በምክር ቤት አባልነት፣ በአምባሳደርነት፣ በሚኒስትርነት፣ በከፍተኛ አማካሪነት፣ በኢጋድ አስተባባሪነት፣ በሱዳን ልዩ መልዕክተኛነትና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በዲፕሎማሲው መስክ ሰፊ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው ናቸው: – አምባሳደር መሐሙድ ዲሪር ጌዲ።
በዓለም አቀፍ ሕግ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተከታተሉት እኚሁ አምባሳደር፤ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በዚምባብዌም በተመሳሳይ መልኩ ለዓመታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ። አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የተለያዩ ተቋማትንም ሚኒስትር ሆነው መርተዋል። የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የአክሱም ሐውልት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ በተደረገው አገራዊ እንቅስቃሴ ሰፊ ጥረት በማድረግ የአስመላሽ ኮሚቴ አባል ሆነው ለተጫወቱት ከፍተኛ ሚና መንግሥት ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
ሽልማታቸው ይህ ብቻ አይደለም። በሱማሌና በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት በኢጋድ ስር ሆነው በማገልገላቸው፤ በሱዳን የሽግግር መንግሥት የሰላም ሂደት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅዖም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የግል ቢዝነስ ድርጅት ላይም ተሳትፎ ያላቸው አምባሳደር መሐሙድ ድሪር፤ የኢስት አፍሪካ ሆልድን ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል።
አምባሳደር መሐሙድ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ከቆየችበት ሕመም ለመፈወስ ” ሁሉን አቀፍ እና አካታች ምክክር ይካሄዳል” መባሉን ተከትሎ የኮሚሽነሮች ሹመት ሲካሄድ አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል ኮሚሽነር ሆነው ተመርጠዋል። የዕለቱ እንግዳችንን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እስከ አሁን እየሠራቸው ስላሉ ሥራዎች እና በአጠቃላይ የኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ አተኩረን አነጋግረናቸዋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከተመሠረተ ጀምሮ የሠራቸውን ተግባራት በአጭሩ ቢያስረዱን ?
አምባሳደር መሐሙድ፡- አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከተመሠረተ ጀምሮ በኢትዮጵያ ዙሪያ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ቆይቷል። በሠራቸው ሥራዎች መሠረት አሁን ዋና እና ትልቁ ምዕራፍ የሚባልለት ደረጃ ላይ ደርሷል። አገራዊ ምክክር በባህሪው በአራት ምዕራፎች ይከፈላል። የመጀመሪያው ከዚህ በፊት እንደገለፅነው ቅድመ ዝግጅት የሚባል ነው። ከዛ የዝግጅት ምዕራፍ አለ። ቀጥሎ የምክክር ዓውድ ይከተላል። በመጨረሻም ከምክክሩ የሚመጡ ምረጥ ሃሳቦች ለይቶ በፖሊሲ ወይም በድንጋጌ መልክ ለመንግሥት አቅርቦ መከታተልንም ያካትታል።
አሁን ያለንበት ምዕራፍ ወደ ምክክር ዓውዱ የሚወስድ ነው። አሁን በአገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚሳተፉት መለየት አለባቸው። ሒደቱ አጀንዳዎችን መለየትንም የሚያካትት ነው። በዚህ ሂደት የሚሳተፉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ ራሳቸውን የሚገልፁበት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው አርብቶ አደሮች ሊሆኑ ይችላሉ ወይም አርሶ አደሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ መምህራንም ከሙያ አንፃር ይሳተፋሉ። ከፆታ አንፃር ካየን ሴቶች፣ ከዕድሜ አኳያ ወጣቶች የሚሳተፉ ይሆናሉ።
በአገራችን የተለያዩ ባሕሎች አሉ። ትልልቅ ዕሴቶች አሉን። ከትልልቆቹ እሴቶች መካከል አንዱ በዕድር የመሰባሰብ ባሕል ነው። ዕድሮች በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊዎች ናቸው። በየአካባቢው ማኅበረሰቡን በባሕል የሚመሩ የማኅበረሰብ መሪዎች የሚሳተፉበት ሁኔታ አለ። ምናልባትም አባ ገዳዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን ባለንበት ዘመንም በድሬዳዋና በሐረር ደሚና የሚባል አለ። በሶማሌ ባሕል ደግሞ ኡጋዞች፣ ገራዶች እና ሡልጣኖች የሚባሉ አሉ። እነዚህ ችግር ፈቺ የሆኑ በአካባቢያቸው አመኔታ የሚጣልባቸው ትልልቅ ሰዎች ናቸው። እነኚህ ሰዎች የሚሳተፉበት ሁኔታ ይኖራል።
