ዘመናዊ የግብይት ስርዓትን ይዞ የመጣው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስራ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል:: በግብርና ምርቶች የነበረውን ኋላቀር የንግድ ስርዓት ዘመናዊ በማድረግ የግብርና ምርቶች ግብይትን ዘመናዊና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የተቀላጠፈ የግብይት ስርዓት በአገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን አስችሏል:: ይህ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ታዲያ አርሶ አደሩን፣ ኤክስፖርተሩንና አጠቃላይ በንግድ ስርዓት ውስጥ ያለው ተዋናይ በሙሉ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል::
ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ አርሶ አደሩ ተመጣጣኝ ክፍያ ማግኘት እንዲችልና ነጋዴው በቆረጠው ዋጋ አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሸጥ እንዳይገደድ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል:: የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ዘመናዊ በሆነ መንገድ ምርት ማገበያየት የጀመረው የወዲያው ግብይት (Spot Trade) በሚባል የግብይት ስነዘዴ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀውን የግብይት ስነዘዴ መጠቀም የግድ በመሆኑ የወደፊት ግብይት ስነዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ችሏል::
በዕለቱ የገበያና ግብይት አምዳችንም የወዲያው ግብይትና የወደፊት ግብይት ምንነትን እንዲሁም የሚኖረውን ፋይዳ አስመልክቶ ከባለሙያ ጋር ቆይታ አድርግናል:: የወዲያው ግብይት ከወደፊት ግብይት ጋር ያለውን ልዩነትና የሚኖረውን አበርክቶ ያስረዱን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና የግብይት መምሪያ ኃላፊ አቶ በረከት መሰረት ናቸው::
እሳቸው እንዳሉት፤ የወዲያው ግብይት ገዢና ሻጭ ዛሬው ተዋውለው ዛሬው ግብይት የሚፈጽሙበት ሂደት ሲሆን የወደፊት ግብይት ስነዘዴ ግን ወደፊት ስለሚከናወን ግብይት ዛሬ ላይ ውል ማሰር ነው ይላሉ:: ይህም ማለት አርሶ አደሩ ወደፊት ለሚያገኘው ምርት ዛሬ ላይ አስቦና አቅዶ ይንቀሳቀሳል:: በዚህም ላመረተው ምርት፣ ገበያ አገኛለሁ አላገኝም የሚል ስጋት አይኖረውም:: ኤክስፖርተሩም በተመሳሳይ ከማን ምን፤ መቼና ምን ያህል መጠን ምርት እንደሚያገኝ አስቀድሞ ያውቃል:: ለዚያም ከወዲሁ ዝግጅት ያደርጋል::
የወዲያው ግብይት ገዢም ሻጭም ምርትና ገንዘባቸውን ወደ ግብይት ስርዓቱ በማምጣት ግብይታቸውን ፈጽመው በሚቀጥለው ቀን ክፍያ የሚፈጸምበት የአሰራር ስርዓት መሆኑን የገለጹት አቶ በረከት፤ ምርት ገበያ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በዚሁ የግብይት ስነዘዴ ሲሰራ መቆየቱን አንስተው፤ ዛሬ ላይ ግን ዘመኑ የሚጠይቀውንና በዓለም አቀፍ የግብይት ማዕከላት ውስጥ ግብይት እየተፈጸመበት ያለውን የወደፊት የግብይት ስነዘዴን በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ነው ያመላከቱት::
የወደፊት ግብይት (Customized Forward Trade) የተባለውን ስነዘዴ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ መሆኑን ያነሱት አቶ በረከት፤ የወደፊት ግብይት መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ ገዢና ሻጭ ዛሬ ላይ ሆነው ወደፊት በሚፈጸም ውል የግብይት ቀንና የግብይት ሁኔታዎችን የሚመርጡበት እንዲሁም እነሱ በመረጡበት አግባብ ግብይት የሚፈጽሙበት ስርዓት መሆኑን ያስረዳሉ፤ እሳቸው እንዳሉት ገዢና ሻጭ ዛሬ ላይ ሆነው ምን አይነት ምርት፣ በምን አይነት የጥራት ደረጃ፣ በምን ያህል መጠን፣ በምን አይነት መረካከቢያ እንዲሁም ግብይት የሚፈጸምበትን ጊዜ ከወዲሁ በመወሰን የሚፈጸም የግብይት ስነዘዴ ነው::
