ግብርና ጤናዋም፣ ኑሮዋም እንደሆነ ታምናለች፡፡ በእርሱ ከህክምና ወጪ ሳይቀር ድናለች፡፡ በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎቿ ህመሟን አስታግሳለች፡፡ ልጆቿን ካለመመገብ ወደ መመገብ አሻግራለች፡፡ ጤናማ የሚሆኑበትን እድል ፈጥራም ለወግ ማእረግ እንድታበቃቸው ሆናለች፡፡ በግብርና ሥራዋ ሌሎችን ጤናማ እንዲሆኑ ማድረጓ ነው፡፡ በተለይም ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ሌት ተቀን መልፋቷ ያስደስታታል፡፡ እናም ግብርና ሕይወትም ገቢም ነው ትላለች የከተማ ገበሬዋ አረጋሽ ተመስገን፡፡
አገረጋሽ በዛ ቢባል ሁለት ሰዓት ብቻ ነው የምትተኛው፡፡ ሙሉ ጊዜዋን በግብርና ሥራ ላይ ታሳልፋለች፡፡ ጊዜው ደግሞ የትበረታታበትና በመንግሥትም ልዩ ትኩረት የተሰጠበት በመሆኑ ከከብት ርባታ አልፋ ዶሮ ማርባቱን ተያይዘዋለች፡፡ ንብ ማነብና አትክልትና ፍራፍሬ ማምረትም የተሰማራችበት ሙያ ነው፡፡ በዚህም ብዙዎች ብርቱዋ ሴት እያሉ ይጠሯታል፡፡ እኛም ይህቺን ብርቱ ሴት ብዙ የሚያስተምር የሕይወት ጉዞ አላትና ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
አባባ
አረጋሽ ተወልዳ ያደገችው በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ነው።እናቷ የቤት እመቤት አባቷ ደግሞ በግብርና ሙያቸው የታወቁ አርሶአደር ናቸው። ይህ ነገር ደግሞ እርሷን በሁለት በኩል እየተሳለ እንዲህ አድርጓታል።በእናት በኩል የቤት ውስጥ ሙያ መልመድ ሲሆን፤ በአባት በኩል ደግሞ ምርጥ አርሷደርነትን ነው።በዚህም እድገቷ በሁለት መልኩ ውጤታማ ነበር።ተወዳጅና ሁሉም የሚፈልጋት ልጅም ነበረች።በዚህም ገና ጉልበቷ ሳይጠና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለች ነበር ለባል የተሰጠችው። ይህ ደግሞ ለተደጋጋሚ ችግር አጋልጧታል። ቤተሰቧን ትታ ጭምር ለስደትና እንግልት ዳርጓታል።
የአረጋሽ ልጅነት ሲነሳ ሌላው የሚወሳው ነገር ብርቱ ሴት መሆኗ ሲሆን ከእናቷ ጋር የቤቱን ሥራ ከጨረሰች በኋላ ከአባቷ ጋር ደግሞ የግብርና ሥራው ላይ ትሰማራለች። ሁልጊዜ አለባበሷም ልክ እንደወንድ ቱታ ነበር። ምክንያቱም ለሥራ የሚመቻት እርሱ ነው ብላ ታምናለች። በዚህም የእህቷ ልጅ ‹‹አባባ›› ይላት እንደነበር አይረሳትም።ወንድሟም ቢሆን ከእርሷ የሚለይበት ነገር አልነበረም።ምክንያቱ ደግሞ ወንድ ስለምትመስለው ነው። እናም ቅጽል ስሟ አባባ ነበር።
