አንድነት ኢትዮጵያዊነት የተሰራበት ድርና ማግ ነው። በታሪክ ድርሳን ላይ ባለታሪክ ህዝቦች ተብለን የተጠራነው አንድም በህብረታችን አንድም ሰላም ወዳድ ህዝቦች ስለሆንን ነው። በጋራ ተጉዘን ያልወጣነው ዳገት፣ ያላሸነፍነው መከራ የለም። ለዚህ ምስክራችን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ጠንስሶት አንድነት የወለደው ብኩርናችን ነው።
በኢትዮጵያ የታሪክ ሰነድ ውስጥ ተሰንደው የሚገኙ ታሪኮቻችን በጋራ የቻልናቸው ታሪኮቻችን ናቸው። ተለያይተንና ለብቻ ተጉዘን የቻልነው ታሪክ የለም። ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ረገድ የአሁኑን መልክ የያዘው በአንድነት በተጓዙ አገር ወዳድ አእምሮና ልቦች ነው።
ትላንትን ተያይዘን እንዳለፍን ዛሬም ለገጠሙን ችግሮች መያያዝ ነው የሚያዋጣን። ችግሮቻችን በልጠውን የመፍትሄ ሀሳብ አጥተን ባለመግባባት ውስጥ የቆምነው በጋራ ከመጓዝ ይልቅ ብቻነትን በመምረጥ አዝማሚያ ነው። የተጀመረው የእርቅና የሰላም ንቅናቄ ከዳር ደርሶ ታሪካችን ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲሸጋገር መያያዛችን መቀጠል አለበት።
ምንም እማኝ አያስፈልገውም፤ ችግሮቻችን በመለያየታችን በኩል የገቡ ናቸው። እነዚህ ቀዳዳዎች እስካልተደፈኑ ድረስ ሰላም ማምጣትም ሆነ ሰላማዊት አገር መፍጠር አይቻልም። ቀዳዳዎቻችንን ደፍነን የአንድነት አገር ለመፍጠር ከመለያየት ማጥ ውስጥ ወጥተን በጋራ መጓዝ አለብን።
መለያየት ማቅ ያለብሳል። መለያየት ሰላምን ነጥቆ የማንግባባባቸውን የንትርክ አጀንዳዎች ከመስጠት ባለፈ እርባና የለውም። ከምንም በላይ ሰላም የሚያስፈልገን ህዝቦች ነን። ከምንም በላይ ብሄራዊ መግባባት ያስፈልገናል። እነዚህ የተስፋ ጭላንጭሎች በሁላችንም ላይ ብርሀናቸውን እንዲረጩ ለሰላም ሂደቱ ሀሳብ በማዋጣት የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል።
ኢትዮጵያዊነት አንድነት ያሾረው የጋራ ድር ነው። በትላንት በአባቶቻችን የእውነትና የእምነት፣ የፍቅርና የአብሮነት እቅፍ የተገመደ ነው። በጋራ ባህል፣ በጋራ ታሪክና ልማድ የጠነከረ ነው። ዛሬ ላይ በፅንፈኛ ብሄርተኝነት ስም የሚላላና የሚበጠስ ማንነት አይደለም።
አገራት የበለጡን አንድነታቸውን አጠንክረው ባለመያዛችን ነው። ለአፍሪካውያን ባለውታ ነን፣ ለዓለም ጥቁሮች የትንሳኤ ጮራ ነን . . . እንላለን። ይሁን እንጂ ዛሬ ለራሳችን መሆን እንኳን እየቻልን አይደለም። ችግሮቻችን ወደ ጦርነት እየወሰዱን ነው፣ በጋራ ተግባቦት ጠንካራ አገር ለመፍጠር እየተንገዳገድን ነው።
አብሮነት በጠንካራ ልቦች ውስጥ የበቀለ በቅሎም የጸደቀ፣ ጸድቆም ፍሬ ያፈራ የለውጥና የተሀድሶ ፍልስፍና ነው። ለአገራችንም ሆነ ለራሳችን አስፈላጊ ሆነን ለመቆም በውስጣችን የመያያዝ መንፈስ ሊኖር ይገባል። ስናብር እናምራለን፤ ስናብር ከራሳችን አልፈን እንደጥንቱ ዘመን አፍሪካን ቀና የሚያደርግ ልዕልና እንላበሳለን።
ካበርን ያለምነውን ሆነን ለመገኘት እንችላለን። ከቻልን እንለወጣለን። ከተለወጥን ደግሞ በኢኮኖሚና በፖለቲካ በማህበራዊ ህይወታችን የተሻለችውን ኢትዮጵያ በመፍጠር ረገድ የተሳካልን እንሆናለን። ከሁሉ በፊት ግን ትግላችን አብሮ ሊያቆመን የሚችል የአንድነት መንፈስን ማዳበር ላይ መሆን ይኖርበታል። አብሮ በመቆም ሳንዳብር ከላይ የተመኘናቸው ምኞቶቻችን እውን አይሆኑም።
ታላቁ መጽሐፍ ፍቅርን የሕግ ፍጻሜ ይለዋል። በዛው ቅዱስ ቃል ላይ ወንድሞች በህብረት እንዲቀመጡ የሚመክር እየሱሳዊ ቃል አለ። በዚህ ሁሉ ምክንያት አብሮነታችን በብዙ መንገድ ጠቃሚያችን ሆኖ እናገኘዋለን። ፍቅር ከምንምነት መውጫ መንገዳችን ነው። አንድነት ከምንምነት ወደ ተዐምር ፈጣሪነት የምንሸጋገርበት የኃይል ሞገዳችን ነው።
በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተከሰተው የህይወትና የኑሮ ልዩነት በማመንና ባለማመን መካከል የተፈጠረ ነው። አለማመን መነጠል ነው። ማመን ደግሞ መዋሃድ ነው። ዓለማችን የሚገነባው ባሰብነው፣ ባመንነውና በይቻላል መንፈሳችን በኩል እንደሆነ የሚናገሩ በርካታ የስነልቦና ባለሙያዎች አሉ። የዚህን ሁሉ ማሰሪያ ገመድ ደግሞ “አንድነት” ሲሉ ይጠሩታል።
እንደ አገር የደመቅንው ኢትዮጵያዊ ተብለን እንጂ በዘርና በማንነታችን አይደለም። አሁንም ከድንዛዜ ወጥተን ወደ ቀደመ ድምቀታችን እንድንመለስ የአንድነታችንን ሰንደቅ የሆነው ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። ፍቅር የጸሀይ ግርዶሽ የለውም። ሁሌም ብርሀን፣ ሁሌም ትንሳኤ ነው። ወንድማማችነት ስ(ሰ)ባሪ የለውም። የኃይልና የአስፈሪነት ወሰን ነው።
የትንሳኤአችንን ብርሀን በጽልመት ደመና የጋረድንው ራሳችን ነን። እንዳንታይ፣ እንዳንደምቅ፣ እንዳንበራ ራሳችንን የከለልነው ራሳችን ነን። የፍቅር ጨረቃችንን በጥላቻ ሰውረን አገር ለመስራት የምንደክም፣ የተስፋ ሰንደቃችንን በራስ ወዳድነት አሳድፈን ሩቅ ለመሄድ የምንታትር ነን።
መጀመሪያ በጥላቻ የጋረድናት የፍቅር ጨረቃችን ትውጣ። በአክራሪ ብሄረተኝነት ስም የደበቅናት ኢትዮጵያ ከደመናው መሀል እንድትወጣ ጭጋጉን ልናጠራላት ይገባል። ፍቅር ደመና የለውም። የፍቅር መልኮች ብርሀናማ መልኮች ናቸው። በፍቅር ካልሆነ ወዳለምነው ሩቅ አንባ መሄድ አይቻለንም። በአንድነት ካልሆነ ከወጠነው የስኬትና የስልጣኔ ወደብ አንደርስም።
እየሄድንባቸው ያሉ መንገዶች በጽንፈኛ ብሄርተኝነት የተበጁ፣ የእኔ፣ የአንተ . . . በሚል ፖለቲካ ወለድ እሳቤዎች የታነጹ እየሆኑ ነው። እነዚህ መንገዶች ሩቅ አልወሰዱንም። አለያይተው እዛና እዚህ ከማቆም ባለፈ ወደ እምንፈልገው የአንድነት ጥግ አያደርሱንም።
መንገዳችንን መቀየር አለብን። መንገዳችንን እስካልቀየርን ድረስ መድረሻችንን ማስተካከል አንችልም። የመጣንበት መንገድ አባቶቻችን የሰሩልን የአንድነት ጎዳና ቢሆንም የምንሄደው ግን ተለያይተን ነው። በብዙ ነገር ላይ ቀዳዳዋ የበዛ አገራችንን ለመታደግ የሎጥ መንገድ ያስፈልገናል።
ሎጥ ከሰዶም ሲወጣ ሚስቱ በተራመደችበት መንገድ አልነበረም። እሱ ቀኙን ሲመርጥ እሷ ግራዋን መርጣ ለብዙ ዘመን አብረው የኖሩ ባልና ሚስት እዛጋ ተለያዩ። እሷ የጨው ሀውልት ስትሆን እሱ የክብር ዘውድ ደፋ።
ወደ ክብርና ወደ ከፍታ የሚወስደንን የሰላምና የአብሮነት መንገድ መስራት መጪውን ጊዜ በበጎ እንድናይ የሚያደርግ ነው። ዋጋ እያስከፈለን ካለው መንገድ ፈቀቅ ማለት አለብን፤ ለሌላ ጥፋት ራስን ማዘጋጀት ነውና አቅጣጫችንን መቀየር አለብን። ከፊታችን ለአንድነታችን መንገድ የሚጠርግ አገራዊ ምክክር አለ። ተቀያይመን ከሆነ ታርቀን፣ ተኮራርፈን ከሆነ ይቅር ተባብለን የጠሸለችውን ኢትዮጵያ መፍጠር አለብን።
ስልጣኔ አብሮነት ነው። ስልጣኔ የብቻን መንገድ እያፈረሱ የጋራ ጎዳናን መገንባት ነው። ፍቅር ካለን በቂዎች ነን። አቅማችንን የሰረቀብን ጥላቻ ነው። በሚገባን ከፍታ ላይ እንዳንቆም ያደረገን ዘረኝነት ነው። ሰንኮፎቻችንን ወደ ኋላ እየጣልን አዲስ መንገድን ማበጀት ከሁላችን የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።
እውነት ነው ድሆች ነን። ሌሎች “አይችሉም” ብለውን ሊሆን ይችላል፤ ብዙ ነገሮችን ሞክረን አልተሳኩልን ይሆናል። በአንድነት የቆምን ጊዜ ግን ነገሮች መልካቸውን እንደሚቀይሩ ልናምን ይገባል።
ኢትዮጵያ እንድትታደስ ራሳችንን እናድስ። የእኛ መታደስ ከበጎ ሀሳብ የሚጀምር፤ በበጎ እውቀት የሚጠናቀቅ መታደስ ነው። በህይወታችን ብሎም በኑሯችን ውስጥ ድንቅ ነገር እንዲከሰት ከፈለግን ደካማ መንፈሶቻችንን አድሰን፣ አልችልም ባይነታችንን ገለን በአንድነት ኃይል የእንችላለንን ንቅናቄ መቀላቀል ይጠበቅብናል።
በፍቅርና በአብሮነት፤ በይቻላልም መንፈስ ወደ ፊት መራመድ ከቻልን የጠየሙ ታሪኮቻችንን የማይቀየሩበት ምንም ምክንያት አይኖርም። የምንፈልገውን ለማግኘት መሮጥና መልፋት ብቻውን ዋጋ የለውም። ሩጫ ከፍቅርና ከወዳጅነት ጋር ሲሆን ነው የሚጎመራው። ራሳችንን በበጎ ሀሳብ የሞላን ማግስት ነው ጽንፈኝነትን ተሻግረን በፍቅርና ፍቅር በሚወልደው መከባበር እና አንድነት አገራችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ማቆም የምንችለው።
ጽንፈኝነት የአገር ፍቅርን ይገድላል። የአገር ፍቅር ስሜት ያለው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ነው። አሁን አሁን ኢትዮጵያዊነትን ሽረው፤ ጽንፈኝነትን የሚካድሙ ጥቂቶች አይደሉም። እኚህ ማንነቶች ለኢትዮጵያ ሰላም ጠንቅ የሆኑ፣ እድገትና ብልጽግናዋን የማይሹ እንደሆኑ ነጋሪ አያሻም። ነብዩ መሀመድ እንዳሉት ”ዘረኝነት ጥንብ ናት” አገር ከማርከስ፣ ትውልድ ከመመረዝ ባለፈ እርባና የላትም።
አሁን እንደ ትውልድ ስለኢትዮጵያ ስናስብ ውስጣችን የሚሰማን ስሜት ምን አይነት ነው? ስለድሀ ህዝብ ስናስብ ምንድነው የሚኮረኩረን? የለውጥና የመታደስ ስሜት ከሆነ ልክ ነን። የማደግና የመበልጸግ እልህ ከሆነ እንግፋበት።
ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ ስሜታቸው አንድ አይነት ፍቅርና አብሮነት ነው። ውስጣችን ፍቅር ካለ ወዴትም ብንሄድ አሸናፊዎች ነን። የፍቅር ልቦች አይዝሉም። የፍቅር ሀሳቦች አገር ከመገንባት ሌላ እውቀት የላቸውም።
አሁን ያሉብን ኢኮኖሚያዊም ሆኑ ፖለቲካዊ እድፎች በእኛው ተቀምጦ መነጋገር የሚጠሩ ናቸው። ጎዳናችንን ማንም መጥቶ እስኪጠርግልን መጠበቅ የለብንም። ወጀቡ አጠገብ ቆመን መሻገሪያ ድልድያችንን መገንባት እንጂ ሌሎች መጥተው እስኪያሻግሩን መጠበቅ ሞኝነት ነው።
ሙሴ ባህር አሻጋሪ የሆነው በቀና ልቡ ነው። ሙሴ አንደበተ ርቱኡ አልነበረም። ባለ ጉልድፍ አፍ ነበር። በውስጡ ግን እልፍ በጎነት ስላለ ፈጣሪ ለህዝቡ እሱን መረጠ። ከሙሴ የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ሙሴ የተመረጠው በቅንነቱ ነው። እኛም አገራችንን ከጦርነትና ከጥላቻ ለመታደግ ተቀምጦ መነጋገርን መልመድ አለብን።
