በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየው ሰላምና መረጋጋት፣ በመሰረት ልማት ዝርጋታ ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት፣ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማበረታቻዎች እንዲሁም አገሪቱ ያላት የሰው ሀብት፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እና ሰፊ የገበያ እድል፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ አገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል፡፡ ይህም ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ዓይነተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ለአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገትም ትልቅ ድርሻ አበርክቷል፡፡
የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻልና እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠሩት የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሀብት ቀውስና ጦርነቶች ጋር ተደምረው በአገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሰናክል መሆናቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ባለፈው በጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በአገሪቱ ከነበረው አለመረጋጋትና ጦርነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከ‹አጎዋ› (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክቷል፡፡ ለአብነት ያህል በተጠቀሰው በጀት ዓመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 64 ነጥብ አራት በመቶ (ከሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ) ብቻ እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡
ጦርነቱ በአገሪቱ ላይ ያሳደሩት ጫና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድሎችን በፈጠሩና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳካት እገዛ እያደረጉ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ አለመረጋጋቱን ተከትሎ የመጣው የአንዳንድ ምእራባውያን አገሮች፣ የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሰሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድሮም ነበር፡፡ በተጨማሪም የውጭ አገራት ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በአገሮቻቸው ኤምባሲዎች በኩል ከፍተኛ ግፊት ይደረግባቸው ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመስራት ተገደው እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት የምርት አገልግሎትና አቅርቦት መቋረጥ፣ የምርት ሽያጭ ገቢ መቀነስ፣ የስነ ልቦና ጫናዎችንና ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱም ይታወቃል፡፡
የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ለነበረው የሰላም መደፍረስ መፍትሄ ይሆናል የተባለውና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የሰላም ስምምነቱ በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩ የማምረት ስራዎች እንዲጀመሩ፣ ተቀዛቅዘው የነበሩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስራዎች እንዲያንሰራሩ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእርግጥም ስምምነቱ እንደተጠበቀው ተጨባጭ ለውጦችን አስገኝቷል፡፡ ስራ አቋርጠው የነበሩ አምራቾች ወደ ስራቸው ተመልሰዋል፤ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲነቃቃና ቀደም ሲል ከነበረው አፈፃፀምም የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት አመራርና አስተዳደር ስርዓት መተግበር እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
አንጋፋው የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፣ ከጦርነት በኋላ የሚኖር የምጣኔ ሀብት ግንባታ በተለመደው አሰራርና የቢሮክራሲ ሂደት ተመርቶ ውጤታማ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ከጦርነት በኋላ በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌሎቹ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች የሚከናወኑ የመልሶ ግንባታ ስራዎች ፈጣን እርምጃዎችን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ራሱን የቻለና ውሳኔ ሊሰጡ የሚችሉ አካላት በቅርበት የሚከታተሉት እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተሰባስበው የሚሰሩበት የአሰራር ዘዴ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሰራር ደግሞ በተለመደው የቢሮክራሲ አካሄድ ሊፈፀም አይችልም፡፡
‹‹ከጦርነት በኋላ መሰረተ ልማቶች የፈረሱበት፣ ቢሮክራሲው የላሸቀበት እና ሰብዓዊ ቀውስ የተንሰራፋበት ነባራዊ ሁኔታ ስለሚኖር፤ እነዚህን ጉዳቶች መልሶ መገንባትና ማካካስ የሚቻለው ከወትሮው በተለየ አካሄድና ስርዓት ነው፡፡ ፈጣን የሆኑ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡›› ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ መደበኛው አሰራር ለድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ ግንባታ ሊመጥን እንደማይችል አስታውቀዋል፡፡ ‹‹መደበኛውን አሰራር የምንከተል ከሆነ፣ ከችግሩ መውጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በአዲስ ጉልበትና በአዲስ አሰራር መጓዝ ያስፈልጋል›› ሲሉ አስገንዝበው፣ ክህሎትና እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በብዛት ማሰማራት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ በጦርነቱ ምክንያት የተዳከመውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት የሚያስችል ልዩ ስትራቴጂ በመንደፍ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚስፈልግ ይመክራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በጦርነት የወደመ ኢኮኖሚን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ኢንቨስትመንት የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የህዝቡን ትብብር የሚፈልግ ተግባር ነው፡፡
