ልጆች እንዴት ናችሁ? በዚህኛው አምድ ላይ ታዋቂ ፈላስፋዎችን፣ ጀግና፣ የአገር መሪዎች፣ ሳይንቲ ስቶችን እና ለዓለም ሥልጣኔ የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ ሰዎችን እናስተዋውቃችኋለን። እስቲ ልጆች የዓለም ሥልጣኔ እዚህ እንዲደርስ ትልቅ ድርሻ አላቸው የምትሏቸውና ከዚህ ቀደም እናንተ ከምታውቋቸው ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን አስታውሱ።
የአገራቸውን ሉአላዊነት ያላስደፈሩ እና መልካም ስብእና ያላቸው መሪዎችንስ ታውቃላችሁ? መልካም፤ ልጆች ሁሉም ሰው በእኩል ደረጃ ለዓለም መሰልጠን እና ዘመናዊ መሆን ድርሻ ባይኖረውም ነገር ግን የራሱን አቅሙ የፈቀደውን ነገር ማድረጉ አይቀርም። እናንተም በተመሳሳይ ለሀገራችሁ እድገት ልማት እና ስልጣኔ የራሳችሁን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባችሁዋል።
ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ይባላሉ። ልጆች ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ማናቸው? ታውቋችዋላችሁ? የምታውቋቸው ካሁኑ ጥሩ ለማታውቃቸው ግን ነጋድራስ ገብረህይወትንና ስራቸውን በመጠኑ አስነብባችኋለሁ። ነጋድራስ ገብረህይወት ዘመናዊውን ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቋደስ እድል ያገኙ ሰው ናቸው። እኚህ ሙሁር ያገራቸው ኋላ ቀርነት እያብከነከናቸው ለውጥ ለማምጣት በጽሁፋቸውም በተግባርም ታግለዋል፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት በ1878ዓ. ም በአድዋ አውራጃ ተወለዱ፡፡ በልጅነታቸው ወደ ኤርትራ በማምራት ምፅዋ አጠገብ ምንኩሉ በሚገኘው የስዊድን ሚሲዮን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀሰሙ፡፡ ከዚያም ወደ አውስትራሊያ በመርከብ ተደብቀው ከሄዱ በኋላ የህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ እንዲሁም የውጪው አለም የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስተጋብሮችን ቀስመው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ችለዋል፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ አፄ ምኒልክ በጠና የታመሙበት ጊዜ በመሆኑ አፄ ምኒልክን ለማከም ከተሰባሰበው የህክምና ባለሙያ መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ እንዲሁም መንግስትና የህዝብ አስተዳደር የተሰኘ አጭር ግን እምቅ ሀሳብ የያዘ መፅሀፍትንም አሳትመዋል፡፡ ይሄ መፅሀፍ ኢትዮጵያን በልማት ጎዳና ወደፊት ለመውሰድ አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ ቋንቋ ያስረዳል፡፡
ገብረሕይወት ባይከዳኝ የህይወታቸውን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ምርምር ብቻ ሳይገድቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሀገራቸው ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ መጀመሪያ በምድር ባቡር በኢንስፔክተርነት ካገለገሉ በኋላ እስካሁን የሚታወቁበትን ማዕረግ ባገኙበት በድሬዳዋ ነጋድራስነት ሰሩ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ በተወለዱ በ33 ዓመታቸው በ1911 ዓ.ም ሕይወታቸው አለፈ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም