ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለውጡን ፣ የለውጡን ኃይል እና አገርን እንደአገር የሚያጠለሹ የተለያዩ ትርክቶች ተፈጥረው በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር ሲደመጡ ተሰምተዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በአገሪቱ እየተካሄደ ስላለለው ለውጥ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
በተለይም ላለፉት አራት ዓመታት በአብዛኛው የምእራቡ ዓለም መንግስታት፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሀን በስፋት በተሳተፉባቸው የአገርና የመንግስትን ገጽታ የማጠልሸት ዘመቻዎች፤ አገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንድታልፍ ተገዳለች።
እነዚህ ዘመቻዎች በዋነኛነት በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ያልተመሰረቱ፤ የባለጉዳዩን ሕዝብና መንግስት የሚያገሉ፤ እራሳቸው ከሳሽ፣ ምስክርና ዳኛ ሆነው የሚቀርብበት፤ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ዓላማ የተሸከሙ እንደነበሩ ለመላው ሕዝባችን የተሰወሩ አልነበሩም።
ዘመቻዎቹ በአገሪቱ ሰሜን ክፍል ለሁለት ዓመታት በተደረገው የእርስ በርእስ ጦርነት ወቅት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሰው የነበር ሲሆን፣ የአገሪቱን አንድነት ጨምሮ አገረ መንግስቱን ከፍ ያለ ስጋት ውስጥ ከቶ እንደነበር አይረሳም።
በተለይም አገረ መንግስቱን በተለያዩ አጣብቂኝ ውስጥ በመጨመር የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሄዱበት ርቀት ምን ያህል እንደነበር ለማንም የተሰወረ አይደለም፣ ስለራሳቸው ገለልተኝነት መሽቶ እስኪነጋ የሚደሰኩሩ፤ በሙያዊ ስብእናቸው ለራሳቸው ከፍያለ ከበሬታ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ሳይቀሩ የዘመቻው አካል ሆነውም ታይተዋል።
እነዚህ አካላት በተለይም የእርዳታ እህል አቅርቦቶችን በተመለከተ በጦርነቱ ወቅት ሆነ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የተለያዩ ዘገባዎችን በማውጣት፤ በአገርና በመንግስት ላይ ጫናዎችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል፤ እየተንቀሳቀሱም ነው።
በጦርነት ወቅት ስለነበረው እውነታ በርግጠኝነት እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ገለልተኛ አካል ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን የማጣራት ስራዎችን ጊዜ ወስደው መስራት እንደሚኖርባቸው ይታመናል። ከዚህ ውጪ የሚደረጉ የማጣራት ስራዎች በራሳቸው ሙሉ ሆነው መተማመንንና ተጠያቂነትን ማስፈን አይችሉም ።
በርግጥ ከጦርነቱ ቀደም ባለው ጊዜ ሆነ፤ በጦርነቱ ጊዜና በኋላ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የእርዳታ አቅርቦቶችን በራሳቸው ተቋማዊ መዋቅሮች፤ ከአካባቢ አስተዳደሮች ጋር በመሆን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
መንግስትም ካለበት ኃላፊነት በመነሳት የእርዳታ አቅርቦቶቹ ለተረጂው ህዝብ በአግባቡ መቅረባቸውን በአስተዳደር መዋቅሮቹ በኩል በጠንካራ ዲስፕሊን ለመቆጣጠር ሰፊ ጥረቶችን አድርጓል።
ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላም በጦርነቱ አካባቢዎች ሆነ በሌሎች የተለያዩ የአገሪቱ ስፍራዎች በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ችግር ውስጥ ለወደቁ ዜጎች ለጋሽ ተቋማት የእርዳታ አቅርቦቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የክልል እና የፌደራል መንግስታትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ”ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል መርህ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቹ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ ዛሬም እያደረገ ነው። ካለው የመረዳዳት የቆየ ባህል አንጻር ወደፊትም ያደርጋል።
