ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለ13 አመታት በሥራ ላይ የቆየውን የማዕድን ሀብት ልማት አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ የማዕድን አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ምክር ቤቱም ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ሲታይ ቆይቷል፤ ሰሞኑን ደግሞ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተመርቶ ውይይት ተደርጎበት የተለያዩ ሃሳቦችን መሰብሰብ ተችሏል፡፡
የረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ መነሻ
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ፤ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልጹ፤ አዋጁ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረ ቢሆንም፤ የኃላፊነትና የባለሥልጣናት እንዲሁም የአስፈጻሚ ተቋማት መቀያየሮች በመኖሩ ምክንያት በተለያየ ጊዜ በተወሰኑ የአዋጁ አንቀጾች ላይ ከተደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎች ባለፈ አዋጁ የተሟላ አልነበረም፡፡ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን እያደረጉ ከመቀጠልና በተለያዩ ምክንያቶች እንዲሁም መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ትኩረትና ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ እንዲሁም ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ እምነት ተጥሏል፡፡
‹‹የማዕድን ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ሀገራዊ ጥቅም አላስገኘም፡፡ ለመጠቀም ስንፈልግ ደግሞ በፍትሐዊ መሆን ይኖርበታል›› ያሉት ሚኒስቴሩ፤ ይህ ሲባል የፌዴራል መንግስቱን፣ የክልሎችንና የማህበረሰቡን አጠቃላይ እንደ ሀገር ያለውን እኩል ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማዕከል ያደረገ ወይንም የሚያስተካክል አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ነው በሚል አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል፡፡ በማለት አስረድተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በረቂቅ አዋጁ የልዩ ፈቃድ ማዕድን ልማትን ማስቀረት፣ የደለል ማዕድን ማምረት ፈቃድን ለውጭ ዜጋ መስጠትን ማስቀረት፣ የባህላዊ ማዕድን ማልማት የሥራ ፈቃድ ጊዜን ማሻሻል፣ የከፍተኛ ደረጃ ኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ለፌዴራል መንግስት እንዲሰጥ ማድረግ በረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ከተካተቱ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ለማዕድን ልማት ፈቃድ ሲሰጥ የፌዴራል መንግስቱና የክልሎች ድርሻ፣ ልማቱን ማስተዳደር፣ ከልማቱ ከሚገኘው ገቢ ክልሎች ተጠቃሚ ስለሚሆኑበት ሁኔታ፣ አካባቢን መልሶ ማልማትና የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ከዚህ ቀደም በህጉ ውስጥ ያልነበሩ እንደሆኑ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ አዋጁ ከሌሎች ህጎች ጋርም ተጣጥሞ መዘጋጀቱን አመልክተዋል። ከተጠቃሚነት አንጻርም ፌዴራል መንግስት በሚያስተዳድራቸው ፈቃዶች ክልሎች የሚያገኙት ሮያሊቲ እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ በአሁኑ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ መካተቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አካባቢ ላይ ከሚደርስ ጉዳት ጋርም ተያይዞ ክፍተቶችና የአፈጻጸም ችግሮች እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡
አዋጅ ማውጣትና ማሻሻል ብቻውን በቂ እንዳልሆነና ወደ ተግባር መቀየር እንደሚያስፈልግ ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ፤ ጥሩ ውጤት ለማግኘትም አፈጻጸሙ ላይ ጠንክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል። ታች ላይ ያለው ተቋም ጠንካራ አለመሆን፣ የፀጥታ ችግር፣ በዘርፉ ላይ የአንዳንድ አካላት ጣልቃ ገብነት ችግሮችም ሌላው የዘርፉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ በመጥቀስ፤ በህግና ፖሊሲ የሀገር ዜጋን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ባለሀብትንም ለመሳብ የአዋጁ መሻሻል ጠቃሚ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በሰባት ክፍሎች የተደራጀውና 79 አንቀጾች ያለው ረቂቅ አዋጅ ከባህላዊ እስከ ከፍተኛ ማዕድን ማምረት የሚያካትት ወደ 51 አርቲክሎች (ገጾች) ሰፊውን ክፍል የያዘ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግብዓቶችን በማከል እንዲያፀድቀው ያስተላለፈው ሲሆን ምክር ቤቱ ደግሞ በዝርዝር እንዲመለከተው ለኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት፣ ለረቂቅ የተሻሻለው አዋጅ ማዳበሪያ የሚሆን ሀሳብ ከባለድርሻ አካላት ተሰብስቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ጥሪ መሠረትም ዘርፉን ከሚመሩ የክልልና የፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ አልሚዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሀሳብ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ከተሰጡት የግብአት ሀሳቦችም የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፡፡
የክልል የዘርፉ መሪዎች ሀሳብ
የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ታደሰ፤ በአዋጁ በተወሰኑ የረቂቅ ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱና ሀገሪቱ ከምትከተለው የፌዴራሊዝም ሥርአት፣ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(1) (መ) ላይ በሰፈረው መሠረት ማዕድንን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብትን ለማስተዳደር ከተሰጣቸው ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን እንዲሁም ከክልሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንጻር ወደፊት አዋጁን ከመተግበር አኳያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ማየታቸውን አንስተዋል፡፡
በማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚው የሥራ ዕድል መፍጠር በረቂቅ አዋጁ እንደ አንድ ዓላማ መያዙን በመጥቀስ፣ ነገር ግን የማዕድን ልማት በሚካሄድበት አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ ቅድሚያ የሥራ እድል የሚያገኝበትና ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆንበት አግባብ በአዋጁ መስፈር እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ የፌዴራል መንግሥት በማንኛውም ባለ ፈቃድ ከሚካሄድ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ሥራ አምስት በመቶ ሥራው በሚካሄድበት ክልል ደግሞ ሁለት በመቶ ድርሻ ያለምንም ክፍያ ተብሎ የተቀመጠውንም አቶ ዘውዱ የፌዴራል ድርሻ ከፍ ማለቱ አሳማኝ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ በልማቱ ለአካባቢ ተጽእኖ ተጋላጭ የሚሆነው የክልሉ መንግሥት እንደሆነ በመጥቀስ የበለጠ ድርሻ የክልሎች መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ መሬት ለማዕድን ሥራዎች ክፍት ይሆናል ተብሎ በማሻሻያ ረቂቁ የተጠቀሰውንም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታቸውን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ የማዕድን ሥራን እንደመርህ ማስቀመጡን ጠቅሰው፣ እንደገና መታየት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
ማዕድን ሚኒስቴር ለሀገር ጥቅም አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን የሕዝብ ማስታወቂያ በማውጣት ማናቸውንም መሬት የማዕድን ሥራ የሚካሄድበት ነው ብሎ መከልከል ይችላል ተብሎ በረቂቁ የተቀመጠውም የመሬት አስተዳደር ጉዳይ እንደሆነና ይህም መሬቱን ለማስተዳደር በሕገ መንግሥቱ ስልጣን ለተሰጠው አካል መተው ያለበት እንጂ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚወሰን እንዳልሆነም አመልከተዋል፡፡
የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ በበኩላቸው፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በስፋትና በጥልቀት እንዳልተወያዩበት ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ሲሉ ገልጸው፣ የሚሻሻለውን ረቂቅ አዋጅ ከማዘጋጀት በፊት 678/2002 የነበረው አዋጅ ጠንካራና ደካማ ጎን ላይ የዳሰሳ ጥናት መሥራት ያስፈልግ እንደነበርም ነው ያመለከቱት፡፡ በቀጣይም በረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መንፈስ ክልሎች ያላቸውን ስልጣን ወደ ፌዴራል መንግስቱ መውሰድ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኃይሌ፤ ከገቢ ጋር በተያያዘ በረቂቁ ላይ የተገለጸውን በተመለከተም ክልሎች ከሮያሊቲም ሆነ ከገቢ ግብር ከሚያገኙት የበለጠ በቀነሰ ሁኔታ በረቂቁ ላይ መስፈሩን ነው ያመለከቱት፡፡
የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በሰባት ክፍሎች ተከፍሎ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ትኩረቱ የሚያጠነጥነው በሶስተኛው ክፍል ላይ ወይንም በአንድ ሀሳብ ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ስለፈቃድ አይነቶች አሰጣጥ በሚያመለክተው ክፍል ሶስት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ስለ ሥነ ምድር፣ ማዕድን ግመታ አይነት ሕገ ወጥ ቁጥጥርና ክትትል፣ የተጠቀሰ ነገር እንደሌለና ትንታኔ እንደሚጎለው አስረድተዋል፡፡
ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው መካከል አንዱ ማዕድን እንደሆነና ይህንን ተከትሎም ክልሎች የየራሳቸውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በመሥራት መንቀሳቀሳቸውን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ ልማቱ ከለውጥ በፊትና ከለውጥ በኋላ የተገመገመበት ሁኔታ አንድ እንዳልሆነም በማውሳት፣ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የክልሎችን መልካም እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ የማዕድን ሥራ በሕግ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ መስተጋብርም እንዳለው ጠቅሰው፣ በተለይም የማህበረሰብ ስምምነት አስፈላጊነት ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባና መታየትም እንዳለበት ጠቁመዋል። በአጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ ጥርጣሬን የሚያሳድር የግልጽነት ችግር እንዳዩበት ከነመፍትሄ ሀሳብ በዝርዝር በጽሁፍ ለቋሚ ኮሚቴው ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ክልል ማዕድንና ኤጀንሲ ቢሮ የማዕድን ዘርፍ ኃላፊ አቶ እያሱ ማሞ፤ በከፊል የከበሩ ማዕድናት በአነስተኛ ደረጃ ለሚገኙት ፈቃድ የሚሰጠው በፌዴራል እንደሆነ በማስታወስ፣ በዚህ ደረጃ ፈቃድ ወስዶ በበቂ ሁኔታ የተንቀሳቀሰ ኩባንያ በየትኛውም ክልል አለመኖሩን እርግጠኛ መሆን የሚቻልበት ምክንያት መኖሩን ነው የገለጹት፡፡ በከፊል የከበሩ ማዕድናት በባህሪያቸው የሰው ጉልበት ካልታከለባቸው የሚከናወኑ እንዳልሆኑም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፍቃድ የመስጠቱ ኃላፊነት የክልል ሆኖ ሥራው ቢሰራ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት ነው እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
የባህላዊ ማዕድን ማምረት ሥራም እንዲሁ በባህሪው ብዙ ሰዎች ጉልበታቸውን አቀናጅተው የሚያከናውኑት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በክልሉ ሥራው ለማህበራት ብቻ እንዲሰጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ወርቅን የሚያህል ሀብት በግለሰብ ደረጃ እንዲለማ ፍቃድ መስጠት ተገቢነት እንደሌለውም አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ ሊተገበር የማይችል ነገርን በአዋጁ ላይ ማስፈር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
አቶ እያሱ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩ በሚኖርበት ስፍራ የሚገኝ ማዕድንን ጥቅም ላይ ለማዋል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማይነካ መልኩ እንዴት መተግበር እንደሚቻል እንዲሁም የካሳ ክፍያው አፈጻጸምም ምን አይነት የማዕድን አይነት እንደሆነ በአዋጁ በዝርዝር መታየት አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡ ለእዚህም በድንጋይ ከሰል ማዕድን ላይ ያጋጠማቸውን ችግር ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኢንጂነር ፍቅሬ ኃይሌ፤ ክልሎች ያላቸው አዋጅና ደንብ መፈተሽ እንደነበረበት በመጥቀስ፤ በክልላቸው ተጨባጭ ሁኔታ ግልጽ የሆነ አዋጅ ባለመኖሩ ከድንጋይ ከሰል ማዕድን ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር አንስተዋል። በፌዴራልና በክልል የሚሰሩ ሥራዎች ተለይተው በግልጽ መቀመጥ እንዳለባቸው እንዲሁም በግለሰብ ይዞታ ላይ የሚገኝ የማዕድን ሀብትን እንዴት መጠቀም ይቻላል የሚለውም ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት የሚለው ግዴታ ለባህላዊ አምራቾች ብቻ ሳይሆን ኩባንያዎችንም ማካተት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የልዩ አነስተኛ ማዕድን ልማት ፈቃድን ማስቀረት በሚለው ላይ የአሰራር ሥርዓት ማበጀት እንጂ ማስቀረት በሚለው እንደማይስማሙም ነው የተናገሩት፡፡ በማዕድኑ ላይ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነት ለማስቀረት በገንዘብ ማበረታቻ ማህበረሰቡ ተባባሪ ሆኖ ሕገወጡን የሚያስይዝበት አሰራር የሚዘረጋበት ምቹ ሁኔታ በአዋጁ እንዲካተትም ጠይቀዋል፡፡
