አሲዮ ብለን፣ የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ስንል ገጥመን፣ በጥሌ ዜማ፣ በዘሪቱ ጌታሁን እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፣ በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ ብለን ተምነሽንሸንና የአዲስ ዓመት ብስራታችንን መስከረምን ሸኝተን፣ ከገናና ከፋሲካ፣ ከአረፋና ከረመዳን በረከት ተቋድሰን፣ በኑሮ ውድነትና በኮሮና ስጋት ተይዘን፣ በጦርነትና በሞት ስጋት ተከበን እየተንገዳገደን እንሆ ሰኔ ላይ ከተምን፡፡
ጊዜ ህይወት ነው..ጊዜ ስኬት ነው፡፡ ጊዜ ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን በጎውን እንድናደርግ እድል የሚሰጠን አጋጣሚ ነው፡፡ እነሆ በዚህ የጊዜ ምህዋር ላይ ተረማምደን የክረምት ሁሉ አባት በሆነው ሰኔ ላይ ቆመን ክረምትን ለበጎነት በሚል እሳቤ እራሳችንን እያዘጋጀን ነው፡፡ እርግጥ የዘንድሮው ክረምት የተፈጥሮን ህግ የሻረ በሚመስል ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ዓመቱን ሙሉ ከበጋ የተኳረፍንበት ጊዜ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
በትላንት፣ ዛሬ እና ነገ ምልልስ ውስጥ ዘመን ይሄዳል ዘመን ይመጣል፡፡ በዚህ ሁሉ የጊዜ ሂደት ውስጥ ክረምትን ታከው የሚመጡ በጎ እና እኩይ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እንደባህሪው ክረምት ነፍራቃ ነው፡፡ ምድርን በጥቁር ጉም ሸፍኖ፣ በነጎድጓድና በመብረቅ ታጅቦ ነፍስን የሚያስጨንቅ የወቅቶች ነጭናጫ ነው፡፡
ጊዜ ህዝብ ለአገር፣ አገር ለትውልድ የምትሰጠው የቅብብሎሽ በትር ነው፡ በጊዜአችን ውስጥ በጎ ነገር ስናጣ፣ ጊዜአችንን ተጠቅመን ለራሳችንም ሆነ ለሌላው መልካም ነገር ማድረግ ሲያቅተን ያኔ ዘመን የሸመነው ሰውነታችን እያረጀና እየጃጀ እንደ ልብስ እናልቃለን፡፡ ከዛም ከእድሜ አመሻሽ ላይ ቆመን ‹ወይኔ እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ› ብለን እንቆጫለን፡፡ ከዚህ መቆጨት በኋላ ራሳችንን የምናጽናናበትትን እውነት ፍለጋ ብዙ እንተክዛለን፡፡
ሰኔ የክረምት መግቢያ በር ነው፡፡ ክረምት በሰኔ በር ገብቶ ነው እስከ አዲስ ዓመትና ከዛ በኋላ እስካለው ጊዜ የሚዘልቀው፡፡ በእኚህ በተለመዱ የክረምት ወራት ውስጥ ቤት የሌለው ብቻ አይደለም ቤት ያለው ሳይቀር በክረምት ለበቅ ይሸነቆጣል፡፡ እናም ያን ሽንቆጣ ከራሳችንም ሆነ ከወገናችን ላይ ለማንሳት ክረምትን ታከው ለሚመጡ ስቃዮች በጎ ስራን በመስራት ተገን መሆን ይቻላል፡፡
ሰኔ ዝርክርክ ብሎ የሚያዝረከርከን የጸጋና የመከራ ጌጣችን ነው፡፡ ወፍራም በመልበስና የላመ በመብላት አንሸሸውም ምክንያቱም ወፍራም መልበስ የማይችሉና የላመ ለመብላት አቅም የሌላቸው ወገኖች አሉንና ነው፡፡ ሰውነት ስለ ሌላው መታመም ነው፡፡ ሰውነት በሌሎች ስቃይ መሰቃየት ነው፡፡ ክረምት ደግሞ ስለሌላው እንድንታመምና እንድንሰቃይ የሚያደርግ ጥሩ አጋጣሚያችን ነው፡፡
ምክንያቱም በክረምት ቤት የሌላቸው፣ በክረምት መሸሸጊያ ያጡ ነፍሶች ብዙ ናቸውና ነው፡፡ ምንያቱም በክረምት ቤታቸው ዝናብ የሚያስገባ፣ በድህነት መውደቂያ ያጡ አሉና ነው፡፡ ክረምት ለሰው ልጅ እንባና ሳቅ ነው፡፡ የሞቀ ቤት ያለን እኔና እናንተ እንደምንስቅ ሁሉ ክረምት በመጣ ቁጥር የሚያለቅሱ፣ መግቢያ የሚያጡ ነፍሶች ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ክረምት ለአገራችን በጎውን እንድንሰራ እድል ከሚሰጡን አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ለበጎ ተግባር ጥሩ አጋጣሚም ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ለበጎ ተግባር ሆነ ለአገር መልካም ለማድረግ ሁሉም ጊዜአቶች እኩል ቢሆኑም የክረምትን ያክል አገር ወገን የሚረዳበት ጊዜ አለ ብዬ አላስብም፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ክረምት ሲመጣ ይዟቸው የሚመጣው ብዙ ችግሮች ስላሉ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ጎርፍ፣ የአካባቢ መጥለቅለቅ፣ የመንገድ መበላሸት፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በቂና አስተማማኝ መኖሪያ ስለሌላቸው በክረምቱ መቸገር የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እንግዲህ ክረምትን ለበጎነት የሚለው መነሻ ሃሳቤ ትርጉም የሚያገኘው እዚህ ጋ ነው፡፡
እንደሚታወቀው አገራችን ብዙ ድሆች የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ የእኛን እርዳታ፣ የእኛን ድጋፍ የሚፈልጉ አያሌ የማህበረሰብ ክፍሎች እዛም እዚም አሉ፡፡ ክረምት ሲሆን ደግሞ ይሄ ማህበራዊ ምስቅልቅል እጅጉን ይጨምራል፡፡ በዚህም መሰረት ለወገናችን የምንደርስለት እና አለኝታነታችንን የምናሳይበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን፡፡
በጎ መሆን ከኪሳችን የምናወጣው ሳይሆን ከልባችን የምናወጣ ነገር ነው፡፡ በዙሪያችን የእኛን በጎ መሆን የሚሹ ብዙ ማህበራዊ ችግሮች አሉ፡፡ አገር የምትቆመው የአንዱን ችግር አንዱ የኔ ነው ብሎ ሲነሳ ነው፡፡ ዜግነት ትርጉም የሚያገኘው የወገኖቻችንን ስቃይ መሰቃየት ስንችል ነው፡፡ ለራስ ብቻ በማሰብ ውስጥ፣ ለራስ ብቻ በመኖር ውስጥ ዜግነት የለም፡፡
አገር ማለት ምንድነው ብሎ ለጠየቀ የመልካም ልቦች ህብረት ነው የሚል መልስ ያገኛል፡፡ በእውቀታችን፣ በጉልበታችን፣ በገንዘባችን ለአገርና ወገን አለኝታ መሆን ካልቻልን እኛ ምንም ነን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ክረምት ይዞብን የሚመጣው ማህበራዊ ቀውስ የታወቀ ነውና ከወዲሁ መረዳዳታችንን ማጠንከር ይኖርብናል፡፡
ክረምት በመጣ ቁጥር የምንሰማቸው በርካታ ሞቶችና የንብረት ውድመቶች አሉ፡፡ ወቅቱን ባልጠበቀው በዘንድሮው ክረምትም ተመሳሳይ ነገር ተስተውሏል፡፡ የባሰው ክረምት ሰኔን ታኮ የሚመጣው ከፊታችን ያለው ወራት በመሆኑ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ መሰል ችግሮችን እንዳናስተናግድ እድል ይፈጥርልናል፡፡
በጎ መሆን የሰውልጅ ሁሉ ባህሪ ነው፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ በጎነትን በሚመለከት ብዙ እየሱሳዊ መልዕክቶች ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ በኤፌሶን መልዕክት ላይ እንዲህ የሚል መልዕክት አለ ‹በጎውን ስራ እንድንሰራ በክርስቶስ እየሱስ ተፈጠርን› የሚል፡፡ መቼም የትም የሰው ልጅ ለሌላው እንዲኖር ነው የተፈጠረው፡፡
በጎነታችንም በዙሪያችን ካሉ የሚጀምር ነው፡፡ በጎነታችን ከሰፈርና ከጎረቤት የሚጀምር ነው፡፡ ክረምቱ ስቃይ እንዳይሆንባቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖቻችንን ችግሮቻቸውን ጠይቆ በመረዳት መፍትሄ መስጠት ሰኔን የምንበቀልበት አንዱ መንገድ ነው፡፡
ቤት ለሌላቸው ቤት በመስራት፣ ቤታቸው ያረጀባቸውን ቤታቸውን በማደስ፣ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖቻችንን ክረምቱን የሚያልፉበትን መንገድ በመፍጠር ክረምቱን በበጎ ስራ ማሳለፍ እንችላለን፡፡ ክረምት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተለይ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡
በዛው ልክ ከተጠቀምንበት ክረምት ጸጋችን ነው። የሚያዘንብልንን ዝናብ ለበጎ ነገር የመጠቀም አቅሙና ህብረቱ ካለን ከነበርንበት የድህነት ዝቅታ ከፍ ማለት ይቻለናል፡፡ በዓለም ላይ ቀዳሚ ያደረገንን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ያሳካነው እኮ በክረምት ጸጋ ነው፡፡
ከራሳችን አልፈን አፍሪካን ያማከለ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ያደረግነው እና እያደረግን ያለነው እኮ በሰኔ ጉርምርምታ ታጅበን ነው፡፡ የታላቁን ህዳሴ የውሀ ሙሌቶች ያስተናገድነው እኮ በክረምት ኃይል ነው። እጆቻችንን ለልማት፣ ልቦቻችንን ለመልካም ስራ ያተጋነው እኮ ክረምት ስለመጣ ነው፡፡ ዘንድሮም ብዙ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ያለነው እኮ በክረምት ጸጋ ነው፡፡
እንደዚሁም ደግሞ የአቅመ ደካሞችን ቤት አድሰን ለመመረቅና ለመመስገን የተነሳነው እኮ በዚህ ጊዜ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የመኖር ዋስትናችን የሆነው የአርሶ አደሩ መሬት የተሻለ ምርት ይይዝ ዘንድ ክረምት እጅግ አስፈላጊያችን ነው፡፡ አብቅለን ለመብላትና እያሰቃየን ካለው የኑሮ ውድነት ተላቀን ጥሩ ኑሮ ለመኖር ክረምት ዋስትናችን ነው፡፡
ከዚህ በተለየ ደግሞ አዲሱን ዓመት በደስታና በፍቅር እንድንኖር ክረምት ያሻናል እንዴት ላለኝ እንዲህ እለዋለው..ሁሉም አዲስ ዓመት የሀምሌና የነሀሴን ክረምት ጠጥተው ያማሩና የቆነጁ ናቸው፡፡ የምንናፍቀው መስከረም እንኳን አምሮና ተውቦ የምናገኘው ከፊቱ ባሉት የክረምት ወራት ተደግፎ ነው፡፡
ዓለም ላይ መለያችን የሆነው፣ ጳጉሜን ተንተርሶ ነፍስ የሚዘራው አደይ አበባ እኮ የሀምሌና የነሀሴ ጽንስ ነው። በዓመት አንድ ጊዜ ብቅ ብላ የምትሰወረው የመስቀል ወፍ እኮ ጎጆዋን የምትቀልሰው በመስከረም ተስፋ ነው..ተስፋዋን የሰጣት ደግሞ ክረምት ነው፡፡ እናም ክረምት ከተጠቀምንበት ጸጋችን ነው ካልተጠቀምንበት ደግሞ መከራችን ይሆናል፡፡
