ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ 130 የሚደርሱ አቅራቢዎችና ከሶስት ሺ በላይ የንግድ ጎብኚዎች የተሳተፉበት 5ኛው አግሮ ፉድ እና ፕላስት ፕሪንት ፓክ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሰሞኑን ለሶስት ቀናት ተካሂዷል:: ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ትኩረቱን ያደረገው በግብርና፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ በንጥረ ነገሮች፣ በህትመት እና በማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች ላይ ነው:: የንግድ ትርዒቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ወቅታዊ የንግድ እድሎችን ለማወቅ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም መፍትሄዎችን ለማመላከት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የንግድ ትርዒቱ ተሳታፊ አምራችና አቅራቢዎች ተናግረዋል::
በንግድ ትርዒቱ ምርቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡ አምራቾች መካከል ሚድሮክ ኩባንያ ከሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ይገኝበታል:: የሆራይዘን ፕላንቴሽን የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ይርጋ ብርሃኔ እንዳሉት፤ ሆራይዘን ፕላንቴሽን ቡናን እና ሌሎች ምርቶችን የሚያዘጋጅ ድርጅት ነው:: ድርጅቱ እሴት የተጨመረበትን ተቆልቶ የተፈጨ ቡናን ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል::
ፕላንቴሽኑ በንግድ ትርዒቱ ላይ መገኘቱ ምርቶቹን ለማስተዋወቅ መሆኑን አቶ ይርጋ፤ አመላክተዋል:: ሆራይዘን ፕላንቴሽን ወደ ውጭ ከሚልከው ደረጃውን የጠበቀና ተቆልቶ የተፈጨ ቡና በተጨማሪ በአገር ውስጥ ገበያ ትላልቅ ሆቴሎችና ሱፐርማርኬቶች ላይ ሰፊ ተደራሽነት ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል::
ዓለም አቀፍ በሆኑ የንግድ ትርዒቶች ላይ መሳተፍ ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚናገሩት አቶ ይርጋ፤ ለአብነትም ሆራይዘን ፕላንቴሽን እሴት ጨምሮ የሚያዘጋጀውን ቡና ከሚፈልጉ ሆቴሎችና ሱፐርማርኬቶች እንዲሁም የውጭ ገዢዎች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችለዋል ይላሉ:: ለተዘጋጁ ምርቶች ማሸጊያ (ፓኬጅ) ከሚያዘጋጁ ድርጅቶች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ይፈጥርለታል ሲሉም ገልጸዋል:: ይህም በዓለም ዙሪያ የገበያ ትስስር ከመፍጠር አልፎ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ለልምድ ልውውጥ ትልቅ በር የሚከፍት ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ እንደመሆኑ ምርት ፈላጊው ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር አምራች ኢንዱስትሪዎችም ማሸጊያ (ፓኬጅ) ከሚያመርቱ አምራቾች ጋር የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ:: በተለይም በአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲህ ያለ መድረክ እጅግ ያስፈልጋል:: አሁን ላይ ለሆራይዘን ምርቶች ማሸጊያ (ፓኬጂ) ድርጅቱ ማሸጊያዎችን ከዱባይ እንደሚያስመጣ ጠቅሰው፣ በአገር ውስጥም ማሸጊያ ፓኬጆችን የሚያመርቱ አምራች ድርጅቶች እንዳሉም ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ለቡና ማሸጊያ በተለይም ወደ ውጭ ለሚላከው ቡና የሚጠቀሙት ማሸጊያ (ፓኬጅ) ከዱባይ የሚመጣ ቢሆንም አልፎ አልፎ ከአገር ውስጥ አምራቾች ይገዛሉ:: ድርጅቱ በተለይም የሚድሮክ እህት ኩባንያ ከሆኑ በተለያዩ ኩባንያዎች የሚመረቱ እንደ ሻይ ቅጠል፣ ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለመሳሰሉ ምርቶች አገር ውስጥ የሚዘጋጀውን ማሸጊያ (ፓኬጅ) ይጠቀማል:: በመድረኩም በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ማሸጊያ (ፓኬጅ) አምራች ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች ጋር የመተዋወቅና የገበያ ትስስር የመፍጠር አጋጣሚን የሚፈጥርላቸው እንደሆነ አመላክተዋል::
ሌላኛው ምርት አቅራቢ ድርጅት ኢኮ ግሪን ነው:: ድርጅቱ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ይዞ ነው በንግድ ትርኢቱ ላይ የቀረበው:: የኢኮ ግሪን ድርጅት የማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ ታዘበ ከበደ እንዳሉት፤ የኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መቶ በመቶ የተፈጥሮ ነው:: የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያው ቀድሞ የሚታወቀውን ዩሪያና ዳፕን ተክቶ የሚያገለግል ሲሆን ኢኮ ግሪን ፈሳሽ ማዳበሪያው በፈሳሽ መልክ ሰብሉ ላይ የሚረጭ በመሆኑ ዩሪያና ዳፕ ተብሎ ከሚታወቀው ማዳበሪያ የሚለይ እንደሆነ ነው የተናገሩት::
