የድሬዳዋ መልከመልካም፤ ቆንጆ ከመባልም በላይ ነች፡፡ የቀይ ዳማ ሆና፤ ፈገግ ስትል ሁለቱም ጉንጮቿ ይሰረጉዳሉ፡፡ አፍንጫዋ ሰልካካ ባይሆንም የደም ግባቷ ያያት ሁሉ እንዲመኛት ያስገድዳል፡፡ ከዘመዶቿ፣ ከጎረቤት እና ከጓደኞቿ ጋር ያላት ቅርበት በፍቅር የተሞላ፤ ሰላማዊ እና የሚያስቀና ዓይነት ነው፡፡
ወንዶችን እንደወንድሞቿ፤ ሴቶችን እንደእህቶቿ ስትቀርብ የማይወዳት እና አብሯት መዋል ማደር የማይፈልግ የለም፡፡ ብዙ ሰዎችን ለማስደሰት ትሞክራለች፡፡ በምንም መልኩ የምታቀርባቸው ሰዎች ጠላት ይሆኑብኛል ብላ አስባ አታውቅም፡፡ ከልቧ ሁሉንም ትወዳለች፤ እየተፍለቀለቀች ሁሉንም ለማስደሰት ትሞክራለች፡፡
ሴቶቹ በእርግጥም እንደእህት እንደአካባቢው ባህል አብረዋት እየበሉ፤ አብረዋት እየሳቁ እና እየተደሰቱ፤ ተሳስበው ይኖራሉ፡፡ ወንዶቹ ግን በተደጋጋሚ በወንድምነት አብረዋት ለመቆየት ይቸገራሉ፡፡ እርሷ የምትፈልገው ወንድምነትን ቢሆንም፤ መልኳ ፈገግታዋ ታክሎበት በፍቅር ይወድቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ በወንድምነት ሳይሆን የፆታ (የፍቅር…) ግንኙነት እንዲኖራቸው ሲፈልጉ ትሸሻቸዋለች፡፡ እርሷ ተዝናንታ ተደስታ ስትኖር፤ ከወንዶች ጋር የሚኖራት ግንኙነት ከወንድማዊነት የዘለለ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ታደርጋለች፡፡
አምሽታ መዝናናት ልማዷ ነው፡፡ ከሴትም ሆነ ከወንድ ጓደኞቿ ጋር ዘና ማለት መለያዋ ነው። ዘና ማለት የምትወደው ግን በእህትነት እና በወንድምነት ግንኙነት እየተሳሳቁ ከመጨዋወት የዘለለ አይደለም። ማክበር እና መከባበር መለያዋ ነው። ነገር ግን ደግሞ በተቃራኒው የድሬዳዋዋን ቆንጆ የአካባቢው ወንዶች ሊረዷት አልቻሉም፡፡ ዙሪያዋን ያንዣብባሉ። አንዳንዶቹ ፍላጎት እንደሌላት እያወቁ አልፎ አልፎ ሊያስገድዷት ይሞክራሉ፡፡ ለማስገደድ ሲሞክሩ እርሷም የዋዛ ባለመሆኗ ባላት አቅም ተከላክላ አስገድደው የፍቅር ግንኙነት ለመፍጠር ከሚጥሩ ወንዶች ጋር ያላትን ጓደኝነት ሙሉ ለሙሉ ታቋርጣለች። ቤቷ አታስገባቸውም፡፡ መንገድ ላይ ስታገኛቸው አታስጠጋቸውም፡፡ አንዳንዶቹ ገብቷቸው፤ተረድተዋት ይተዋታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ጥቃት በመፈፀም እያስፈራሩ አስገድደው አብረዋት ለመቆየት ያስባሉ፡፡
ሃኪም ጣሰው
ሃኪም ጣሰው ጀማል ጎልማሳ ነው፡፡ ሥራውን በአግበቡ ይሠራል፡፡ ሞያው የተከበረ ነውና ሁሉም ያከብረዋል፡፡ ከዚህችው የድሬዳዋ ቆንጆ ጋር የፍቅር ግንኙነት መመስረት ፈልጓል፡፡ ሆኖም ፈቃደኛ አልሆነችለትም፡፡ ጠዋት እና ማታ በቤቷ አካባቢ እያንዣበበ ስትገባ ስትወጣ ያያታል፡፡ ፍዝዝ ብሎ ቢመለከታትም፤ ነገሬ ብላ ፊት አልሰጠችውም፡፡ ቢያፈጥባትም፤ ፊቷን አዙራ አይኗን ገልጣ ለማየት ፍቃደኛ አልነበረችም፡፡ ሊያባብላት ቢሞክርም አልፈቀደችውምና እምቢ አለችው፡፡