ከእኛ የሚጠበቀው በክረምት ጸጋ እየተጠቀምን ችግሩን በጋራ ማሸነፍ ነው፡፡ ክረምት የፍቅር ወቅት ነው። ከመቸውም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት መዋደድና መፋቀር ይኖርብናል፡፡ በክረምት ጠብና ቁርሾ የማይታሰብ ነው። በክረምት ሁሉም ጦረኞች ጦር የሚጥሉበት፣ ይቅር ለእግዜር ተባብለው ወደ ስራ የሚገቡበት ጊዜ ነው፡፡
በክረምት እልሀኞች እልሃቸውን ትተው ወደ ልማት የሚሰማሩበት ነው፡፡ ምክንያቱም የክረምት ጸጋ በዓመት አንዴ ስለሆነ ነው፡፡ ቤታችንን በጋራ ሰርተን፣ ፍቅራችንን በጋራ አለምልመን ቀጣዩን የበጋ ወራት በደስታና በአንድነት እናልፍ ዘንድ ዛሬን መረዳዳት ግድ ይለናል፡፡ መንግስት ይሄን የክረምት ወቅት ለብዙ የልማት ስራዎች መጠቀም አለበት፡፡ እኛም ዜጎች በዚህ ክረምት ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች በጎ ስራ በመስራት ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡
ክረምትን በጦርነት ያሳለፈ ማህበረሰብ ቀጣዩ ጊዜው የስቃይ ጊዜ ነው የሚሆነው፡፡ በክረምት ያላበቀለ፣ በክረምት ይቅር ያልተባባለ ጠበኛ መጪው ጊዜ ጥሩ አይሆንም፡፡ በክረምት ቂማችንን ካልተውን፣ በክረምት ሞፈር ካልጨበጥን መጪው ጊዜ ይበረታብናል፡፡ እናም ክረምትን ለይቅርታና ለልማት፣ ለመረዳዳትና ለመተጋገዝ እናውለው፡፡
አገር መውደድ ሰውን መውደድ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት ከሚገለጽባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ አስቸጋሪ ጊዜዎችን በጋራ ማለፍ ነው፡፡ ከፊታችን ያሉ ጊዜዎች መልካም የሚሆኑት ዛሬ ላይ በምናደርገው ድርጊት ነውና ከነውር ወጥተን ሊጠቅመን በሚችል በጎ ስራ ላይ ማሳለፍ ችግሮቻችንን የምናሸንፍበት መንገድ ነው፡፡
ልባችንን ለበጎ ምግባር ካስገዛን ክረምት አስቆን የማያልፍበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ክረምት መከራ የሚሆነው የሌላውን ጩኸት ላለመስማት ጆሯችንን ስንደፍን ነው፡፡ ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ ከመቸውም ጊዜ በላይ ክረምት ስቃይ የሚሆንባቸው ብዙ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ከመከራው አንጻር ጭራሽ ክረምት ባልመጣ ብለው የሚመኙ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ይሄ ደግሞ ክረምት ምን ያክል ችግረኛው ማህበረሰብ ላይ እንደሚበረታ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ለወገናችን ልንደርስለት የሚገባው፡፡ በእንዲህ ያለው ወቅት ነው አጋርነታችንን ልናሳይ የሚገባን፡፡ በክረምት የሚያለቅሱ አይኖች፣ የሚባቡ ልቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ ዙሪያችንን ቃኘት ማድረግ ብንችል ብዙ ችግረኛ ሰዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡
በክረምት ቤታቸው ዝናብ እያስገባ የሚሰቃዩ እናቶች ጥቂት አይደሉም የነሱን እንባ ማበስ ደስታው ምን ያክል እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ በክረምት መጠጊያ አጥተው ጎዳና ላይ እትት የሚሉ ችግረኛ ወገኖች አሉ እነሱን መታደግ በረከቱ ምን ያክል እንደሆነ አይጠፋንም።
