ኢትዮጵያ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ አያሌ ለውጦችን አስተናግዳለች። በዚህ ጥቂት ጊዜ ውስጥ “የደፈረሰው ሲጠራ፣ የጠራው ሲደፈርስ” ተመልክተናል። በውይይትና በስምምነት የፈታናቸው አገራዊ ሽንቁሮች ያሉትን ያህል ወደ አላስፈላጊ ግጭቶች፣ ጥፋቶችና መቃቃሮች ውስጥ የከተቱንም በርካታ ጉዳዮች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ተመልክተናል። በጥቅሉ ተደማምጠንም፤ ሆድና ጀርባ ሆነንም እነዚህን ጊዜያት አልፈን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከሁለቱም ክስተቶች ትምህርቶችን መውሰዳችንም አልቀረም።
ሰክነን በመወያየታችን የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውንና ፓርቲዎቻቸውን ወደጎን ትተው ለአገር እድገትና ለህብረተሰብ ልማት በጋራ መንግሥት በሚለው ጥላ ስር የተሰባሰቡ የኢትዮጵያ ምሁራንን አፍርተናል። ለዚህ ሁነኛ ማሳያው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔና በተዋረድ ባሉ የሥራ ሃላፊነት ቦታዎች የሚሰሩ ፖለቲከኞች ናቸው።
በተቃራኒው ገመድ በመጓተታችን፣ ቃታ በመሳባችን የሃሳብ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ባለመቻላችን ምክንያት ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ የአገር ኢኮኖሚ እንዲደቅቅና በግሽበት ተፅእኖ ውስጥ እንዲይ ሆነናል። እነዚህ ሁለት ተቃራኒ መንገዶች ለቀጣይ ውሳኔያችን፣ ለአብሮነታችን እና ለትውልድ አስረክበን ለምናልፋት አገራችን ትልቅ ትምህርት የተውልን ክስተቶች ናቸው።
ዛሬ ላይ ያሳለፍናቸውን የለውጥና የነውጥ ጊዜያት የምንገመግምበት እና የተቀመጡ አማራጮችን በስክነት መርጠን መደላድል የምንፈጥርበት ነው። ኢትዮጵያ በፖለቲካ ልዩነት በተፈጠረ የሰሜኑ ጦርነት በቆየችባቸው ጊዜያት ከንብረት ውድመት፣ ከዜጎች ሞትና መፈናቀል ባሻገር አብሮነትንና አንድነትን የሚሸረሽር ፈተናዎች ገጥመዋት ነበር።
ይህ ግጭት አያሌ ጥፋቶችን ቢያደርስም በቶሎ መፍትሄ ለማበጀት ውሳኔ ላይ መድረሳችን ከዚህም የከፋ አደጋ ውስጥ እንዳንወድቅ ታድጎናል። ይሁን እንጂ ውሳኔያችን ለጊዜው ለማህበረሰቡ እረፍት የሰጠና ከባድ ግጭቶችን የገታ ቢሆንም፣ በዘላቂነት በውይይት መፈታት ያለባቸው አሁንም ድረስ መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉብን መዘንጋት የለብንም። እነዚህን ችግሮች በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ልንሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ አያሌ እድሎች ፈጥረዋል።
ለዘመናት የቆዩ ቁርሾዎችን ፈር ለማስያዝ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት እና በንግግር ብቻ ለመፍታት፣ የልማት፣ የወሰን ግጭት እና ሌሎችም አያሌ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ለማስቻል በቅርቡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ አይዘነጋም። ይህ ኮሚሽን “በፍፁም ተቀራርበን ማውራት አንችልም” በሚል ቁርሾ ፈጥረው ፅንፍ የያዙ ፖለቲከኞችን ወደ አንድ ጠረጴዛ ለማምጣት ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ ይገኛል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩት አካላት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በተፈጠሩ ልዩነቶች በውይይት ዘላቂ ዕልባት መስጠት የሚያስችሉ ህዝባዊ ምክክሮችን በማካሄድ ችግሮችን ለይቶ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ለማመላከት እንደሚሰራ በተለያየ ጊዜ ሲናገሩ አዳምጠናል።
ለዚህም አካታችና አሳታፊ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ትብብር፣ ሕጋዊነትና ተዓማኒነትን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ነግረውናል። በምክክር መድረኩ በተከታታይ የሚሳተፉ አካላትን የመምረጥ ስራም እያከናወኑ መሆኑን በተለያየ መገናኛ ብዙሃን አድርሰውናል።
በርግጥ በጦርነት እና ቃታ በመሳሳብ ለችግሮቻችን መፍትሄ እንደማናገኝ በተጨባጭ ተምረናል። በተቃራኒው ጥቂት የመወያያ አብሮ የመስራት በር በመከፈቱ ምክንያት “እንደ አይጥና ድመት” የሚተያዩ ሰዎች ጭምር አብረው ሲሰሩና ውጤት ሲያመጡ ተመልክተናል።
በመሆኑን ዛሬም ድረስ ለቆዩት ችግሮቻችን መፍትሄው ውይይት፣ መፍትሄው ልዩነትን አቻችሎ አብሮ ለመስራት ቁርጠኝነት ማሳየት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ከዚህ መነሻ አገራዊ ውይይቱን እና አመቻች አካላትን በፍፁም ፍቃደኝነትና ቅን ልቦና ልንደግፋቸውና በጋራ አብረን ልንሰራ ይገባል።
ምሁራን፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ጦር የሰበቁ አካላት ሁሉም በየፊናቸው የሚያነሱት የልዩነት ጥያቄዎች ሊኖራቸው ይችላል። የማያግባቡ “ሊያቀራርቡ አይችሉም” ተብለው የሚታሰቡ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ርእሰ ጉዳዮችና አጀንዳዎችም አይጠፉም። በዚህ ምክንያት ማንኛውም ፖለቲከኛ ምሁርም ይሁን የማህበረሰብ ክፍል ልዩነቶቹን ወደ ጠረጴዛው ይዞ ከመምጣት ሊያፈገፍግና የተለየ አማራጭ ሊፈልግ አይገባም።
ማእቀፍ ሉዓላዊነትን በማይጥስ አግባብ ሃሳቦቹን ይዞ ሊመካከርና በጋራ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባ መታመን አለበት። አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑም ለእቅዱ መሳካትም ሆነ ለኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ሲባል ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ለማካተትና ውክልና እንዲያገኙ ለማድረግ እየሄደበት ያለው መንገድ ተገቢውን እውቅና ሊሰጠውም ይገባል።
“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደሚባለው አገራዊ ብሂል መጪውን ትውልድ ዳግም በማይፈትኑ፣ የአገር ህልውናን እና ሉዓላዊነትን በሚያስጠብቁ መልኩ በጥልቅ ውይይትና መፍትሄ አመላካች ሳይንሳዊ መንገዶች ችግሮቻችንን መፍታት ይኖርብናል። ለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልዩነት ባላቸው አካላት መካከል እየተመለከትን የምንገኘው የሚበረታታ መቀራረብ፣ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ግንኙነት ሊበረታታና ሊቀጥል ይገባል።
አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ከምንከ ተለው ሳይንሳዊ መንገድ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚያጎሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይኖርብናል። ለአገር በቀል እውቀቶች ባህላዊ ሀብቶች እንዲሁም የልዩነትና ግጭት አፈታት ሥርዓቶችም ቦታ መስጠት አለብን። ይህንን በቅን ልቦና በፍፁም ቁርጠኝነት መተግበር ከቻልን ግጭትና ጦርነትን አቁመን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለመምጣት ፍቃደኛ እንደሆንነውና እራሳችንን በመልካም መንገድ እንዳሸነፍነው ሁሉ ዳግም በተመሳሳይ መልኩ በውይይት ከችግሮቻችን በላይ መሆናችንን በተጨባጭ ማስመስከር ይጠብቅብናል።
በተጨማሪም ለአገራዊ ችግሮቻችን በውይይት ለመፍታት የጀመርነው አዲስ መንገድ አስቀድሞ ህዝቡ ምን ይፈልጋል? የሚለውን ተረድቶ ባህልና ወጉን መሠረት ባደረገ መንገድ ምላሽ መፈለግን ያካተተ ሊሆን ይገባል ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለመነጋገር መቀራረባችን በራሱ ድል መሆኑን ተገንዝበን ለመጪው ትውልድ ከግጭት ነጻ የሆነች ሰላማዊ አገር ለመፍጠር የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ጥረት በሁለንተናዊ መልኩ መደገፍ ይጠበቅብናል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015