
የፋሺስት ኃይል ኢትዮጵያን ወረረ እንጂ ከቶ ኢትዮጵያውያንን ሊገዛ አልቻለም፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ባለፉት ክፍለ ዘመናት እንደሽምብራ ኩሬው፣ እንደዶጋሊው፣እንደመቅደላው፣ እንደመተማውና እንደዓድዋው ሁሉ የትግሉን ምዕራፍ በማያዳግም ድል አጠናቀዋል፡፡ እኛም እነሆ ዛሬ የእነዚህን ጀግኖች አርበኞች የድል መታሰቢያ ቀን 78ኛ ዓመቱን እያከበርን እንገኛለን።
ሚያዝያ 27/1933 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን በታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት አደባባይ ላይ የኢትዮዽያን ሰንደቅ ዓላማ መልሰው አውለበለቡ፤መድፍም ተተኮሰ። በዕለቱም የኢትዮዽያ ብሄራዊ የነፃነት ትንሳኤና የመላው ህዝቦቿም ድል አድራጊነት ተረጋጠ፤የነፃነት አዲስ ዘመን አንድ ተብሎ ተጀመረ። ይህንን የነፃነት የድል ቀን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ጭምር የሚያደንቀው ቀን ሆኖ በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፈረ።
ዛሬ በነፃነት አንገታችንን ቀና አድርገን፤ ደረታችንን ነፍተን የምንሄደውና አፋችንን ሞልተን የምንናገረው አያት ቅደመ አያቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው፣አካላቸውን አጥተው ትተውልን ባለፉት አኩሪ ታሪክ ነው።
ይህንን የአርበኞች የድል ቀንን ስናከብርም ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ይዘን ነው። አንደኛው ይሄንን ድል ለማስገኘት ለሀገራቸው ነፃነት የወደቁትን፣ የታገሉና የቆሰሉትን ሀገር ወዳድ ጀግና ህዝቦች ከልብ በማመስገን እና እውቅና በመስጠት እንዲሁም ታሪካቸውን ለትውልድ የምናስተላልፍበት ሲሆን ሁለተኛው እኛም ከእነሱ ሀገር ወዳድነትን ተምረን ለሀገራችን ምን መሥራት አለብን የሚለውን አሁን ሀገርን ለተረከበው ወደፊትም ለሚረከበው ትውልድ ትልቅ የአደራ መልዕክት የምናስተላልፍበት ነው።
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነፃነት ብለው የኢትዮጵያ አፈር የሆኑት ጀግኖች ውለታቸውን የምንከፍላቸው ታሪካቸውን በየዓመቱ በማውራት እና በመዘከር ብቻ መሆን የለበትም። የእነሱን ውለታ የምንከፍለው እኛም የራሳችንን አኩሪና ተጠቃሽ ታሪክ ስንሠራ ብቻ ነው። ታሪክ የሚሠራው በጦርነት ብቻ አይደለም። አሁን ለሀገሪቱ እና ለህዝቡ የሚያስፈልገው ሀገርንና ህዝቧን ከድህነት የሚያወጣ ታሪክ በመሥራትና የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን መቀየር ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀውን አንድ ሆነን በፍቅር እና በሰላም መሥራት ይገባል።
ዛሬ የምናከብረው የአርበኞች ቀን በቀላሉ የተገኘ አይደለም። በርካታ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል። ትልቅ ሀገራዊ የአንድነት መንፈስና የሀገር ፍቅር ስሜት ታክሎበታል። በአንድ የመንግሥት የክተት ጥሪ ቃሉን አክብሮ ያለብሄር፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ሃይማኖትና የፆታ ልዩነት ሁሉም በአንድነት ስሜት ለአንድ ሀገር ሉአላዊነት መከበር በጋራ ባደረጉት ትንቅንቅ የድሉ ባለቤት ሆነው እነሆ እኛም ታሪክ ተናጋሪና ዘካሪ ሆነናል።
አሁንም ይሄ ወቅት የሚጠይቀው ተመሳሳይ ቆራጥነትን ነው። ለሀገራዊ ጥሪው ቀና ምላሽን ነው። ያለፈውን ማወደስ ሌሎች በሠሩት ጀግንነት መኮፈስ ብቻ ሀገርን ወደፊት አያራምድም። እኛ ምን ሠራን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በተለይም አሁን በሀገራችን የተጀመረው አዲስ የለውጥ ጉዞ በተስፋና ስጋት መካከል ባለበት ወቅት የኢትዮጵያውያን አንድነት ለውጡን ወደፊት ለማራማድ እጅና ጓንት መሆንን ይጠይቃል። “ኢትዮዽያውያን አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራትን አይችሉም” የሚለውን አባባል ልንቀይር ይገባል። ይሄ የሚሆነው ደግሞ የጥፋት እጆችን ሰብስበን፣ የተንኮል አዕምሮን በንጹሕ አድሰን በአንድነትና በሀገር ፍቅር ስሜት መሥራት እና ሀገራችንን ወደ ከፍታው ማማ ማውጣት ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ሰላም ወሳኝ ነው፤ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ልናስብ ይገባል።
አሁን አሁን በተማረውም ሆነ ባልተማረው፤ በፖለቲከኛውም ሆነ በሌላው ወገን በኩል የሚታዩትና የሚሰሙት ጥግ የያዘ ብሄረተኝነትና ዘረኝነት፤ የእኔ ለእኔ ብቻ የሚሉ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች ናቸው። ይሄ ደግሞ ህዝብን ከህዝብ እያጋጨና እያፈናቀለ ያለ ለሀገር ነቀርሳ የሆነ በሽታ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ከዚህ በሽታ መዳን የሚቻለው ለእኩይ ተግባር ባለመተባበር፣ለሀገርና ህዝብ የማይጠቅሙ የአክቲቪስቶችንም ሆነ የፖለቲከኞችን ሃሳቦች ባለመሸመት መሆን አለበት። በተለይ ወጣቱ እኩይ ከሆኑ የዘረኝነት አስተሳሰብ በመውጣት በምክንያት ላይ የተደገፉ ሃሳቦችን በማራማድና በመደገፍ ለሀገር አንድነት ጠንክሮ መታገል አለበት። ለሀገር አንድነት አንድ ሆኖ መገኘት ውጤታማነቱን ከጀግኖች አርበኞች ታሪክ መማር ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም