ወጣት አሸናፊ ሚልኬሳ ይባላል። ትውልዱም ሆነ እድገቱ ከአዳማ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ከቆቀ እና መቂ መሐል በምትገኘው እና በተለይ በሽንኩርት እና በቲማቲም ምርት በስፋት በምትታወቀው ቦቴ ወይም በሌላ መጠሪያዋ ዓለም ጤና በምትባል የገጠር ከተማ ነው።
አሸናፊ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ቆይታ በትምህርታቸው ጎበዝ ከሚባሉ ወይም የደረጃ ተማሪዎች ከሚባሉት መካከል አልነበረም። ከትምህርት ይልቅ ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ ያስብ የነበረው በስፖርት በተለይ በእግር ኳስ መስክ ነበር። ነገር ግን የሕይወቱ አቅጣጫ የተቀየረበትን አጋጣሚ ወጣት አሸናፊ ወደኋላ ተመልሶ ሲያስታውስ፤ የ7ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጥሩ ክህሎት ስለነበረው የእንግሊዘኛ መምህሩ ኮድ ኢትዮጵያ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በአካባቢያቸው ቤተመጽሐፍት አስገንብቶ የመክፈቻ ፕሮግራም ስለነበረው በዚህ ዝግጅት ላይ ተሳታፊ እንዲሆን እሱን ይልኩታል። በዚህ ዝግጅት ላይ እንግሊዝኛ ቋንቋ ማንበብ ከዛ ውስጥ ያነበቡትን በቃል የማናገር ውድድር ነበረው። በዚህ ውድድር ጥሩ ውጤት አገኛለሁ የሚል ግምት እንዳልነበረው የሚናገረው ወጣት አሸናፊ፤ በውድድሩ ከ10ኛ ክፍል ተማሪ ጋር ተወዳድሮ 9 ነጥብ 5 በማምጣት እኩል ነጥብ ማስመዝገብ ቻለ።
ይህ አጋጣሚ ለካ እኔም በትምህርት ጥሩ ውጤት ማምጣት እችላለሁ ብሎ እራሱን በማሳመን ጠንክሮ መሥራት እንዲጀምር መነሻ እንደሆነው ይገልፃል። የ9ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲጀምር በወቅቱ ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን የሚከታተለውን ታላቅ ወንድሙን አንድ ነገር ቃል እንዲገባለት ይጠይቀዋል። ‹‹ጥሩ የእንግሊዝኛ ችሎታ አለህ። ስለዚህ ቢያንስ ዘንድሮ ከ5ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ይዘህ ማጠናቀቅ አለብህ። ይህ ካደረክ ደግሞ ሽልማት ይኖርሃል›› ይለዋል። እሱም በምላሹ 1ኛ ወጥቶ እንደሚጠብቀው ነግሮት ቃሉንም በመጠበቅ ከክፍል 1ኛ ከአጠቃላይ 9ኛ ክፍል 2ኛ ደረጃ ይዞ እንዳጠናቀቀ እንዲሁም 10ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እንደጨረሰ ወጣት አሸናፊ ይናገራል።
ወጣት አሸናፊ በተወለደበት አካባቢ ፕሪፓራቶር ማለትም የ11ኛ እና 12ኛ ትምህርት ቤት አልነበረም። ስለዚህ ሁለት አማራጮች ብቻ ነበሩት። ትምህርቱን ማቋረጥ አልያም ራቅ ያለ አካባቢ በመሄድ ቤት ተከራይቶ ትምህርቱን መቀጠል ። ሁለተኛውን አማራጭ በመምረጥ የአምስት ልጆች አባት እና የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነው ወላጅ አባቱ ጋር በመነጋገር የነበራቸውን መሬት እርካሽ በሆነ ዋጋ 25 ሺህ ብር እንዲሸጥ በማድረግ ቢሾፍቱ ከተማ በመምጣት የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርቱን እንደቀጠለ ይገልፃል።
ከቤተሰብ በመለየቱ ብዙ ከባድ ፈተናዎችን ቢያሳልፍም ቀጣይ ሕይወቱን ያማረ የሚያደርግ አጋጣሚ አገኘ። በ16 ዓመቱ በ 2005 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ 400 በላይ ውጤት በማምጣት የከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል የሚያስችል ነጥብ አገኘ። በዚህም ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ።
ወጣት አሸናፊ፤ የተፈጥሮ ትምህርት ጥሩ መረዳት ስለነበረው ሁለት ትምህርት ማለትም ባዮሎጂ እና ፊዚክስ መማር ፍላጎቱ አደረበት። በመጨረሻም የባዮሎጂ ትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ።