እንደ መንግስትም እንደ ዜጋም ለአገራችን አስፈላጊዎች እንድንሆን የሰላም ሀሳብ ሊሞላን ይገባል። ከምንም የቀደመ በአገር አውድ ውስጥ መሰረት ያለው የሰላም ሀሳብ ነው። ተነጋግረን ስንግባባ፣ ተግባብተን አብረን ስንቆም ነው ባለታሪክ የምንሆነው። ሰላም የሌላት አገር ታሪክ የላትም። ሰላም የሌለው ህዝብ ራዕይ አልባ ነው። ለሰላማችን ሁሉንም አይነት መስዋዕት በመክፈል አብሮነታችንን ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ዋስትናችን ነው።
በአንድነት ከቆምን ከራሳችን አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ ብርሀን አለን። ብርሀናችን ከጥላቻ ጉም ልንታደገው ይገባል። እንደ አገር ብዙ ነን። በባህል፣ በታሪክ፣ በስልጣኔ እልፍ ነን። ይሄ ሁሉ ብዙሀነታችን ግን በጽንፈኝነት በትር ሸኮናውን ተብሎ የእንቅብ ውስጥ መብራት እንዳይሆን መንቃት አለብን።
ራሳችንን ለአብሮነት ካስገዛን አሁን ካለንበት በመነሳት ወደ እምንፈልግበት ከፍታ መድረስ እንችላለን። የፍቅር ጽንሰ ሀሳብ የለውጥና የእድገት ቀመር ነው። የአንድነት እሳቤ የመሻገርና የመታደስ ንቅናቄ ነው። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ራሳችንን ስናጥር ነው ከህልም ዓለም ቅየታችን የምንነቃው።
አሁን ካለንበት የስንፍናና የስልቹነት ብሎም ጽንፍ የረገጠ የዘረኝነት እሳቤ ወጥተን ለህዝብ ወደ’ሚበጅ ማንነት እንመለስ። በስራችን፣ በተግባራችን ባለንበት የስራ መስኩ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት የሚፈልገውን የባህሪ ለውጥ በማምጣት ለአገርና ህዝብ ከሚቆረቆሩት፣ ከምርጦቹ ጎን መሰለፍ እንችላለን። ለውጥ ራስን ከመለወጥ፤ አመለካከትን ከመግራት የሚጀምር ነው። የራስ ለውጥ ነው ወደ አገርና ወደ ማህበረሰብ ደርሶ የምንፈልገውን የሚሰጠን።
ወርቃማ እድሎቻችን በወርቃማ ሀሳቦቻችን ውስጥ የተቀመጡ ናቸው። ወርቃማ ሀሳቦች ሁልጊዜም መፍትሄ አመንጪ የሰላምና የእርቅ አንደበቶች ናቸው። አንደበታችን ስለሰላም እንዲናገር፣ ልባችን ስለእውነት እንዲነቃ ካጸናነው አሁን እየሆነ ካለው የዘር ፖለቲካ ወጥተን ለሁላችን የምትሆንን ኢትዮጵያ መገንባት እንችላለን።
ኢትዮጵያ ዛሬ ብቻ አይደለም፣ ነገም አለች። ዛሬና ከዛሬ ቀጥሎ በሚኖረው ኢትዮጵያዊነታችን ውስጥ ሰላምን አንቆ የሚገል ሳይሆን ወልዶ የሚያሳድግ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ያሻናል። ይህንን መሰሉ ልምምድ ነው ከችግሮች አውጥቶ ወደ ከፍታ የሚያመጥቀን።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለማመድናቸው ልምምዶች ዋጋ ሲያስከፍሉን እንደነበር ለሁላችንም ግልጽ ነው። የጥላቻ ልምምድ ጥላቻን ከመውለድና ነውረኛ እሳቤን ከማስፋፋት ሌላ ዓላማ የሌለው የሰነፎች ልማድ ነው። ኢትዮጵያን የምንወድ፣ እኛ ግን በሰላም ሀሳብ ሰላማዊ አገር ለመፍጠር ዛሬውኑ መሰረት እንጣል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015