ስህተትን ለማረም፣ ለማስተካከል፣ ራሳችንን ለማነጽ ስንፈልግ ቅድሚያ የምንፈልጋቸው የቀደሙትን ባለውለታዎቻችንን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም:: ምክንያቱም እነርሱ ዘንድ ታሪክ አለ፤ በእነእርሱ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ድል፣ ተስፋና ፍቅርም አለ:: ለሌሎች መኖርና ሌሎችን ማቆምም እንዲሁ ስንፈልግ ከእነርሱ ጋር የምናገኘው ነገር ነው::
በእነርሱ ቀጣዩን ትውልድ በመልካም ስነምግባር ይታነጻል፤ በመልካም ጎዳና ይመራል:: ምክንያቱም ሕይወታቸው መምህርም መሪም ነው:: አርኣያነታቸው መንገድ ጠራጊ ነው:: እነርሱ ጋር እውቀትና ልምድን፣ ማስረጃንና በቂ መረጃን ማግኘትም ይቻላል:: ያንን ይዞ ደግሞ በአመክንዮና በምክንያት ሂስ መስጠት ይቻላሉ:: ምክንያቱም ሀሳባቸው ምጡቅና ተቀባይነት ያለው ነው::
እነርሱ ጋር ለአገር መሥራትና ለአገር መሞት እንዲሁም የአገር ፍቅር ዘላለማዊ ነው:: ስለዚህም በዚህ ውጣውረዳቸው ታሪካቸውን አስቀምጠው ለሌሎች መማሪያ ገድል ሆነዋል:: ተቀባይ ከሆንን፤ እኛም ታሪክ ሰሪ እንድንሆን አቅጣጫን ጠቁመውናል:: እነዚህና መሰል ባህሪያትን ከተላበሱት መካከል ለዛሬ ‹‹የባለውለታዎቻችን›› አምድ እንግዳ ያደረግንላችሁ አንጋፋ ዲፕሎማት ናቸው:: እኝህ ባለውለታችን የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ሲሆኑ፤ አያሌው ማንደፍሮ ይባላሉ::
አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ የተወለዱት ከአባታቸው ከአቶ ማንደፍሮ ኃይለጊዮርጊስ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘውዲቱ አየለ ግንቦት 27 ቀን 1927 ዓ.ም (እ.ኤ.አ June 4, 1935) በሐረር ከተማ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በሐረር ከተማ በሚገኘው በራስ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት መከታተል ችለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ደግሞ የተከታተሉት በቀድሞው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው:: የተመረቁበት የትምህርት መስክ ምኅንድስና ሲሆን፤ ቀጥለው ደግሞ ወደ ውጪው ዓለም በማምራት ሌላኛውን የከፍተኛ ትምህርት በአሜሪካን አገር ታፍት ዩኒቨርሲቲ ቦስተን ማሳቹሴት ሲሆን፤ በኢንተርናሽናል ግንኙነት ተመርቀዋል።
በ1950 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1958) ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ አሜሪካን ክፍል ተመድበው ሥራ የጀመሩት አምባሳደር አያሌው፤ በዚህ መሥሪያ ቤት ውስጥ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የልጅ ሚካኤል እምሩ ልዩ ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል። ቀጥሎም ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው፤ የእርሳቸው የቅርብ ረዳትና አማካሪ በመሆን ለዓመታት በሙሉ ታማኝነት ሰርተዋል:: በእርግጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲገቡ መጀመሪያ በረዳት ሚኒስትርነት በኋላም በምክትል ሚኒስትርነት ማዕረግ የአሜሪካንን ክፍል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
ከአቶ ከተማ ጋር በነበራቸው ወዳጅነትና የቅርብ ግንኙነት በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ተሰሚነታቸው በጉልህ የሚታይበት ወቅት እንደነበርም ታሪካቸው ያስረዳል። ይህ ከሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ቅርርበት ደግሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረቱ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ አግዟቸዋል:: ማለትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከመመስረቱ በፊት የአፍሪካ መሪዎችና መንግስታት ለድርጅቱ መመስረት ድጋፋቸውን ለማረጋገጥ በተደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት ትልቅ ጉዞ በየዋና ከተሞቹ በማከናወን ውጤታማ አስተዋፅዖ ሲያደርጉ ነበር::
