(የመጀመሪያ ክፍል)
ሽሽት ላይ ነኝ ። በሴራፖለቲካ ፣ በበሬ ወለደና በግነት ያበደ ሟርት ፣ መርዶንና መባተትን የማምለጥ ሽሽት ። የገባንበትና እያለፍነው ያለው ወጀብ ፣ ማዕበልና ቀውስ ሳያንስ ፤ ቀውስን ፣ ሞትን፣ ግዳይን፣ መፈናቀልን ፣ ኀዘንንና መከራን እንደ ምርጥ ዘር ከሚያባዛው ዩቲውበር ፣ ፌስቡክኛ ፣ ቴሌግራመኛ ቲዊተረኛ ፣ ቲክቶከኛ ፣ ቴሌቪዥንኛና “ጋዜጠኛ” ሽሽት ላይ ነኝ። አዎ ! ከመርዶ ፣ ከለቅሶ፣ ከዋይታ ፣ ከጭንቀት፣ ከድብርት ፣ ከመብሰክሰክና ከመብሰልሰል ውጭ መፍትሔና ጥሩ ዜና ጠብ ከማይለው ማህበራዊ ሚዲያ ኃይለኛ ሽሽት ላይ ነኝ። ሽሽቱ አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ያካትታል።
ከቴሌቪዥን ቻናል ስሸሽ ፣ ስዘልና ስቅበዘበዝ ነው ከ”ebs ውሎ” ጋር ፊት ለፊት የተገጣጠምሁት። ጋዜጠኛዋ ውሎ የምታደርገው እናቱ “ሰው መሆኔ “አይቀርም ብላ የህልሟን ዘር በዘራችበትና ሰውመሆን ስትል ስም ባወጣችለት “ሰውመሆን” ይስማው ጋር ነው ። አዎ ወላጅ እናቱ ልጇ ለወግ ለማዕረግ በቅቶ፤ እሷም አምስት የልጅ ልጅ አይታ በሰውመሆን ሰው ሆናለች ። ስምን መልዓክ ያወጣል አይደል ብሂሉስ። “አንድ ቀን ሰው እሆናለሁ።” ማለት ሌላ አይደለም ህልሜ እውን ሆኖ አያለሁ ነው ።
ችግሩ ፣ መከራውና ፈተናው አልፎልኝ አያለሁ ። ያሰብሁት ሰመሮልኝና ተሳክቶልኝ ሰው ከደረሰበት እደርሳለሁ ። እሱም እንደ ስሙም እንደናቱም ሰውሆኗል ። አንድ ቀን ሰውመሆኔ አይቀርም ብሎ እንዳለመውና ርዕይ እንዳደረገው ፤ ሰውመሆን ይስማው ሰው ሆኗል ። የልጅነት ሕልሙን በመኖር ሰውመሆን ሰው ሁኗል ። በልጅነቱ የተቆራኘውን የፊልም ፍቅር ፤ አንድ ጊዜ ደራሲ ፣ ሌላ ጊዜ ፕሮዲውሰር ወዲህ ዳይሬክተር ወዲያ ሲኒማቶግራፈር በመሆን እንደ ዝሀ ዘጊ እየተመላለሰበት ሰውመሆን ሰው ሆኗል ። በ16 ፊልሞችና ከዚህ በማይተናነሱ የሙዚቃ ክሊፖች ተንሸራሽሯል።
ሰው መሆንን የስኬት ፣ የስምረትና የውጤት መገለጫ ሲደረግ የተዋጣለትና የተሳካለት ነገር ሊገለጽበት ይችላል ። አምባሳደር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን የገለማውንና የጨረተውን የፊውዳል ሥርዓት በተዋበ ቋንቋ ፣ በማይረሱና ህያው በሆኑ ገጸ ባህሪያት ፣ በተዋጣለት ትልም ፣ ሴራ አወቃቀር ፣ ግጭት ፣ ጡዘት ፣ ልቀትና አተራረክ የህያው ስትንፋስ በአፍንጫው እፍ ብለው ሕይወት ዘሩበት ። በሰውመሆንኛ አነጋገር ያን የበሰበሰን ሥርዓት ሰው አደረጉት ። ዘመንና ትውልድን አሻገሩት ።
ዘመንና ትውልድ ያረጃል። ያልፋል እንጂ “ፍቅር እስከ መቃብር” ዛሬም ብላቴና ፣ ዛሬም ወጣት፣ ዛሬም ህያው ነው ። ገና የሚመጣውና የሚሄደው ትውልድ ይቀባበለዋል ። በፈንታው ወጋየሁ ንጋቱ ደግሞ በወርቃማ ድምጹ ፤ ትንግርተኛ ፣ ምትሀተኛ፣ ተአምረኛና አስማተኛ በሆነ አተራረኩ “ፍቅር እስከ መቃብር”ዳግም ወለደው። ሰው አደረገው ። አድማስ ገመገሙን አሻግሮ በየህይወታችን በየቀያችን ናኘው ። አደረሰው ።
አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም ቴዲ አፍሮ ደግሞ በ”ማር እስከ ጧፍ”ወይም “ፍቅር እስከ መቃብር”በሚል ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃውና በተዋጣለት የዘፈን ግጥም ፣ ጀሮ ገብ በሆነው ቅንብሩና ዜማው በጣት በሚቆጠሩ ደቂቃዎች ፤ 552 ገጽ ያለውን ረጅም ልብ ወለድ በሙዚቃ እንደገና አስነበበን። ከአእምሮ ጓዳችን ቀስቀሶ በእዝነ ህሊናችን ህያው አደረገው ። ሰውአደረገው ። አቧራውን አራግፈን እንደ አዲስ በጉጉት እንድናነበው አደረገን ። የሙዚቃ ክሊፑን ተከትሎ አዲሱ ትውልድም የፍቅር እስከ መቃብር ያለህ አለ ። በተደጋጋሚ ታተመ ። እንደ ከረሚላ ተቸበቸበ ።
ዘመንን ሽሮ ፣ ርቀትን አጥፍቶ ተራርቀው የነበሩ ትውልዶችን ድልድይ ሆኖ አገለገለ ። ለተጨማሪ ህትመቶች ምክንያት ሆነ ። ከዚህ ድንገቴ ፈንጠዝያ አንጎቨር በቅጡ ሳንወጣ ፤ “ማር እስከ ጧፍ” ወይም “ፍቅር እስከ መቃብር” በክሊፕ መጣና ሁላችንንም ያለ ልዩነት ጉድ አስባለን ። 10 ደቂቃ ባልሞላ የሙዚቃ ክሊፕ “ፍቅር እስከ መቃብር” ግዘፍ ነስቶና ስጋ ለብሶ ተገለጠ ። ወጋየሁ ንጋቱ አንድ ጊዜ ሕይወት ዘራበት ። ቴዲ አፍሮ ግን በዘፈን ግጥሙ በየአእምሮ ጓዳችን አመላለሰው ፣ በሙዚቃና በዜማ አስውቦ አይረሴ አደረገው ። በክሊፑ ከምናባዊነት አውጥቶ በእያንዳንዳችን አእምሮ ሐውልት አቆመለት። ደጋግመው ቢያነቡት የማይጠገበውን ረጅም ልቦለድ፤ ደጋግመው ቢመለከቱት የማይጠገብ ክሊፕ አደረገው። ፍቅር እስከ መቃብርን ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ፈጠረው ። ሰው አደረገው ።
ለምን ግን እንደሌሎች ታላላቅ ድርሰቶች ወይም ማስተርፒሶች ወደ ፊልም አልተቀየረም የሚለውን የትውልዶች ጥያቄና ቁጭት እንደ አዲስ አጫረው። በክሊፑ እንደሚቻል አስረግጦልን አደፋፈረን ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቴዲ አፍሮ ካጀገናቸውና ካደፋፈራቸው ተቋማት አንዱ ነው ማለት ይቻላል ። በድፍረትና በልበ ሙሉነት “ፍቅር እስከ መቃብር”ን በተከታታይ ፊልምነት ለመስራት ወኔ እንዲሰንቅ አድርጎታል ። እውነት ለመናገር የኢቲቪ የወቅቱን አመራር ለዚህ ቆራጥና ደፋር ውሳኔው አለማድነቅ ንፉግነት ነው ።
ከመቀመጫዬ ተነስቼ ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌያለሁ ። ETV/EBC “ፍቅር እስከ መቃብር”ን ሙሉሰው ሊያደርገው ውል ያሰረው ፤ ከዘመን አይሽሬና አይረሴ “ማር እስከ ጧፍ”ወይም “ፍቅር እስከ መቃብር”ክሊፕ ጀርባ የማይተካ ሚና ከተጫወቱ እንቁ ባለሙያዎች አንዱ በሆነውና በሲኒማቶግራፈርነት ከተሳተፈው ዳይሬክተርና ሲኒማቶግራፈር ሰውመሆን ይስማው ጋር መሆኑ “ፍቅር እስከ መቃብር” በአስተማማኝ ሰው እጅ ላይ እንዳረፈ እንዲሰማኝ አድርጓል ።
ለምን ብትሉ በአምስት ወር ውስጥ በዩቲውብ ወደ 8,000,000/ስምንት ሚሊዮን/የሚጠጋ እይታ ያገኘው የአስቻለው ፈጠነ/አርዲ/ “እናትዋ ጎንደር” እንዲሁም ከአንድ ወር በፊት በዩቲውብ ተለቆ ወደ 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/እይታ ያገኘው የዚሁ ሀገረሰብኛና ቱባ አቀንቃኝ አርዲ ስራ የሆነውን “ካሲናው ጎጃም”ን በሲኒማቶግራፈርነትና በዳይሬክተርነት ያዘጋጀው ሰውመሆን ስለሆነ “ፍቅር እስከ መቃብር” ምንም ከክሊፕ በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የራቀ ፤ ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ማስተፒስ እና የአገር ቅርስ ስለሆነ የፊልም ስራው ሕዝብ በጉጉት ብዙ የሚጠብቅበት ስለሆነ ኃላፊነቱ ከባድ ነው ። በነገራችን ላይ እነዚህ ክሊፖች ጎጃምና ጎንደር ማዶ ለማዶ ነው የሚለውን የአበው ይትበሀል የሻረ ሆኖ ይሰማኛል ። በ”እናትዋ ጎንደር” እና በ”በካሲናው ጎጃም” ጎጃምና ጎንደር ማዶ ለማዶ መሆናቸው ቀርቶ ቤተኛ ሆነው ተመልክተናል ።
ወደ “ፍቅር እስከ መቃብር”ፊልም የመሆን ነገር ስንመለስ ፤ ሰውመሆንና ለዚሁ ሥራ የሚያዋቅረው ቡድን ይህን ወርቃማ እድል ላለማባከንና ለማሳካት ብርቱ ጥንቃቄ ይጠበቅበታል ። እንደ ኖሊውድ ፣ ቦሊውድና ሆሊውድ ባሉ ኩባንያዎች እንደ “ፍቅር እስከ መቃብር” ያሉ ክላሲካል ልቦለዶች እንዴት ፊልምነት እንደተቀየሩ ልምድ መቀመር ፤ ዓለምአቀፍ ባለሙያዎችን ማሰተፍ ይጠበቅበታል። ታላቁን የፊልም ሰው ኃይሌ ገሪማን ልብ ይሏል ። የሰው ሰራሽ አስተውሎትንም ወይም AI በብቃት መጠቀም ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን አለበት። ፊልሙን ከEBC አድማስ ባሻገር ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ ፤ እንደነ ኖሊውድ የኢትዮውድ መሰረት የሚጣልበት ፣
የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪም ወሳኝ መታ ጠፊያ critical juncture ፤ የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባትና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት ከሁሉም በላይ የማያዳግም ዘመን ፣ ትውልድ ፣ የቆዳ ቀለም ፣ ድንበር፣ ዘር ፣ ሃይማኖት ፣ ወዘተረፈ የተሻገረ ስራ ለመስራት አሁን ከተያዘለት ወጭ በላይ ከፍተኛ ወጭ ይጠይቃልና እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮቴሌኮም ያሉ የአገር ምልክቶች ድጋፍ ያደርጋሉ ብዬ እጠብቃለሁ ። ለቀረጻና ለስርጭት መጣደፍ አያሻም ። ሰከን ማለት ያሻል ።
እንደ “ፍቅር እስከ መቃብር”ያለ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ወይም ማስተርፒስ ሥራ ወደ ፊልም ሲቀየር ውስብስብ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ ። ለፊልሙ እንዲመች የመጽሐፉን ታሪክ የመቀየር ፣ ታሪኩን ለፊልም እንዲመች ሲባል ማቅለል ወይም ሲምፕሊፋይ ማድረግ ፣ ድርጊት ወይም አክሽን ላይ የማተኮር አባዜ ፣ ገጸ ባህሪያትን መቀየር ፣ ለፊልሙ መነሻ የሆነውን ድርሰት ችላ የማለት ፣ ታሪኩን ማፍጠንና አጨራረሱን መቀየር ከተግዳሮቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ከሁሉም በላይ ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን “ፍቅር እስከ መቃብር”ወደ ፊልም ለመቀየር ሲታሰብ ድርሰቱን በጥልቅ መረዳት እና ለምን የተዋጣለት ዘመን ተሻጋሪና ተወዳጅ ሥራ እንደሆነ አላባውያንን ቁጭ ብሎ በጥሞና በቅጡ መገንዘብ ያሻል። ስራውን ዘመን ተሻጋሪ ላደረጉት ጭብጥ ፣ ገጸ ባህሪያትና ትልም መታመን ግድ ይላል ። ወደ ሲኒማቶግራፈርና ዳይሬክተር ሰውመሆን ይስማው ስመለስ በአንድ ወቅት የዶቸ ቬለዎች ተስፋለም ወልደየስና ሸዋዬ ለገሠ ወዳጠናከሩት ዘገባ እንመለስ።
የተዋጣለት ሲኒማቶግራፈርና ዳይሬክተር በአዳጊው የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ አብዛኛውን ስራ የሚያከናውኑት ወጣቶች ናቸው ፡፡ በዘርፉ ካለው የሰው ኃይል እና የልምድ እጥረት የተነሳም በርካታ ዘርፎችን ደራርበው ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹ በሚሰሯቸው ፊልሞች እየተማሩ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት ላይ ይገኛሉ ፡፡ ሰውመሆን ይስማው አንዱ ነው ፡፡ ወጣቱ የፊልም ባለሙያ ሰውመሆን ይስማው በአስራ ስድስት የኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ አሻራውን ያሳረፈ ነው ፡፡
የዘመን ተጋሪው ወጣቱ የፊልም ዳይሬክተር ዳዊት ተስፋዬ “ስለሰውመሆን ሲወራ” መረሳት የሌለበትን ይጠቁማል ፡፡ ሰውመሆን ሲኒማቶግራፈርም ፣ ዳይሬክተርም ፣ ስክሪን ፕሌይ ጸሀፊም ስለሆነ ስለሰውመሆን ስናወራ ስለየትኛው እንደሆነ ማወቅ ወሳኝ ነው ብዬ አስባለሁ ፡፡ የራሱ ቀለም ያለው፣ የሰራውን ሥራ አይተህ የሰውመሆን ሥራ ይመስላሉ የሚባሉ ሥራዎቹ ብዙ ናቸው ፡፡ በሰኒማቶግራፊም፣ በዳይሬክቲንግም ያ ነገር አለው ብዬ አስባለሁ” ይላል ዳዊት ፡፡
የሥነ መቼት እና የሜካፕ ባለሙያው ተስፋዬ ወንድማገኝ የሰውመሆን የቅርብ ጓደኛ ነው፡፡ የሰውመሆን የቅርብ ሰዎች እንደሚጠሩት ጓደኛውን “ሶሚክ” ነው የሚለው፡፡“እውነት ለመናገር ሰውመሆን 24 ሰዓት ስለፊልም የሚያወራ ፊልም የሚወድ ልጅ ብዙ ቮካብለሪ ያለው ልጅ ነው። ሶሚክ ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳለፋቸው ጊዜያቶች በጠቅላላ ቀጥታ ወደፊልም ሥራ እያንደረደሩ ነው ያመጡት። ሁልጊዜ ስለአባቱ፣ እናቱ፣ ስለሰፈሩ ልጆች እንዳለ ታሪካቸውን በሚያወራኝ ጊዜ በቃ ይሄ ልጅ ታሪክ ተናጋሪ እንዲሆን ተመርጧል ብዬ አስባለሁ፡፡ እርሱ ጋር ያለው የፊልም ፍቅር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነገር ነው” ይላል ተስፋዬ፡፡
ጎንደር ተወልዶ ያደገው ሰውመሆን “የነፍስ ጥሪው” ወደተባለለት የፊልም ሙያ እንደው በቀጥታ ዘው አላለም፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲቀላቀልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ ያጠናው “ፐርቼዚንግ” ነበር። ምንም እንኳ ትምህርቱ ንግድ ተኮር ቢሆንም ለዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ በአዲስ አበባ መቆየቱ ወደ ፊልም ሥራ የሚሳብበትን አጋጣሚ ፈጥሮለታል፡፡
ሰውመሆን ትምህርቱን የሚከታተልበት የንግድ ሥራ ኮሌጅ የማደሪያ አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ አጎቱ ሻለቃ ተስፋዬ ይግረም ዘንድ እንዲያርፍ ይሆናል። ፎቶ አንሺ የሆኑትን አጎቱን ለመርዳት ከትምህርቱ ጎን እርሳቸው ፎቶ ቤት ያዘወትር ያዘ። ያኔ እንዳሆኑ ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ዲጂታል ፎቶ ካሜራዎች አልነበሩም እና በአናሎግ ካሜራዎች ሲሰራ ቆየ፡፡ “አንዳንድ ሰርጎች አነሳ ነበር፡፡ ሌላም ሌላም ሥራዎች እየሰራሁ ከዚያ ቀስ ብሎ ከፎቶግራፍ ማንሳት ወደ ቪዲዮ መቅረጽ መጣ፡፡ ግን ምንድነው ከድሮም ጀምሮ ሲኒማ ላይ ለየት ያለ ፍላጎት ነበረኝ። ልጅ እያለሁ፣ ሁለተኛ ደረጃም ሆኜ ቪዲዮ ቤቶች አዘወትር ነበር፡፡ ሲኒማ ይሄ ታሪክ መንገር የሚባለው አካባቢ መንፈሴ ነበር፡፡ እና ቀስ እያለ ወደ ፊልም እያደገ መጣ” ይላል ያን ጊዜን ሲያስታውስ ፡፡
የቪዲዮ ፊልሞችን ለሰፈር ተመልካች የሚያከራይበት የራሱ ሱቅ የነበረው ሰውመሆን የመጀመሪያ ፊልሙን ሊሰራ ሲነሳ ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር ለመሞከር ተነሳ፡፡ ከርዕሱ ጀምሮ ወጣ ያለ የነበረው ይህ ፊልም የወቅቱ መነጋገሪያ ነበር። “862” የተሰኘ ስያሜ ስለሰጠው ስለዚህ ፊልሙ ሰውመሆን ሲገልጽ “ቅዥት የመሰለ” ይለዋል፡፡ “ለምንድነው ፊልም ሀ፣ ለ፣ሐ…ተብሎ የሚተረከው?፡፡ ለምን ከመጨረሻ አይጀምርም? የሚል ፍልስፍና የነበረው ፊልም ነው ይዤ የመጣሁት” ይላል ስለ መጀመሪያ ፊልሙ አካሄድ ሲናገር ፡፡ “ታሪኩ ወደ ፊት እየሄደ ወደ ኋላ ይመጣል። በጊዜው አንዳንድ ልጆች የፈረንጅ ተጽእኖ ያለበት ታሪክ ነገራ ዘዴ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
እኔ ደግሞ ከዚያ የተለየ ተቃራኒ የሆነ የእኛ ነው ብዬ ነበር የማምነው፡፡ ለምሳሌ ቢሊጮ የሚባል ገጸባህሪ ተረት ሲነግሩህ ‘ቢሊጮ ከዚያ ምንጣጥሊት እያባረረችው ሄደና እና ወንዝ ተሻገረ፤ ከዚያ እርሷ ወንዝ ወሰዳት’ ይሉህና ‘መጀመሪያማ እንደዚያ አይደለም፤ እንዴት ተሻገርሽ ብሎ ጠየቃት’ ይሉሃል።ይሄ ነው ቅርጹ፡፡ ሄደህ ታልፍና ተመልሰህ መጥተህ ‘እንዴት እዚህ ደረሰ ?’ ስትል ‘እንዲህ የሆነው በዚህ መንገድ ስለሄዱ ነው’ ብሎ በሚናገር መንገድ ነው ታሪኩን የተረኩት፡፡ እና ሕይወት ራሱ ሁሌ ቀጥተኛ አይደለም፡፡ ዛሬ ቁጭ ብለን ነገን እናስባለን፡፡ ነገ ላይ ሆነን ከአራት፣ ከአምስት ቀናት በፊት ወይም ከዓመታት በፊት የሆነን ነገር ነጋችንን ተጽእኖ እንደሚያሳድርበት እናስባለን፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሲኒማ ለምን አንሰራም የሚል ሃሳብ ነበረኝ፡፡ ትንሽ ይለይ ነበር” ሲል ሰውመሆን አጀማመሩን ይተርካል ፡፡
(በመጨረሻው ክፍል ከዚህ እንቀጥላለን)
ሻሎም ! አሜን×፫።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015