በትምህርት ዘርፉ በመጀመሪያ ዓመት ከወሰዳቸው 14 ኮርሶች 13 A+ እና 1 A አመጣ። ሆኖም አሸናፊ አንድ ከባድ ነገር አጋጠመው። አሸናፊ በስምጥ ሸለቆ አከባቢ ተወልዶ እንደማደጉ የደብረ ታቦር እና አካባቢውን ብርድ እና የአየር ሁኔታ መቋቋም ባለመቻሉ ትምህርቱን በማቋረጥ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ታላቅ ወንድሙ ጋር ተመለሰ።
ዩኒቨርሲቲ ቀይሮ ትምህርቱን መቀጠል እንዲችል ታላቅ ወንድሙ ባደረገው ጥረትም ጅማ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሎ የሁለተኛ ዓመት ትምህርቱን ቀጠለ። በመጨረሻም 4 ነጥብ ወይም 28 A+ በማምጣት 2009 ዓ.ም ላይ በአፕላይድ ባዮሎጂ በከፍተኛ ማዕረግ ከጅማ ዩኒቨርስቲ መመረቁን ይገልፃል።
2009 ዓ.ም ክረምት ላይ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል በሰው ኃይል ሙሉ ስለነበረ ሥራ ፍለጋ አዲስ አበባ እንደመጣ ይናገራል። ባዮሎጂ እንደመማሩ በወቅቱ ያለኝ ዕድል ሁለት ነበረ የሚለው ወጣት አሸናፊ፤ መምህር መሆን አልያም የምርምር ተቋም መቀላቀል።
የምርምር ተቋማት ሄዶ ደጅ ቢጠናም ከአራት ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ስለሚጠይቁ በዛ ሳይሳካለት ቀረ። ሁለተኛ አማራጭ ብሎ የያዘው መምህርነት ስለነበረ እሱንም ሞከረ። በወቅቱ ለመምህርነት ያመለከተበት ትምህርት ቤት ሁለት ዓመት የሥራ ልምድ ይፈልግ ስለነበረ ይህም ሳይሳካለት ቀረ።
ወጣት አሸናፊ እንደሚናገረው፤ ይህ ሳይሳካ ሲቀር አጠገቡ ወደሚገኘው አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በማቅናት የቅጥር ጥያቄ ቢያቀርብም በሁለተኛ ዲግሪ ካልሆን ሊቀጥሩት እንደማይችሉ ገለፁለት።
ይህ አለመሳካቱን ሲያውቅ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል እንዲሰጡት ጠየቀ። ሆኖም በዩኒቨርሲቲው ስላልተማረ ይህም እንደማይሆን ተነገረው። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ወጣት አሸናፊ ተስፋ አልቆረጠም። ወደ ዩኒቨርሲቲው ምርምር ዲን ኃላፊ ጋር በመሄድ ጥያቄውን ዳግም አቀረበ። ኃላፊውም ከአንድ ወር በኋላ ተመልሶ እንዲመጣ በማድረግ ፈተና እንዲቀመጥ አደረገው። የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆነው አሸናፊም ፈተናውን በጥሩ ውጤት አለፈ። ዩኒቨርሲቲውም የመጀመሪያውን ሴሚስተር ያለክፍያ አስተማረው። በዚህ የተበረታታው ወጣትም ሁሉንም የትምህርት አይነት A+ አመጣ። ይህን ውጤት የተመለከተው የአዳማ ዩኒቨርሲቲም ለወጣት አሸናፊ ነፃ ስኮላር ሺፕ ሰጠው። ውለታውን ያልረሳው ወጣትም በሁሉም የትምህርት አይነት A+ በማምጣት ትምህርቱን አጠናቀቀ።
የሁለተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፍ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ እንደነበረ የሚናገረው ወጣት አሸናፊ፤ ለምርምሩ መነሻ የሆነውን ጉዳይ ደግሞ ወላጅ አባቱ የሚያረቧቸው ዶሮዎች በገፍ ማለቅ ነበር። ወላጅ አባቱ ካሏቸው ዶሮዎች ውስጥ 200 ያህሉ በድንገት አለቁ። ለዶሮዎቹ በድንገት ማለቅ ደግሞ ዶሮ ፈንግል የሚባል ቫይረስ እንደሆነ እንዳረጋገጠ። ናሙናውንም ጀርመን ድረስ በመላክ አረጋገጠ። ይህንንም ለሁለተኛ ዲግሪ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደ መነሻ ተጠቀመበት። ይህ የምርምር ሥራው በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ላይ እንደታተመ ወጣት አሸናፊ ይናገራል። ሰው ለምን ያረጃል? በሚል ምርምር እየሠራ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት አሸናፊ ባደጉት ሀገራት ሰው ለምን ያረጃል ? በሚል የተሠሩ ምርምሮች ያተኮሩት ሥጋው ላይ ብቻ ነው። እሱ ግን ከሦስት አቅጣጫ በማየት ሰው ስጋ፣ ነፍስ እና መንፈስ ያለው እንደመሆኑ በማርጀቱ ሂደት ነፍስ እና መንፈስም አበርክቶ አላቸው ብሎ በመነሳት እርሱን ለማረጋገጥ ጥናታዊ ጽሑፍ እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች (infectious disease) ላይ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች ላይ ከበግ፣ ከፍየል፣ ከከብት እና ከግመል ናሙና በመውሰድ ከእነርሱ ወደ ሰው በሚተላለፍ በሽታ ዙሪያ የምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ተናግሯል።