በእርሻና በአረም ማንም የማይችላት ልጅ የነበረችው አረጋሽ፤ የትናንት መሰረቷ ለዛሬ ስኬት አብቅቷታል።ለግብርና ያላት ፍቅርም ከፍ እያለ የመጣው ትናንት በተሰራባት ነገር ነው።ጥቅሙንም ቢሆን በሚገባ ታውቀዋለች።እናም ግብርናን ‹‹እንኳን ተማርኩት›› ትላለች።
ቀን እስኪያልፍ
አረጋሽ የትውልድ መንደሯ እጅግ አድርጋ ትወደው ነበር። በቤተሰብ መታገዝ ያለበት፣ በቤተሰብ መቀጣትና እድሜን እያወቁ ማደግ የሞላበት ነውና በዚያ መኖር ለእርሷ ልዩ ደስታን ይፈጥርላታል። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ ያለ እድሜዋ ቢሆንም ለትዳር በቅተሻል በሚል በተደጋጋሚ ለጠየቀ ወንድ ሁሉ ይድሯት ነበር።ይህ የሚሆነው ደግሞ ከአንዱ ቤት ጠፍታ ስትመጠጣ ማመላለስ ስለሚደክማቸው ነው።እርሷም ብትሆን አንዱንም ተቀብላ አልተቀመጠችላቸውም።
ለስድስት ሰዎች እንደተዳረች የምታስታውሰው አረጋሽ፤ ለመጥፋቷ ዋነኛ ምክንያት ልጅነት ስላለ ከሌሎች ሰዎች ጋር መላመድ አለመቻሏ ነው። ከቤተሰብ ተለይቶ ለያውም ራቅ ብሎ መኖር እጅግ ይከብዳል። ምርጫም መቀመጫም የባል ቤተሰቦች ብቻ ናቸው። ይህንን መቀበሉ ደግሞ ለእርሷ ቀላል አልሆነላትም። ስለዚህም እነርሱም ሆኑ እርሷ የሰለቻትን ተግባር በተደጋጋሚ አድርገዋለች።ባስ ሲልባት ደግሞ የመጨረሻ ውሳኔ እንድትወስን ሆናለች። ይህም ቤተሰቧን ትቶ መጥፋትና የማያገኙዋት ቦታ መሄድ ።
በአስር ብር ደሞዝ ወደ አዲስ አበባ
የለመደችውንና የምትወደውን አካባቢ ትታ ወደማታውቀው ግን በዝና ወደሰማችው አዲስ አበባ ከተማ ለመሄድም አንድ አጋጣሚ አስወሰናት። ከመጨረሻውና ስድስተኛው የትዳር አጋሯ ጋር ጠፍታ በምትሄድበት ጊዜ ሰራተኛ የሚፈልግ አንድ ሰው አገኘች።ይህ ሰውም በወቅቱ አስር ብር ሊከፍላት ተስማማና የት እንደሚሄዱ ነግሯት ወሰዳት።ምንም የማታውቀውን ቦታ ለማየትም ቋምጣ ተነሳች። ቤተሰቧን እርግፍ አድርጋ ትታ መሸሸጊያዋን በዚህ ሰው ቤት ለማድረግ አምናው ተከተለችው።
ሥራ አድክሟት የማታውቀው አረጋሽ በወቅቱ የገባችው አዲስ አበባ አልነበረም። ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው ጫንጮ ከተማ ቢሆንም አልከፋትም። በገባችበት ቤትም ቤተሰባዊነት እየተሰማት ወራትን አሳለፈች። ቀጣሪዋ ከባለቤቱ ጋር ተጣልቶ የሚኖር ልጆቹን ብቻውን የሚያሳድግ በመሆኑ እናትም ሰራተኛም ሆና ቆየችው። ነገር ግን እያደር ባህሪው ተቀየረባት። መልካምነቷ አሸነፈውና የጠላችውን ትዳር አነሳባት።‹‹ የልጆቼ እናት ሁኝልኝ፤ በጋብቻ እንተሳሰር›› አላት። ይህን ጊዜ እጅጉን አዘነች። ደስታዋ ጨለመ። ቤተሰቧን ያስተዋት፣ አካባቢዋን ያስለቀቃት ነገር እዚህም ተከትሏት መጣ።እናም ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ገባት።