ከሚኒስትሩ ጋር በጣምራ አያሌ የአፍሪካ መሪዎች ዘንድ የግርማዊ ጃንሆይን መልዕክቶች በማቅረብና በየግላቸው በማነጋገር እንዲሁም በማግባባት የፈጸሙት ሚናም ዘላለም የሚረሳ እንዳልሆነም የህይወት ታሪካቸው ያወሳል። በዚያኑ ዘመን አፍሪካ በካዛብላንካና በሞንሮቪያ ቡድኖች በመከፋፈሏ አዲስ አበባ ላይ ሁሉንም ያካተተ ስብሰባ ለማካሄድ አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት የአምባሳደር አያሌውና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ድርሻ ላቅ ያለ ነበር::
በዲፕሎማሲው ዘመቻ ታላቁን ኃላፊነት ወስደው በመስራታቸው ታላቅ አክብሮት እንዲሰጣቸው እና ባለታሪክ ሆነው እንዲታወሱ አስችሏቸዋል። በተጨማሪ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመመስረቻ ቻርተር በሚዘጋጅበት ጊዜ አምባሳደር አያሌው በማቀነባበርም ሆነ ባበረከቱት ሃሳብ ሥራው እንዲጣደፍ ማድረጋቸውም ይነገራል። ስብሰባው በተከናወነበት ጊዜም ቢሆን ለሊት እና ቀን ቀልጣፋ በሆነ መንገድ የኮንፈረንሱን ጽህፈት ቤት ተግባር በኃላፊነት ከፈጸሙት መካከልም ስማቸው ይጠራል።
በሴኔጋል ዳካር ከተማ በመጀመሪያው የአፍሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ የደርጅቱ ዋና መቀመጫ የት ከተማ እንዲሆን በሚከራከርበት ጊዜ አምባሳደር አያሌው ከኢትዮጵያውያን መልዕክተኞች መካከል ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከዳካር ከተማ ይልቅ አዲስ አበባ የድርጅቱ ዋና መቀመጫ ሆና እንድትመረጥ ካስቻሉት ውስጥ ግንባር ቀደም ናቸው:: ካይሮ ላይ በ1964 ዓ.ም በተደረገው የመሪዎች ጉባዔ በፀደቀው ውሳኔ አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ እንድትሆንም አሻራቸውን ያሳረፉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
በ1957 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1965) አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ መጀመሪያ በረዳት ሚኒስቴርነት ቆየት ብሎ ደግሞ በምክትል ሚኒስትርነት ማዕረግ የአሜሪካንን ክፍል ከመሩ በኋላ ደግሞ በ1963 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1971) የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሶማሊያ ተሹመው በዚያድባሬ ዘመነ መንግስት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል እንዲሰሩ ተደርገዋል::
በውጤታማ ተግባራቸውም ብዙ አስደሳች ለውጦችን ማምጣት ችለዋል:: ለአብነት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ በአምባሳደር አያሌው ጉትጎታና ተደጋጋሚ ጥሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞቃድሾን እንዲጎበኙ ሆኗል። ይህ ደግሞ በጉብኝታቸው የተመኙትን ያህል ውጤት ባያገኙም ሁለቱን መሪዎች በቀጥታ ማነጋገር መቻላቸው ተስፋ ጫሪ ሥራ ነበር:: ምክንያቱም በወቅቱ የሁለቱን መንግስታት የአቋም ልዩነት በጣም ሰፊ ነበር:: እናም በእርሳቸው ሥራ ልዩነቶቹ መቀነስ እንደቻሉ ታሪካቸው ይናገራል።
በሞቃዲሾ በአምባሳደርነት በቆዩበት ወቅት አምባሳደር አያሌው ሌላም ሥራ ሰርተዋል:: በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን ውጥረት ማብረድ የቻሉ ሲሆን፤ በተለይም ከጦርነት አፋፍ ላይ የነበሩበትን ሁኔታ ማቅለል ችለዋል። ከሞቃዲሾ ወደ ሐረርጌ ደጋግመው በመመላለስ ሶስተኛውን ክፍለ ጦር በሚጎበኙበት ጊዜ አምባሳደር አያሌው የሰሩትም ተግባር ዛሬ ድረስ የሚታወሱበት ነው:: የሶማሌን መንግስት የመስፋፋት ፖሊሲና የትጥቅና የጦር ዝግጅት ላይ ሙሉ መረጃ በማካፈልም በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ጉድለት በግልፅ በመወያየት የሞራል ድጋፍ ለሰራዊቱ አድርገዋል::
የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት ሥርዓት በአብዮቱ ተገርስሶ ደርግ ስልጣኑን በያዘበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሲቪሉ አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ ሲሆኑ፤ የጦር ሰራዊቱ በሞቃዲሾ አምባሳደር በነበሩበት ጊዜ ያሳዩትን ትጋትና የአገር ፍቅር በመገንዘቡ ለዚህ ሹመት መብቃታቸው ይነገራል።
አምባሳደር አያሌው በመከላከያ ሚኒስትርነት ዘመናቸው የሶማሌ የጦር ኃይል ለወረራ መዘጋጀቱን በማወቃቸው ለኢትዮጵያ ጦር መሳሪያ ለማግኘት አያሌ መንግስታት ዘንድ በመልዕክተኝነት ተዘዋውረው ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት በብርቱ የጣሩ ባለውለታ እንደሆኑም ታሪካቸው ይናገራል።
ሌላው አምባሳደር አያሌው የሰሩት ተግባር በሱማሊያ ጠረፍ የተከሰተውን አስጊ ሁኔታ እየባሰ በሄደበት ወቅት ያደረጉት ነገር ነው:: ይህም ከምዕራብ ዓለም ጋር ደርግ የሚተሳሰርበትንና አቅም የሚፈጥርበትን ሁኔታ ማመቻቸታቸው ሲሆን፤ በተለይም በፖለቲካ፣ በመሳሪያ ድጋፍና መሰል ነገሮች አጋር ይሆናሉ ያሏቸውን ሁሉ እንዲጠቀሙ ከአገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያሻሻሉ በምክር ደግፈዋል:: በዚህም ምክንያት ከ30 ወራት ኩርፊያ በኋላ የደርግ መንግስት አምባሳደር አያሌውን አምባሳደር በማድረግ ዋሽንግተን እንዲሰሩ ሾሟቸዋል። ግን ከአሜሪካን ጋር የተቀራረበ ግንኙነት የማይደግፉ ወገኖች አምባሳደሩ አዲስ አበባን በመልቀቂያቸው ዋዜማ የግድያ ሙከራ አድርገውባቸው በተአምር ከአደጋ እንደተረፉ በታሪካቸው ላይ ተቀምጧል።
ዋሽንግተን ገብተው ለጥቂት ወራት ሥራቸውን እንደጀመሩ ከደርግ መንግስት ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየሻከረ የሄደው አምባሳደር አያሌው፤ በግንቦት ወር 1970 (እ.ኤ.አ June, 1978) ዓ.ም ሥራቸውን ለመልቀቅ ወስነዋል:: መልቀቅ እንደሚፈልጉም አሳውቀው ተሰናብተዋል:: በዚህም በቨርጂንያ አሌክሳንድሪያ ከተማ በስደት ኖረዋል:: ነገር ግን በዚያ ሳሉ ዝም ብለው አልተቀመጡም:: ለኤመርሰንና ለኮሞሳት በተባሉ ኩባንያዎች ውስጥ ለመሥራት አመለከቱ:: በኃላፊነትም ለዓመታት ሰሩ:: እንዲያውም በምክትል ፕሬዚዳንትነት እስከ ጡረታ እድሜያቸው ድረስ አገልግለዋል::
አምባሳደር አያሌው ረቂቅ እና አስደናቂ ባህሪ ነበራቸው:: በዋሽንግተን ዲሲ በስደት በኖሩበት ወቅት የዳያስፖራው መናኸሪያ ኮከብ የነበሩ ሲሆን፤ የአፍሪካ ሶሳይቲ መስራች መሆናቸውም ይነገራል::
አምባሳደር አያሌው ሌላም ሊያስጠራቸው የሚችል ገድል የፈጸሙ ሲሆን፤ ይህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ባገለገሉባቸው ዓመታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከባልደረቦቻቸው ጋር የጎላ ሚና ተጫውተዋል::
አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ በመከላከያ ሚኒስቴር በሥራ ላይ እያሉ ከወይዘሮ ፀዳለ ከበደ ጋር የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ፈጽመው ሁለት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፤ ልጆቻቸውም ዶክተር ምህረት ማንደፍሮ እና ልጅ ሙሴ ማንደፍሮ ይባላሉ:: አያት መሆን የቻሉት እኚህ ባለውለታ፤ ዞሮዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከሞት አይቀርምና እርሳቸውም ታሪክ ተክለው በደረሰባቸው የአንድ ሳምንት ሕመም ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በ84 ዓመታቸው በአሜሪካን ፌርፋክስ ሆስፒታል ሕይወታቸው አልፏል:: መልካም እረፍትን ለላይኛው ቤታቸው ተመኘን:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015