ኮንፊሺየስ ከክርስቶስ ልደት በፊት 551 እስከ 479 ዓመተ ዓለም የኖረ የቻይና ፈላስፋ፣ መምህር እና ፖለቲከኛ ነው። የዚህ ሰው የፖለቲካ አስተምሮ “ በአንድ አገር ሰላም እንዲሰፍን፣ እድገትና ልማት እንዲመጣ ሁሉም መክሊቱን አውቆ በመክሊቱ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል “ በሚል ጽኑ መሰረት ላይ የተዋቀረ ነው።
ይሄ የፖለቲካ አስተሳሰብ ዛሬ ላይ አጠቃላይ በሆነው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አባት የአባትነትን፣ ሚስት የሚስትነትን፣ ልጅ የልጅነትን፤ ሌላውም በቤተሰብ ውስጥ ያለ አካል እንደተዋረዱ የሚገባውን ቦታ ይዞ በኃላፊነት ካልተንቀሳቀሰ በቤተሰቡ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተድላ አይኖርም። ችግሩ እልፍ ሲልም ቤተሰቡን ሊበትን የሚችል ነው።
በቤተሰብ ፍቅር፣ እንክብካቤና ቁጥጥር በሥርዓትና በወግ ተኮትኩቶ ያላደገ ልጅ ደግሞ ነገ ላይ ከራሱ አልፎ ለአገርና ለህዝብ ይጠቅማል ተብሎ አይታሰብም፣ ከዚህ ቤተሰብ ነገ አገርና ህዝብን የሚጠቅም ትውልድ ይወጣል ብሎ ማሰብም ያልዘሩትን እንደማጨድ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ከዚህ የተነሳ መክሊትን አውቆ መክሊትን በኃላፊነት መንፈስ በአግባቡ የመወጣቱ እውነታ አይደለም አገር፤ ቤተሰብ እንደቤተሰብ አቅም አግኝቶ ለአገር የሚጠቅም ትውልድ እንዲያፈራ ትልቅ አቅም ነው። ነገዎች ላይ ሆና ለምናስባት የበለፀገች አገር ምስረታም ዋነኛ መሰረት ነው።
ዜጎች በመክሊታቸው በሥራ ላይ ያለመሰማራታቸው ጉዳይ፤ ላለፉት ስድስት አስርታት በአገራችን ለተፈጠሩና አሁንም ዋጋ እያስከፈሉን ላሉ ችግሮች እና ችግሮቹ እየፈጠሩት ላለው ውጥንቅጥ መንስኤው እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
በአገሪቱ ብዛት ያላቸው ዜጎች በመክሊታቸው በኃላፊነት መንፈስ እራሳቸውን፣ ማህበረሰባቸውንና አገራቸውን በታማኝነት ከማገልገል ይልቅ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ያለቦታቸውና መክሊታቸው ተሰማርተው ፍሬ ቢስ ሲሆኑ ማየት የተለመደና ትኩረት የተነፈገ ጉዳይ ነው።
ለአብነት በጥሩ ሥነ-ምግባር ቀርፆና አስተምሮ ተማሪዎችን ለውጤት ማብቃት ለመምህር የተሰጠ መክሊት ነው። አንዳንድ መምህራን በተሰጣቸው መክሊት ጠንክረው ሠርተው ተማሪዎቻቸውን ለፍሬ ማብቃት ሲገባቸው፤ በተለያዩ አስገዳጅ ችግሮች ያለመክሊታቸው ሲደክሙ ማየት፤ በተለይም በአገራዊ ፖለቲካ ጉዳይ ተጠልፈው ሲዳክሩ ማየት ከተለመደ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ይህም በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ላይ ለተፈጠረው ችግር እንደ አንድ ምክንያት ሊቆጠር የሚችል ነው። መምህራኑ የተማሪዎችን እውቀትና ውጤት ከማሻሻል ጀምሮ እራሳቸውን ለማብቃት የሚያስችል መነቃቃት በማጣታቸው፤ የተማሪዎች ውጤት ሆነ፤ የትምህርት ጥራቱ ከፍያለ አገራዊ አደጋ ውስጥ ወድቋል።
ለዚህ ደግሞ ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡት ሦስት በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸው ችግሩ የቱን ያህል የገነገነ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በተመሳሳይ የኃይማኖት አባቶችና መምህራን ጉዳይ ብንወስድ፤ ምዕመናንን በኃይማኖት እና በስነ-ምግባር አስተምህሮዎች በመቅረጽ፤ በእምነቱ የጸና፣ ፈሪሃ እግዚኣብሔር ያለው፣ ከሌሎች ኃይማኖት ተከታዮች እህትና ወንድሞቹ ጋር ተከባብሮና ተቻችሎ እንዲኖር ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።
ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነታ የተገላቢጦሽ እየሆነ ነው፤ አንዳንድ የኃይማኖት አባቶች ከተሰጣቸው መንፈሳዊ ኃላፊነት ወጥተው በተለያዩ የፖለቲካ እሳቤዎች ተጠልፈው፤ ምዕመናን በምዕመናን ላይ ሲያስነሱ፣ የተሰጣቸውን መክሊት የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሲያደርጉ ይታያል። በዚህም አገር እየታመሰች፤ ምዕመኑም ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል እየተገደደ ነው።
የኃይማኖት አባቶች በተሰጣቸው መንፈሳዊ ኃላፊነት ወጥተው ወርደው ባለማትረፋቸው፤ ፈጣሪውን የሚፈራ፣ ወግና ባህሉን ያልለቀቀ፣ ፍትህን የማያዛባ ህዝብ ያለባት ምድር ተብላ በዓለም ላይ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ ወንድም ወንድሙን የሚያሳድድባት፣ ቀማኛና ወንበዴ የበዛበት፣ ሰው ተዘቅዝቆ የሚሰቀልበትና የሚቃጠልባት፣ የአንድ አገር ዜጎች ጽንፍና ጽንፍ ቁመው እርስ በእርስ ጦርነት የሚያካሂዱበት አገር ሆናለች።
ለዋቢነት ትውልድ የሚቀረጽባቸው ትምህርት ቤቶች እና ህዝብ በመንፈሳዊ ሕገ የሚመራበትን የቤተ እምነቶችን ጉዳይ አነሳን እንጂ፤ በሌሎች የሙያ መስኮች (በጤና፣ ግብርና፣ ፍልስፍና፣ ምህንድስና፣ ፖለቲካ ወዘተ.) የተሰማራው አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል በተመሳሳይ በተሰማራበት የሙያ መስክ ጠንክሮ ሠርቶ አገርና ህዝብን ለእድገትና ብልጽግና ለማብቃት በሙላት ሲታትር አይስተዋልም።
በተለይ ዛሬ ላይ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት ከማሰራጨት አንጻር ቴክኖሎጂው ይዞት የመጣውን እድል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁሉም የፖለቲካ ተንታኝ የመሆኑ እውነታ በኛ አገር የፖለቲካ አውድ ውስጥ ይዞት የመጣው አደጋ የከፋ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ነገ ላይ የበለጸገች አገር ለመፍጠር ከሁሉም በላይ ዛሬ ላይ አርሶ አደሩ ስለ ግብርናው፣ ሃኪሙ የህብረተሰቡን ጤና ስለሚያሻሽሉ ጽንስ ሃሳቦች፣ መምህሩ መማር ማስተማሩ ስለሚሻሻልበት፣ የኃይማኖት አባቶች የእምነቱን አስተምሮ ለምዕመኑ ከማስተማር በዘለለ ስለአገር ሰላምና ህዝብ ደህንነት መጸለይ እንደሚገባቸው ይጠበቃል።
ለአገር ብልጽግና ሁሉም የተሰማራበት መሥክ ስለሚያድግበትና ስለሚሻሻልበት መንገድ ማሰብ፣ ማቀድና መፈፀም እንደሚኖርበት ይታመናል። ነገር ግን አርሶ አደሩ፣ ሃኪሙ፣ መምህሩ፣ የኃይማኖት አባት፣ ተማሪው፣ በጥቅሉ ከሊቅ እስከደቂቅ በማህበራዊ ሚዲያ ሁሉም ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የሚዳክር፣ መሽቶ እስኪነጋ አጀንዳው ፖለቲካ ከሆነ አገር አገር የመሆኗ እውነታ ተጠየቅ ውስጥ የሚገባ ይሆናል።
እዚህ ላይ ስለማህበራዊ ሚዲያ ሳነሳ፤ ለአገር ዕድገትና ብልጽግና፤ ለህዝቦች ነጻነትና ፍትህ ተብለው የሚቀርቡ ጽሁፎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ ይሰማኛል። በተለይ እንደኛ ባሉ ያደሩና የዋሉ አጀንዳዎች ላሉባቸው ህዝቦች የሚቀርቡ ጽሁፎች ተጨማሪ የችግሮቻችን ምንጮች እንዳይሆኑ አብዝቶ ማሰብ ተገቢ ነው። በመሆኑም የሚቀርቡ መረጃዎች ለአንባቢው በትክክለኛ መረጃ እና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል።
በአገራችን ባለው አሁነኛ እውነታ ግን ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያስነሱ፣ አገር ለማተራመስና ለማፍረስ ሆን ተብለው የሚሰራጩ፣ የማህበረሰቡን ለዘመናት ተከባብሮ የመኖር አገራዊ እሴቶችን ሆነ ብሎ ለማጥፋት የሚውተረተሩ አሉ።
“አንድ አይና በአፈር አይጫወትም” እንደሚባለው፤ ያለችን አንድ አገር ናት። ይቺን አገር ደግሞ የተሻለች፣ ለዜጎቿ ምቹ፣ የበለጸገች፣ የተከበረችና የታፈረች የምናደርጋት እኛው ልጆቿ ነን። ይህንን ለማድረግ ሁላችንም ወቅቱ የሚጠይቀውን ዋጋ በመክፈል መክሊታችንን አውቀን በመክሊታችን ልንሠማራ ይገባል። ከዚህ በተቃርኖም የጦርነት አውድማ፣ ሰላም የራቃት ሲኦል ልናደርጋት የምንችለውም እኛው ነን።
ይህንን በሌላ ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፤ ኢትዮጵያን እንደ ፍጥረታዊ አካላችን እናስባት። እጅ፣ እግር፣ አፍንጫ፣ ዐይን፣ ጥርስ፣ ጉበት፣ ሳንባ፣ ወዘተ. የአንድ ሰው፤ ሰው የመሆኑ መዋቅሮች እና ንዑስ አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት የተበታተኑና በየራሳቸው ሕልውና ያላቸው ቅርንጫፎች አይደሉም።
አንድ ላይ ሲሆኑ ዋናውን አካል ወይም ሰውየውን ህያው ፍጡር ያደርጉታል። ነገር ግን አይን የእግርን ሥራ ልሥራ፤ እግር ደግሞ የአይንን ሥራ ልተካ ቢል የሚሆን አይደለም። ልንቀሳቀስ ቢል እንኳን ፍጻሜው ሁለንተናዊ ጥፋት ነው የሚሆነው።
ምክንያቱም የዐይን ተግባር ማየት እና ለአዕምሮ ክፍላችንን የዕይታውን መረጃ ማቀበል ነው፤ እግርም ከዐዕምሮ በሚደርሰው ትዕዛዝ መሰረት የሰውዬውን አካል ይዞ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ነው፡፡ ነገር ግን ዐይን በእግር ቦታ ተተክቼ ልሥራ፤ እግርም በአይን ቦታ ተተክቼ ልሥራ፤ ወይም የራሴንም የሌላውንም ተግባር ልከውን ቢል አይቻለውም፡፡
ዐይን እግር ሆኖ አይራመድም፤ እግርም ዐይን ሆኖ አያይም፡፡ በአንድ አገር ያሉ ሕዝቦችም መክሊታቸው እንዲሁ ነው፡፡ ሁሉም በመክሊታቸው ሊተጉ እንጂ ያለ መክሊታቸው ገብተው ያልሆኑትን ሆነው ለመገኘት መሞከር የለባቸውም፡፡ ይህ ከሆነ እንደ አገር የሚፈለገው ብልጽግና ቀርቶ የማይፈለገው ምስቅልቅል ነው የሚፈጠረው፡፡ ስለዚህ አገር እንደ አገር እንድትቀጥል “የቄሳርን ለቄሳር” መስጠት ያስፈልጋል።
በብዙ ነገር ከዓለም በፊት የነበርን ህዝብ እርስ በእርስ እየተጓተትን ዛሬ ላይ የዓለም ጭራ ለመሆን የበቃነው የቄሳርን ለቄሳር ብለን ሁላችንም በየመክሊታችን ባለመገኘታችን ነው። አንድ ሰው በሙያው ተሰማርቶ እና በተሰጠው መክሊት ተጠቅሞ ከሠራ ውጤታማ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በአንጻሩ ያለሙያው ገብቶ ያለመክሊቱ ልሥራ ቢል ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል።
አሁን ላይ ያለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም ይሄንን የሚገልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የፖለቲካ ተንታኝና አክቲቪስት ሆኗል። የራሱን ኃላፊነት ተገንዝቦ መሥራት ያልቻለ ሁሉ በሌላው ሥራ ገብቶ ሲያቦካ ውሎ ያድራል፡፡ እኔ ምን ተሰጥቶኝ ምን ሠራሁ ከማለት ይልቅ እከሌ ይሄን ማድረግ አልቻለም፤ እከሌ ይሄንን ማድረግ ሳይገባው አደረገ፤ እከሌ ከእከሌ ጋር እንዲህ አይነት ቦታ ተገኘ፤… የመሳሰሉ ወሬና አሉባልታዎች ላይ ተጠምዶ ይውላል፡፡
