የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአሁኑ ወቅት በግብአት አቅርቦት በተለይ በሲሚንቶ እጥረት በእጅጉ ፈተና ውስጥ መሆኑ ይታወቃል። የሲሚንቶ እጥረቱ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ፣ የፕሮጀክቶች ዋጋ እየናረ እንዲሄድ፣ ተቋራጮች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ ስለመሆኑም በተለይ የዘርፉ ተዋንያን አጽንኦት ሰጥተው ይጠቁማሉ። የዘርፉ ፈተና የግብአት እጥረት ብቻ አለመሆኑንም ነው እነዚሁ አካላት የሚያመለክቱት።
በቅርቡ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በቀጣይ ሊያዘጋጀው ላቀደው አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሰነድ ግብአት ለማሰባሰብ ከዘርፉና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመከረበት መድረክ ላይ እንደተጠቆመውም፤ ከግብአት አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ የፋይናንስ አቅርቦት እጦት፣ የተቋራጮች የመወዳደር አቅም ውስንነት ሌሎች የዘርፉ ፈተናዎች ሆነዋል።
የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ በአጠቃላይ የፋይናንስ እጥረት ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን ለማግኘት፣ ግብአቶችን ከውጭ ለማስመጣት ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል። ኢንዱስትሪው በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን መቸገሩን ተቋራጮችን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይጠቁማሉ።
መንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለውጭ ኩባንያዎች እየሰጠ ያለበት ሁኔታ እንዳሳሰባቸውም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ተዋንያን ይናገራሉ። በአጠቃላይ ዘርፉ ክፉኛ መታመሙን በመጥቀስ፣ ለመፍትሄው መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል። በአንድ ወቅት ኮንስትራክሽን ያበበባት ኢትዮጵያ አሁን ዘርፉ ለመቀዛቀዝ የተዳረገባት መሆኗ ተጠቁሟል።
አንዳንዶች ችግሩ ሰፊ መሆኑን በመጥቀስ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውድቀት አርገው ወስደውታል። በአንጻሩ ዘርፉ ብዙ ፈተናዎች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም እድሎች እንዳሉትም በመድረኩ ተጠቁሟል። አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀት ግብአት ለማሰባሰብ በተካሄደው መድረክ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሶስት ጥናቶች ቀርበዋል። ጥናቶቹ በኮንስትራክሽን ግብአት እንዲሁም በፋይናንስ አቅርቦትና ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በመፍጠር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ መድረኩ ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት ሀሳብ ሰፊ ጊዜ የሰጠና በርካታ ጉዳዮች የተነሰቡትም ነው።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለኢትዮጵያ መሰረታዊ ኢንዱስትሪ መሆኑን በመድረኩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ታምራት ሙሉ ይገልጻሉ። ከአገሪቱ ካፒታል በጀት ውስጥ ከ60 እስከ 65 በመቶው በኮንስትራክሽን ዘርፉ እንደሚንቀሳቀስ ጠቁመው፣ ስለአገር ልማት ሲታሰብ ቅድሚያ ኢንቨስትመንት ሆኖ የሚመጣው ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መሆኑን አመልክተዋል። የአገሪቱ የልማት አጀንዳዎች ሊሳኩ የሚችሉትም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፍጥነት ልክ መሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ የኮንትስትራክሽን ኢንዱስትሪው ካላደገ አገራዊ እድገትን ማሰብ አይቻልም፤ ይህን ኢንዱስትሪ ረስተን የትም መድረስ አንችልም ሲሉም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪው እንደ አገር ብዙ እድሎች አሉት። ከእነዚህ እድሎች ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የአስር አመቱ መሪ እቅድ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተያዘውን ራእይ ይጠቀሳል።
በእዚህ ራእይ ሁሉም ግቦች ወስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሚና ከፍተኛና ዘርፉ ለሁሉም ልማት መግቢያና ፈር ቀዳጅ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፤ ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ በአስር ዓመቱ እቅድ ከ102 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ፣ ከ28 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገዶችን ደረጃ የማሳደግና ማጠናከር ስራ፣ ከ3 ሺ ኪሎሜትር በላይ የባቡር መስመር ግንባታ፣ ከ4 ሚሊየን በላይ ቤቶች ግንባታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎችና ሌሎችም ግንባታዎች የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሚፈልጉ ናቸው።
እድሎች አንዳሉ ሁሉ አብረው ደግሞ ፈተናዎችም አሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ እነዚህን ፈተናዎች በአግባቡ መለየት፤ የሚፈቱበትን መንገድ ማስቀመጥና ዘርፉ ለአገር ማበርከት ያለበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አሁናዊ ችግሮች በመፍታት የኢኮኖሚ እድገት ፍላጎትን የሚመጥን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመፍጠር የዘርፉን ችግሮች የሚፈታና የእድገት ፍላጎትን የሚመጥን የአሰራር ስርአት መዘርጋት ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑንም አስታውቀዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ይህንን እድል በመጠቀም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ችግር መፍታት ያስፈልጋል። በእነዚህ እድሎች የተመለከቱ ግቦች ያለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪነትና ብቃት አይሳኩም። የዘርፉን ችግር መፍታት ለእነዚህ ግቦች መሳካት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በዘላቂነት ተወዳዳሪ ሆኖ አቅሙ ተገንብቶ እንደገና ለሚቀጥሉት የልማት ግቦች አቅም የሚሆንበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይም መስራት ይኖርበታል።
በአዲሱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሰነድ እንዲታይ የተጠቆመው አንዱ ጉዳይ የተቋራጮች የተወዳዳሪነት አቅምን ማሳደግን ይመለከታል። በአስር አመቱ አገራዊ እቅድ የአገር በቀል ተቋራጮችን የተወዳዳሪነት አቅም በማሣደግ ቢያንስ 75 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ድርሻ፣ ከዚያም ባለፈ ደግሞ ቢያንስ 25 በመቶ የሚሆኑን ሪጂናል/የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ/ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታቅዷል። አሁን ያለው የተቋራጮች የተወዳዳሪነት አቅም ግን አነጋጋሪ መሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል። ተወዳዳሪ መሆን መቻል ቀርቶ ኢንዱስትሪው ውስጥ መቆየትም ስጋት እየሆነ እንደሚገኝ ነው የተመለከተው።
መንግስትም በሚዘጋጀው አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንዱም ይሄው ሆኗል። የተቋራጮች የመወዳደር አቅም፣ የአማካሪዎችና የባለሙያዎች አቅም ግንባታ በመድረኩ በሰፊው ተዳሷል።
ሚኒስትር ዴኤታው ኢንጂነር ወንድሙ እንዴት ተደርጎ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መገንባት እንደሚቻል ሲናገሩ፤ ቅድሚያ ስራ አርገን የወሰድነው ትላልቆቹ ተቋራጮች በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር እንዲችሉ ማድረግ እንዲሁም ውድድሮችን መቋቋም የሚችሉ ኩባንያዎችን መፍጠር፣ ትንንሾቹ ደግሞ አቅማቸውን እየገነቡ እንዲሄዱ ማድረግ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ከዚህ አኳያ እንደ መንግስት ዘርፉን እንደሚቆጣጠር አካል የራሳችንን የአሰራር ስርአት ማስተካከል ላይ መስራት ይኖርብናል ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፣ ከዚህ አኳያ እስከ አሁን ስራ ላይ ያለውን የተቋራጭ፣ የአማካሪ እና የባለሙያ የምዝገባ መመሪያዎችንና የአሰራር ስርአቶችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