በክረምት መንገዶች በጎርፍ ይጥለቀለቃሉ፣ ይቦረቦራሉ፣ ጉምና ጭጋግ ስለሚበዛ በዚህም የትራፊክ አደጋ ከፍ ይላል፡፡ እኚህ ሁሉ ክረምት ወለድ አገራዊና ማህበራዊ ችግሮቻችን እልባት የሚያገኙት በእኛ መልካም ተግባር ነውና ትብብራችን እንዳለፈው ጊዜ አደጋዎች እንዳይፈጠሩ ቅድመ ዝግጅት ስለሆነ ልንበረታ ይገባል፡፡
በክረምት የመሬት መንሸራተት አደጋ ያይላል፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር እንዲህ አይነቱ አደጋ የተለመደ ነው፡፡ ይሄን አይነቱን አደጋ ለመቅረፍ ከአሁኑ የእርከን ስራዎች ቢሰሩ መልካም ይሆናል፡፡ አምና በዚህ ሰዐት የክረምትን መግባት ተከትሎ የተከሰቱ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች አሉ፡፡
እነዛን አደጋዎች ለመከላከል ሁላችንም ባለንበት ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ግድ ይላል፡፡ ክረምትና የትራፊክ አደጋም እንደዚሁ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሆነው ከትላንት ዛሬ የዘለቁ ናቸው፡፡ የመሬት መንሸራተት ስለሚኖር በዛው ልክ የትራፊክ አደጋው ይጨምራል፡፡
ጉሙና ጭጋጉ ሲጨመርበት ደግሞ ወትሮ ሀይ ባይ ያላገኘው የትራፊክ ችግራችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ለከፋ አደጋ ተጋላጭ ነው የሚያደርገን፡፡ እግረኛም ሆነ አሽከርካሪ መጪውን ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት ከወዲሁ ለራሱ ዋስትና ቢሰጥ እንደአገር የሚደርስብንን ክስረት መቀነስ እንችላለን፡፡
በሁሉም ነገር ለአገራችን ዘብ የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በልማቱም በሰላሙም በእርቁም ለአገራችን ውለታ የምንውልበት ሰሞን ላይ ነን፡፡ ብልህ ሰው ነገውን ዛሬ የሚሰራ ነው፡፡ ብልህ ሰው አስቸጋሪ ጊዜዎችን በመተባበር የሚያልፍ ነው፡፡ እኛም በቀና ልብ በበጎ ስራ ነጋችንን ዛሬ ማነጽ ይቻለናል፡፡ እንዲህ አይነቱ የመተባበር መንፈስ በግለኝነት የደበዘዘችውን ኢትዮጵያ የሚያነጻ ነው፡፡
አስቸጋሪ ጊዜዎች ለብቻ የሚታለፉ አይደሉም። በተለይ አሁን ያለንበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን የሚፈልግ ነው፡፡ መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን በመልካም ልብ የምናከናውናቸው ተግባራት ብዙ ናቸው፡፡ ከወዲሁ ተጋግዘን እልባት ካልሰጠናቸው በቀር ክረምትን ተከትለው የሚመጡ ማህበራዊ ቀውሶች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡
ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ እንደሚባለው ክረምት ወለድም ሆኑ በጋ ወለድ ችግሮቻችን በአንድነት ከተነሳንባቸው የሚረቱ ናቸው፡፡ አገር በመረዳዳት ውስጥ ውብ ናት፡፡ ለብቻ ቆመን፣ ለብቻ አስበን የምናሳካው አንዳች ነገር የለም፡፡ የኔ ችግር የማህበረሰቡ ችግር ነው። የአንተ ችግር የኔና የሌላው ሰው ችግር ነው፡፡ እናም በአንድነት ወደበጎነት..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015