‹‹የጠሉት ይደርሳል ፣ የፈሩት ይወርሳል›› እንዲሉ አሁንም ከዚህ ቦታ መሰደድ እንዳለባት ወሰነች። ግን የት እንደምትሄድ አታውቅም።አዲስ አበባን አለማወቋም ያናደዳት የዚህን ጊዜ ነው።ግን ወደ አዲስ አበባ ከማምራት በስተቀር አማራጭ አልነበራትምና አደረገችው።አዲስ አበባ የሰማቻትና በአዕምሮዋ የሳለቻት አይነት አይደለችም።እንደገጠሩ ማህበረሰብ ቤት የእግዚአብሔር ነው አይባልባትም። ሰው በጎዳና ላይ ያድራል። ስለዚህም ከቤት ወጥታ ለማታውቀው አረጋሽ ሲኦል የገባች አይነት ስሜትን ፈጠረባት።ለቀናትም በመንገድ ላይ አደረች።በብዙ ተፈተነች።
ከፈተናዎቿ የከፋው ደግሞ ማረፊያ ማጣቷ ሲሆን፤ማንን አነጋግራ ሥራ ማግኘት እንደምትችልም አለማወቋ ሌላው ችግር ነበር። ቆንጆና ወጣት በመሆኗ ደግሞ ደላሎች ይከተሏት ጀመር። በዚህ አይነት ሁኔታ ላይ ሳለችም መልካም ከመሰላት ደላላ ጋር ተነጋግራ ግሮሰሪ ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጠረች።በእርግጥ ቀጣሪዋ ሥጋዋን ሸጣ ጭምር እንድታካፍላት የምትፈልግ ብትሆንም እርሷ ቁርጠኛ ነችና ያንን እንዳታስበው አድርጋት ተስማምታ ወደሥራ ገባች።
ቀጣሪዋ ቃሏን አጥፋ ማታ ወጥተሸ ካልሰራሽ ማለት ጀመረች።ከሦስት ሳምንት በላይ ግን በዚህ ቤት መቆየት አልቻለችም። ልትታገሳት ብትሞክርም ተደጋጋሚ ጥያቄዋ ግን በዚያ ለመቆየት አላስቻላትም።እናም ‹‹ ይብቃኝ ደሞዜን ስጪኝና ልውጣ›› አለቻት።ሴትዬዋ ግን ደሞዟን ብቻ ሳይሆን ልብሷን ጭምር ቀምታት አባረረቻት።በሆነው ነገር እጅግ አዘነች።በአንድ በኩል ደግሞ ተጽናናች።ምክንያቱም ይህ ቤት የማታውቀውን የአዲስ አበባ ክፍል እንድታውቅበት አድርጓታል።ከዚህ ቀጥሎም ማን ጋር ሄዳ ማነጋገርና መቀጠር እንዳለባት አሳውቋታል። ስለዚህ ዛሬ እንደዚህ ቀደሙ አትንገላታም። የፈለገችው ቦታ ተንቀሳቅሳ በፈለገችው ገንዘብ ትቀጠራለች።
መኖሪያ ቤት በሰራተኝነት መግባት የመጀመሪያ ምርጫዋ ያደረገችውም ለዚህ ነበር። የገባችበት ቤት እጅግ መልካም ሰው ያገኘችበት ነበር።ደመወዝ ግን የላትም።እርሷ የፈለገችው ማደሪያ ቦታና የምትበላው ነገር በመሆኑ ይህ ነገር በምትፈልገው ልክ ተሟልቶላታልና ደመወዙ አላሳሰባትም።ነገር ገን እየዋለች እያደረች ሰትሄድ መልካም ከሆነው አባወራ የሚደረግላት እንክብካቤ አክብሮት ባለቤቱን ሳያስደስታት ቀረ በዚህ ምክንያትም በረባ ባረባው ቁጣና ወቀሳ በዛ። አሁንም መልካሙን አባወራ አመስግና ወደሌላ የሕይወት አቅጣጫ ዞረች።
የአረጋሽ ቀጣዩ መኖሪያ በልጅነቷ የተዳረ ችለት የባለቤቷ እናት ቤት ሆነ። እንደ እናት የሚንከባከባት ሰው በማግኘቷ አጋጣሚውን እጅግ ወደደችው።የልጅነት ባሏ የነበረው ሰው ውትድርና ሄዶ በመሞቱ ብቻቸውን ናቸውና እርሷም ብትሆን እንደ ምትንከባከባቸው አምናለች። እርሳቸው ‹‹ከአንቺ ልጄ በረከት የሚሆን ፍሬ ባይኖረውም፤ የልጄ ማስረሻ ትሆኝኛለሽ›› ሲሏት እርሷ ደግሞ ‹‹ ትቼያቸው የመጣሁት ቤተሰቦቼ ምትክ ሁኑኝ›› በማለት ተደጋግፈው መኖሩን ተያያዙት።ነገሮች በብዙ መልኩ የተለወጡበት ጊዜም ሆነ።
ሆድ ሳይጠና …
ባለቤቷና እርሷ ከዚያ ቤት ሲወጡ ነብሰጡር ነበረች።ሆኖም አብረው የቀጠሉበት ሁኔታ አልነበረምና የእርግዝናዋንም ሆነ የአራስነቷን ጊዜ ያሳለፈችው ብቸዋን ነው።በብዙ ውጣውረድና ትግል ውስጥም ቆይታለች።ለአብነት አዲስ ለምትመጣው ልጅ ብዙ መልፋትና የተሻለ ገቢ ማግኘት አለባትና ሌት ተቀን ትሰራለች።ራሷን ለማረስም የሚያስፈልግ ነገር አለ።እናም ዳግም ወደ ሥራ ሊያስገባት የሚያስችል ገንዘብ ማጠራቀም አለባት።በዚህም መጀመሪያ ያላትን ገንዘብ ሰብሰብ በማድረግ ቤት ተከራየች።ስፌት እየሰፋች ፤ ጥጥ እየፈተለች ልቃቂቱን መሸጡን ተያያዘችው።ሆዷ እስኪገፋ ድረስም በተመላላሽነት ከስድስት በላይ ቤቶችን ይዛ እንጀራ ትጋግራለች፤ ልብስ ታጥባለች፤ ልጆችም ትንከባከባለች። ከፍ ሲል ደግሞ በራሷ እንጀራ እየጋገረች ትሸጣለች ።ይህንን ሥራ ከወለደች በኋላም ቀጥላበታለች።እንደውም ለ16 ዓመት ያህል በሥራው ላይ ቆይታለች።
አረጋሽ ይህንን ሁሉ ብታደርግም ስትወልድ ግን ነገሮች ተመሰቃቀሉ።አትረፊ ያላት ነፍስ ቤቱን ልቀቂ ተባለች።የሚያርሳት በሌለበትና ራሷን በራሷ እያኖረች ስትታገል ሌላ ችግር መጣባት።የት እንደምትገባም ግራ ገባት።እናም አራስ ልጇን ይዛ ጎዳና ወጣች።ግን እድል ከእርሷ ጋር ነበረችና የመሰረተ ትምህርት ተምረው የሚወጡ ሰዎች አገኟት።በወቅቱ ባለሥልጣን የነበሩ ሰውም ችግሯን ጠየቋት።አስረዳቻቸውና መፍትሄ ተፈለገላትም።ጊዜያዊ መፍትሄው የራስ እምሩ ጥበቃ ቤትን መጠቀም ነበር።በወቅቱ እራሷ ነበረች ያደረገችው።ሰብራ ከገባች በኋላ ግን በባለሥልጣኑ ትግል ስምንት ዓመት እንድትኖርበት ሆናለች።ከዚያ ስትወጣ ደግሞ አሁንም እድል ቀናትና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቤት ካሰራላቸው የተወሰኑ ሰዎች መካከል አንዷ ሆነች።
በር የሌለው ቤት
እርሷና ገና የተወለደችውን ልጇን ጎዳና ላይ ይዛ መኖር እጅግ አሰቃቂ ነበር።ስለዚህም አማራጯን አንድ ነገር አደረገች። የራስ እምሩ የዘበኛ ቤትን ሰብራ መግባት።ሰው ስላልነበረበት ለጊዜው ማንም ምንም አላላትም።እየቆየ ሲሄድ ግን የደርግ መንግሥት ኢህአዴግን እየፈራ የመጣበት ወቅት ነበርና የአካባቢው ነዋሪ በዚያ መኖሯን ተቃረነ።ቦታውን እንድትለቅ በተደጋጋሚ በቀበሌው ጭምር ተጠየቀች።ገ ንዘብ አሰባስበው ወደ ቤተሰቧ ሊልኳት ፈለጉ። እርሷ ግን ከዚያ የወጣችበትን ምክንያት በሚገባ ታውቀዋለችና ዳግም ወደዚያ ጭንቀት ውስጥ መግባት አትችልም።እናም ያልሞቱትን እናትና አባቷን ገላ ቤተሰብ እንደሌላት ተናገረች። ይህን ጊዜ ሰዎቹ ታገሷት፤ የመንግሥት አካላትም ተቀበሏት። በሸራ በር ሰርታ መኖሩን ተያያዘችው።ከልጇ ጋር በዚያ ቤት ስምንት ዓመታትን ኖረች።
ይህ ስምንት ዓመት ግን በእጥፍ ችግር የሞላ ነበር።በር በሌለው ቤት ሴት ልጇን ማሳደግ ከባድ ሆኖባታል። ቀን ላይ ሥራ ከጨረሰች ለተወሰነ ደቂቃ ራሷን ካሳረፈች እንጂ ለልጇም ሆነ ለራሷ ስትል ብዙ ጊዜ እንቅልፍ በዓይኗ
አይዞርም።አካባቢው በ12 ጥበቃ በፈረቃ ይጠበቅ ነበርና አንዱ ዘሎ ቢገባስ የሁልጊዜ ስጋቷ ነበር። በተጨማሪም በር ስለሌለው እብድና ሌባም ዘሎ መግባቱ እንደማይቀር ታስባለች። እናም አዳሯ ዘነዘና ይዛ ይነጋል። የሌሊቱ ጊዜ በመጠቀም እንጀራና ዳቦ ትጋግራለች።መጀመሪያ ተሸክማ ጉልት አስቀምጣ ትሸጥ ነበር።እየታወቀች ስትመጣ ደግሞ ፈላጊዎች ቤቷ ድረስ እየመጡ ይገዟት ጀመር።
‹‹ችግር ችግር ብቻ እንደሆነ አምነን ከተቀበልን መቼም አንለውጠውም።በዚያ ከመኖር በስተቀር አማራጭ እንደሌለን እናስባለን።ይህ ደግሞ ሕይወታችንን ከድጡ ወደማጡ ያደርገዋል›› የምትለው ባለታሪካችን፤ ለእርሷ ችግር ድህነቷን ማባረሪያ መንገድ ያየችበት ነው።መሥራትን የለመደችበትና አስተዋይነቷን ያበዛችበት ነው።በዓላማ ነው የተፈጠርኩት ብላ እንድታስብ አድርጓታልም።
ይህ ቤት ከችግር መውጫዋ መንገድ ሆነላት። ትዳርን በፍቅር እንድትቀበለው ያደረጋትም ነው።ፍራቻን ሽሽት ከአንድ የአካባቢዋ ነዋሪ ጋር ተዋወቀች።በራስ እምሩ ቤት የኖረችበትን ስቃይ እንዲያከትም አግዟታልም።ምክንያቱም የዛሬውን የልጆቿን አባት አግኝታበታለች። በመተጋገዝ ችግራቸውን አብረው እንዲወጡት እድል ሰጥቷታል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ
ልጄ አደገችልኝ ብላ ሳትጨርስ ልክ አራት ዓመቷ ላይ ሌላ መከራ አገኛት።ነገሩ የተከሰተው በድርቁ ወቅት በ1977 ዓ.ም ነበር።እርሷ ግን እንጀራ እየጋገረች ለራሷ ተርፏት ጭምር ለሌሎች ትሸጥ የነበረ ቢሆንም መብላት ብቻውን ከህመም አያድንምና አብዝታ በመስራቷ እረፍት ባለማድረጓ ብሽሽቷ ላይ እንደ እባጭ ሆኖ በመውጣት ቢያማትም እውቀትና ግንዛቤው ስላልነበራት ወደሀኪም ቤት አልሄደችም።እያደር ግን ህመሙ አላንቀሳቅስ አላት።ወጥታ ገቢ ማግኘት እንኳን እንዳትችል አደረጋት።የዚህ ጊዜ ቁርጥ ሆነና ወደ ሀኪም ዘንድ ሄደች።ቁስሉ ወደ ካንሰርነት ተቀይሮ ነበርና የካንሰር ህመምተኛ እንደሆነች ተነገራት።
