• 4ኛው የፈርኒቸር፣ ቤተ-ውበት እና የግንባታ አጨራረስ ዓለም አቀፍ አውደ-ርዕይና ጉባዔ ተከፈተ
አዲስ አበባ፡- መንግስት በፈርኒቸር ዘርፊ ለሚደርገው እንቅስቃሴ ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
“ንግድዎን በመቅረዝ ላይ ያኑሩ” በሚል መሪ ቃል 4ኛው የፈርኒቸር፣ ቤተ-ውበት፣ የግንባታ አጨራረስ ምርቶችና ቴክኖሎጂዎች ዓለም አቀፍ አውደ-ርዕይ እና ጉባዔ በትላንትናው እለት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።
አውደ-ርዕይው ከሰኔ 8 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይም ተገልጿል።
በመክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር አማካሪና የኢትዮጵያ ታምርት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አበበ እንደተናገሩት፤ መንግስት የፈርኒቸር ዘርፊ ለሀገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ በዘርፉ ለሚደርገው እንቅስቃሴ ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንዱስትር ዘርፎች አስደናቂ እድገትና ብልጽግናን ለማምጣት ጥረት እያደረገች በመሆኑ የቤትና የቢሮ እቃዎች የኮንስትራክሽን ዘርፎች በሀገርቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የስራ እድል በመፍጠር የራሳቸውን ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ይህ አውደ-ርዕይ መካሄዱ ለዘርፉ ተስፋን የሚሰጥ በመሆኑ አምራቾች ትርጉም ያለው አጋርነት በመፍጠር የትብብር፣ የእውቀትና የጋራ ተግባራትን መሰረት በማድረግ ፈተናዎችን በማሸነፍ ለተሻለ ለውጥ መትጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ግብርናውን ከእንደስትሪው ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የተለየ ትኩረት በመስጠት የማዘመን፣ በስፋት የማስተዋወቅ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የሚያግዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን በመገንዘብ የፈርኒቸር፣ የቤተ-ውበት እና የግንባታ አጨራረስ አውደ-ርዕይ መዘጋጀቱ ጠቄሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ ዳይረክተር ወይዘሮ ዘምዘም አህመድ በበኩላቸው፤ የብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የፋይናንስ ስረዓት የሚቆጣጠር በመሆኑ ዘርፉን ለማሻሻል የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት በኢኮኖሚዉ ላይ በስፋት እየታየ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ እየሰራ እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም አካታች የፋይናንስ ስረዓትን መዘርጋት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ልስጠው የሚገባ በመሆኑ ከግል ባንኮች ጋር በቅርበት እየተሳራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፈርኒቸር አምራቾች ማሀበር ምክትል ፕሬዚደንት ወይዘሮ ትህትና ሙሉሸዋ እንደጠቆሙት፤ የፈርኒቸር አምራቾች ማሀበር አምስት ድርጂቶችን ይዞ እንደተቋቋመ በመግለጽ በወቅቱ ማህበሩን ማቋቋም ከባድ እንደነበረ አስታውሰው አሁን የተደረሰበት ደረጃ አበረታች ነው ብለዋል፡፡
በመንግስት በኩል ለዘርፉ መሻሻል በፖሊስና በተለያዩ ዘርፎች አበረታች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ ትህትና እንደነኝህ አይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ለዘርፉ ተዋናኞች ትልቅ አስተዋጽኦ የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ይህ አውደ-ርዕይ በእንጨት ስራ፣ በቤት፣ በቢሮ እና በኢንዱስትሪ ፈርኒቸሮች እንዲሁም የውስጥ እና ውጪ ማስዋቢያ ምርቶች፣ መብራቶች፣ መጋረጃዎች እና ልዩ ልዩ ግብዓቶችን የሚያቀርቡ የሀገር ውስጥ አምራቾች በስፋት የሚሳተፉበት ሲሆን ከ400 በላይ ገዢዎች እንዲሁም ከ4 ሺህ በላይ የንግዱ ማሀበረሰብ አባላት እና ጎብኝዎች እንደሚስተናገዱበት ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በቃልኪዳን አሳዬ