዙ መልኩ አስፈላጊ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ትልቁ የቱሪዝም አቅም ያለው በማይስ ቱሪዝም በኩል ነው ያሉት አቶ ሰርፀ፤ ከማይስ ቱሪዝም መተግበሪያ መካከል አንደኛው የኪነ ጥበብ ፌስቲቫሎችን ደጋግሞ ማዘጋጀት የከተማዋን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጠቅሰው ሲናገሩም፤ ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሳይ ባሕሪ ያላቸው ዓለም አቀፍ ከተማዎች በከተሞቻቸው ዓመቱን ሙሉ መሰል ፌስቲቫሎች በማዘጋጀታቸው በርካታ የዓለም ሕዝብ ወደ ከተሞቻቸው እንዲጎርፍ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑም አስቻሏቸዋል ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ይህንን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመውሰድ ደግማ ደጋግማ የኪነጥበብ ፌስቲቫሎች የማዘጋጀት የቤት ሥራ መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ፌስቲቫሉች ካላቸው ማህበራዊ ጠቀሜታ ባሻገር እየፈጠሩ ያሉት አኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ሠርፀ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ከፍ ያለ የከተማዋ ኢኮኖሚ ሊያንቀሳቅስ የሚችል ሰፊ የእሴት ሰንስለት የሚነካ የሥራ እድል መስክ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ባህልና ኪነ ጥበብ ነክ ፌስቲቫሎች ከተማዋን ከማስተዋወቅና ከተማዋን ለቱሪዝም ተመራጭ ከማድረግ በተጨማሪ ለኢኮኖሚው ዘርፍ የጎላ ፋይዳ አለው ሲሉ ንግግራቸውን አሳርገዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015