በአገሪቱ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች እና ባለሙያዎች ብዛትና ብቃት ጉዳይ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ መሆኑም በመድረኩ ተጠቁሟል። ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ በአገሪቱ አጠቃላይ ያለው ተቋራጭ ብዛት ከ26ሺ ይበልጣል፤ በቅርቡ ባለው መረጃ ደግሞ 22 ሺ ተቋራጭ ነው ያለው፤ ከዚህ ውስጥ በሚገባ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ደግሞ ሁለት ሺ995 ብቻ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት፤ አማካሪዎችን በተመለከተ ደግሞ አንድ ሺ ሶስት መቶ አካባቢ አማካሪዎች ናቸው በአገሪቱ እንዳሉ የሚታወቀው፤ አሁን ገበያ ላይ ያሉት ግን 285 ብቻ ናቸው። ወደ 138 ሺ እና 140 ሺ ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ በገበያው ውስጥ በየዓመቱ እያደሱ ያሉት ከ25 እስከ 26 ሺ የሚደርሱት ብቻ ናቸው።
‹‹በዚህ ላይ የውሸት ቁጥር ነው ያለን። ካሉን ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ተቋራጮች መካከል አገሪቱ ልትሰራ የምትፈልገውን አፋጣኝ ፕሮጀክት የሚሰራ ተቋራጭ ብንፈልግ 20 አናገኝም›› ሲሉም ጠቅሰው፣ ከ20ውም መካከል በተለያየ ምክንያት የሚንጠባጠብ እንደሚኖር ተናግረዋል። ይህን ማጥራትና ወደምንፈልገው ደረጃ ማምጣት ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከዚህ አኳያ የተቋራጮች፣ አማካሪዎችና ባለሙያዎች ምዝገባ ስርዓት ማሻሻል አለብን ብለን የጀመርነው ስራ አለ። ከባለሙያም አኳያ እንዲሁ ብቁ /ሰርቲፋይድ/ ያልሆኑ ባለሙያዎች ዘርፉ ውስጥ መቆየት አይኖርባቸውም፤ እንዲህ ስንል ስለብቃት /ኮፒተንስ/ ማሰብ ይጀመራል፤ እንዲህ ሲሆን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውም ገበያ ውስጥ ዘላቂ ሆኖ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ያስባል ብለዋል። ስለዚህ በብቃት የሚሰራበት ከባቢ መፍጠር ይኖርብናል፤ ከዚህ አኳያ ማሰልጠን፣ መመዘን፣ ሰርቲፋይድ ማድረግ ከዚያም የሙያ ፈቃድ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በቀጣይ የተቋራጮችን ደረጃ ለማውጣት አንዱ መስፈርት የሚሆነው ፕሮጀክት የመምራት አቅም ይሆናል። ቁጥር ብቻ ተይዞ ደረጃ አይሰጥም፤ ደረጃ የሚሰጠው የፕሮጀክት አስተዳደር ብስለት መስፈርት /ኢንዴክስ/ እየታየ ነው። አስር ኢንዴክሶች አሉ፤ በእነዚህ ኢንዴክሶች መሰረት የብቃት ደረጃው ከደረጃ ሶስትና ከዚያ በላይ የሆነ ብቻ ደረጃ አንድ ተቋራጭ እንዲሆን ይደረጋል።
ከዚያ በታች የሆነው ደግሞ እዚያው እንዳይቆም አቅሙ እየተገነባ ወደ ላይ የሚመጣበትን ስርአት ይገነባል። ይህም በአንዴ የሚፈጸም አይደለም፤ የስልጠና ሞጁሎች ተዘጋጅተዋል፤ የምዘና ሰርአትም እየተዘረጋ ነው፤ በዚህም በቅተው እንዲመዘኑ ይደረጋል። በስልጠናው የሚጎላቸው ነገር ካለም የሚገባቸው ደረጃ እየተሰጠ እንዲበቁ እየተደረገ ወደሚፈልጉበት ደረጃ የሚደርሱበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውንም እየተገነባ እንዲመጣ ይደረጋል።
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ /ሰርተፊኬሽን/ ጋር ይያያዛል፤ ከኢትዮጵያ ሚዲያ ወጥቶ ለመስራት የአይሶ የብቃት ማረጋገጫ፣ ዓለም አቀፍ የምዘና ስርእት፣ ዓለም አቀፍ የማኔጅመንት ሲስተም ሊኖር ይገባል። ይህን ማድረግ የሚቻለው ኩባንያዎቻችን በዚያ ደረጃ የተደራጁ፣ የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅምን የገነቡ ሲሆኑ ነው።
ይህን ስራ ደግሞ ለተቋራጮች ብቻ ሰጥተን የምንተወው አይደለም ሲሉ ኢንጂነሩ ተናግረዋል። ተቋራጮችም አማካሪዎችም የሙያ ማህበራትም ባላቸው አደረጃጀት በስራቸው ያሉ ኩባንያዎችን ባለሙያዎችን እያሰለጠኑ የሚያበቁበት፣ እኛም የራሳችንን ሚና የምንጫወትበት በዚያ ደረጃ ኢንስቲቲዩቶች የሚኖሩበትን ስርአት መፍጠር እንደሚገባም አስታውቀዋል። ይህ ሂደት ህጋዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያለው ስርአት ይሆናል ማለት ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ወጪ ሄዶ ተወዳድሮ መስራት የሚችል በአገር ውስጥ መቆየት /ሰስቴይን ማድረግ/ የሚችል ኩባንያ ለማፍራት በመጀመሪያ በዚህች አገር ውስጥ የኮርፖሬት ባህል/ ኮርፖሬት ካልቸር/ እንዲገነባ ማድረግ ያስፈልጋል። የኮርፖሬት ባህል ማለት አምስት ስድስት ኩባንያዎችን መጨፍለቅ አይደለም፤ ብቻውንም ቢሆን በሚገባ የተዋቀረ የኮርፖሬት የአሰራር ስርአት ያለው ተቋራጭ እንዲኖር ማድረግ ከተቻለ ጠንካራ ተቋም ማግኘት ተችሏል ማለት ነው።
የተቋራጮችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እኛ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት እንቀርጻለን፤ በዚህም መስፈርቶችን በማዘጋጀት ኩባንያዎችን በማብቃት ትልልቅ ኩባንያዎችን እንፈጥራለን ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፣ ይህ የሚሆነው ግን በሂደት ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ አንጻር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተለየ አሰራር/መካኒዝም/ ይፈልጋል፤ የቻይና ኩባንያ እዚህ አገር መጥቶ ለመስራት ድንገት አልመጣም፤ የአገሪቱ መንግስት ኩባንያው ወጥቶ ሰርቶ ገንዘብ እንዲያመጣ ይደግፈዋል። ከዚህ አንጻር የኛ አገር መንግስት ተቋራጮች ወጥተው አንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ላይ የሚመጣው ተወዳዳሪነት የሚባክነውን ሀብት ከመቀነስ ባሻገር የሚመደበውን ሀብት በውጤታማ መልኩ ስራ ላይ ማዋል የሚቻልበትን ከባቢ ይፈጥራል። ይህን ተወዳዳሪነት ከፈጠርን በኋላ ይህን ለውጥ /ዳይናሚክ/ የሚሸከም አዲስ ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አብቦ የነበረባቸውን የቀደሙትን ዓመታትም አስታውሰው፣ በዚያን ወቅት ላይ ያንን እድገት የሚጠብቅ ተግባር አልሰራንም፤ ቁጥር አበዛን፤ ተወዳዳሪነት ላይ ግን እዚህ ግባ የሚባል ተቋራጭ ሳናገኝ ቀረን ሲሉ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉትም፤ ከዚህ አንጻር አዲስ ለውጥ /ዳይናሚዝም/ መፍጠር ይገባል፤ ያለውን የገበያ እድል ማስፋት፤ አዳዲስ የገበያ እድሎች መፍጠር ያስፈልጋል። የዛሬ ሰባት ዓመት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደርሳለን ስንል መንገዱ ኮንስትራክሽን ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ኮንስትራክሽን የሚፈጥረው አሴት፣ ለውጥና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው መካከለኛ ገቢ ላይ የሚያደርሰን ብለዋል።
ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዘጋን ማለት መንገዱን ዘጋን ማለት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በየዓመቱ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንት እየጨመረ ነው፤ ከመጨመርም አልፎ ጥሩ ጥሩ ግንባታዎችም አሉ ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፣ ‹‹ሁሉም ሊባሉ በሚችል መልኩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው። የስራ ተቋራጮቻችንን የባለሙያዎቻችንን የአማካሪዎቻችንን ተወዳዳራነት ካላሳደግን በስተቀር እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች መቶ በመቶ ለውጭ ተቋራጮች ሊሰጡ ይችላሉ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ እዚህ ላይ መያዝ ያለብን ሁሉም አገሮች ያደጉበት መንገድ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ነበር። የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ግን የአጭር ጊዜ መሆን አለበት። በእነሱ ተሳትፎ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ቴክኖሎጂ እየተሸጋገረ እውቀት እየተቀሰመ ከዚያም የአገር ውስጥ ተቋራጭነት አቅም እያደገ መምጣት አለበት። የአገር ውስጥ ተቋራጮች ከውጪዎቹ ጋር ያላቸው ትስስር እንዲጠናከር ማድረግ ላይ መሰራት ይኖርበታል። እሰከ አሁን ያንን ጠንክረን አልሰራንበትም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህ የተነሳም በሚባለው ደረጃ ቱሩፋቱን ማግኘት አልተቻለም ይላሉ።
የቻይና ወይም የአውሮፓ ኩባንያ መጥቶ አይስራ ማለት የለብንም ሲሉ ተናግረው፣ እነሱም ይስሩ፤ እኛ ግን የተገነባውን ህንጻ፣ ድልድይ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ያለብን፣ እውቀት ቴክኖሎጂና ልምድ ማግኘት ላይ መስራት ይኖርብናል ብለዋል። ከዚህ አንጻር የውጭ ኩባንያዎች ሲመጡ ስንት እጁን ስራ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ሰጥታችሁዋል፤ ምን እውቀትና ቴክኖሎጂ አሸጋግራችኋል የሚል ስታንዳርድ እናስቀምጣለን፤ ይህ እስከ አሁን አልነበረም ››ሲሉም ጠቅሰው፣ ከዚህ አንጻር ሰፋ ያለ ስራ ከእኛ፣ ከእናንተ ከተቋራጮች ደግሞ ለእዚህ የሚያበቃ ዝግጁነት ይጠበቃል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015