እርሱ እየለመናት እምቢ ስትለው ሰው ላከባት። ለሰዎቹም ፍቃደኛ አልሆነችም፡፡ መልሷ ‹‹ከማንም ጋር ምንም ዓይነት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡›› የሚል ነበር፡፡ ሃኪም ጣሰው እምቢ ማለቷን ተከትሎ ሊተዋት አልቻለም፡፡ ጭራሽ ፍቅሩ ጨመረበት፡፡ በስጦታም በመለማመጥም ለማሳመን የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡ ነገር ግን ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡
ሥራውን መሥራት ተሳነው፤ የቀንና የሌሊት ህልሙ ሆነች፡፡ በተቃራኒው እርሷ ግን ሃኪሙን ጭራሽ አታስታውሰውም፡፡ እንደለመደባት እየሳቀች እየተደሰተች ኑሮዋን ቀጥላለች፡፡ ሃኪሙ በበኩሉ ቢያንስ ሰውነቷን መንካት ከሆነለት ደግሞ ሌሎችም የሚፈልጋቸውን ተግባሮች ለመፈፀም መመኘቱን ቀጠለ፡፡ በማባባል ባይሆንለት በግድም ቢሆን ተግባሩን ለመፈፀም ማውጠንጠን ጀመረ፡፡
የመውጫ እና የመግቢያ ሰዓቷን መከታተል ጀመረ፡፡ በተለይ ስታመሽ በተደጋጋሚ ያያታል፡፡ እንዳታመልጠው ሊጨብጣት፤ በቤቷ እንዳትከለል ብብቱ ስር ከቷት ሊያድር ወደደ፡፡ ይህንን ህልሙን እውን ለማድረግ ቀን መጠበቅ ጀመረ፡፡ እርሷ ግን ጭራሽ እንደሚከታተላት ስታውቅ ጭራሽ ትጠላው ጀመረ፡፡
መስከረም አንድ
ቀኑ የዓመቱ መጀመሪያ መስከረም 1 ነበር፡፡ የድሬዳዋ ቆንጆ የአንድ ክፍሏን መስኮት ስትከፍት የጠዋቱ የፀሃይ ብርሃን ልቧን በሃሴት ሞላው። ለወትሮም ሞቅ ደመቅ የምትለው ድሬዳዋ በዛ በበዓል ቀን የበለጠ ተሟሙቃለች፡፡ ከአልጋው ወርዳ የለሊት ልብሷን አውልቃ በግርጌ የተቀመጠውን ድሪያዋን ለበሰች። ፊቷን ታጥባ ኩሏን ከተኳለች በኋላ ከቤት ወጣች፡፡ እጣኗን እና ቡናዋን ገዝታ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
የበዓል ወጥ መስራት ጀመረች፡፡ ወጧን ሠርታ ስትጨርስ ጉዝጓዟን አሰናዳች፡፡ ቤቷን ሞቅ አድርጋ ጎረቤቶቿን ለመጥራት ቡና መቁላት ጀመረች። ቀን ከጎረቤቶቿ ጋር ማታ ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር ለማመሻሸት አስባለችና በጊዜ የሚበሳሰለውን ከማበሳሰል አልፋ፤ በጠዋት የምትጠራቸውን ጎረቤቶቿን ጠራራች። አብረው እየተጎራረሱ በልተው፤ የሚጠጣውን ጠጥተው ሁሉም ወደየቤቱ ሲሔድ፤ እርሷ ደክሟታልና አይኗን የቤቷ ጣራ ላይ ሰክታ ካፈጠጠች በኋላ መልሳ በጎኗ ጋደም አለች፡፡
