አገራችን ባለፉት ዓመታት ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረችም፡፡ እዛም እዚህም ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ሕዝቡ ቁም ስቅሉን ሲያይ ኖሯል፡፡ በተለይ ከወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የአገራችን ክልሎች አውዳሚ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ሁከትና ብጥብጦችም እየተባባሱ መጥተው፤ሰላማዊው ሕዝብም በዚሁ ምክንያት አላስፈላጊ መስዕዋትነት ሲከፍል ቆይቷል፡፡
ሰላም መደፍረሱ ሕገ ወጥነት እንዲበረታታ መንገድ ከፍቷል፡፡ ሙስና እንዲነግስና የቆዬ የአብሮ መኖር መስተጋብራችን እየተሸረሸረ እንዲመጣም አድርጓል፡፡ እንዲሁም ራስን መግዛት የሚያስችሉንን የኃይማኖቶቻችን እሴቶች ዋጋ እንዲያጡ አድርጓል። የትራንስፖርት እንቅስቃሴን አስተጓጉሎ የከፋና ጥግ የደረሰ የሕብረተሰብ ምሬት የሚሰማበት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮቻችን በውጭ ግንኙነታችን ላይም መልካም ያልሆነ የግንኙነት ጥላ አጥልተው ቆይተዋል፡፡
የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመጋበዝ የራሳችንን ችግር ራሳችን እንዳንፈታ ከባድ ጫና ፈጥረውበንም ከርመዋል፡፡ በንግድ ግንኙነትና በአንዳንድ የኢኮኖሚ ሁኔታዎቻችን ላይም ማዕቀብ ከማስጣል አልፈው ኃያላን ነን ከሚሉ በተለይም ከምዕራባዊያኑ አገራት ሉዓላዊነታችንን በብርቱ የሚፈታተን ማስፈራራትና ዛቻ እንዲሰነዘርብን አድርገዋል፡፡ በተለይ ከአሜሪካ በግልጽ ‹በእናንተ ጉዳይ እኔ ነኝ የሚያገባኝ፤ እኔን ስሙኝ› የሚል ዓይነት ግልጽ ጣልቃ ገብነትን በትዕግስት አስተናግደናል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላም በመውረዱ ከሕ.ወ.ሓ.ት ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ እነዚህን ሁሉ ችግሮቻችንን መፍታት የሚያስችለን መደላድል ፈጥረናል፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመደላድሎቹ አንዱ እንዲሆንም አድርገናል፡፡ ኮሚሽኑ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከላይ የተዘረዘሩን ዋና ዋና ችግሮች ጨምሮ ሌሎች እስከ ታች የወረዱ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
የዚህ ይህንን ዓይነቱን የእንቅስቃሴ ሂደቱን ለማሳለጥ በተቋቋመው በአማካሪ ኮሚቴ እገዛ እያከናወነ የሚገኘው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ዓላማው ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎቹን ችግሮቻችንን በመፍታት አገራዊ መግባባት መፍጠር ነው፡፡ በተጨማሪም አገራዊ መግባባት ሲፈጠር አገርና ሕዝብ ሰላም የመሆኑ ጉዳይ እሙን እንደመሆኑ አገርን ሰላም ለማድረግ፤ በፊት የነበሩ የተወሳሰቡ ሂደቶችን፤የተሳሳቱ ታሪኮችን የሚያጠራበትም ሂደት አለው፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ ሂደት ተሳታፊዎችን የመለየቱ ተግባር የሚጀመረው በጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ የሚያከናውነው፤ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚከፍታቸው ቅርንጫፎች መሆኑ ደግሞ ሥራውን የበለጠ የተቃና እንደሚያደርገው ይታሰባል። ከዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን የሚከፍትበት ሁኔታ መኖሩ ሂደቱን የበለጠ ያፋጥነዋል፡፡
በሲቪክ ማህበራትና በሌሎች ተቋማት የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ መሥራት ማሰቡም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይሄን ተንተርሰው ነው በአራቱ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባሉ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ “የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች” “ይወክሉኛል” የሚሏቸውን ተሳታፊዎች ይመርጣሉ፡፡ እንደ አገር በጥቅሉ ከ700 ሺህ በላይ ሕዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎም ታስቧል፡፡
ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው የተለዩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችም የተካተቱ ሲሆን ሴቶችና ወጣቶች ዋናዎቹ የአስመራጭ ወገን ተዋናዮች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን እና የማህበረሰብ መሪዎች እንደሚገኙበት ከኮሚቴው በወጣ መግለጫ ማድመጣችን ይታወሳል፡፡ እንደኮሚሽኑ መግለጫ፣ የተገለሉ ህብረተሰብ ክፍሎችን ማሳተፉ የኮሚሽኑን ፍትሃዊነትና የሚያመላክት ከመሆኑም
