ተሰማ መንግስቴ፤ ዘውዴ መታፈሪያና ገብረየስ ገብረማሪያም ከምን ጊዜውም በላይ ከፍቷቸዋል። ተሰማ መንግስቴ ዛሬ መጠጣት የፈለገው እንደሌላ ጊዜው ቢራ ብቻ አይደለም፤ ጠንከር ያለ ቮድካ ቢጤ እንጂ። ዘውዴ መታፈሪያም ጭንቅላቱ ከብዶታል፤ እርሱም ከቢራ ማለፍ ፈልጓል። ጂን አዞ በአምቦ ውሃ እና በበረዶ እየተጎነጨ እንዳንገሸገሸው በሚያሳብቅ መልኩ ፊቱን እያጨማደደ የተጎነጨውን ያዋውጣል። ገብረየስ ግን የለመደውን ቢራ እየጠጣ እነርሱ የሚሉትን ለማዳመጥ ጆሮውን ቀስሯል።
ተሰማ ምርር ያለው ይመስላል። ‹‹ተሰማ ብባልም ሰሚ አጥቻለሁ። ሁሉም ነገር ሰልችቶኛል። የሚባለውን የሚሰማ የለም። ማንም እየተነሳ ይበጠብጣል። ለመጥራት ጫፍ የደረሰውን ጉዳይ ያደፈርሰዋል። መቼም ጆሮ አይጾም! በሩቅ የምሰማውና አይድረስ ! እያልኩ የማልፈውን ነገር ዛሬ ቢሮዬ ሰማሁ። በተደጋጋሚ ፈጣሪዬን እንዳታሳየኝ! እንዳታሳማኝ ! ብዬ የምለውን ነገር እዚሁ አጠገቤ አየሁ ፤ ሰማሁ።
ሰው የማይፈልገው ነገር እየበዛ ሲሔድ ዝም ለማለት ይገደዳል። ነገር ግን የተፈለገውን ያህል ዝም ማለት ተገቢ ነው ተብሎ ቢታሰብም በቁም ነገር ጊዜ ከተናጋሪው በላይ ዝምተኛነት ያስቆጣል። እየተነጋገሩ እና እየተጨቃጨቁ ዝም ማለት ተገቢ ስላልመሰለኝ፤ እንደአስፈላጊነቱ የሚመስለኝን ሃሳብ ለማካፈል እና ለማስታረቅ ስሞክር በተቃራኒው ሌላውን ወገን ቅር የሚያሰኝ ነገር ተፈፀመ። ›› ብሎ ተጎነጨ።
ዘውዴ ‹‹ውይ ተሰማ ነገሩን እንደዘመኑ ፖለቲካ አረዘምከው፤ ጆሮ እንደሆነ ጥሩውንም ሆነ መጥፎውን ይሰማል። ለማለት የፈለግከውን በቀጥታ እንደመናገር ከገባህ ጀምሮ ከኔ የባሰ ተደብረህ እኔንም የባሰ እያስደበርከኝ ነው። ለራሳችን ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው እንደሚባሉት ዓይነት ሰዎች ሆነናል። ›› አለው።
ተሰማ በበኩሉ ‹‹ምን ላድርግ እኔም የጨነቀው ሙቅ አነቀው እንደሚባለው ሆኖብኝ ነው። ችግር ያለበት ሰው ትንሽ ነገር ያደናቅፈዋል፤ የቸገረው ሰው የሚሳካ እየመሰለው የማይሞክረው ነገር የለም። በቢሮዬ ሰራተኞች መካከል ሃይለኛ ጠብ ተነስቶ ነበር። ጉዳዩ እንደቀደመው የፖለቲካ አጀንዳ እያነሱ በብሔር እና በሃይማኖት መዳቆስ አልነበረም። በወንዶች እና በሴቶች መካከል እኩልነት መኖር አለበት የለበትም የሚል ክርክር ተነሳና መልሰው ጉዳዩን ወደ ሃይማኖት እና ወደ ፖለቲካ አሻገሩት። በኋላም ለጠብ ተጋበዙ፤ በተለይ አንደኛው ‹ይኸው እኩልነት እያላችሁ የበታችነታችሁን ስላላመናችሁ የባሰ ተጎጂ ሆናችሁ› አለ።
በተቃራኒው ሌላኛዋ የቢሯችን ሰራተኛ ‹ እኩልማ እኩል ነን። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሴቶች በቤት ውስጥ ሥራ ተወስነው በሚኖሩባት አገር ውስጥ ሴት ሆነን ተፈጥረን ተጎጂ ሆንን እንጂ ሌላ የአውሮፓ አገር ብንኖር ኖሮ ህግ መውጣት ብቻ ሳይሆን ህግ ተከብሮ ተጠቃሚ ሆነን እንኖር ነበር። › አለች። በኋላ ጉዳዩ በዚህ ሳያበቃ ተቀጣጠለ፤ ‹ከራሴ ላይ አልወርድ አለ፤ ዘወትር ሊበድለኝ ይፈልጋል፤ በክፉ ዓይኑ ይከታተለኛል። ይኸው ከሁለት ወር በፊት እኔን ተክተህ ሥራ ሥራልኝ ብለው እምቢ አለኝ።