በወቅቱ በቀላሉ ለማመን የተቸገረች ቢሆንም ስር የሰደደ በመሆኑ አልጋ እንድትይዝ አደረጋት፤ ስራ አቁማም ትናንት ትታቸው የመጣችውን ቤተሰቦቿን ናፈቀች።ወደ እነርሱ ጋር ለመሄድም ተገደደች።እነሱም ያድናታል ብለው ያሰቡትን ሁሉ አደረጉላት።ሆኖም አንዱም ሊሳካ አልቻለም።ስለዚህም ሌላ አማራጭ መውሰድ እንዳለባት ገባት ።ወደ አዲስ አበባ ተመልሳም በቤተእምነት ደረጃ እንዲጸለይላት አደረገች አጋጣሚው ጥሩ ሆኖ ከህመሟ ተፈወሰች።
ከአንዱ ተላቀቅሁ ብላ ሳትጨርስ ሌላኛው ፈተና ይደረብባታል።አንዱ የግብርና ሥራን ከጀመረች በኋላ የገጠማት ትሰራበት በነበረው አካባቢ ከጎረቤቶች ጋር በነበረው አለመግባባት ለከብቶች ማደሪያ ያሰራችው በረት ፈረሰ በዚህ ምክንያት ደግሞ ላም ሞተችባት ። ይህም ‹‹የሞተ ላም ስጋ ስትሸጥ በአራዳ ክፍለከተማ 04 05 አግኝተን በቁጥጥር ስር አውለናል›› የሚል ነበር።ማንበብና መጻፍ ባትችልም ወዳጆቿ ብዙ ነበሩና የሰሙ ተሰብስበው መጡና ነገሩን አስረዷት።በዚህም እጅግ አዘነችና ጎረቤቶቿ በነገሯት መሰረት ነገሩ ውሸት መሆኑን ለማስረዳት ወደ ዜና አገልግሎት አመራች።ዜናውን በቃሏ ሸምድዳው ነበርና የተሳሳተ ዜና እንዳወጡባት አስረዳች።ዜናውንም እንዲሰረዝ አደረገች።
አረጋሽ ለፈተና የተፈጠረች ይመስል ነብሰጡር ሆና በር በሌለው ቤት ኖራለች።ብዙ ስቃይን አሳልፋለች።ከዚያ አረፍኩ ስትል ደግሞ በጥሩ ሁኔታ ተገንብቶ የተሰጣት ቤት በመፍረሱ
የቆሻሻ መከመሪያ የነበረ ቦታ ላይ እንድታርፍ ሆነች። ጎዳናውን አጽድታ መኖር፣ ልጆቿን ደስተኛ ማድረግ ይጠበቅባት ነበርና በብዙ ደክማለች።ቦታው በቀላሉ የሚጸዳ ባለመሆኑም ሸራ ወጥራ ወራትን አሳልፋለች።ልጆቿም ቢሆኑ በየጊዜው በምግብ እጥረት ይታመሙባት ነበር።
ቤትን በራስ ጉልበት
ከ11 ዓመት ቆይታ በኋላ ጤና ጥበቃ የሰጣቸው ቤት በልማት ፈረሰ።በቀጥታ ዛሬ ወዳለችበት አካባቢም ሄደች።ባዶ መሬት የተሰጣት ሲሆን፤ ጫካ ሁሉ መንጥራ ነው በራሷ አቅም ቤቷን የሰራችው።ጫካውን ስትመነጥር በጥበብ ነበር።ምክንያቱም አጸዶቹ ለቤቱ ግርግዳ የሚሆንም አለባቸው።እናም ያንን አስተካክላ ጠርባ ቋሚና ወራጁን አዋቀረች።በኋላም ጭቃ አቡኩልኝ ለጥፉልኝና ለስኑልኝ ሳትል ረሷ አድርጋ ጨረሰች።የቆርቆሮ ማገርም ቢሆን መትታ ዝግጁ ማድረግ ቻለች።የቤቷን ውስጥ ሊሾም ራሷ አሳመረችው።አረጋሽ አሁንም ቢሆን ለከብት ማደሪያና መሰል ቤቶችን በግቢዋ ውስጥ መስራት ብትፈልግ ማንንም አትጠራም።
የስሙኒ ውለታ
ነብሰጡር እያለች አንድም ቀን እረፍት አልነበራትም።ምንም በሆዷ እንዳልተሸከመ ሰው ተሯሩጣ ትሰራለች።አንዱ ስራዋ ደግሞ መርካቶ ሄዶ የወዳደቁ ድንችና ሽንኩርት እንዲሁም ቲማቲም ለቃቅመው ከሚሸጡት ላይ ገዝቶ ዳግም አትርፋ መሸጥ ነበር።ለአምስት ሳንቲም ትርፍ ሁሉ ደፋ ቀና ትላለች።ብዙ ጊዜ ስሙኒ ይዛ ነው ገበያው ላይ የምትገኘው።ሸጣ ወደቤቷ ስትገባ ግን ሃምሳ ሳንቲም ትሆናለች።ያተረፈቻትን 25 ሳንቲም ለአንዳንድ ነገር መገዛዢያ ታደርገዋለች።ይህ አይነት ንግዷ በዛ ከተባለ 75 ሳንቲም ድረስ ከፍ ይላል።‹‹ይህንን ያህል ሸክም በደረሰ እርግዝናዬ ላይ ተሸክሜ እየሄድኩ ለምን ይህችን ብቻ አተረፍኩ›› ብላ አታውቅም።በምታገኘው ትርፍ ሁልጊዜ ደስተኛ ናት።ወራት እየተቆጠሩ ሲሄዱ ደግሞ አመስጋኝነቷ ብሩን ጨመረው፤ብዙ ከሰራች ሻይና ዳቦ በልታና ጠጥታ ሁለት ብርና ሦስት ብር ወደቤቷ ይዛ ትገባለች።
ከመርካቶ ያመጣችውን ከጨረሰች በኋላም ቢሆን አረጋሽ ለራሷ እፈፍት አትሰጥም።ቆሎ በየጠጅ ቤቱ እየተዘዋወረች ለመሸጥ ትነሳለች።እነዚህና መሰል ሥራዎቿ የምታርፍበትንና ተረጋግታ የምትሸጥበትን እድል አመላክተዋታል።ይህም ቡና በኪሎ፣ ዘይት በሊትር ገዝታ ቡናውን በችርቻሮ መልክ በመለኪያ ዘይቱን ደግሞ በቡትሌ ትሸጣለች።ከሰል እያስመጣች መድባ በትንሹ ለሚገዙት ታቀርባለች።ስለዚህም ‹‹እጅ ካልቦዘነ ስሙኒም ባለውለታ ነች›› ብላ ታምናለች።‹‹ትልቅ ነገር መመኘት መልካም ቢሆንም ከፍተኛ ገንዘብ ሳገኝ ይህንን እሰራለሁ ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ግን ለድህነት ራስን አሳልፎ መስጠት ነው›› ትላለች።ትልቅ ገንዘብ ሳይሆን ትልቅ አዕምሮና የመስራት ፍላጎት እንደሚያስፈልግ ማመን ይገባል ባይ ናት።
“እኔ ስሙኒ ባለውለታዬ እንደሆነች የማምነው ያለምክንያት አይደለም። የለውጥ መሰረትን ጥላልኛለች። መስራት ከተቻለ ገንዘብ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚመጣ አሳይታኛለች። ስለዚህም ትንሹን መናቅ ሳይሆን ማክበር ያስፈልጋል” ስትልም ትመክራለች።
ያላትን ማካፈል
አረጋሽ ያላትን ማካፈል የምትወድ፣ ቤቷም ሰብስባ የምታሳድር ሰው ወዳድ ሴት ነች። ማንም ሰው ችግር ይፈጥርብኛ ብላ አታስብም።ቤት እንኳን ሳይኖራት የተቸገረ ካለ በተከራየችው ቤት ሳይቀር ሰዎችን መሰብሰብ ያስደስታታል። ዛሬም ቢሆን ይህ ባህርይዋ አብሯት ነው።በዚህም ‹‹ አታጣ ማርያም›› የሚል ስም አውጥተውላታል።ተግባቢነቷንና ተወዳጅነቷን በእጥፍ ጨምሮላታል። ብዙዎች እንዳይረሷትም ሆናለች።