በላይ በአገራቸው ጉዳይ ተገልለው በቆዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የተለየ በጎ ስሜት ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንደዚሁም እድሮች እና የንግድ ማህበረሰብም በአስመራጭነት የተካተቱበት ሁኔታ አለ። ከነዚህም ባሻገር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችም፤ “በባለድርሻ አካልነት” እንደሚቆጠሩ ሲነገር ተደምጧል፡፡ በአጠቃላይ ከተሳትፎ አንፃር ሁሉንም ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያሳትፍ መሆኑ ነው እየተነገረለት የሚገኘው፡፡
እነዚህ አስመራጭ የማህበረሰብ ክፍሎች እያንዳንዳቸው በየወረዳቸው 50 ተወካዮችን እንደሚመርጡም ተጠቅሷል፡፡ የመረጧቸውንም ለልየታ ወደ የዞን ማዕከላት እንደሚልኩ ተመላክቷል። ወደ ዞን ከመጡት የእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ውስጥ ሁለት ሰዎች የሚመረጡበትም ሂደት አለ፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች በክልል ደረጃ በሚካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ይሳተፋሉ ተብሎ ይታሰባል። በክልል ደረጃ የሚሰበሰቡት ተወካዮች፤ በየወከሉት ህብረተሰብ ክፍል ተከፋፍለው “ኮከስ” ይፈጥራሉ፡፡ ኮከሶቹ በፊናቸው “የወከልነው የህብረተሰብ ክፍል ዋነኛ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው” ሲሉም የለዩዋቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡበት የአሰራር ሂደት እንዳለ ተነግሯል፡፡
በእያንዳንዱ ወረዳ አንድ አባል ይሄንኑ ሂደት የሚታዘብበት ሁኔታ በኮሚሽኑ በኩል ተመቻችቷል፡፡ ሂደቱን ከሚታዘቡ ተባባሪ አካላት ውስጥ፤ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የመምህራን ማህበር ይጠቀሳሉ። የአካባቢው “የዓውድ ጎሳ መሪዎች”፣ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት እና የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ተካትተዋል፡፡ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የወረዳ አስተዳደር ተወካዮችም ሂደቱን በመታዘብ ይሳተፋሉ፡፡
ለኮሚሽኑ ከሚቀርቡት አጀንዳዎች ከላይ በመግቢያችን የዘረዘርናቸውና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተከታትለው ሲገጥሙን የነበሩ ችግሮች ጎልተው ይነሳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ጦርነቱም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰቱ የነበሩትና አሁንም ያልቆሙት ግጭቶች ትልቅ ቦታ የተሰጠው አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ተብሎ ይገመታል፡፡
ወንድማማችነት ይንገስልን፤ የአብሮነታችን መስተጋብር ወደነበረበት ስርዓት ይመለስልን፤ የተሸረሸረው የየዕምነቱና ኃይማኖቱ እሴቶቻችን ዋጋ ኖሯቸው ችግሮቻችንን ለመፍታት ይብቁ እንጂ የግጭትና ሁከት መነሻ እንዳይሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበት የሚለውም ትኩረት ተሰጥቶት የሚነሳ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሕገ ወጥነት ይቁም፤ ሕግ ይከበርልን እና ሰላም ይስፈንልን የሚለውም ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት የሚነሳ አጀንዳ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
የዋጋ ንረት አባዜ ይታይ፤ የኑሮ ውድነት ጫና ይቅለል ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ችግር ሁሉ ሊፈታበት የሚችል መፍትሄ ይዘየድ የሚለውም ሕዝባዊ አጀንዳ ሆኖ የሚነሳበት ሰፊ ዕድል ይኖራል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለቀጣይ ትውልድ በምን መልኩ ትተላለፍና የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ምን ይሁን የሚለው የአገረ ኢትዮጵያ ጉዳይ ከትክክለኛ የታሪክ ትርክት ጋር ተጣምሮ የሚገነባበት ጥያቄ ቁልፍ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አሁን ላይ የምክክር ኮሚሽኑ ወደ ተሳታፊዎች መረጣ ገብቷል፡፡ በመሆኑም አገርን የመታደጉ ሰፊ ዕድልም ከ700 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደዚሁም ቀጥተኛ ያልሆነ ተዘዋዋሪ ተሳትፎ ባላቸው ሌሎች ታዛቢዎች፤ በአጠቃላይ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እጅ ላይ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡ ተግባሩ ለስኬት ሲበቃ የኮሚሽኑ አስተዋጽኦ ቀላል አይሆንም፡፡ አሁን ላይ እንደ አገር እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ እንድንሻገር ይረዳል፡፡ ለመሻገር መርዳት ሳይሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያሻግራል፡፡ የነገ ተስፋችንንም ብሩህ ያደርግልናል፡፡ የአገረ መንግስቱን ግንባታ ጥሩ መሰረት ላይ በማሳረፍም አገሪቱን ከመፍረስ አደጋ፤ ሕዝቧን ከስደት፤ ከረሀብ፤ ከርዛትና ከግጭትና ሁከት ይታደጋል ተብሎ ይጠበቃል!
ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015