ሴት ሕፃን ልጄን ጎረቤት ትቻት መጣሁ፤ እንደርሱ አይነት ክፉ ሰው ልጄ ላይ ጥቃት ፈፀመ። ለአንድ ቀን ስራዬን አልሸፍንም ያለኝ ሰውዬ ሆስፒታል፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ፍርድ ቤት ስመላለስ አንድ ወር ሙሉ ስራዬን ለመሸፈን ተገደደ። › ስትል ‹ መቼ አመሰገንሽኝ? ብሎ ልጁ አፈጠጠ› አንተ ባመጣኸው ጣጣ ልጄ ለጉዳት ተዳረገች› ስትለው ብልጭ አለበት። ‹ ያልዘሩት አይበቅልም፤ አይገባሽም እንጂ ማንኛውም ነገር የአንድ የተፈፀመ ነገር ውጤት ነው። እኔን ስራ ሸፍንልኝ እያልሽ እየደጋገምሽ ከምታስቸግሪኝ ባልሽን አታስጠብቂም ነበር? ለትዳር መቃናት እና ለልጆች እድገት እንደውም ስኬታማ ቤተሰብ እንዲኖር ቁም ነገረኛ የቤት ምሰሶ የሆነ ባል ያስፈልጋል። ስለዚህ ለሆነው ተጠያቂው አንቺ እና ባለቤትሽ ናችሁ። › ሲል ምላሽ ሰጠ።
‹ኑሮዬንማ የምገፋው ያለጥርስ ቆሎ ያለአጋዥ አምቧጓሮ እንደሚባለው አጋዥ ሳይኖረኝ ስንደፋደፍ ዐቅም አንሶኝ እየተደፋው መሳቂያ የሆንኩት ለአዳሪ አልጋ ለቤት ቀጋ የሆነ ሰው አግብቼ ነው። እንጂማ ብቁ ሳልሆን ቀርቼ አይደለም። አንተ ከመቀጠርህ በፊት ሥራዬን ቀጥ አድርጌ ስሠራ ነበር። ይህንን ማንም የሚመሰክረው ነው። ከውጭ ደግ ሆኖ ቤት ውስጥ ግን አስቸጋሪ ፀባይ ያለው ባለብልሹ አመል ባል አግብቼ ቁልቁል መታየት ጀመርኩ።
እንኳን የቤተሰብ ኃላፊነትን ወስዶ ማስተዳደር ቀርቶ ‹ገበጣ ላዋቂ፤ ወሬ ለጠያቂ › እንደሚባለው ማንኛውም ነገር ተከታታዩን እንደሚፈልገው ሁሉ እርሱም የሚፈልገው መሸታ ቤት እና መጠጥ፤ አልፎ ተርፎ ሴት እያሳደደ መወሸም ላይ በማመዘኑ ልፈታው በቃሁ። ከእናቱ ጋር ያለ እንቁላል አይሰበርም ብዬ፤ እንኳን እንደኔ ባል ዓይነት ቀርቶ ልጅን ከእናቱ የበለጠ የሚንከባከብ ማንም የለም ብዬ ለብቻዬ ለማሳደግ ብሞክርም ይኸው ሳይሆንልኝ ቀረ። › ብላ ማልቀስ ጀመረች።
ልጁ አላዘነላትም ‹ሚስትም ብትሆን ጥሩ የቤተሰብ ኃላፊ መሆን ይጠበቅባታል። አንቺ ግን መሆን አትችይም፤ ምክንያቱም እዚህ ሥራ ላይም በጣም አስቸጋሪ ሰው ነሽ። ሁሉንም በተገቢው ሥራ ሳይሆን በግድ ለማስፈፀም ትሞክሪያለሽ፤ ይሄ ደግሞ ለብዙ ሰው የሚመች አይደለም። አሁንም ልጅሽ ላይ ጥቃት ከተፈፀመ እልፍ የሴቶች ማህበራት አሉ። እነርሱ ጋር ሔደሽ ንገሪያቸው ይሟገቱልሻል።
