የማዕድን ግብዓቶችን ከሚጠቀሙ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መካከል በግንባታው ዘርፍ እንደ ሲሚንቶ፣ ብሎኬትና ሌሎች ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ። የቀለምና የመስታወት እንዲሁም ለሕንፃ ማጠናቀቂያና ለቤት ውስጥ ቁሳቁስ የሚውሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም እንዲሁ የማዕድን ግብዓቶችን ይጠቀማሉ። እነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎችም በአካባቢያቸው ከሚገኝ የማዕድን ሀብት ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ ይበረታታሉ። ይህም የአካባቢውን የማዕድን ሀብት መጠቀም ግብዓቱን ከውጭ አጓጉዞ ለማምጣት የሚወስደውን ጊዜ ለመቆጠብ፣ ለግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረትና የሀገርንም ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በማስቻል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች የሚያስገኝ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ላይ በገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓቶችን ከውጭ ለማስመጣት የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ የሀገር ውስጥ የማዕድን ግብዓት መጠቀም አማራጭ ነው። በሌላ በኩልም እንደሀገር ሥራ ላይ በዋለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የማዕድን ዘርፉ በምጣኔ ሀብት እድገት እንዲኖረው ያደርጋል። በወርቅ፣ በከበሩ የጌጣጌጥ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ብቻ ሳይሆን፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው በግብዓትነት የሚውለውን የማዕድን ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል አበርክቶው ጉልህ ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የማዕድን ግብዓቶችን ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማቅረብ በተጨማሪ እሴት የተጨመረበት ግብዓት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚቻልበት እድል አለ። በዚህም ኢንቨስትመንትን መሳብ ይቻላል። አምራች ኢንዱስትሪዎች የማዕድን ግብዓት የመጠቀም ተሞክሮ ምን እንደሚመስልና በዚህ ረገድ ዘርፉን የሚመራው የማዕድን ሚኒስቴር እያከናወነ ስላለው ተግባር ተመልክተናል። ከዘርፉ ባለሙያም እንዲሁ ጠቃሚ ሃሳቦችን ተጋርተናል።
የማዕድን ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ እንዲመራ በአቅም ግንባታ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር የጋራ ስምምነት በማድረግ እየሠራ ስለመሆኑ በማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሠ ያስረዳሉ።
እንዲህ ያለው የጋራ ግንኙነት የማዕድን ግብዓት ከሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋርም ተጠናክሮ የሀገር ውስጥ የማዕድን ግብዓት ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ምን እየተከናወነ ስለመሆኑ የጠየቅናቸው ዶክተር ጉታ፤ ጥያቄው ተገቢነት እንዳለው በመጥቀስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ ረገድ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ የማዕድን ግብዓት ተጠቃሚ የሆኑ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግብዓት አጠቃቀም፣ አቅማቸውና አስተዳደራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት ሁኔታና ግብዓቱ ያለበት ደረጃ የዳሰሳ ጥናት ሥራ ተካሂዷል። በዳሰሳ ጥናቱ ግብዓት መቀየር ካስፈለገም ለመቀየር የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ተግባርም በዳሰሳው ተካትቷል። ከሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታና የፋብሪካ መለዋወጫ ዕቃ ግዥ ለመፈጸም ከሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸውና በሌሎችም ምክንያቶች የአምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅም አለመንቀሳቀስ ክፍተቶች መኖራቸው በዳሰሳ ጥናቱ ተለይቷል። በዚህ የዳሰሳ ጥናት አዋሽ መልካሳ የሚገኘው የኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ ታቦር ሴራሚክ፣ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካተታቸውን የጠቆሙት ዶክተር ጉታ፤ በዳሰሳ ጥናቱ ከታዩት መካከል አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የማዕድን ግብዓቱን ከየት እንደሚጠቀሙ፣ አቅራቢዎቻቸው እነማን እንደሆኑና አማራጮቻቸው ለአብነት ይጠቀሳሉ ብለዋል። አዋሽ መልካሳ የሚገኘው የኬሚካል ኢንዱስትሪ ካኦሊን የተባለውን የማዕድን ግብዓት እንደሚጠቀም ለአብነት አንስተዋል። በተመሳሳይ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ የዳሰሳ ጥናት ሥራ መከናወኑን የጠቀሱት ዶክተር ጉታ፣ በተለይ ደግሞ የሲሚንቶ የማምረቻ ወጪ ምን ያህል እንደሆነና የወጭ ምንጩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንዲያካሂድ መደረጉን አመልክተዋል።
እንደሳቸው ገለጻ፤ የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ፋብሪካዎቹ የሚጠቀሟቸውን የተለያዩ የማዕድን ግብዓት ዓይነቶች፣ የአቅርቦት መጠንና እሴት የተጨመረበት መሆኑና አለመሆኑን እንዲሁም ግብዓቱን ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡ በማኅበር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ተጠቃሚነት፣ በአጠቃላይ ከአቅርቦቱ ጋር በተያያዘ ያሉትን ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሀሳቦችን ያካተተ በ12 ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ የጥናት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት። አሁን ባለው ሁኔታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከፍተኛው የማዕድን ግብዓት የድንጋይ ከሰል መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጉታ፣ የጥናት ውጤቱን መሠረት በማድረግም ሥራውን በመቀጠል ኢንዱስትሪዎችና ማዕድን አምራቾች ከመንግሥት የሚፈልጉትን ድጋፍና ክትትል መሠረት በማድረግ፣ አምራቾችም ሆኑ ፋብሪካዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲፈትሹ ምክረ ሀሳብ የመስጠት ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው ያስረዱት።
ወደፊት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የራሱ ማሠልጠኛና የሙከራ ሥራ የሚሠራበት ወርክሾፕ ሲኖረው ወይንም ሲያቋቁም ደግሞ በራሱ በተለያዩ የማዕድን አይነቶች ላይ የሙከራ ሥራዎችን በመሥራት የትኛው ማዕድን ለየትኛው አምራች ኢንዱስትሪ ይውላል የሚል ደረጃ ላይ ሲደርስ በጥራትና በመጠን የተሻለ የግብዓት አቅርቦት ደረጃ ላይ ሊደረስ እንደሚችል ነው የገለጹት።
በማኅበር ተደራጅተው በዘርፉ ላይ ለተሰማሩና ዘርፉን ለሚመሩ የክልል ባለሙያዎች በአጫጭር ጊዜ ሥልጠና የማብቃት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጉታ፤ በመወያያ መድረኮችም ከክልሎች ጋር ምክክር በማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንዲሁ እንደየትኩረት አቅጣጫቸው በጋራ የሚሠሩበትን ሁኔታ ምቹ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል። ለአብነትም በቤንሻንጉል ክልል ላይ ከድንጋይ ከሰል፣ ከወርቅና ከእምነበረድ ጋር በተያያዘ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ በሌሎችም አካባቢዎችም በተመሳሳይ ይህ ሥራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የዳሰሳ ጥናት ባካሄዱበት ወቅት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ የማዕድን ግብዓትን የመጠቀም ተሞክሯቸውን በተመለከተ ዶክተር ጉታ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ግብዓት የመጠቀም ተሞክሮ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይ ከውጭ ሀገር የሚገባ የድንጋይ ከሰል በመጠቀም ለረጅም ጊዜ ጥገኛ ሆኖ በመቆየት የሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪው ይጠቀሳል። ድንጋይ ከሰል ጥቅም ላይ አለመዋሉ የሀገር ውስጥ ግብዓት መጥፎ ገጽታም እንዲኖረው አድርጎ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥናት የተደገፈ እርምጃ ተወስዶ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ለምቶ የሚቀርበውን የድንጋይ ከሰል በግብዓትነት የመጠቀም ሁኔታ የተሻሻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