የድሬዳዋዋ ቆንጆ ቢደክማትም በዓል በመሆኑ ደስ ብሏታል፡፡ ለብሳ ለመዝናናት ከመውጣቷ በፊት ለመተኛት አሰበች፡፡ ጋደም ብላ ብዙም ሳትቆይ የጓደኞቿ የሥልክ ጥሪ ሸለብ ካደረጋት እንቅልፍ በድንገት አባነናት፡፡ አመሻሽ ላይ ለመገናኘት ተቀጣጥረው እንቅልፏን ተኛች፡፡
እኩለ ሌሊት
ሃኪም ጣሰው ጀማል በድሬዳዋዋ ቆንጆ ቤት አካባቢ እያንዣበበ ነው፡፡ እርሷ በበኩሏ አጭር ቀሚስ፤ ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ አጥልቃ እና ፀጉሯን በረዥሙ ለቃ ከቤቷ ወጥታ በስልክ ጠርታ ያስመጣችው ባጃጅ ውስጥ ገብታ ወደ ጓደኞቿ ሔደች። ሃኪም ጣሰው በባጃጁ ውስጥ የሄደችውን ቆንጆ በአይኑ ሸኝቷት ወደ ቤቱ ገባ፡፡ በየአንድ ሰዓት ልዩነት እየወጣ ቢያያትም አልተመለሰችም፡፡
ቤቷ ሔዶ አንኳኳ ፤ከውስጥ መልስ አላገኘም። የቤቷ አንፖል አልበራም፡፡ መቅናት ጀመረ፡፡ ንዴት ይተናነቀው ያዘ፡፡ ጃኬት ደርቦ ቢላዋ ይዞ መንገድ መግቢያ ላይ ቆሞ መጠበቅ ጀመረ፡፡ ሰዎች ሲመጡበት ወደ ጨለማው ገባ ብሎ ቢላዋውን ጃኬቱ ሥር ከቶ ዚፑን ዘጋ፡፡ እጁን ኪሱ ውስጥ ከቶ መጠበቁን ቀጠለ። የድሬዳዋዋ ቆንጆ ወደ ቤቷ አልተመለሰችም፡፡
ወጣ ብለው የነበሩ ጎረቤቶቿ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሃኪም ጣሰውን ቆሞ ማየታቸው ጥርጣሬ አሳድሮባቸዋል፡፡ ሃኪሙን ወጣ ብለው በድጋሚ ሲመለከቱት ወደ ቤቱ አልገባም፡፡ አንዳች ነገር አስቦ ሊሆን እንደሚችል ጠርጥረዋል፡፡ ሰዓቱ እየገፋ እኩለ ለሊት ሆነ፡፡
ከመዝናናት መልስ
መሸታ ቤት ስትዝናና የቆየችው የድሬዳዋ ቆንጆ እንደልማዷ ለጓደኞቿ ወደ ቤቷ መሔድ እንደምትፈልግ ነገረቻቸው፡፡ እንሸኝሽ ብለው ተከተሏት፡፡ ከሩቅ ቆንጆዋን የያዘ ባጃጅ እየመጣ መሆኑን የጠረጠረው ሃኪም ጣሰው ወደ ጥግ በመጠጋት ራሱን ጨለማ ውስጥ ከቶ ላለመታየት ሞከረ፡፡ ሸኚዎቿ ልብ አላሉትም፡፡ እርሷም አላየችውም፡፡ እርሷን እና ሸኚ ጓደኞቿን ይዞ የነበረው ባጃጅ እርሷን አውርዶ በፍጥነት ከአካባቢው ሲርቅ ሃኪም ጣሰው ቆንጆዋን ተከተላት፡፡
የድሬዳዋዋ ቆንጆ ብዙም በእግሯ ሳትራመድ ከጀርባዋ በጠንካራ እጅ አፏና አፍንጫዋ ታፈነ። በእጇ ለማስለቀቅ ብትሞክርም አልቻለችም። ምራቋ አነቃት። እንደምንም እየተንፈራፈረች እጇን እያወራጨች ጠንካራውን እጅ ከአፍንጫዋ እና ከአፏ ለማስለቀቅ ሞከረች፡፡ ቢላዋውን ወደ አንገቷ ሲያስጠጋው አይኗ ፈጠጠ፡፡ በድንጋጤ ከመንቀጥቀጥ ይልቅ ድርቅ አለች።
ሃኪም ጣሰው ይወዳታልና ሳሳላት፤ መጨከን አልቻለም፡፡ ይልቁኑ ቢላዋውን ጥሎ፤ አፍና አፍንጫዋን ያፈነበትን እጁን አንስቶ አጭሩን ቀሚሷን ሲገልብ እየተንቀጠቀጠች ኡኡታዋን አቀለጠችው። ከየአቅጣጫው ጎረቤቶቿ በራቸውን እየከፈቱ ሲወጡ፤ ሃኪም ጣሰው እግሬ አውጪኝ ብሎ ፈረጠጠ፡፡ ቆንጆዋ ግን በድንጋጤ እየተንቀጠቀጠች ግድግዳ ተደግፋ ተቀመጠች፡፡ ሰዎች ተሰበሰቡ። የሆነውን ሲጠይቋት በሚንቀጠቀጥ ድምፅ ከሞት ማምለጧን እና ሃኪም ጣሰው ሊደፍራት ሲሞክር እንደነበር ተናገረች፡፡ የአካባቢው ወጣቶች ሃኪሙን ለማግኘት ሮጡ፡፡ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ሔደው አመለከቱ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
በማግስቱ ማለትም መስከረም 2 ፖሊስ የተፈፀመውን ወንጀል በተመለከተ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ የቆንጆዋን ቃል ተቀበለ፡፡ ሃኪም ጣሰው ለቀናት ከመሰወር አልፎ ከተማዋን ለቆ ለመውጣት ቢያስብም እንዳሰበው አልሆነም፡፡ ብዙ ቀናቶች ሳይቆጠሩ ያለበት ታወቀ፡፡ ፖሊስ እና የአካባቢው ሕብረተሰብ በመረባረቡ ብዙም ሳይቆይ ቆንጆዋን ልጅ እጁ ለማስገባትም ሆነ አቅፎ ለማደር፤ እንዲሁም የፈፀመውን ወሲባዊ ጥቃት ተከትሎ ከሚመጣበት ተጠያቂነት ለማምለጥ ያደረገው ሙከራ ሁሉም ሳይሳካለት ቀረ፡፡
ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ብርቱ ክትትል በማድረጉ ሃኪም ጣሰው ጀማል በቁጥጥር ስር ለማዋል ቻለ፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሶስት ልዩ ስሙ ዲፖ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሊፈፅም የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ውሏል በሚል ፖሊስ የምርመራ መዝገብ አሰናዳ፡፡
የድርጊቱን ሁኔታ ከሳሽ የድሬዳዋ ቆንጆ አስረዳች።ተከሳሽ ሃኪም ጣሰው ጀማል ቢላዋ ይዞ ተዝናንታ ወደ ቤቷ ስትገባ በጨለማ ተሸሽጎ የያዘውን ቢላዋ ወደ አንገቷ አስጠግቶ የአስገድዶ መድፈር ሙከራ ሊያደርግ መሞከሩን ገለፀች፡፡ ፖሊስም ድርጊቱን ተጠርጣሪው ስለመፈፀሙ አረጋገጠ፡፡
ውሳኔ
ፖሊስ እና አቃቤ ህግ በጋራ ያጣሩትን የምርመራ መዝገብ ለድሬዳዋ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን መረጃ ተመርኩዞ፤ የግራ ቀኙን ክርክር ከተከታተለ በኋላ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ጣሰው ጀማል ጥፋተኛ ነው ሲል ብይን ሰጠበት፡፡ በመጨረሻም የድሬዳዋ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰባት ዓመት ከ3 ወር እስራት ወሰነበት፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015