የተበጠሰ ገመድ ለመቀጠል አያንሱም፤ በትክክል በዳይ ካለ ገደል መግባቱ አይቀርም። ይሟገቱልሻል ሥራሽን ትተሽ አትንከራተቺ ብዬ፤ ደጋግሜ ወደ ሥራሽ ተመለሺ አልኩኝ። ነገር ግን ፈቃደኛ አይደለሽም። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር፣ የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር፣ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እንደውም ከማህበር በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሴቶች ቢሮ፣ የፌዴራልም የሴቶች እና ህፃናት ሚኒስቴር እና ሌሎችም ከሴቶች ጋር ተያይዞ በየፌስ ቡኩ የሚጮሁ ብዙ አካሎች ባሉበት አገር አንድ ጥቃት ደረሰብኝ ብሎ እየዞሩ ሥራ መበደል አይገባም። ይሄ አገርን መበደል ነው። › ሲላት ከቁጥጥር ውጭ ሆነች።
‹ አህያ የተጫነችውን አትበላም፤ አደራ ክር ነው። ፈጣሪ ልጅ የሰጠኝ ጠብቂያት ተንከባከቢያት አሳድጊያት ብሎ ነው። ለተበደለችው ልጄ ፍትህ ሳላገኝ ትቼያት የትም አልሔድም። አልተኛሁም። አይኔ እያየ እንኳን ሥራ ልሠራ እንቅልፍ አልተኛም። ማህበራት ያልካቸውንም ዞሬ ለምኛቸዋለሁ። ብዙ ተበዳዮች በየቢሮው አሉ። በአብዛኛው ትኩረት የሚሰጡት ለራሳቸው የተመቻቸውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዴት የልጄን በደል ልተወው› ብላ መጮኋን ቀጠለች።
ለጊዜው ግራ ተጋብቼ ነበር። በኋላ ላረጋጋት ስሞክር ለካ ልጇ ከሩቅ በእናቷ ጓደኛ ኮምፒውተር ተደብቃ ስታየን ነበር። የእናቷን ሁኔታ አይታ ማልቀስ ጀመረች። የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ እንደሚባለው አይደል፤ ሕፃኗ ወዲያው ማልቀሷን አቆመች። ትኩስ መንፈስ ነገሮችን ፈጥና በማወቅ እናቷን የማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራትም መልሳ ረሳችው። ወዲያው ወደ እናቷ ጓደኛ ኮምፒውተር ተመለሰች። እናትየዋን እና አብሯት የሚሰራውን ልጅ ይዤ ወጥቼ ላነጋግራቸው ሞከርኩ። ነገር ግን ጭራሽ መግባባት አልቻሉም። ልጁ እውነት አለው፤ ‹አጥፊን በህግ ለማስቅጣት ጥረት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ሕይወት ደግሞ ይቀጥላል። የእርሷን ሥራ ደርቤ መስራት አድክሞኛል። › አለ።
በመጨረሻም የልጇን ጉዳይ እንደማግዛት እና ከማህበራት ጋር እንደማገናኛት ቃል ገብቼ ስራዋን እንድትቀጥል አበረታታኋት። ሆኖም ግን ከልጇ ተለይታ ወደ ሥራ እንደማትመጣ ተናገረች። ወደ ማህበራቱ ብደውልም ባሰብኩት ልክ ለማገዝ ፈቃደኛ አልሆኑም። እኔ እንደታዘብኩት በአብዛኛው ሥራቸው መግለጫ መስጠት ነው።
ሴትየዋም ልጇም አጉል ሆነዋል። ልጁ ምሬቱ በሴትየዋ ቦታ ሌላ ሰው ይቀጠር እያለ ነው። ያለበለዚያ ግን በገዛ ፍቃዱ ሥራውን እንደሚለቅ እየገለጸ ነው። እርሷ በበኩሏ ያለባትን ክፍተት አውቃ በሥራ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፤ እየተጎዳሁ ያለሁት በሴትነቴ ነው። ከማለት አልፋ ሳነጋግራት እየተጎዳሁ ያለሁት የእዚህ ብሔር ተወላጅ በመሆኔ ነው። ወይም የምከተለው ሃይማኖት ይሄ በመሆኑ ነው ብላ ትሞግታለች። ›› ብሎ ተሰማ ጉዳዩ እንዳደከመው በሚያሳይ መልኩ ምን ዓይነት ሃሳብ እያስጨነቀው እንዳለ ተናገረ።