ይሄን መሰል የራስን ተግባር በወጉ እንኳን ተገንዝቦ ኃላፊነትን ሳይወጡ ወደሌሎች ጣት መጠቆም፤ በማይመለከት ጉዳይ ገብቶ ስምና ግብርን የማጠልሸት አካሄድ አገርና ህዝብን ወደተሻለ ምዕራፍ አያሸጋግርም። ይልቁንም መሥራት ያለብንን ሳንሠራ እና ኃላፊነታችንን ሳንወጣ በመቅረታችን ምክንያት መተኪያ የሌላትን አንድ አገራችንን በገዛ እጃችን እንድናጣ እሰጋለሁ።
ከዚህ የተነሳ የሁሉም ዜጎች የአፍ ማሟሻ እየሆነ የመጣውን የፖለቲካ ጉዳይ ለፖለቲካ ልሂቃን እና ለፖለቲከኞች ትቶ፤ ሁሉም በተሰጠው መክሊት በተሰማራበት መስክ ተግቶ በመሥራት አገሩ ወደ ብልጽግና ማማ የምታደርገውን ጉዞ እውን ማድረግ ይጠበቅበታል።
እዚህጋ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፤ ፖለቲካው ለፖለቲከኞች ይተው ሲባል፤ ፖለቲካው ለፖለቲካው ያለ ተመልካችና ሃይ ባይ ተዋናዮች ብቻ ይተው ማለት፤ ወይም ዜጎች የአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ አያገባቸውም ማለት አይደለም።
ይልቁንም ፖለቲከኞች መረን እንዳይወጡ እና ፈር እንዳይስቱ የሰላና አስተማሪ ትችት መስጠት፣ አቅጣጫ ማሳየት ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ነው። በተመሳሳይም ፖለቲካኞች የፖለቲካውን መንገድ በወጉ ተገንዝበው እና የአገርንና ህዝቡን ተጨባጭ እውነትና መሻት አውቀው የተሻለ ነገር ለመፍጠር መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ እውቀት፣ ቁርጠኝነት፣ የዓላማ ጽናት፣ ለሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ራስን ማስገዛት፣ ከራስ ይልቅ የአገርን የነገ ብልጽግና እውን ማድረግን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡
አገርን ወደ ከፍታ ከማውጣት ይልቅ ወደ ገደል ከሚያንሸራትቱ የሴራና የመጠላለፍ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል መላቀቅ፤ በጋራ ቆሞ ስለ አገርና ሕዝብ ጥቅም መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም ፖለቲከኞች በመካከላቸው ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ አገርና ህዝብን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግር የጋራ ዕራይ ሰንቀው በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል።
አገርን የሚያሻግረው፤ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠው፤ የሚፈለገውን ብልጽግናም እውን የሚያደርገው ይሄው መክሊትን አውቆ መሥራት፤ ኃላፊነትን ተቀብሎ በብቃት መወጣት ነው፤ ያለመክሊትና ሙያ ገብቶ የሌሎችን ተግባር ከመንቀፍ ይልቅ ሁሉም የየራሱን የቤት ሥራ በውጤት መፈጸም ይጠበቅበታል፡፡
መንግሥትም ለዚህ አይነቱ አካሄድ ችግር የሚፈጥሩ አሠራሮችና በአተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ፈትሾ ማረም፤ ከዚህ ባለፈ የሀሳብ ብዝሀነት እንዲጎለብት በማድረግ ለአገሪቱ የፖለቲካ እድገት የአንበሳውን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ይህ ሲሆን ነገ ላይ ተፈጥራ ለማየት የምንናፍቃት አገር ስለመፈጠሯ ጥርጣሪ አይገባንም።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015