የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከትናንት እስከ ዛሬ የቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃያላን አገራት ተፅዕኖ ሳይላቀቅ ኖሯል:: በተለይም በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እየተለወጠ ያለውን ዓለም አቀፍ ስርዓት ተከትሎ የቀጣናው ጂኦ ፖለቲክስ ላይ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ ነው:: እንደ ሰውዲ አረቢያ እና ኢራን የመሳሰሉ የመካከለኛ ምስራቅ ቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት፣ እንደ ዩ.ኤስ.ኤ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ አውሮፓ ህብረት ያሉ ዓለም አቀፍ ተዋናዮችም በአካባቢው ያላቸውን ተፅዕኖ ለማሳደግ፣ የኃይል የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የአካባቢውን ሀብት ለመቀራመት የሚያደርጉት ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል::
ለዚህም ነው ቀይ ባህር እና ባብኤል ማንደብ አካባቢ ከዚህ ቀደም የጦር ሰፈር ከገነቡት አገራት በተጨማሪ አዳዲስ አገራትም የጦር ሰፈራቸውን ለመገንባት ደፋ ቀና እያሉ ያሉት:: ይህ ቀጣና ኑክሌይርን የታጠቁ ሁሉም ኃያላን አገራት የጦር ሰፈራቸውን የሚገነቡበት አካባቢ ከሆነ ሰነባብቷል:: አብዛኞቹ የኑክሌር ኃይል የታጠቁ አገራት የጦር ሰፈር በዚህ አካባቢ ገንብተዋል:: በቅርቡ ሩሲያም ከሱዳን ጋር በመነጋጋር በቀይ ባህር ላይ የጦር ሰፈር ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯ ተሰምቷል::
እነዚህ አካባቢዎች ለኢትዮጵያ ካላቸው ቅርበት አንጻር በአካባቢዎቹ የሚካሄዱ ኩነቶች ለኢትዮጵያ የራሱ ትርጉም አለው:: በአካባቢው አገራት የሚሆኑ ነገሮች ኢትዮጵያ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የራሱ ጫና የሚያስከትል ነው:: ይህ ሁሉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ:: የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምን ያስቀደመ መሆን አለበት:: ለዚህም አገራዊ ክብርን ማስጠበቅ፣ ጠላትን መቀነስ እና ወዳጅ ማብዛት አስፈላጊ ነው::
የቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገራት እሽቅድድም ሜዳ የሆነው ምስራቅ አፍሪካ በተለይም አፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ሁል ጊዜም ከኢትዮጵያ ከዲፕሎማሲ አጀንዳዎቿ መካከል ዋነኛው አድርጋ ልትይዘው ይገባል:: ኢትዮጵያ የቀጣናውም ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት አስገብታ መንቀሳቀስ ያለባት ለራሷ ብሄራዊ ጥቅም እና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ስትል ነው:: በዚህ ረገድ የተሰሩ መልካም ጅምር ስራዎች ቢኖሩም አሁንም ሊሰሩ የሚገቡ በርካታ ስራዎች አሉ::
ለምሳሌ፣ በጎረቤት አገሮች ሰላም ለማውረድ ኢትዮጵያ ጥረት እና የጎረቤት አገራትን የጸጥታ ተቋማት ለማጠናከር ጥረት ስታደርግ ቆይታለች:: በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሱዳን ሰላም ለማምጣት ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች:: በዚህም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አድናቆት ተችሯታል:: አሁንም ጥረት እያደረገች ነው:: እነዚህ ጥረቶች ለኢትዮጵያ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው::
የኢትዮጵያን ጥቅም የማይጎዳ እና ኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት የማያደናቅፍ እስከሆነ ድረስ ከየትኛውም አገር ጋር መስራት ያስፈልጋል:: ከምዕራቡ ጎራ ሆነ ከምስራቁ ጎራ አገራት ጋር ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ማድረግ አለባት:: የአገራቱ የፖለቲካ ርዕዮት ጉዳይ ኢትዮጵያን ሊያስጨንቃት አይገባም:: ኢትዮጵያ የየትኛውም ርዕዮት እስረኛ መሆን የለባትም::