በዚህ ረገድ የጦርነቱን ጫና ሊያቃልሉ ለሚችሉ የኢንቨስትመንት ተግባራት ቅድሚያና ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ጦርነቱ የበለጠ ጉዳት የሚያስከትለው በመሰረተ ልማቶች ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጦርነቱን ጫና ሊያቃልል የሚችለው ዐቢይ ተግባርም በጦርነቱ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ባለሀብቶች፣ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችንና ጉዳቶችን ያስተናገዱ በመሆናቸው፣ ከጦርነት በኋላ ስራቸውን ለመቀጠል አስተማማኝ ዋስትና ይፈልጋሉ። ስለሆነም መንግሥት ለኢንቨስተሮች ዋስትና መስጠት ሌላው ተግባሩ ይሆናል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ መገንባት የሚቻለው ከወትሮው በተለየ አካሄድና ስርአት ነው ሲሉ የገለጹትን ዶከተር ሞላም አጠናክረውታል፣ ዶክተር ሞላ ከጦርነት በኋላ የሚኖረውን አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ከጦርነት በፊት በነበረው አሰራር መምራትና ማስተዳደር እንደማይቻል ጠቅሰው፣ የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ስራ አስገዳጅ አሰራሮችን እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በጦርነቱ የተጎዱት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች እንዲያገግሙ ለማድረግ ዘርፎቹ ከጦርነቱ በፊት ሲያስመዘግቡ ከነበረው እድገት በተሻለ አቅም እንዲያድጉ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል አዲስ አሰራር ነድፎ መንቀሳቀስና ጉዳቱን ማካካስ ያስፈልጋል›› በማለት የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ስራ የተለየ አካሄድ እንደሚያስፈልገው ያብራራሉ፡፡
በድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚና ካላቸው ግብዓቶች መካከል አንዱ የፋይናንስ አቅርቦት ነው፡፡ በጦርነቱ የተጎዳው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲነቃቃ የሚተገበረው የአመራርና አስተዳደር ስልት ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ብቁ የሆነ የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት አመራር ስልት አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል። የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ሰሞኑን ይፋ ሲደረግ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልና በሌሎች ክልሎች የነበረው ግጭት ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት ፋይናንስ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ንቁ ተሳትፎ እንደሚፈልግ የሚናገሩት አምባሳደር ጥሩነህ፣ በመልሶ ግንባታው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF)ን ጨምሮ ለጋሽ መንግሥታትን ማሳተፍ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ዶክተር ሞላ፣ ‹‹ጦርነቱ ‹ምን ዓይነት ጉዳቶችን አደረሰ? በጣም የተጎዱት ዘርፎች የትኞቹ ናቸው? ምን ዓይነት ኢንቨስትመንቶች ያስፈልጋሉ? የሚሉት ጉዳዮች በጥንቃቄ ከተለዩና ከተጠኑ በኋላ የፋይናንስ ምንጩ ከየት እንደሚገኝ ማሰብ ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡ ‹‹የፋይናንስ ምንጭ መፈለግ ወሳኝ ጉዳይ ነው›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ ከመንግሥት በተጨማሪ፣ ባለሀብቶች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ተቋርጠው የነበሩ ግንኙነቶችን በማስቀጠል፣ እቅዶችን በመከለስ እና ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው፡፡ የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ስራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን ተወስኖ ውሳኔውን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው፡፡
አዲሱ የኢንቨስትመንት አዋጅ (1180/2012) ኢትዮጵያን ተወዳዳሪና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት ታምኖበታል፡፡ አዋጁ ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለውጭ ባለሀብቶች ሰፊ የኢንቨስትመንት እድል የሚፈጥርና ገደብ የማያስቀምጥ አዋጅ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ሰፊ እድል ያገኛሉ፡፡ ቀደም ሲል አገሪቱ ትጠቀምበት የነበረው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ሊሰማሩባቸው የሚችሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የሚገድብ (Positive Listing Approach) ነበር፡፡ ይህ አሰራር ኢንቨስተሮቹ ሊሰማሩባቸው ከሚችሉባቸው ዘርፎች ውጭ ባሉት ሌሎች ዘርፎች ላይ እንዳይሳተፉ ገደብ የሚጥል ነው፡፡ ይህ የቀደመው አሰራር በተሻሻለው አዋጅ (1180/2012) ተቀይሯል፡፡ አዲሱ የኢንቨስትመንት አሰራር ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የማይችሉባቸውን ዘርፎች የመዘርዘርና የቀሩትን ክፍት የማድረግ አቅጣጫ (Negative Listing Approach) በመሆኑ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
የኢንቨስትመንት ሕግጋት መሻሻልን ጨምሮ ሌሎቹ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እርምጃዎች በድህረ ጦርነቱ ወቅት የሚኖረውን አገራዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው ዶክተር ሞላ ያስረዳሉ፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የኢንቨስትመንት አዋጁ መሻሻል የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ብዙ ባለሀብቶችን በመሳብ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ትልቅ አቅም ያላቸው ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ከሆነ ለፋይናንስ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዘላቂ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሽ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ባለሀብቶቹ የወጪ ንግድንና የተኪ ምርቶችን ምርት በሚያሳድጉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ከጦርነት በኋላ የሚኖር የኢኮኖሚ ግንባታ፣ በተለይም የኢንቨስትመንት ዘርፍ አስተዳደርና አመራር፣ የተለየ አሰራር እንደሚፈልግ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ‹‹የማርሻል እቅድ›› (Marshall Plan) በመባል የሚታወቀውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምዕራብ አውሮፓን ምጣኔ ሀብት ለማነቃቃት የተተገበረው የምጣኔ ሀብት ማገገሚያ መርሃ ግብር (Economic Recovery Act of 1948) ለዚህ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ከተፈረመው የሰላም ስምምነት በኋላ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በብቃት በመተግበር የሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱን ግንባታ ማፋጠን ይገባል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2015