በየጊዜው የሚስተዋለው ፈጣን የከተሞች ዕድገት እሰየው ያስብላል። ቀድሞ በአሮጌ ገጽታቸው የሚታወቁ በርካታ አካባቢዎች ዛሬ በዘመናዊ ሕንጻዎች ተተክተዋል። ትናንት ያለአንዳች ፋይዳ ዓመታትን የዘለቁ ስፍራዎች አሁን ይበል በሚያስብል ተግባራት መታየት ጀምረዋል።
እንደ እኔ ዕምነት በየጊዜው ይህን መሰሉን ለውጥ ማስተዋል በጎውን ትርጉም ከፍ ያደርጋል። ለምን ከተባለም በነዚህ ለውጦች ውስጥ ሌሎች በርካታ የእድገት እርከኖች ስለሚኖሩ። እውነት ነው የአንድ አካባቢ መለወጥና ማደግ ጠቀሜታው ለአንድ ወገን ብቻ አይደለም። በየጊዜው ታላቅ የለውጥ ግሰጋሴ በተፈጠረ ቁጥር ሌሎች በርካቶችም የቱርፋቱ ተቋዳሾች ይሆናሉ።
አንዳንዴ ግን በአንዲህ አይነቶቹ ለውጦች መሐል የሚታዩ እንከኖች ከፍ ያለችግር ሲያስከትሉ ይስተዋላል። ለምሳሌ የመንገድ ግንባታዎችና ተያያዥ ችግሮቻቸው።
ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ለከተሞች ለውጥና ዕድገት መኖር የመንገድ ግንባታዎችም ከፍ ያለ አስተዋፅዖ አላቸው። ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ መንገዶቹ ሲጀመሩ አንስቶ እስኪጠናቀቁ ድረስ የሚስተዋሉ ችግሮች ደግሞ በአሳሳቢነታቸው ይጎላሉ።
ለአብነት የሚሆን አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። እርስዎ በሚኖሩበት፣ አልያም በሚሠሩበት አካባቢ አንድ ቁፋሮ እየተካሄደ ነው። ይህ ቁፋሮ ረዘም የሚል መንገድ በመያዙ በአንድ ስፍራ ተገድቦ የሚቆይ ላይሆን ይችላል። ርቀቱን እየጨመረ፣ ጉድጓዱን እያጠለቀ የሚካሄደው ቁፋሮ በራሱ ብቻ አለመገደቡ የእግረኛ መንገዱን አስፋፍቶ ይዟል።
ይህ ብቻ አይደለም። የግንባታ ግብዓቱ ባልተገባ ቦታ በመዘርገፉ መራመጃ መላወሻ ይሉት መንገድ አይኖርም። ይህ አጋጣሚ ደግሞ በአካባቢው ለሚንቀሳቀስ ሁሉ ፈተና ሆኖ ይውላል። መንገዱ በእጅጉ መጨናነቁ በእግረኞች ብቻ አይወሰንም። የጎዳናውን ዳርቻ ተጠግተው የሚተላለፉ ተሽከርካሪዎች ሳይቀሩ ስፍራውን የሚሻሙት ይሆናል።
ወዳጆቼ እዚህ ላይ ለአብዛኞቻችን ስጋት የሆነን አንድ ጉዳይ ልብ እንድትሉት እሻለሁ። በእግረኞች መንገድ ላይ የተቆፈረው ጉድጓድ ሳያንስ የግብዓቱ መሙላትና የመኪኖች መተራመስ ብዙዎችን ለትራፊክ አደጋ እያጋለጠ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ በትራፊክ አደጋ ሰዎች ሲሞቱ፣ አልያም ሲጎዱ ሊቀርብ የሚችለው ሪፖርት የተለመደው ዓይነት ነው። የአደጋው ዝርዝር ሁኔታና ዕለታዊ ሁኔታዎች ብቻ። ሁሌም በሪፖርቱ መስማት እንደለመድነው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑ ተጠቅሶ ይታለፋል። ምን አልባትም በእንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮች ትኩረት አይሰጣቸውም።
እንዲህ በሆነ ቁጥር ግን ችግሮች ከስሩ እንዳይቀረፉና እንዲባባሱ ምክንያት ይሆናል። በየጊዜው አካፋና ዶማቸውን ይዘው የእግረኞች መንገድን ለሚጋፉትም ኃይልና ብርታት እንደ መስጠት ይቆጠራል።
በአንዳንድ ስፍራዎች ለከባድ መኪኖችና አውቶቡሶች ሲባል የሚሠሩ መንገዶች ከያዙት ዓላማ አኳያ ግንባታቸው ለየት ያለ ትኩረት የሚሰጠው ነው። መንገዶቹ ጥራት፣ ስፋትና ጥንካሬ የተላበሱ እንዲሆኑም ልካቸውን የሚመጥን በጀት ተይዞ ግንባታ ይካሄድባቸዋል።
የመንገዶቹን ግንባታ ስንመለከት ሁላችንም እንደዜጋ የሚሰማን በጎ ስሜት ይኖራል። ትናንት በድንጋይ አልያም በጭቃማነት ገጽታው የምናውቀው ስፍራ ተለውጦ በዘመናዊነት ስናየው ከልብ ደስ ይለናል። ግንባታው ተጀምሮ የሚያልቅበትን ጊዜ እንናፍቃለን። የነገውን ውጤት አሻግረን እናያለን።
አንዳንዴ ግን እነዚህ ታላላቅ መንገዶች በታሰበው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ዋጋ ሲያስከፍሉ እናያለን። እንዲህ በሆነ ጊዜ ዋና የሚባሉ አዳዲስ መንገዶች ላይ ያልተገባ እንቅስቃሴ ይስተዋላል። በነዚህ መስመሮች መኪኖች ያለቦታቸው ይጓዛሉ። የፈረስ ጋሪዎች፣ ባጃጆች፣ እግረኞች በእኩል ይጋፋሉ።
ጥቂት የማይባል በጀት የፈሰሰበት፣ የመንገድ ግንባታ በጊዜ ያለመቋጨቱ ብዙ ሊገኝበት የሚችለውን ጥቅም እንደዋዛ ያሳጣል። በዚሁ ልክም ሥርዓት አልባው ጉዞ የትራፊክ አደጋውን ለማባባስ ምክንያት ይሆናል። ቁፋሮው ጉድጓድ፣ ጉድባና ሌሎች መሰናክሎች አሁንም ለመንገደኞች እንቅፋት ሆነው ይቀጥላሉ።
ይህን ጉዳይ በዚህ መልኩ ስንቃኝ ለችግሩ መከሰት ምክንያት በምክንያትነት ለሚጠቀሱ አካላት ደግሞ እውቅናን መስጠት ያስፈልጋል። ለተመሳሳይ ዓላማ ቦታውን የሚቆፍሩ አንዳንድ አካላት በስፍራው ሲገኙ ሊደርስ የሚችለውን ችግር አስቀድሞ በመከላከል ነው።
እነዚህ ተቋማት አካባቢውን ከጉዳት ለመጠበቅ በቁፋሮው ዙሪያ ጽሑፍ የታተመበት ባለቀለም ሪቫን ያስራሉ። ይሔኔ በስፍራው የሚንቀሳቀስ ሁሉ ምልክቱን እያስተዋለ ራሱን ከጉዳት ይጠብቃል። እንዲህ ማድረጋቸው የሰውን ሕይወት ሀገርን ሀብትና ንብረት ከጥፋት ለመታደግ አስተዋፅዖው የጎላ ነው።
በከተማችን የአስፓልት ዳርቻዎች የሚስተዋሉ ሕገወጥ ንግዶች ዓመታትን አስቆጥረዋል። በሥራው ያሉ ነጋዴዎች ከሸማቹ በቀጥታ ለመገናኘት ቀዳሚ ምርጫቸው የመንገድ ዳርቻዎች ናቸው። የዚህ ዓይነቶቹ ተግባራት ባብዛኛው የእግረኞችን መንገድ አስፋፍተው የሚይዙ ከመሆናቸው ጋር ለብዙኃን መሰናክል ሲሆኑ ቆይተዋል።
በስፍራው የሚዘወተረው የንግድ እንቅስቃሴ በተለይ ምሽቱን ይዞ የሚካሄድ ከሆነ የችግሩን ስፋት ይበልጥ ያጎላዋል። ብዙ ግዜ እንደሚስተዋለው እነዚህ ዳርቻዎች ለእግረኞች ፈጽሞ የተከለከሉ እስኪመስሉ የተጨናነቁ ናቸው።
በአጋጣሚ ጠርዙን ተከትሎ በአካባቢው የሚያልፍ መንገደኛ ቢኖር እንደነውር ሊቆጠርበት ይችላል። ምናልባትም ቦታውን አስፋፍተው ከያዙት ነጋዴዎች ውግዘትና ተቃውሞ ሊደርስበትም ይችላል።
አንዳንዴ ደግሞ መንገድ ሲዘጋጋ አማራጭ ፈላጊዎች በእግረኞች መንገድ መጓዝን እንደመብት ይቆጥሩታል። ዋናውን አስፓልት ለቀው በእግረኞች መራመጃ ላይ ሲጓዙ የማንም ፈቃድ አያሻቸውም። እንደውም መንገደኞች መንገድ ያለመልቀቃቸውን ጥፋት አድርገው በጡሩንባ እያጨናነቁ በስድብና በቁጣ መብት መንጠቅ ልማዳቸው ይሆናል።
በዚህ አይነቱ ልማድ የሚታወቁት አንዳንድ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ ሞተረኞችና ሕግ አልባ የቤት መኪኖች ፊትና ኋላ እየተመራሩ ጎዳናውን ሲያጨናንቁ ሕግ አክብሮ የሚጓዘው እግረኛ መድረሻ የሚያጣበት አጋጣሚ የሰፋ ነው። እናም መንገድ መንገደኞችና ሕግ በአግባቡ ታርቀው እንዲጓዙ ማስተዋል ያሻል መልዕክታችን ይሁን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015