ድርጅቱ ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያን ወደ ገበያ ይዞ ከመጣ ከአስር ዓመታት በላይ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታዘበ፤ ምርቱን ለማምረት የእንስሳትና የእጽዋት ተዋጽኦን የሚጠቀም እንደሆነ ነው የተናገሩት:: ማዳበሪያው ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ በሆኑ በአገር ውስጥ ግብዓቶች የሚመረት ሲሆን፣ ድርጅቱም በቀን እስከ 100 ሺ ሊ ትር ማዳበሪያ የማምረት አቅም አለው::
ማዳበሪያው መቶ በመቶ ተፈጥሯዊ በመሆኑ በጊዜ ሂደት የአፈር ለምነትን እየመለሰ የሚመጣ ስለመሆኑ አቶ ታዘበ ጠቅሰው፤ ድርጅቱ ተሸላሚ እንደሆነም ተናግረዋል:: ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ ምርቱን እንዴትና መቼ መጠቀም እንዳለበት የድርጅቱ ባለሙያዎች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ታች ላለው አርሶ አደር ጭምር እንደሚያስገነዝቡ አመልክተዋል:: አጠቃቀሙ ልዩነት ያለው መሆኑን ሲያስረዱም መሬቱ ከታረሰና ዘር ከተዘራ በኋላ ምርቱ ብቅ ማለት ሲጀምር የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያው እንደሚረጭ አቶ ታዘበ ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት:: በንግድ ትርዒቱ ላይ በርካታ ኩባንያዎችና ትላልቅ የእርሻ መሬት ያላቸው አምራቾች ተሳትፈዋል:: ከእነዚህ አምራቾች ጋር በቀላሉ መገናኘትና የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላል:: በንግድ ትርዒቱ የተሳተፉ የተለያዩ አካላትን የመተዋወቅና የልምድ ልውውጥ እንዲሁም ተሞክሮን ማስፋት የሚያስችል መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፈ ብዙ ከሆነው አበርክቶው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ነው የተናገሩት::
በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ መተካት የቻለው ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ችግር በተወሰነ መጠን ማቃለል እንደቻለም ተናግረዋል:: ድርጅቱ በቀጣይም ሥራውን በማስፋት የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያውን ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል:: ምርቱ ከሰባት ዓመት በላይ ጥናትና ምርምር የተደረገበት መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ተጨማሪ ጥናቶች በደብረብርሃን እና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተደረጉ መሆናቸውንም ነው ያስረዱት:: ጥናቶቹ ሲጠናቀቁም የሚገኘው ውጤት ግብርናው ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ነው ብለዋል::
ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ከአፈር ማዳበሪያ የተሻለ ዋጋ ያለው ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ታዘበ፤ በኩባንያው ዋጋ በሊትር 60 ብር እንደሚሸጥም አስታውቀዋል:: አያይዘውም የግብርና ምርት እንደመሆኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል ሲሉ ምርቱን እንደማንኛውም ሸቀጥ በማንኛውም ሱቅ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፣ በተለያዩ ዩኒየኖች፣ ማህበራትና በሌሎች ማዕከላት አማካኝነት አርሶ አደሩ ማዳበሪያውን ማግኘት እየቻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ምርቱን ለመጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል:: ለአብነትም ቅጠላቸው ሰፋፊ የሆኑ እንደ ጎመን አይነት ሰብሎች የሚጠቀሙት የማዳበሪያ መጠን ትንሽ መሆን አለበት:: ምክንያቱም መሬት የሚወድቀው ጠብታ በጣም ትንሽ ነው:: እንደ ጤፍ አይነት ትናንሽ የሆኑ ሰብሎች ደግሞ ሰፋ ያለ ርጭት ይፈልጋሉ:: ይህም አብዛኛው ርጭት መሬት የሚወድቅ በመሆኑ ነው::
አብዛኞቹ የአፈር ማዳበሪያዎች ኬሚካል ስለመሆናቸው የጠቀሱት አቶ ታዘበ፤ ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመሆኑ የአፈር ለምነትን እየመለሰ በጊዜ ብዛት መሬቱ ወደ ተፈጥሮ ቦታው እንዲመለስ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረው፣ ዩሪያና ዳፕ ግን የአፈር ለምነትን እየቀነሰ እንደሚሄድም ገልጸዋል::
ሌላው ትላልቅ ማሽነሪዎችን ይዞ የቀረበው የቱርክ ኩባንያ ነው:: 32 ዓመታት ልምድ ያለው ኩባንያው በንግድ ትርዒቱ የተለያዩ ግዙፍ ማሽነሪዎችን ይዞ ስለመቅረቡ የኩባንያው ተወካይ ወጣት አክሱማዊት ዓባይ ትገልጻለች:: ተወካይዋ ኩባንያው ከፍተኛ ልምድ እንዳለው ጠቅሳ፣ መፍጫ ማሽነሪዎችን ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስመጣም ጠቁማለች::
እሷ እንዳለችው፤ ወደ አገር ውስጥ ከሚያስመጣቸው ማሽነሪዎች መካከልም የስንዴ፣ የበቆሎና የጤፍ መፍጫ ማሽኖች ይገኙበታል:: ከዚህ በተጨማሪም የእንስሳት መኖ የሚዘጋጅበትን ማሽንም ያስመጣል:: ኩባንያው ማሽነሪ ከማስመጣት ባለፈ ሰዎች ማሽነሪውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ስልጠና ይሰጣል::
ኩባንያው አገር ውስጥ ካቀረባቸው ትላልቅ ማሽነሪዎች ተጠቃሚዎች መካከል ካኦ ጄጄ እና ዲኤች ገዳ ይገኙበታል:: ኩባንያው ለእነዚህ ድርጅቶች ማሽነሪዎቹን ከማስረከብ ጀምሮ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ስልጠና በመስጠት ጭምር ምርትና አገልግሎታቸውን አስተዋውቋል:: በዚህም የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ተችሏል ትላለች::
ቱርኮች የሚያመርቷቸው ማሽነሪዎች ጥራት እንዳላቸው የምትገልጸው አክሱማዊት፤ በእንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ መሳተፍ ደግሞ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳም ጠቁማለች:: አምራች ኢንዱስትሪዎች ለምርታቸው የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን ማስመጣት የሚችሉት ዓለም አቀፍ በሆኑ ኤግዚቢሽኖች ላይ በሚፈጠር የገበያ ትስስር እንደሆነም ጠቁማለች::
በኤግዚቢሽኑም ቱርክን ጨምሮ የቻይና፣ የኩዌትና የሌሎች አገራት ኩባንያዎችን መመልከት ችለናል:: የአገር ውስጥ አምራቾች ከእነዚህ ኩባንያዎች የሚፈልጓቸውን ምርቶች ከማግኘት ባለፈ የገበያ ትስስር መፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ የሚችሉ ሲሆን፤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ከንግድ ትርዒቱ ማግኘት እንደሚችሉም ከተሳታፊዎች መረዳት ችለናል::
በንግድ ትርዒቱ የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሃሰን መሐመድ እንዳሉት፤ የንግድ ትርዒቱ በዓለም ዙሪያ የገበያ ትስስር ከመፍጠር አልፎ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ለልምድ ልውውጥ ትልቅ በር ይከፍታል። በተለይም በኢትዮጵያ ሶስት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ መግባታቸው ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ማድረግ አስችሏል። እነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በአማራ ክልል ቡሬ፣ በኦሮሚያ ክልል ቡልቡላ፣ በሲዳማ ክልል ይርጋለም የሚገኙ ናቸው::
ፓርኮቹን በታቀደው ልክ መጠቀም እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው፤ የአገሪቱን ምርቶች በጥሬያቸው ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ በመላክ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተሻለ መልኩ መገንባት እንደሚቻል ነው ያመላከቱት:: የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከ280 ሺ አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር እንደቻሉ የገለጹት አቶ ሃሰን፤ የሥራ እድል ፈጠራውንም ከ40 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግብርና ከኢንዱስትሪ እና ከንግድ ጋር ተሳስረው በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ዓለም አቀፍ አምራቾችን እንዲሁም ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ውስጥ መሳብ ተችሏል:: በዚህም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተጠናከሩ ይገኛሉ:: መንግሥትም በእነዚህ ዘርፎች ምቹ አካባቢ እና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል::
በተለይም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በተመለከተ አምስት ክላስተሮችን በማዋቀር ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በግብርና፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ በንጥረ ነገሮች፣ በህትመት እና በማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች ላይ ያተኮረው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትም የዚህ ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል:: ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ለገበያ ትስስር፣ ወቅታዊ የንግድ እድሎችን ለማወቅ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና መፍትሄዎችን ለማመላከት ትልቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተመላክቷል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015