ነገር ግን ደግሞ የሚያኮሩ በጎ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፤ የምናፍርባቸው ባሕሎችም አሉ። ለምሳሌ በሥራቸው የሚናቁ የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል። እነዛን የተገለሉ ሰዎች ድምፃቸው መሰማት መቻል አለበት። ብሶታቸው ሊደመጥ ይገባል። እንደዜጋ ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል። ከሚል መነሻ እነርሱን በሂደቱ ውስጥ ተሳታፊዎች ናቸው። የንግዱ ማኅበረሰብም ይሳተፋል። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በግጭቶች ወይንም በጦርነት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችም አሉ። እነርሱም ይህ ሂደት ይመለከታቸዋል።
ኮሚሽኑ ይህንን ሁሉ ሥራ የሚሠራው ብቻውን አይደለም። በጣም ግዙፍ ከፍተኛ ሎጀስቲክ ማንቀሳቀስን የሚጠይቅ ሥራ ነው። ሌሎች በኮሚሽኑ በኩል አመኔታ የተጣለባቸው ወገኖች አሉ። እነዚህ አመኔታ የተጣለባቸው በልየታው እንዲሳተፉ ይደርጋል። ይህ የተሳታፊዎች የልየታ ሥራ በዋናነት የኮሚሽኑ ነው። በበላይነት የሚከታተለውም ሆነ የሚቆጣጠረው እርሱ ሆኖ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ይሠጣሉ።
ከተሳታፊዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዕድሮች ማኅበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች እና አንዳንድ ጊዜ ልዩ ወረዳም ሊሆን ይችላል፤ ወይም የአስተዳደሩ ተወካዮች እነዚህ በሙሉ በሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉ ናቸው። ምክንያቱም አስራ አንድ ኮሚሽነሮች ብቻቸውን ይሔንን ሥራ ሊወጡት እንደማይችሉ የታወቀ ነው።
በሌሎች አገሮችም ይህ ተሞክሮ እንዳለ ተገንዝበናል። ከእነዚህ ከጠቀስኳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በሂደቱ በሙሉ በዕቅዳችን እና በአሠራሮቻችን ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ የተደረጉ ናቸው። ስለዚህ አሁን ይሄ ምዕራፍ በጣም ወሳኝ እንደመሆኑ መጠን፤ ከላይ ከጠቀስኳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ማለትም ራሳቸውን የሚገልፁበት በግብርና መተዳደሪያ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ዕድሮች እና የማኅበረሰብ መሪዎች ወዘተርፈ ያልናቸውን የእነርሱን ክፋይ ሰዎች ይመረጣሉ።
እዚህ ላይ ማኅበረሰቡ ራሱ ተመካክሮ እና ተወያይቶ አጀንዳዎችን ለሚመለከተው መድረክ ያደርሱልኛል ብሎ አመኔታ የሚጥልባቸውን ሰዎች ይመርጣል። ኮሚሽኑም እዚህ ላይ እጁን አያስገባም። ሌሎች ተባባሪ ወገኖችም ከማስተባበር ውጪ፤ ይህንን እርስ በእርሱ የመመራረጥን የኅብረተሰብ ሥራ ጣልቃ አይገቡበትም። ይሄ አካታችነትን፣ ተዓማኒነትን እና ግልፅነትን የሚያሳይ ነው።
በዚህ ሒደት ውስጥ የሚሳተፉት ዜጎቻችን፤ በዚህ አግባብ ይንቀሳቀሳሉ። ይህን ታሳቢ በማድረግ ለሚመለከታቸው በሙሉ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል። ለምሳሌ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና ለሐረር ክልል ሥልጠና ሰጥተናል። ሌሎች የኮሚሽኑ አባላትም በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል፤ ይህንኑ ተመሳሳይ ሥልጠናዎች እና ግንኙነቶችን በመፍጠር ላይ እንዳሉ እናውቃለን። ይህንን ሥራ ጨርሰን፤ እነዚህ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በራሳቸው የሚመርጡበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። እኛም ተገኝተን ይህንን ሂደት ተከታትለን ልየታው የተሳካ መሆኑን ወደ ፊት የምንገልፅ ይሆናል።
የአገራችን የፖለቲካ ልሂቃን በሃሳቦች መለያየት በተለይም መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች እንዳሉ ተደጋግሞ ይነገራል። እነዚህን ልዩነቶች በጋራ መግባባት በምክክር ለመፍታት ይሄ ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጥሩ! በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ይታያሉ፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አይቸግርም? ይህንን ኮሚሽኑ የሚወጣው እንዴት ነው?
