በምርመራ ጋዜጠኝነት በርካታ ተግባራት የሚሰሩ ቢሆንም መልስ ያገኙ ጉዳዮች ከምን ላይ ደረሱ የሚለውን ማረጋገጥ የጋዜጠኛው አንዱና ዋነኛው ተግባር ነው:: ከዚህ አንጻር ምርመራው የተዋጣለትና ጥንቅቅ ያለ እንዲሆን ለማስቻል ምላሽ ያገኙ የምርመራ ዘገባዎች ምላሽ አግኝተዋል በሚል የሚተው ሳይሆን አፈጻጸማቸው ከምን ደረሰ የሚለውን በየጊዜው መቃኘት ያስፈልጋል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዛሬው ዝግጅታችን መልስ አግኝቶ የነበረ አንድ ጉዳይ በምን ደረጃ ይገኛል የሚለውን እንዳስሳለን:: የዛሬው ዘገባችን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር እና በአዋሽ ቆዳ ፋባሪካ ዙሪያ ነዋሪዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብና የመጨረሻ ውጤትን የሚዳስስ ነው::
ከዚህ ቀደም በነበረን የምርመራ ዘገባ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጋር በጉዳዩ ላይ መግባት ላይ ደርሰን ነበር:: መግባባቱን ተከትሎም የተወሰኑ ስራዎችም ተጀምረው ነበር::
የተግባባንባቸው ነጥቦች ምን ያህል መሬት ላይ ወርደው እየተተገበሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ወደ ክፍለ ከተማው አምርተን ነበር:: ወደ ክፍለ ከተማ በሄድንበት ወቅት እንኳንስ የተጀመሩ ስራዎችን ሊጨርሱ ይቅርና የተግባባንባቸውንም ነጥቦች ዘንግተዋቸዋል:: አመራሮችም ከዚህ ቀደም ደርሰንባቸው ከነበሩ ስምምነቶች ያፈነገጡ አስተሳሰቦችን አስተውለናል::
በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን ስንከታተል የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር አመራሮች ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ አንድ ደብዳቤን በመፍራት የገቡትን ቃል ወደ ጎን ሲሉ ተመልክተናል::
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሬሰ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጉዳዩን ለምን ወደኋላ መመለስ አስፈለገ? ሲል ከዚህ ቀደም አነጋግሯቸው የነበሩ የክፍለ ከተማውን ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኃላፊ እና ከዚህ ቀደም ስለጉዳዩ ያላነጋገራቸውን የክፍለ ከተማውን የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አነጋግሮ ምላሽ ይዞ ቀርቧል::
የአመራሮችን ምላሽ ከማቅረባችን በፊት ከዚህ ቀደም የሰራናቸው ሁለት ዘገባዎች ከሁለት ወር በፊት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አንባቢያን የምርመራውን ፍሬ ነገር ሊዘነጉት ስለሚችሉ ከዚህ ቀደም በዘገባችን ቀርበው የነበሩ አንዳንድ መረጃዎችን በወፍ በረር ላስቃኛችሁ::
የምርመራ ዘገባው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀድሞው መጠሪያ ስሙ ወረዳ 19 ቀበሌ 57 በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ እየተባለ ወደሚጠራው ሰፈር ይወስደናል።
ለትውስታ ከአቤቱታ አቅራቢዎች አንዱን
አቤቱታ አቅራቢዎቹ በርካታ ቢሆኑም ስለተፈጠረው ውዝግብ በአግባቡ ሊያስረዱ ይችላሉ የተባሉ የተወሰኑ ሰዎችን በቃለ መጠየቅ አካተናል። ከእነኚህ መካከል አቶ አሥራት አራርሶ አንዱ ናቸው። አቶ አሥራት አራርሶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 160 ነዋሪ ናቸው። እድሜአቸው በሃምሳዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ አሥራት፤ ውዝግብ በተነሳበት ቤት ውስጥ ተወልደው ማደጋቸውንና አሁን ላይም በቤቱ ልጅም ወልደው እየኖሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ አሥራት ገለጻ፤ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የራሳቸውን ቤት ሠርተው የሚኖሩ 65 የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች ነበሩ። እነኚህ ሠራተኞች ምንም እንኳን በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ተቀጥረው የሚሠሩ ቢሆንም ይኖሩበት የነበረውን ቤት በራሳቸው ገንዘብና ጉልበት የሠሩት ስለነበር ፋብሪካው በደርግ ዘመነ መንግሥት በአዋጅ 47/67 ሲወረስ የፋብሪካው ተቀጣሪ ሠራተኞች ቤቶች ግን አልተወረሱም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የነበረው አስተዳደር ቤቶቹ በሠራተኞች ገንዘብና ጉልበት የተሠሩ መሆናቸውን አረጋግጦ ስለነበረ ነው።