አረጋሽ ዛሬ
አረጋሽ ከሌሎች ሥራዎቿ ተላቃ ግብርናውን የጀመረችው ሲሲሰኤፍ የሚባል ግብረሰናይ ድርጅት በፈጠረላት የሥራ እድልና ገንዘብ አጠራቅማ በገዛቻት አንድ ላም ነበር።ጎረቤቶቿ በሚደፉት ውሃ ሳይቀር ትጠቀማለች።የእርሷም ፍሳሽ ቢሆን የተከለችውን አትክልት ያጠጣል እንጂ ግቢዋ ጥሶ የትም አይሄድም። ቆሻሻውንም አጠራቅማ ማዳበሪያ በመስራት ወደ ግልጋሎት ታስገባዋለች።በዚህም አሁን ጥሩ አርሶ አደር ሆናለች።በሌማት ቱሩፋት የተካተቱትን ሁሉ አሟልታ እየሰራች ትገኛለች። በርከት ያሉ ከብቶች አሏት።በዚህም የወተት ገቢ ታገኛለች።ዶሮ እርባታና ንብ ማነብም እንዲሁ ተግባራቶቿ ናቸው።በዚህም የምታገኘውን ገቢ ከፍ ታደርጋለች።ጓሮዋን በአትክልትና ፍራፍሬ ሞልታዋለችና ከራሷ አልፋ ለሌሎች ተርፋለች።
ይህና መሰል ጥንካሬዎቿ ደግሞ ለሁለተት ዓመታት ያህል ስራዋን ብታቆምም አሁንም ብዙዎች እንዳይረሷት የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።አንዱ ትናንት ይገዟት የነበሩ ሰዎች ዛሬም ከእጇ ፍሬ ለመቋደስ ቤቷ ድረስ ይመጣሉ።
አረጋሽ ብርቱ ሰራተኛ በመሆኗ ከተለያዩ አካላት ሽልማትን ተቀብላለች።ለአብነት በከተማ ግብርና ብቻ በዓለም ላይ ካሉ የተለያዩ አደረጃጀቶች ሽልማት ተበርክቶላታል።በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም እንዲሁ በተደጋጋሚ ተሸልማለች።በግብርናው ዘርፍ አምባሳደር ነሽ የሚል የምስክር ወረቀትና ዋንጫም ተሰጥቷታል።
መልዕክት
ሴቶች አገርን ማዳንም ሆነ መግደል ይችላሉ። ምክንያቱም ወላጆች ናቸው። ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ልጆች ማሳደግ፣ መንከባ ከብና በሥነምግባር ማሳደግ የሚችሉ። ስለዚህም ለአገራቸው ባለውለታ መሆን ከፈለጉ ለሁሉም ሥራቸው ፍቅር መስጠት አለባቸው። በተለይም እንደእኔ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩትና አገልግሎት የሚሰጡ አካላት አንድ ነገር እንዲያደርጉ እመክራለሁ። አትክልትና ፍራፍሬውን፣ እንቁላልና ወተቱን ሲያቀርቡ በንጽህና መሆን አለበት። ሰው እንዲድንበት፣ ጤናማ ሆኖ እንዲኖርበት ማድረግ መቻል ይኖርባቸዋል። ከሁሉም በላይ ወተት ላይ ምንም ነገር ባይጨምሩ መልካም ነው። ትርፍን በዚህ መልኩ ለማግኘት ማሰብ ነውር ስለሆነ። እናም ትርፋቸውን ለነብሳቸው አድርገው ጤናማ ትውልድ ላይ መስራት አለባቸው ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015