ዋናው ጉዳይ የአገር ውስጥ ጥቅም በኃያላኑ እንዳይጠመዘዝ ጥንቃቄ ማድረጉ ላይ ሊሆን ያስፈልጋል:: ለዚህም የሚቀርቡ ብድሮች እና እርዳታዎች እንደ ቅድመ ሁኔታ በመጠቀም አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይሻል:: በተለይም ኃያላን አገራት እና የፋይናንስ ተቋማት የሚያቀርቧቸው ምክረ ሀሳቦች በጥርጣሬ መመልከት ጠቃሚ ነው:: እ.አ.አ በ1980ዎቹ እና ዘጠናዎቹ የብሪተን ውድስ ተቋማት (የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ( አይ ኤም ኤፍ)) ስትራክቸራል አጀስትመንት በሚል ሰበብ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ ያደረሱት አይነት ቀውስ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይሻል::
ከምንም በላይ ግን ዲፕሎማሲው የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ሲቻል ነው:: የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ካልተቻለ ለውጫዊ ጥቃት የመጋለጥ እድል ይሰፋል:: በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው::
በዚህ ረገድ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በንግግር እና በውይይት ለማስቆም የተሄደበት ርቀት የሚያስደስት ነው:: የሰሜኑ ችግር ከተፈታ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን ችግርም በንግግር እና በድርድር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት እስኪያመጡ መቀጠል አለበት:: ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረውን አገራዊ ምክክር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የዲፕሎማሲ ስራው ፍሬ እንዲያፈራ የሚያበረክተው ሚና የላቀ ነው::
ውስጣዊ አንድነትን ከማጠናከር ጎን ለጎን ኢኮኖሚያዊ ስኬት ለዲፕሎማሲው መቃናት ፋይዳው ከፍ ያለ ነው:: ጠንካራ ኢኮኖሚ የሌለው አገር እሳት የላሱ ዲፕሎማቶችን በመላው አገር ቢያሰማራ የሚፈልገውን ለማሳካት ሊቸገር ይችላል:: በኢኮኖሚ ጡንቻ ያልተደገፈ ዲፕሎማሲ ከንቱ ድካም ነው:: በመሆኑም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ረገድ ባለፉት ጊዜያት ሲታይ የነበረውን በጎ ጅምሮችን ዳግም ለማሳካት መንቀሳቀስ ይገባል:: በተለይም በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች እድገት ለማስመዝገብ የተጀመሩ ስራዎች ሊቀጥሉ ይገባል::
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ኃያል አገር ናት:: ይህ በተለያዩ ምክንያቶች የመጣ ኃይል ነው:: ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ኢኮኖሚውን ለማንሰራራት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክሮ ከቀጠለ ቀጣናዊ ኃያልነቷን ወደ አህጉራዊ ኃያልነት የማታሳድግበት ምክንያት የለም:: ከአፍሪካ አህጉር አልፎ መካከለኛ አቅም ያላት ኃይል፤ እንዲሁም በቀይ ባህር አከባቢ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኃይል የመሆን እድሏ ከፍ ያለ ነው::
ውስጣዊ አንድነት ከሌለና ኢኮኖሚ አቅም ከሌለ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት ያላት ተሰሚነት አነስተኛ ይሆናል:: ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት ከሌለ የአገርን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ ኃያላንን ላለማስቆጣት መጨነቅ ይመጣል:: የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ሳይሆን የኃያላን ፍላጎት አስፈጻሚ እንሆናለን:: በመሆኑም ከምንም በላይ ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማፈርጠም በትኩረት ሊሰራ ይገባል:: ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖና ተደማጭነት ማግኘት፤ ዲፕሎማሲዋንም ማጠናከር ትችላለች::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015