በወቅቱ የነበረው መንግሥት ሁሉን አቀፍ ማጣራት አድርጎ ቤቶቹ የሠራተኞች የግላቸው መሆኑን ተረድቶ ያልወረሳቸው ቢሆንም በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ግን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቦታ እና ዲዛይን ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ግለሰብ በ24/12/2002 ዓ.ም በክፍለ ከተማው እና በወረዳው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ለአንዳቸውም ሳያማክር በራሱ ተነሳሽነት ከ60 ዓመት በላይ የኖሩበትን ቤት ባለቤት አልባ በማለትና ለክፍለ ከተማ በማስተላለፍ እንዲሁም ክፍለ ከተማ ደግሞ ለአዲስ አበባ ቤቶች በማስተላለፉ ሳቢያ የወረዳው ቤቶች ልማት አስተዳደር ነዋሪዎችን የቀበሌ ቤት ኪራይ ውል እንዲዋዋሉ የሚል ማስታወቂያ ለነዋሪዎቹ መላካቸውን ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ በወቅቱ በነበሩት ኃላፊ የተወሰነው ውሳኔ እውነታን ያላገናዘበ እና መነሻው ምን እንደሆነ ስለማይታወቅ በራሳችን ገንዘብ እና ጉልበት በሠራነው ቤት የኪራይ ውል ሊዋዋሉ እንደማይችሉና አንድ ግለሰብ ከመሬት ተነስቶ ይህን መሰል ውሳኔ እንዴት በግሉ ሊወስን ይችላል? ሲሉ ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር አቤት ማለታቸውን ያስረዳሉ።
አቤቱታውን ተከትሎ የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደርም ስለእነዚህ ቤቶች የሚያውቀው ነገር እንደሌለ እና ግለሰቡ ከመሬት ተነስቶ በግሉ ይህን የመሰለ ውሳኔ መወሰኑ አግባብ ባለመሆኑ ቅሬታቸውን ለክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ እንዲያመለክቱ ተደረገ። ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢዎቹም ለክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ማመልከታቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ የነበሩት የክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊም ስለጉዳዩ ለማጣራት በጣም ቀላል ዘዴዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ቤቶቹ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ መሆናቸውን እና አለመሆናቸውን ለማጣራት ለፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ፣ የባላደራ ምክር ቤትና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ስለቤቶቹ የሚያውቁትን ነገር አጣርተው እንዲያሳውቁ የሚል ደብዳቤ እንደሚጽፉና እነኚህ መሥሪያ ቤቶች ውዝግብ ያስነሱትን ቤቶች አናውቅም ካሉ በእውነትም ግለሰቡ ሐሰተኛና ትክከል ያልሆነ በመሆኑ ይህንን ቦታ ለአቤቱታ አቅራቢዎች እንመልሳለን በማለት ከላይ ለተገለጹት መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤ መጻፉን ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ የፕራይቬታዜሽን ኤጀንሲ ስለቤቱ ምንም የምናውቀው ነገር የለም የሚል ምላሽ ሲሰጥ፤ የባላደራ ምክር ቤት ደግሞ ቤቱ ቀድሞ የቤቶች አስተዳደር ቢሆን ኖሮ ቤቱን ድርጅቱ ለእነሱ ያስረክባቸው እንደነበር ነገር ግን አሁን ላይ ቤቶቹን እነሱ እንደማያውቋቸው የሚገልጽ ምላሸ ሰጡ።
ሌላው ስለጉዳዩ እንዲያብራራ የተጠየቀው ደግሞ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ነበር። የክፍለ ከተማው መሬት ማኔጅመንትም ስለቤቶቹ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በደብዳቤ ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር አሳወቀ። ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞው አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የአሁኑ ኢትዮጵያ ሌዘር ስለጉዳዩ ተጠይቆ ለሠራተኞች የመብራትና የውሃ ክፍያ ከመክፈል ውጭ ስለቤቶቹ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በደብዳቤ ምላሽ ተሰጠ።
የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደርም እነኚህን ደብዳቤዎች ካሰባሰቡ በኋላ ከደብዳቤዎቹ የተገኙ ቀን እና ቁጥሮችን በመጥቀስ «ይህ ቤት የመንግሥት ነው ተብሏል። ስለዚህ ጥያቄያችሁ በቂ መልስ የሚያሰጥ ሆኖ አላገኘንም» ሲሉ እንደመለሱላቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ ጉዳዩን በይግባኝ በ2006 ዓ.ም ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቅሬታ ሰሚ አቀረቡ። ይሁን እንጂ የክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ይህን ቅሬታ ‹‹አልቀበልም›› ይላሉ። ምክንያቱም ቅሬታ ሰሚ ኃላፊ የነበሩት ሰው ቀደም ሲል ችግሩን ከፈጠረው የወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጋር በአንድ ቦታ ይሠሩ ስለነበር መሆኑን አመላክተዋል። ይህን ተከትሎ ቅሬታ ሰሚ ቢሮ ቅሬታቸውን ሊቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ጠቅሰው ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቤት አሉ።
በክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስገዳጅነት ክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት በግድ አቤቱታቸውን እንዲቀበል ሆነ። ይሁን እንጂ የአቤቱታውን ምላሽ ቀጥታ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ መስጠት ሲገባቸው ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ቅሬታ ሰሚ እንዲላክ አደረገ። ይህም የአሠራር ሂደቱን ያልተከተለ ከመሆኑም ባሻገር ሆነ ተብሎ ጉዳዩን ለማወሳሰብ የተደረገ ተግባር መሆኑን አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅሬታ ሰሚ የነበሩትም በወቅቱ ‹‹አጣሪ ኮሚቴ አደራጅተን ስለጉዳዩ ምርመራ እንጀምራለን›› ብለው እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ የጀመሩትን ምርመራውን አቁመው የደረሰበትን የመጨረሻ ምላሽ ነው በማለት ወረዳው ላይ የነበረውን ምላሽ ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እንደወረደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ምላሽ እንደሰጧቸው ይገልጻሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎችም ‹‹እውነታን ይዘን እያለ በአንድ ግለሰብ በተፈጠረ የክፋት አካሄድ ስለምን እንዲህ ያለ መልስ እንሰጣለን?›› ሲሉ መጠየቃቸውንና ከተማ አስተዳደሩ ቅሬታ ሰሚም ‹‹መንግሥት ከሚቀየመን እናንተ ብትቀየሙ ይሻላል፤ ሲደክማችሁ ትተውታላችሁ›› የሚል በማስፈራራትና ማንጓጠጥ በተቀላቀለበት አግብብ ትክክለኛና ተገቢ ያልሆነ ምላሽ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ። ይህንን የደረሰባቸውን አስተዳደራዊ በድል እንዲፈታላቸው እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎችን ቢያንኳኩም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
እነኚህን ክርክሮች መከራከር ከጀመሩ አንስቶ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ከአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጋር ምንም አይነት የኪራይ ውል አልገቡም። ምንም የተጣራ ነገር በሌለበት እያንዳንዱ አባወራ የኪራይ ውል መግባት አለባችሁ በማለት ማስፈራራት ቢሞክሩም እስከዛሬ ማንም ሊቀበለው ያልቻለ ነገር ነው። ቤቱ የግላቸው ስለሆነ በምንም አይነት አግባብ የኪራይ ውል ሊገቡ እንደማይችሉ አመላክተዋል።
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች አንደኛውን
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች በርካታ በመሆናቸው ሁሉንም ማቅረብ አይቻልም። ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ ይፈርድ ዘንድ ያስችሉታል ያልናቸውን ሰነዶች መርጠን በዚህ ጽሑፍ አካተናል።
ሰነድ አንድ፡- አቤቱታ አቅራቢዎቹ ቤቶች የመንግሥት ስለሆኑ የኪራይ ውል ተዋዋሉ ተብለው መነገሩን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢዎች ችግራቸው እንዲፈታ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር አቤት ይላሉ። የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደርም ስለጉዳዩ ለማጣራት በቁጥር አቃ/ቃ/ክ/ ከ/ቤ/ል/ማኔ በቀን 07/01/2006 ለባላደራ ቦርድ፣ ለፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ፣ ለአቃቂ ቃሊቲ መሬት ልማት ማኔጅመንት እና ለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ደብዳቤ ጻፈ።
ለሁሉም መስሪያ ቤቶች የተጻፈው ደብዳቤ በአንድ ቁጥር እና ቀን ነው። ይህን ተከትሎ የባላደራ ቦርድ፣ ፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ እና የአቃቂ ቃሊቲ መሬት ልማት ማኔጅመንት አቤቱታ ስለተነሳባቸው ቤቶች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ሲገልጹ፤ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካም ለቤቶቹ ለተወሰኑ ዓመታት የመብራትና የውሃ ወጪ ይችላቸው እንደነበር፤ ነገር ግን ስለቤቶቹ ምንነት እንደማያውቅ ለቤቶች አስተዳደር በደብዳቤ አሳወቀ።
ሁሉም መስሪያ ቤቶች ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ይግለጹ እንጂ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቤቶቹ የመንግሥት ናቸው ተብሎ ከመስሪያ ቤቶች እንደተገለጸ በማስመሰል ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምላሽ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ የወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ቶፊቅ ከድርን በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ስለሚገኙ ቤቶች ምን ያውቃሉ? ሲል ጠይቆ ነበር። አቶ ቶፊቅም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቶፊቅ እንደገለጹት፤ ስለቤቶቹ የተወሰኑ ጉዳዮችን ቢያውቁም የተሟላ መረጃ ግን የላቸውም። ይሁን እንጂ በእነዚህ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች ከወረዳው ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎቶች እያገኙ አለመሆናቸውን ይገነዘባሉ። አሁን ላይ ነዋሪዎቹ ከወረዳው ማግኘት የነበረባቸውን እንደ ውሃ፣ መብራትና መሰል አገልግሎቶችን እያገኙ አይደለም። በዚህም ለከፋ ችግር ተዳርገዋል።
ከቤቶች ጋር ተያይዞ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ባለመኖሩ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ፈልገው ወደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢሮ በመጡ ጊዜ ከመንግሥት ማግኘት የሚገባቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ለመስጠት መቸገራቸውን አቶ ቶፊቅ ያስረዳሉ። አንዳንዴ ችግሩ በጣም የከፋ ሲሆን በሕግ የሚደገፍ ባይሆንም ነዋሪዎችን የንግድ ፈቃድ እንዲያመጡ በማድረግ አንዳንድ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በዚያ ቦታ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ትውልዶችን እንጂ መጀመሪያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አይገኙም። ስለሆነም ቦታቸው በሰነድ አልባ ታይቶ ወደ ሕጋዊነት መምጣት አለበት። በወረዳቸውም አሠራሩና መመሪያው በሚፈቅደው ልክ በርካታ ቤቶችን በሰነድ አልባ ሕጋዊ አድርገዋል። የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ነዋሪዎች ጉዳይም በሰነድ አልባ ወደ ሕጋዊ መስመር ቢገባ ለመንግሥት አሠራርም ሆነ ነዋሪዎቹ በሰላም ይኖሩ ዘንድ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ እነዚህ ያሉ ቤቶች በሊዝ አዋጁም ሆነ ሰነድ አልባ በምንለው መንገድ ተላልፈውም ጭምር ሰነድ እንዲኖራቸው ቢደረግና ሰዎች እንዲጠቀሙበት መብት ቢፈጠር፤ እኔ እንደ ዜጋ ደስተኛ ነኝ። እንደ አንድ አመራርም የምደግፈው ጉዳይ ነው የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ የክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ጽፎ በነበረው ደብዳቤ ተነስተን በደፈናው ቤቶችን ወደ መንግሥት ይግቡ ለማለት ሕጋዊ የሆነ የሕግ መሠረት ለመያዝ የሚያስቸግር መሆኑንም ተናግረዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ምላሽ