አምባሳደር መሐሙድ፡- እውነት ለመናገር መጀመሪያ የቅድመ ዝግጅቱ እና የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች ተዟዙረን ከአስተዳዳሪዎች፣ ከኅብረተሰብ መሪዎች፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች እንዲሁም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሂደቱን ለማስተዋወቅ እና ለመተዋወቅ የተንቀሳቀስንባቸው ሁኔታዎች አሉ። በዚያን ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው ጦርነት እና ግጭት ወደ ትግራይ ክልል እንዳንሔድ አድርጎናል። ጦርነቱ ትልቅ ተግዳሮት ነበር።
ነገር ግን ይሄ አገራዊ ምክክር በሁሉም ክልሎች ሊካሔድ ስለሚገባ፤ በዚያን ወቅት በገጠመን ችግር አለመሔዳችንን ለማኅበረሰቡ በመገናኛ ብዙኃንም ገልፀናል። አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉት ችግሮች ከእኛ ጋር ለወደፊትም ለዘላለም የሚኖሩ ናቸው የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ጦርነትን የሚያክል ነገር፤ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ መፍትሔ እና እልባት አግኝቷል። ስለዚህ መንግሥት በሚያደርገው ጥረት የመደራደር፣ ችግሮችን የመፍታት፤ ሰላምን የማስፈን ሁኔታዎች ይኖራሉ ብለን እናምናለን። ድርድር እና ምክክር አንዱ ሌላውን አይተካም። ነገር ግን ይመጋገባሉ፤ ይደጋገፋሉ። ስለዚህ በዚህ መልኩ አገራችንን ካለችበት አስቸጋሪ ምዕራፍ ለማሻገር እንችላለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ ምክክሩ አገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ ለመውጣት ምን ያህል አስተዋፅዖ ይኖረዋል? በተጨማሪ ለሌሎች አገሮች ምርጥ ተሞክሮ እንዲሆን በምን ዓይነት ጥንቃቄ ለመሥራት ታስቧል? የመንግሥት ተባባሪነትስ እንዴት ይገለፃል?
አምባሳደር መሐሙድ፡- በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት አዋጅ አውጥቶ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲመሠረት አድርጓል። ይህ የመንግሥት ወገንን ቁርጠኝት የሚያሳይ ነው። አንድ አገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመንግሥት ቁርጠኝነት ነው።
ሌላው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ነው። ተሳትፎ ደግሞ በአገራችን ውስጥ የተለያዩ ብዝኃነቶች አሉ። የቋንቋ ብዝኃነት ፣ የባሕል፣ የሃይማኖት፣ የእምነት እና ሌሎችንም ብዝኃነቶችን ተመርኩዘን አካታች የሆነ አሳታፊ ሒደት ውስጥ እንገባለን ብለን እናምናለን። የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወይም አደረጃጀቶች ከእኛ ጋር በቅርበት እንዲሠሩ የተደረገው ለዚህም ነው።
ስለዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳ ወይም የልዩ ወረዳ አስተዳደር ተወካዮች ፣ የመምህራን ማኅበር እና ሌሎችም የሚሳተፉበት ዋና ምክንያት ሁሉም ወገን ድርሻውን እንዲያበረክት ለማድረግ እና አካታች አገራዊ ምክክር ለማካሔድ እንዲሁም አመኔታ እንዲመጣ ለማስቻል ነው።
ኢትዮጵያ በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ኅብረተሰቡ በሙሉ የሚረዳው ነው። ይህንን የአገራዊ ምክክር ጉዳይን ሕዝቡ በታላቅ ጉጉት እየጠበቀው ነው። ስለዚህ ሕዝቡ ዘንድ ሲመለስ እና የሕዝቡ ተሳትፎ በሰፊው ሲታከልበት ማለትም የተሳታፊዎች ልየታው በሰፊው ተከናውኖ የአጀንዳ አሰባሰቡ ሒደት ከተጠናቀቀ እና የአገራዊ ምክክሩ ዓውድ ውስጥ ሲገባ፤ አገራዊ ምክክር በራሱ ኢትዮጵያን ይፈውሳል። አገራዊ ምክክር በራሱ ፈዋሽ ነው።
በመጠራጠር እና በመለያየት ከዚህ በፊት በሞከርናቸው መንገዶች ሁሉ ችግሮቻችንን መፍታት አንችልም። በጦርነት ችግር መፍታት አንችልም። አንዱ ሌላውን በማብጠልጠል፤ በመናናቅ ችግሮቻችንን መፍታት አንችልም። በግጭት ውስጥ ሆነን ችግሮቻችንን መፍታት ይከብደናል። እነዚህ ያለያዩን ጉዳዮች አሁን ባለው ፖሊሲ እና ባሉን ሕግጋቶች ልንፈታቸው አንችልም። ችግሮችን የሚቻለው በአገራዊ ምክክር በመፍታት ብቻ ነው።
እነዛን ችግሮች ሰከን ባለ ሁኔታ ተማምነን፣ ተመካክረን የአንዱ ብሶት የሌላው ብሶት እንደሆነ ተረድተን ችግሮችን ለመፍታት የምናደርገው ጥረት አገራዊ የጋራ መግባባት ላይ ሊያደርሰን ይችላል። በአገራዊ ምክክሩ ውስጥ አገራዊ መግባባትን ስንፈጥር፤ ከዚህ በፊት የተሸረሸሩ እሴቶቻችን የምንጠግንበት፤ ጠንካራ አገረ መንግሥት የምንገነባበት ይሆናል። እንዲሁም በኅብረተሰቡ እና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን የምናጠናክርበት ሲሆን፤ አገራችንን አሁን ካለችበት ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ የምናሸጋግርበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ ምክክሩ ከተሳካ ትልቅ ዕድል ካልተሳካ ደግሞ ትልቅ አገራዊ ስጋት ሊሆን እንደሚችል እየተገለፀ ነው። ይህንን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ጽንፍ የያዙ ሰዎች ምክክሩ ላይ የሚያሳድሩት ስጋት እንዴት ይገለጻል?
አምባሳደር መሐሙድ፡- ከተሳካ ሳይሆን ይሳካል እንበል፤ ምክንያቱም ይሳካል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ መንገድ የለንም። ሌሎች አገሮች እንዳሳኩት ሁሉ ኢትዮጵያም ማሳካት ትችላለች ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም እንደሕዝብ እና እንደአንድ ማኅበረሰብ የሚያገናኙን እሴቶቻችን ከሚያለያዩን የበለጡ ናቸው። ይህንን መዘንጋት የለብንም። ምክክሩ የፖለቲካ ልዩነቶችን የምንፈታበት፤ መንገድ የምንቀይርበት ነው። ምክንያቱም በጦርነት እና በግጭት ሳይሆን ችግሮቻችንን የምንፈታው በመመካከር ነው።
ተጨማሪው ለሌሎች አገሮች ምሳሌ እንሆናለን የሚለውን ስንደርስበት የምናወራው ነው። አሁን ግን በትክክል ተዓማኒ፣ አሳታፊ እና አካታች የሆነ አገራዊ ምክክር ለማካሔድ በኮሚሽኑም ሆነ በኮሚሽነሮች በሙሉ ቁርጠኝነት መኖሩ መታወቅ አለበት።
ይህንን ምክክር ሕዝቡ ካመነውና ከተቀበለው ጽንፍ የያዙ ሰዎች የሚባሉት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ስትንቀሳቀሱ የሚያጋጥሙ ነገሮች አይጠፉም። ሰላማዊ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ በተቃውሞ በተለያየ የትግል ስልት ውስጥ ያሉ አሉ። እነዚህንም በሙሉ ለማካተት የተጀመረ ነገር አለ? በዚሁ ላይ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል ?
