” ሰዎች ወደዚህች ዓለም ሲመጡ አራት ዝንባሌዎችን ይዘው ይመጣሉ። እነርሱም የምጣኔ ሃብት ዝንባሌ (Homo Economicus)፣ የኃይማኖተኝነት ዝንባሌ (Homo Religious)፣ የፖለቲከኛነት ዝንባሌ (Homo Politicus) እና የንድፈ-ሃሳብ ዝንባሌ (Homo Theoreticus) ናቸው። ስለዚህ የአንድ መምህር ተግባሩ ዝንባሌዎቹን ከተማሪው ውስጠ-ልቡና ፈልፍሎ ማውጣት ይሆናል ”
ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚል ርዕስ በ1956 ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይ ስለ ትምህርት አስፈላጊነትና ፋይዳ ያስቀመጡት ሃሳብ ነው። ከላይ በመንደርደሪያነት ያነሳኋቸው የሊቃውንቱ ሐሳብ የመምህር እና የትምህርትን ወሳኝነትና ከፍተኛ ፋይዳ የሚያሳይ፤ የአንድ አገር እድገት ቁልፍ ያለው በትምህርት ዘርፍ ላይ መሆኑንም የሚጠቁም ነው።
ባለፉት ሁለት አስርቶች በአገራችን ለትምህርት ተደራሽነት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሰራ ይነገራል። ለአብነት በአሁን ወቅት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ሃምሳ ሊደርሱ ተቃርበዋል። በግሉ ዘርፍም 150 ስለመድረሳቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የተሰራው ስራ ከጥራት አንጻር ሲመዘን ግን ውጤቱ አንገት የሚያስደፋ ስለመሆኑ በተጨባጭ የሚታይ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአንድ ወቅት፣ ስለ ትምህርት ጥራት “…የትምህርት ተደራሽነት ማደጉን ሳንረሳ፣ ዘርፉ በእጅጉ በመጎዳቱ ላይ ግን ምንም ክርክር አይኖርም፡፡ በመሠረታዊነት ትምህርትን ማዳረስ አስፈላጊ ቢሆንም፤ ነገር ግን በቂ የትምህርት መሣሪያ፣ አስተማሪና የትምህርት አሰጣጥን ሳይፈጥሩ ሕንፃ እየገነቡ ብቻ ተማሪዎችን መሰብሰብ ችግሩን እንዲፈጠር አድርጓል ” ሲሉ መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱ የቁልቁለት መንገድ ከታች ከመሰረቱ ጀምሮ እስከ ላይ እንደካንሰር የተዛመተ ነው። የስርዓቱ አካሄድ ብዛትን ተከትሎ የጥራትን መንገድ በመሳቱ፤ በብርቱ ሲታመም እና ሲሰቃይ ቆይታል፡፡ ዛሬም የትምህርት ዘርፍ ከገባበት ጥልቅ የችግር ጉድጓድ፣ ከገጠመው ውስብስብ ችግር መውጣት አቅቶታል። ይሄንኑ ለመረዳት ደግሞ ብዙ ርቀትን መመለስ ሳይፈልግ የቅርቡን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስደንጋጭ ውጤት ማስታወስ በቂ ነው፡፡
ለፈተናው ከተቀመጡት 980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 30 ሺህ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘታቸው የሚታወስ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር በብሔራዊው ፈተና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የፈተና ስርቆት እና ኩረጃን ለማስቀረት የተከተለው አሰራር ደግሞ ተሸፋፍኖ የሰነበተውን ሃቅ አደባባይ አውጥቶታል፡፡
በርግጥም በ12ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገበው ውጤት እንደ አገር የቱ ጋር እንዳለን የሚጠቁም ነው። ለችግሩ ቀጣይ መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችል እድል የፈጠረ ጭምር ነው። በተለይ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማንቂያ ደውል እንደሚሆን ይታመናል።
ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ቀደም ሲል በጠቀስኩት መጻፋቸው፤ “ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው፣ ይህንን ያልተረዳ ማኅበረሰብ ሆነ ሥርዓተ ትምህርት፣ በትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ መቸገሩ አይቀርም፤” ይላሉ፡፡
በዚህ ረገድ መንግስት ችግሩን የተረዳው ይመስላል። በሁሉም ደረጃ የትምህርት ስርዓቱን ስብራት ለመጠገን እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ስርዓቱ ውድቀት ማሳያ በመሆን በሚጠቀሰው በከፍተኛ የትምህርት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ይጠቀሳል። ትምህርት ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት በ2015 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናው በሁሉም የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት ወስኗል። ፈተናው በመጪው ሀምሌ ወር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ እርግጥ ሆኗል።
እንደ ማሌዢያ፤ ጃፓንና ቻይና የመሳሰሉ አገራት ያሉ ተማሪዎች ራሳቸውን የሚገመግሙት በየዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና እየወሰዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ አገራት ለፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች ምን ያህል እንዳለፉና እንደወደቁ በማየት የትምህርት ስርአታቸውን ይገመግማሉ። ይህም የትምህርት ስርአታቸውን ጉድለቶች ፈጥነው ለማየት እንደሚረዳቸው ይታመናል።
በኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ዓይነት ልምድ ተጀምሮና ተጠናክሮ ቢቀጥል፤ የትምህርት ጥራቱ የተሻለ እንደሚያደርገው ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። በተለይ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ በኩረጃ እየተፈተነ ላለው የትምህርት ስርአታችን አንድ እፎይታ ነው፤ ትውልዱ ራሱን እንዲፈትሽ፤ መጭው ትውልድም ትርጉም ላለው ትምህርት እራሱን እንዲያዘጋጅ ይረዳዋል። ይህን አይነቱ ተስፋ አዘል አዲስ አሰራር ሲመጣ ተግባራዊነቱን ከመደገፍ ባሻገር ለውጤታማነቱ አብሮ መሰለፍ ያስፈልጋል።
ከዚህ አንጻር ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለመውጫ ፈተናው ብቁ ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎች እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየሰሩ መታየታቸው፤ አንዳንዶችም፤ ከዋና የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ቀድመው የሞዴል ፈተና አዘጋጅተው እየሰጡ የሚገኙበት ሁኔታ የሚበረታታ እና እውቅና የሚሰጠው ነው።
ይህም ተማሪዎቻቸው ፈተናው አዲስ ከመሆኑ አንጻር፤ በፈተናው ዙሪያ በቂ ልምምድ እንዲኖራቸው ከማድረጉም በላይ የተሻለ የሥነ-ልቦናና የክህሎት ዝግጅት እንዲኖራቸው ያስችላል። የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ለመውጫ ፈተናው በስነ- ልቦናም በእውቀት እራሳቸውን የዓመታት ልፋታቸው ትርጉም እንዳያጣ መትጋት ይኖርባቸዋል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015