ገብረየስ ምንም አልተነፈሰም። ዘውዴ ግን ብዙ ጊዜ የሚከነክነውን ሃሳብ አፈነዳው። ‹‹አይ አንተ ስንት የሚያስጨንቅ ጉዳይ እያለ የአንዲት ሕፃን ልጅ እና የአንዲት እናት ጉዳይ እንዴት አእምሮህን እንዲህ ይበጠብጣል? የማህበራቱ ጉዳይ እንደሆነ ቁጥራቸው ብዙ ቢሆንም ማሽላ ለማሽላ ተያይዞ ቆላ እንደሚባለው ሥራቸው ተመሳሳይ ነው። በሃሳብ የሚመሳሰሉ ይስማማሉ፤ ነገር ግን ተጋግዘው ሴቶቹን በማገዝ ላይ ናቸው የሚለውን እኔም እጠራጠራለሁ። ያለጎረቤት ቡና ያለሙያ ዝና አያስደስትም እንደሚባለው፤ ማህበራቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና በሰዎች ዘንድ ተዋቂነትን እንዲያተርፉ በፌስቡክ ላይ ለሚጮህለት ሰው ከመሮጥ ይልቅ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች በተፈናቀሉ ሴቶች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተደራራቢ የሴቶች ጥቃትን በተመለከተ ያለመታከት ቢሰሩ መልካም ነበር። ነገር ግን ሁሉም ነገር ዘመቻ ነው። ቀጣይነት ያለው ነገር አይታይም።
ነገር ግን ይህንን ግዴታቸውን በቅጡ ሲወጡ አይታዩም። ግዴታቸውን በቅጡ ቢወጡማ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ብዙ ለውጥ ያስገኝ ነበር። ለነገሩ ተወው የሴትየዋ ጉዳይ በቅርቡ መስመር ይይዛል። ወይ ራሷ ሲደክማት ትተወዋለች አሊያም በራሷ መንገድ ፍትህን ታገኛለች›› ብሎ ንግግሩን ሲያጠቃልል፤ ጆሮውን ሰጥቶ ሲያዳምጥ የነበረው ገብረየስ የሚጠጣውን ቢራ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦ
“ሳላነሳው ውየ ሳላነሳው ባድር፤
እንዴት ይታዘበኝ የቆምኩበት ምድር ። ” ብሎ ሁለት ስንኝ ግጥም ከተናገረ በኋላ “ምነው ጎበዝ ወድየት እየሄድን ነው ? እንዴት የሴቶች ማህበራት የተነሱበትን አላማ ዘነጉ። እነ ጣይቱን ፣ ምንትዋብ፣ አበበች ጎበና ፣ ደራርቱ ቱሉ በፈጠረች ሀገር ከአፍ በዘለለ በትግባር ለሴቶች መብት የሚቆም ማህበር እና ድርጅት እንዴት ይጠፋል ?
ሌሎች ዓለማት የሴቶችን እኩልነት ሳያውቁ የእኛ ሀገር እኮ በሴት መሪዎች ትመራ ነበር ። ሌሎች አለማት ሴቶችን “በማጀት” ብለው ሴቶች መምርጥ በማይችሉበት እና እንደዜጋ እንኳን በማይቆጠሩበት ወቅት በእኛ ሀገር ግን ጦር መርተው ሀገርን ከጥቃት የተከላከሉ ንግስቶች ነበሩን ።
የእነዚህ ነግስተ ነገስታት መፍለቂያ በሆነች ሀገር የሴቶች ጠለፋ አለመቆሙን ስመለከት በህልም ዓለም ውስጥ ያለሁ ያህል ይሰማኛል ብሎ ንግግሩን አጠቃለለ። ” ያስወቀመጠውን ቢራ አነሳ… የጨዋታውም ርዕስ ተቀየረ ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015