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ እያስተዋወቀ ያለው የወደፊት ግብይት ስነዘዴ፤ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ስንል ላነሳነው ጥያቄ አቶ በረከት ሲመልሱ፤ የወደፊት ግብይት ከወዲያው ግብይት በበለጠ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመጥቀስ ነው:: እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በነበረው በወዲያው ግብይት ገዢም ሆነ ሻጭ ግብይት ለመፈጸም ገንዘቡንም ሆነ ምርቱን አስቀድመው በምርት ገበያው ቋት ውስጥ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል:: ነገር ግን በወደፊት የግብይት ስነዘዴ ዛሬ ላይ ሆነው የዛሬ ሶስትና አራት ወራት ለሚፈጽሙት ግብይት ውል ማሰር ይችላሉ:: ይህም በወቅቱ ገዢው ገንዘቡን አምራቹም ምርቱን ይዞ ካልመጣ ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ መግባት እንዳይችሉ የሚያደርገውን ቅድመ ሁኔታ ማስቀረት ያስችላል ነው ያሉት::
ለአብነትም አምራች አርሶ አደር ግንቦትን ጨምሮ ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴ አርሶ ጥቅምትና ኅዳር ላይ ምርት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ቢሆንም በወዲያው ግብይት ምርት ካልያዘ በስተቀር ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ መግባት አይችልም ነበር:: አሁን ላይ ግን ተግባራዊ በተደረገው የወደፊት ግብይት ስነዘዴ፣ አርሶ አደሩ ዛሬ ላይ ሆኖ ጥቅምትና ኅዳር ለሚደርሰው ምርት ከገዢው ጋር ውል ማሰር ይችላል:: ይህም ዛሬ ላይ ያለውን የገበያ ዋጋ እንዲሁም ነገ ምርቱ ሲደርስ በሚኖረው የገበያ ዋጋ መካከል የሚፈጠሩ መዋዠቆች ቢኖሩም ይህን ለመከላከል ከወዲሁ ግብይቱን ጤናማ በሆነና ውድድርን መሰረት በማድረግ ውል መዋዋል ይቻላል:: ይህም ያልተጠበቀ የዋጋ መውጣትና መውረዶችን ለማስወገድ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል::
‹‹ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱ የተለያዩ የገበያ አማራጮችን የሚሰጥ ነው›› ያሉት አቶ በረከት፤ አንደኛው አማራጭ በወዲያው ግብይት ምርትና ገንዘብ አስቀድመው በማምጣት የሚገበያዩበት ሲሆን፤ ሌላው አማራጭ ምርትም ገንዘብም ወደፊት እንደሚያመጡ ታሳቢ በማድረግ ግብይት የሚፈጽሙበትን ዕድል ይሰጣል:: ይህም አምራቹ የትኛውን ምርት ቢያመርት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል አስቀድሞ መተንበይ የሚያስችለው እንደሆነ ተናግረዋል:: አምራቹ ቀድሞ ውል መዋዋል ከቻለ በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ ቢጨምር ቢቀንስ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በሚኖራቸው ድርድርና በውላቸው መሰረት የሚያስተካክሉ ይሆናል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ ወድቋል በሚል ምርቱ አይወድቅም:: ይህም ለአምራቹ የሚሰጠው ጠቀሜታ አዋጭና አበረታች እንደሆነ ተናግረዋል::