እንደ አገር ስኬታማ እየሆንበት ያለው የበጋ እርሻ ስንዴ ከፍያለ አስተዋጽኦ እንደነበረው ማስታወስም ተገቢ ነው።ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ መንግስት በምግብ እህል እጥረት ሊያጋትሙት የሚችለሉ የአደጋ ተጋላጭነቶችን ለዘለቄታው ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የእርዳታ አቅርቦቶች ህገወጥ በሆነ መንገድ ላልተገባ ተግባር ውለዋል የሚሉ ክሶች ከምዕራባውያኑ የእርዳታ ተቋማትና የመገናኛ ብዙሀኖቻቸው መደመጥ ከጀመሩም ውለው አድረዋል። ክሶቹንም ተከትሎ ያልተገቡ ውሳኔዎች ሲተላለፉ እየተስተዋለ ነው።
የእርዳታ ተቋማቱ የእርዳታ አቅርቦቶችን ወደ ተረጂው ሕዝብ በራሳቸው አደረጃጃት እያቀረቡ ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ መንግስትን በተናጠል ለችግሩ ተጠያቂ ማድረጋቸው ግርታን የሚፈጥር ነው።
መንግስት ክሶቹን ለማጣራት ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ እየገባ ባለበት ሁኔታ፤ ለማጣራቱ ሂደት ተአማኒነት ከኮሚቴው ጋር ተባብሮ ከመስራት ይልቅ ተገቢውን የማጣራት ሂደት ያሳለፈውን ሪፖርት ይፋ ለማድረግ መቻኮላቸው የሪፖርቱን ተአማኒነት በራሱ የሚፈጥረው ሆኗል።
በከፍተኛ የህዝብ ውክልና ወደ ስልጣን የመጣው የአገሪቱ መንግስት ፤ ከአገርና ከህዝብ የሚበልጥ አጀንዳ ፤ የፖለቲካ መሰረትም የለውም፤ እስካሁን በመጣባቸው መንገዶችም ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ የሄደው የአገር ሉአላዊነትንና የህዝቦችን ሁለንተናዊ ደህንነት ነው።
በምግብ እራስን ለመቻል እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ርብርብ፤ በእርዳታ ጠባቂነት የወየበውን አገራዊ ክብር ድምቀት በመመለስ ፤ ዜጎች በልበ ሙሉነት ቀና ብለው የሚሄዱበትን ጠንካራ መንፈስና የስነልቦና መሰረት ለመጣል ነው።
ለዚህም አገርን ወደ ብልጽግና ሊወስድ የሚችል ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሪፎርሞችን በስፋት በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ከገባ ውሎ አድሯል። እያስመዘገባቸው ያሉ ውጤቶችም ተስፋ ሰጪ ከመሆን አልፈው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና እየተሰጣቸው ነው።
ለዚህም በበጋ የስንዴ እርሻ በተገኛው ስኬት አገር በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ከውጪ ስታስገባው የነበረውን የስንዴ ምርት በማቆም የዓለም የስንዴ ገበያን መደባለቅ የምትችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
አገር ከጠባቂነት ወጥታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርጉም ባለው መልኩ በምግብ እህል እራሷን ለመቻል የጀመረቻቸው ጥረቶች በዚህ መልኩ ፍሬ ማፍራት በጀመረበት ማግስት የመንግስትን ስም ባልተገባ መልኩ ለማጠልሸት የሚደረጉ ጥረቶች ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው።
ጠባቂነትን በመጠየፍ ፣ ከዚህ የአገርና የህዝብን ክብር ከሚያሳንስ እውነታ አገርና ህዝብ ለመታደግ ሌት ተቀን የሚሰራን መንግስት በእርዳታ አቅርቦቶች ዙሪያ ለመክሰስ መሞከር፣ የመንግስትን ስኬቶች ለማጠልሸት ከሚደረጉ የፖለቲካ ሴራዎች ተለይቶ የሚታይም አይሆንም !።
በርግጥ ካለንበት አገራዊ ተጨባጭ እውነታ አንጻር ይህንን ክስ ሊሸከሙ የሚችሉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሊኖሩ ይችላል፤ ይሕም ቢሆን መንግስትን የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ጠንካራ የማጣራት ስራ የሚጠይቅ ነው።
ከመርደቂዮስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015