ከዚህ ባሻገር በኮቪድ 19 የመጀመሪያ ዓመት የዶክትሬት ተማሪ በነበረበት ወቅት የኮምፒውተር ሲሙሌሽን በመጠቀም ከአማካሪ መምህሩ ጋር በጋራ በመሆን በሠራው የምርምር ሥራ ከጤና ሚኒስቴር ሰርቲፊኬት እንደተሰጠው እና የምርምር ሥራውም ለሕትመት እንደበቃ እና ሌሎች ከአስር በላይ የምርምር ሥራዎች ስለመሥራቱ ወጣት አሸናፊ ይናገራል።
2011ዓ.ም የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በማጠናቀቅ አሁን በመምህርነት እያገለገለ በሚገኘው አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቱን በመቀጠል ዘንድሮ አራተኛ ዓመት የዶክትሬት ተማሪ እንደሆነ እና የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቱን በማገባደድ ላይ እንዳለ ይናገራል።
ጊዜ በሦስት ይከፈላል ያለፈ፣ የአሁን እና የሚመጣ የሚለው ወጣት አሸናፊ ‹‹የተሰጠን ጊዜ ውስን ነው፤ በወጣትነት ጊዜ ቶሎ የሚያልፍ አይመስለንም፤ ሆኖም ካልተጠቀምንበት የኋላ ኋላ ጉዳቱ የከፋ ነው ።›› ይላል። ጊዜን መጠቀም ወሳኝ ነው የሚለው ወጣት አሸናፊ ብዙ ሰው ትኩረት የሚያደርገው ባለፈው ላይ እና ወደፊት ባለው ጊዜ ላይ ነው የሚለው ወጣት አሸናፊ ወጣቶች ዛሬ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይመክራል። ከፈጣሪ እርዳታ ቀጥሎ ለደረሰበት ስኬት ምክንያት ይህ ነው ብሎ እንደሚያምን ወጣት አሸናፊ ይነገራል።
ከዚህ ውጪ ወጣቱ ትውልድ ሰው አክባሪ፤ ፈጣሪውን የሚፈራና ለሀገሩና ለወገኑ ቅን አሳቢ መሆን እንደሚገባው ይመክራል። የሰው ልጅም በሕይወት ሲኖር የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፤ ነገር ግን ለችግር ሳይንበረከክ ችግሩን አልፎ የሚሄድበትን ጥበብ መፈለግ እንዳለበት ወጣት አሸናፊ ይገልፃል።
ሕይወት ፈተና ሲኖራት ጥሩ ነው የሚለው ወጣት አሸናፊ እንቁላል ሰው ሲሰብረው እና በራሱ ጊዜ ከውስጥ ሰብሮ ሲወጣ የተለያየ እንደሆነው ሁሉ ሰው ሁሉ አሸናፊ የሚሆነው ችግሮችን በራስ አሸንፎ መውጣት ሲችል እንደሆነ ይናገራል። ወጣቶችም በጊዜያዊ ፈተና ሳይረቱ ከችግራቸው በላይ ሆነው መገኘት አለባቸው ይላል።
‹‹እያንዳንዳችን የምናልፈው የሕይወት ፈተና የተለያየ ነው። ነገር ግን በምናልፍበት ፈተና ሁሉ ፈተናው እያጠናከረን ወደፊት እየገፋን እንሄዳለን። ብረት በእሳት እንደሚፈትን ሁሉ የሰው ልጅም በመከራና ችግር ይፈተናል። ስለሆነም በመከራና በችግር ምክንያት ከጉዟችን ወደኋላ ማለት አይገባም›› ሲል ምክሩን ይለግሳል።
ነገሮችን የምናይበት መነፅር ወሳኝ ነው የሚለው ወጣት አሸናፊ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን ችላ በማለት ጥሩ ጥሩ በሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚገባም ይገልጻል። እርሱ ባለፈባቸው የሕይወት ውጣ ውረዶችም ያጋጠሙትን ችግሮች ሳይሆን በሚኖሩት ተስፋዎች ላይ በማተኮሩ ለውጤት መብቃቱን ያስረዳል።
እንደአሸናፊ እምነት በአጠቃላይ ጥበብ ከፈጣሪ የሚሰጥ ችሮታ ነው። በዓለም ላይ የተሠሩ አስደናቂ ፈጠራዎች ሁሉ የተወሰዱት ወይም የተኮረጁት ከተፈጥሮ ነው። ሳይንስ ማለት ደግሞ ተፈጥሮን መረዳት ነው።
ወጣት አሸናፊ ለደረሰበት ስኬት ሁሉ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን በመቀጠል አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፣ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩቱ እና ቤተሰቦቹን ያመሰግናል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015