የአልሚዎች ሀሳብ
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ፕሮጀክታቸው የሚገኘው የኩርሙክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያው አቶ መርዕድ አማረ ያነሱት የጉምሩክ ቀረጥና ታክስን የተመለከተ ነው፡፡ በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች በሌሎች ዘርፎች እንደተሰማሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ሁሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማዕድን ሚኒስቴርና ገንዘብ ሚኒስቴር የተናበበ ሥራ እንዲሰሩ በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በዝርዝር መታየት እንዳለበት አንስተዋል።
በሲሚንቶ ምርት ላይ የተሰማራውን ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ ወክለው ሀሳብ የሰጡት አቶ ገዛኸኝ፤ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለልማቱ ኃላፊነትን ወደ ላይ መውሰድ ሳይሆን፣ ወደ ማህበረሰብ እንዲወርድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ሮያሊቲ ላይ ጭማሪ ሲደረግ ተጠቃሚው ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጫናና ተያያዥ ጉዳይ የታየ ነው ብለው እንደማያምኑና ትንታኔ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ ሮያሊቲ በማምረቻ ዋጋ ወይንም በመሸጫ ዋጋ ስለመሆኑም በግልጽ በድንጋጌው ላይ እንዳልተቀመጠም አመልክተዋል፡፡
ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አቶ ቶላ መኮንን፤ ማዕድን በባህሪው ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና ሰፋ ያለ ጊዜ እንደሚፈለግ ጠቀሜታውም ሰፊ እንደሆነ አንስተው፤ ከዚህ አኳያ በዘርፍ ውስጥ አብዛኛው ኢንቨስተር እንዴት ገብቶ ሊሰራ ይችላል፣ ለኢንቨስትመንቱ አሳሪ የሆኑ ነገሮችን ለይቶ ምቹ ነገሮችን በመፍጠር ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ነገሮች ከሚሻሻለው አዋጅ ይጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል። ከተረፈ ምርት በተሻለ ቴክኖሎጂ ማምረት እንደሚቻልና የወርቅ ተረፈ ምርት የማይደፋበት ማዕቀፍ ቢዘጋጅ የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል።
ማጠቃለያ
የልዩ አነስተኛ ፈቃድን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ፤ በሰጡት ምላሽ፤ በልዩ አነስተኛ ፈቃድ አወጣን የሚሉ አካላት ያልተፈቀደላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር በመሳተፍ የአካባቢውን ማህበረሰብንም ሆነ ሀገርን በሚጎዳ ሕገወጥ ድርጊት ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የሀገር ሀብት በዚህ መንገድ ሲዘረፍ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንንም ሕግ በማስከበር መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሕገወጦቹ ገንዘብ በመስጠት ወርቁን ሌላ ቦታ እንደሚወስዱት ሚኒስትሩ ተናግረው፣ ማዕድን የማውጣቱ ስራ አካባቢው ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ሳይታይ ማሽኖች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ባህላዊ አምራቾችን ማሳደግ ተገቢ ቢሆንም በዚህ መንገድ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀገር ሆና ነገር ግን በሀብቷ ተጠቃሚ አይደለችም። ለአብነት ደቡብ አፍሪካ በአመት እስከ 123 ቶን ወርቅ ታመርታለች፤ ጋናም እንዲሁ እስከ ከ100ቶን በላይ ታመርታለች፡፡ በኢትዮጵያ 10 ቶን ወርቅ የተመረተው በጥቂት ወቅቶች ነው፡፡ አዋጁ ይህን ሁሉ ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ የማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ አብሮ ይዘጋጃል በማለት ሕጎች የሚወጡት እየታዩ ካሉ ችግሮች መነሻ እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች በካሎ እና ምክትል ሰብሳቢው ዶክተር ፍቃዱ መንግሥቱ በየበኩላቸው በሰጡት ሀሳብ፤ ከቤቱ የተነሱት ሀሳቦች ግብዓት እንደሚሆኑና ቋሚ ኮሚቴውም በጥልቀት የሚያየው ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ አዋጁ በተቻለ መጠን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሀሳብ ያካተተ እንዲሆን በማድረግ ግልጽነት ያለው አዋጅ ጽድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2015