አምባሳደር መሐሙድ፡- አገራዊ ምክክር ከተካሔደባቸው አገሮች አንፃር ሲታይ አንዳንድ የሚያመሳስሉን ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የታጠቁ ኃይሎች ያሉበት አገር እንደ ኮሎምቢያ ዓይነቶቹ ችግራቸው የተፈታው በድርድር ነው። በድርድር ከተፈታ በኋላ ፋርክ የሚባለው ግንባር ተቀናቃኝ ሆኖ፤ መሣሪያውን ያነገበው ኃይል፤ መሣሪያውን አስቀምጦ ወደ ሰላማዊ ሒደት ገብቶ በምክክሩ ላይ ተሳትፏል። እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ምክክር እና ድርድር ይለያያል። ይህንን ያልኩበት ምክንያት ምክክር በራሱ ሰላማዊ ዓውድ ይፈልጋል። የታጠቀ ኃይል ማለትም ጠመንጃ ያነገበ እና በሌላ በኩል ያልታጠቀ ሰው ቁጭ ብሎ መመካከር የሚታሰብ አይደለም። በሌሎች አገሮችም ይህ ክስተት በዚህ መልኩ አልተካሔደም፤ የሚከወነው በድርድር የሚፈቱ ነገሮች በድርድር ይፈታሉ።
አገራዊ ምክክር ለአገረ መንግሥት ግንባታ፣ መንግሥት በሕዝቡ ውስጥ ያለውን አመኔታ ለማጠናከር እና የማኅበረሰብ ውልን ለማደስ እንዲሁም የተሸረሸሩ እሴቶቻችንን ለመጠገን የምንከተለው ሒደት ነው። ስለዚህ በዚህ ሂደት ውስጥ ማንም መቅረት የለበትም። ሁሉም ወገኖች መሳተፍ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ኢትዮጵያ አለመግባባቶችን የምትፈታበት ድንቅ ባሕሎች ያሏት አገር ናት። ሆኖም የልምድ ልውውጥ ለማግኘት ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በጋራ የተሠራ ነገር ካለ ቢገልፁልኝ? የመገናኛ ብዙኃንን ሚናስ እንዴት ይመለከቱታል ?
አምባሳደር መሐሙድ፡- ሥራችንን ትተን የሌሎች አገሮችን ልምድ ለማየት ከአገር ወጥተን ስንዞር አልከረምንም። ነገር ግን የተለያዩ አገሮችን ልምዶች አይተናል፤ አንብበናል፣ ተረድረናል እንዲሁም ተገንዝበናል። ካየናቸው ውስጥ የሚመሳሰሉን አሉ። በሌላ በኩል ከእኛ የተለዩ አሉ። ጭብጣቸው እና የራሳቸው የባሕሪ ችግር ያለባቸውም ነበሩ።
ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የተካሔደው አገራዊ ምክክር በራሱ በአፓርታይድ ጊዜ የነበረውን ጠባሳ እና ችግር ለመፍታት ያለመ ነበር። በኬኒያ የተካሔደው አገራዊ ምክክር ደግሞ በድሕረ ምርጫ የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት እና መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፅናት የተካሔደ ነበር። በሩዋንዳም እንደሚታወቀው ሁቱ እና ቱትሲ የሚባሉ ሁለት ማኅበረሰቦች ላይ በተደረገው ዘር የማጥፋት ሒደት ውስጥ የነበረውን ጉዳይ ለመፍታት ነው። ስለዚህ ከኛ የተለዩ ሲሆኑ፤ ከእኛ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ያላቸው አገሮችም አሉ።
በሌላ በኩል በቱኒዚያ፣ በማሊ እና በሴኔጋል የተካሔዱ ሒደቶች አሉ። ነገር ግን ከሕዝብ ብዛት አንፃር የእኛ የሕዝብ ብዛት እንደሚታወቀው ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ወኪሎችን ወይም ሕዝቡ የሚያምንባቸውን በውክልና የሚያሳትፍ መሆኑ ግድ ነው። ስለሆነም በራሱ ለእኛ ከሁሉም አስቀድሞ እንደአገር ጠቀሜታው በጣም የጎላ ነው። የልምድ ልውውጥ የሚለውን ያየነው በዚህ ነው። የተለያዩ አገሮች የተሳካላቸው ምን ስለሠሩ ነው? የከሸፈባቸውስ ምን ውስጥ ስለገቡ ነው? የሚለውን አጥንተናል።
መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ ሚዲያዎች በአንድ በኩል ፈዋሽ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። በሌላ በኩል ግን ችግር ሊፈጥሩ የሚችልበት ሁኔታም መኖሩ አይሸሸግም። ስለዚህ በሰከነ እና ከሁሉም በላይ አገርን በማሰብ የአገርን ጉዳይ ላይ የሚያገለግል የሚዲያ መንገድ ያስፈልገናል። ይህ አገራዊ ምክክር ምን እንደሆነ ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ የምንሠራቸውን ሥራዎች በየጊዜው ለኅብረተሰቡ የማስገንዘብ፤ መልዕክቱን በትክክል ሳይዛነፍ፣ ሳይሸረፍ፣ ሳይበረዝ የማድረስ ኃላፊነትን መወጣት አለብን። በዚህ መልኩ መገናኛ ብዙኃኑ ቢሳተፉ ለአገራችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። ነገር ግን የእኛ መገናኛ ብዙኃን ሁሉም በዚህ መልኩ ይዘግባሉ? መገናኛ ብዙኃኑ የሚገለፁት በዚህ መልኩ ነው? የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ሊታሰብበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
አምባሳደር መሐሙድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015