በተመሳሳይ ከኤክስፖርተሮች አንጻር የወደፊት ግብይት ስነዘዴ ያለውን ጠቀሜታ ያስረዱት አቶ በረከት፤ በአገሪቱ ያለው የኤክስፖርት ሂደት ቀጣይነትና ዘለቄታ ያለው የአቅርቦት ትስስር ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ የውጭ ገዢዎች በአገር ውስጥ ካሉ ኤክስፖርተሮች ጋር ግብይት ለመፈጸም ያላቸው ትስስር ዘላቂ አይደለም:: ለአብነትም በዚህ ዓመት ሰሊጥ የገዛ አንድ የውጭ ገዢ በቀጣይ ዓመትም ከኢትዮጵያ ገበያ ይህን ያህል ሰሊጥ ወይም ሌላ ምርት እገዛለሁ ብሎ ያቅዳል:: ነገር ግን ምርቱን ማግኘት የማይቻልበት አጋጣሚ ይፈጠራል:: ይህም ቀጣይነት ያለው የአቅርቦት ሰንሰለትን ከማጠናከር አንጻር ክፍተት ፈጥሮ ቆይቷል:: ስለዚህ በወደፊት ግብይት ስነዘዴ ገዢዎች የሚፈልጉትን ምርት በሚፈልጉት ጊዜ ማግኘት ያስችላቸዋል:: ከዚህም ባለፈ ከዋጋ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችንም መቅረፍ የሚያስችል የግብይት ስርዓት ነው ብለዋል::
የወደፊት ግብይት ስነዘዴ የግዢና የሽያጭ ውሳኔዎችን በተመሳሳይና ጤናማ በሆነ የግብይት መረጃን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም በመሆኑ ከአምራቹና ከኤክስፖርተሩ ባሻገር በአገር ደረጃ ዲጅታላይዜሽንን ከማበረታታት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አቶ በረከት አንስተዋል:: በተለይም በአሁን ወቅት እየተቋቋመ ላለው ካፒታል ማርኬት ወይም የአክሲዮን ገበያ አሁን ላይ ምርት ገበያ ቀድሞ በጀመረው የወደፊት ግብይት ቴክኖሎጂውን በማስተዋወቅ ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት::
በወደፊት የግብይት ስነዘዴ ለመገበያየት አሁን ላይ ያለው የሰሊጥ ግብይት ጥሩ እንደሆነ ለአብነት ያነሱት አቶ በረከት፤ ወደ እርሻ የሚገባው አርሶ አደር አሁን ላይ ያለውን የሰሊጥ ዋጋ ታሳቢ በማድረግ ምርቱን አስቀድሞ በመሸጥ ያመርታል:: ከሶስትና አራት ወራት በኋላም በገባው ውል መሰረት ምርቱን አስረክቦ ገንዘቡን የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ይህም ቀጣይነት ያለውን የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችልና ዛሬ ላይ ሆኖ ወደፊት የሁለትና የሶስት ዓመት ከዛም በላይ የብዙ ዓመት ሽያጮችን የመሸጥ ዕድልን የሚሰጥ ነው::
የወደፊት ግብይት ስነዘዴን በማጠናከር እንዲህ አይነት ስምምነቶችን ማስፋት ከተቻለ እራሱ አርሶ አደሩ ከኤክስፖርተሮችና ከውጭ ገዢዎች ጋር ዘላቂነት ያለው የረጅም ጊዜ ውል እየተዋዋለ መቀጠል የሚያስችለው ይሆናል:: በዋጋ መውረድና መውጣትም ውስጥ ቢሆን የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን በመድፈን ጤናማ የሆነ የግብይት ስርዓትን መዘርጋትና ምንም እሴት የማይጨምረውን ደላላ ከመሀል ማስወጣት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት በመሆኑ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ ነው በማለት አብራርተዋል::
ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገቡ የምርት አይነቶች 22 የሚደርሱ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ በረከት፤ ሁሉንም ምርቶች በወደፊት የግብይት ስነዘዴ ማገበያየት እንደሚቻል ገልጸዋል:: ይሁንና አሁን ላይ የወደፊት የግብይት ስነዘዴን በመጠቀም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ቢቻልም ቀድሞ የነበረውን የወዲያው የግብይት ስነዘዴ ማስቀረት አለመቻሉን አመላክተዋል:: ለዚህም ምክንያቱ አዲስ አሰራራ እንደመሆኑ ግንኙነቱ በሚገባ እስኪጠናከር መማማርና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው ጊዜ የሚፈልግ ነው:: ስለዚህ ሁለቱንም የወዲያውና የወደፊት የግብይት ስነዘዴዎች ጎን ለጎን የሚሄዱ እንደሆነ ነው ያስረዱት::
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በወደፊት የግብይት ስነዘዴ ምርቶችን ማገበያየት የጀመረው በቅርቡ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ በረከት፤ ከፍተኛ ፍላጎት ስለመኖሩ አመላክተዋል:: ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በተጀመረው የወደፊት ግብይት ስነዘዴ አስር ሺ ኩንታል የሚደርስ ምርት ማገበያየት እንደተቻለ ተናግረዋል:: በመጀመሪያው ግብይት ሲጀመር 500 ኩንታል ምርት ያገበያዩ ሲሆን በቀጣይ ሶስትና አራት ቀናት ውስጥ እንዲሁ ቀይ ቦለቄ፣ ቡና እንዲሁም ሌሎች ምርቶችንም እያገበያዩ ስለመሆናቸው አመላክተው በአጠቃላይ በአንድ ሳምንት ውስጥ አስር ሺ ኩንታል የሚደርስ ምርት በወደፊት የግብይት ስነዘዴ ማገበያየት እንደቻሉ ነው ያመላከቱት::
በወደፊት የግብይት ስነዘዴ ሂደት ውስጥ መካካድና ምርቱንና ብሩን በወቅቱ ያለማስገባት ችግር እንዳይፈጠር ገዢና ሻጭ የመተማመን ችግር እንደሚኖርባቸው ካመኑ ማርጅን የሚባል ጽንሰ ሃሳብ ስለመኖሩ ጠቅሰው ገዢም ሻጭም የሚያሲዙት ገንዘብ ስለመኖሩ አቶ በረከት አስረድተዋል:: በትንሹ አስር በመቶና ከዚያም በላይ ቀብድ በማስያዝ ምርቱ በሚደርስበት ወቅት ገዢው 90 በመቶ ገንዘቡን ገቢ በማድረግ ሻጭም 90 በመቶ የሚሆነውን ምርት በማምጣት ግብይታቸውን መፈጸም ይችላሉ:: ይህም በህግ ከሚደረገው ስምምነት በተጨማሪ ገዢና ሻጭ የማይተዋወቁ ከሆኑ መካካድ እንዳይፈጠር የሚያስችል የቀብድ አሰራር /ሞዳሊቲ/ ነው ይላሉ::
የወደፊት ግብይት ስነዘዴ አንድ የገበያ አማራጭ ሆኖ በስፋት ማገልገል እንዲችል የተለያዩ ሥራዎች መሥራት ይጠይቃል ያሉት አቶ በረከት፤ አዲስ ጅማሮ እንደመሆኑ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ለአምራቹና ለገዢው የማስተዋወቅና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን የሚሠሩ እንደሆነ አንስተዋል:: በተለይም ለአዲሱ የምርት ዘመን ገዢውም ሆነ ሻጩ በሚገባ አውቀውት ቢገቡ ዓለም የደረሰበት የግብይት ስነዘዴ እንደመሆኑ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብና ተወዳዳሪ መሆን ያስችላቸዋል:: ወደፊትም የምርት ገበያው በራሱ እንደሌሎች አገራት የውጭ ገዢ ገብቶ በዶላር መገበያየት የሚችልበትን መንገድ ያመቻቻል ያሉት አቶ በረከት የወደፊት ግብይት በቀጣይ አምራቹን ወደ ኤክስፖርት የማሳደግ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል::
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የወደፊት ግብይትን በዘንድሮ ዓመት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ሳምንት የወደፊት ግብይት ስነዘዴ (Customized Forward Trade) ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ማከናወን መቻሉ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል::
በሻጭና ገዢ መካከል በተፈፀመ ህጋዊ የወደፊት ግብይት ውል መሰረት ግብይቱን የፈፀሙት የወደፊት ግብይት ውል በሁለቱ ወገኖች ስምምነት በሻጭ ወገን ምርቱን ወደ ምርት ገበያው መጋዘን ሳያስገባና የምርት ማረጋገጫ ሳይሰጠው፤ በገዢ በኩል የተስማሙበትን ገንዘብ በግዢ የክፍያ ሂሳብ ውስጥ ከውሉ ማብቂያ ከሁለት ቀናት በፊት ለማስገባትና በተዋዋይ ወገኖች መካከል ግብይቱን መፈጸም ተችሏል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2015