እንደ ድንጋይ ከሰሉ ሁሉ ጥሩ በሚባል ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ሌሎች ግብዓቶችም አሉ። እንደ ሰልፈር ያሉ የማዕድን አይነቶች ለምተው ጥቅም ላይ መዋል ባለመጀመራቸው ሳቢያ አምራቾች ከውጭ በግዥ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይታያል። ይህም ግብዓት በሀገር ውስጥ ግብዓት እንዲተካ የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን፣ በዘርፉ ለመሰማራት ፍቃድ ወስደው በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙና ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ አልሚዎችም ስለመኖራቸው ተናግረዋል። ለማዕድን ልማቱ የሚውል የሥራ መሣሪያና በልማቱ አካባቢ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ ግብዓቱን ወደተለያዩ አካባቢዎች ለገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ አለመኖር አልሚዎችን ለማበረታታት እንዳላስቻለ በአንዳንድ ቦታ ስለሚነሳው ቅሬታም ላቀረብልናቸው ጥያቄ ዶክተር ጉታ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ለሥራ የሚውል ማሽን አቅርቦት ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው። የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መምጣትም ሌላው ተግዳሮት ነው። ባደረግነው ዳሰሳም የአስተዳደር ችግር የሚያነሱም አሉ›› ሲሉ ጠቁመዋል። ‹‹ገበያ ከመፍጠር አኳያም ወደፊት ከመንግሥት ፕሮጀክቶች ጋር በማያያዝ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት በራስ አቅም በማምረት ግዥው ወደ ሀገር ውስጥ አምራቾች ትኩረት እንዲያደርግ ጥረቱ ይጠናከራል›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። አቅርቦትን በተመለከተ መንግሥት በጀመረው አዲስ የማበረታቻ የትኩረት አቅጣጫ ማዕድኑን በጥሬው የሚያቀርቡም ሆነ እሴት ጨምረው የሚያቀርቡ እንደሚበረታቱም ገልጸዋል። በዚህ ረገድም አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የኢንዱስትሪ የማዕድን ግብዓቶችን ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ላይ ብቻ እንደማይሠራ ጠቅሰው፣ እሴት የተጨመረበት ግብዓት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት እድል መኖሩንም አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለሲሚንቶ ደረጃ ያልደረሰ ግብዓት ለውጭ ገበያ ያቀርቡ እንደነበርና መቀጠል እንዳልቻለ ዶክተር ጉታ አስታውሰዋል።
ፋብሪካዎቹ ለገበያ የሚያውሉት እነርሱ ተጠቅመው የሚተርፋቸውን እንደሆነና በሽያጩ ገቢም የመለዋወጫ ወጪያቸውን ይችሉ እንደነበር ጠቁመዋል። ፋብሪካዎቹ ቀድሞ ያደርጉት እንደነበረው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ግፊት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ‹‹እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረቡ ተግባር የሚበረታታ ቢሆንም ኢንቨስትመንቱ ግን ከባድ ነው። የትራንስፖርት ወጭው ላይ መንግሥት ማበረታቻ እንዲያክል እንደ አንድ ሀሳብ ተነስቶ በፖሊሲ አውጭዎች ደረጃ ውይይት ተካሂዶ ጉዳዩ እየታየ ነው። ይህም ወደፊት አንዱ የለውጥ ሂደት ይሆናል፤ እሴት ያልተጨመረበት ግብዓት መሸጥ ግን አይቻልም›› ብለዋል። በወሎ ዩኒቨርስቲ የሥነምድር ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ደሳለኝ ገዛኸኝ፣ በማዕድን ዘርፍ የማማከርና ከልማት ጋር በተያያዘ የአካባቢ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ይታወቃሉ። ዶክተር ደሳለኝ፤ ማዕድን ሲባል በግራም የሚለካ ወርቅና የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ብቻ እንዳልሆኑ ይገልጻሉ። ድንጋይን ጨምሮ ምድር ውስጥ እምቅ የማዕድን ሀብት መኖሩን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያም በዚህ የታደለች መሆኗን ያስረዳሉ። የማዕድን ግብዓትን ለተለያዩ ቁሳቁስ ሥራ ጥቅም ላይ ማዋል ጥንትም የነበረ ነው። ሸክላ፣ ጡብ ከጥንት አንስቶ አባቶች ለግንባታ ይጠቀማሉ፤ ከጥንት ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረን ግብዓት እያሳደጉ እንደመሄድ ከውጭ በግዥ ከውጭ ማምጣት ተገቢነቱ የሌለው መሆኑን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያን የመሬት ክፍል ከሸፈነው የማዕድን አይነት 10 በመቶ የሚሆነው ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚውል እንደሆነና ይህን ወደ ምርት መለወጥ ባለመቻሉ ከውጭ በግዥ የማዕድን ውጤት መግባቱ እንደሚያስቆጫቸው ይናገራሉ። አያይዘውም ገዝቶ መሸጥ እየተለመደ መምጣቱንም አስረድተዋል።
የማዕድን ልማት አድካሚነቱ ለተወሰነ ጊዜ ነው። ያ ጊዜ ካለፈ በኃላ ግን ግለሰብንም ሀገርንም ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፤ ዘርፉን የሚመራውም በተጠናከረ አሠራር አልሚውን ከመደገፍ ይልቅ ጫና የሚፈጥር ነገር ላይ ማተኮሩ ለክፍተቱ ሌላው ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል። ‹‹ባለሀብቱ ባንክ ሄዶ ዶላር አምጡ ብሎ ከሚያስጨንቅ ዶላር የሚያስገኝ ሥራ ይሥራ›› በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ትሸጋገር ሲባል የማዕድን ዘርፉም ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ደሳለኝ፤ መንግሥትም ባለሀብቱን የሚያበረታታ እስከ ታችኛው መዋቅር የተዘረጋ አሠራር ሊኖረው እንደሚገባም ገልጸዋል። አሁን ላይ ባለው አሠራር በአማራ ክልል ላይ ያስተዋሉትን ክፍተት ለአብነት በመጥቀስ ሲያብራሩም፤ ደቡብ ወሎ ላይ አንድ ባለሀብት የማዕድን ፍለጋ (ኤክስፖሎሬሽን) ፍቃድ ለማውጣት ባሕርዳር ይሄዳል። በዚህም 500 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅበታል። ጉዳዩም ቶሎ ሳይቀላጠፍለት ለቀናት ይቆያል ይላሉ።
እዚህ ላይ ዩኒቨርስቲዎች ሊኖራቸው ስለሚችለው አበርክቶም ዶክተር ደሳለኝ እንደገለጹት፤ በዩኒቨርስቲዎች የምርምር ሥራዎች አልተቋረጡም። ችግሩ ምርምሮቹ አለመተግበራቸው ነው። ‹‹ምርምሩ ወደ ተግባር ካልተቀየረ የጋን ውስጥ መብራት ነው የሚሆነው። ለምርምር ሥራ ከፍተኛ ገንዘብ ይወጣል። ግን ይባክናል›› በማለት ዩኒቨርስቲዎችና ባለሀብቱ በጋራ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ባለሀብቱ ገንዘብ ይዞ ሲመጣ፣ ዩኒቨርስቲው ደግሞ የትና እንዴት እንደሚሠራ ሀሳብ ይሰጠዋል። እንዲህ ሲደጋገፉ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል ብለዋል። በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ አካባቢ ስላለው የማዕድን ሀብትም ዶክተር ደሳለኝ ሲገልጹ፤ አባይ ሸለቆን ይዞ በበሽሮ ወንዝ በሚባለው ከደላንታ ጀምሮ ባለው አካባቢ ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግብዓት ሊውሉ የሚችሉ የኖራ ድንጋይ፣ ጂብሰም፣ ለብርጭቆ ፋብሪካ የሚውል ግብዓት፣ ደሴ ዙሪያ ኩታ በር አምባሰል ውጫሌ በሚባሉ አካባቢዎች ደግሞ የድንጋይ ከሰል፣ በሰሜን ወሎ ቦረና አካባቢ የብረት ማዕድን በስፋት እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የብረት ማዕድኑን የአካባቢው አርሶአደር ለእርሻ መሣሪያ በባህላዊ መንገድ በመሥራት እንደሚጠቀምበት ጠቅሰው፣ በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ደግሞ ወሎ ደላንታ ላይ የሚገኘው የወሎ ኦፓል እንደሚጠቀስ ይናገራሉ። ወረኢሉ ላይ መሬት ሰንጥቆ የወጣው የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብትም የአካባቢው አርሶአደር ለኩራዝ መብራት እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ይገልጻሉ። በአንድ አካባቢ ብቻ ካለው ሀብት ከብዙ በጥቂቱ መጥቀሳቸውን ተናግረው፣ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ገና ያልተለየ እንደሆነ ነው ዶክተር ደሳለኝ የተናገሩት።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015