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍል ስለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ቤቶች ምን ያውቃሉ? ተብለው የተጠየቁት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳኛው ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል። የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞችና ቤቶቻቸውን በሚመለከት ቀደም ሲል ከነበሩ መረጃዎችና ሰነዶች መሠረት ተደርጎ ታሪካዊ አመጣጣቸው ቢገለጽ ስለቤቶቹ ምንነት የተሟላ እይታ እንዲኖረን ያደርጋል። አሁን ላይ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ተብሎ የሚጠራው ድርጅት በ1948 ዓ.ም በአርመን ዜጎች የተመሠረተ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ስሙም ዳር ማር ቆዳ ፋብሪካ ነበር። አርመኖች ፋብሪካውን ለመመስረት በማሰብ ፋብሪካው የሚገኝበትን ቦታ በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩ ባለእርስቶች ገዙ። ፋብሪካውንም ገነቡ። በ1948 ዓ.ም ዳር ማር ቆዳ ፋብሪካ ተብሎ የተመሠረተው ድርጅት የደርግ መንግሥት መምጣቱንና መወረሱን ተከትሎ በ1969 ዓ.ም የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የሚል ስያሜ ተሰጠው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ድርጅቱ ለሠራተኞቹ በማሰብ በፋብሪካው አካባቢ ከእንጨትና ከጭቃ የተሠራ ፎቅ መሰል ባለ አንድ ወለል (ጂ ፕላስ ዋን) ቤት ሠርቶ በመኖሪያ ቤትነት እንዲገለገሉበት አደረገ።
ቀንን ቀን ሲወልደው ለሠራተኞች መኖሪያ የተሠራው ቤት በእርጅና ምክንያት ፈራረሰ። የድርጅቱ ሠራተኞችም ለመኖር ይቸገሩ ጀመር። ይህን ተከትሎ ድርጅቱ ለሠራተኞች የሚሆን የጭቃ ቤት ለመሥራት በማሰብ ለበላይ መስሪያ ቤቱ ጥያቄ አቀረበ። በወቅቱ ለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የበላይ መስሪያ ቤት የነበረው ብሔራዊ ቆዳ እና ጫማ ድርጅት ነበር። የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ለብሔራዊ ቆዳና ጫማ ድርጅት የጭቃ ቤቶች ለሠራተኞች እንዲሠራላቸው ሲጠይቅ የዋጋ ግምቱንም ጭምር አስቀምጦ ነበር ጥያቄውን ያቀረበው። ጥያቄውም ተቀባይነት አግኝቶ ተፈቀደ። በዚህ መሠረት ለሠራተኞች በርካታ ቤቶች ተሠሩ። ሠራተኞችም እዚያው እየኖሩ ሥራቸውን ማከናወን ጀመሩ።
ቤቶች ከተገነቡ በኋላ ቀጥሎ የመጣው የመብራትና ውሃ ጥያቄ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ መሬት አስተዳደር አመልክቶ መብራትና ውሃ ገባላቸው። መብራቱ ሲገባ ሙሉ ወጪ በድርጅቱ የተሸፈነ ቢሆንም ከሠራተኞች የሦስት ወር ደመወዝ የሚቆረጥ ነበር። ይህ የሆነው አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ወደ ግል ተቋም ዙሮ ኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ በሚባልበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ በግላቸው የሚያስተዳድሩት መብራትና ውሃ ተፈቀደላቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2002 ዓ.ም የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በክፍለ ከተማው የቤቶች ቆጠራ አካሄደ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ክፍለ ከተማው በራሱ ተነሳሽነት የቤቶች ቆጠራ ያካሂድ እንጂ የቤት ቆጠራው አገራዊ አልነበረም።
ይህን ተከትሎ በወረዳ 6 ውስጥ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኙ ቤቶች በነዋሪዎችም ሆነ በመንግሥት ያልተመዘገቡ ሆነው ተገኙ። ይህን ተከትሎ እነዚህ ቤቶች ምን ይሁኑ የሚል ጥያቄ ተነሳ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ንዑስ የሥራ ሂደትም ለእነዚህ ቤቶች ለምን የኪራይ ተመን አይወጣላቸውም? ሲል በቀን 22/2/ 2003 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን ጠየቀ።
በዚህም ምክንያት በጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም በክፍለ ከተማ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ የከራይ ግምት ተዘጋጅቶ ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ተላከ። የተላከውን የኪራይ ግምትም ተከትሎ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሚያዝያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የቤቶች የኪራይ ግምቱ መጽደቁ ተገለጸ። በዚህ መሠረት ቤቶቹ በኪራይ እንዲተዳደሩ የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ታዘዘ። በተያያዘም፣ ስለቤቶቹ የሚቀየር ነገር ካለ ወደፊት ሊቀየር እንደሚችል በደብዳቤው ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎ «የቤቶች አስተዳደር የወሰነው ውሳኔ ትክክል አይደለም» ሲሉ 61 ሰዎች ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች አቤቱታ አቀረቡ። አቤቱታ ከቀረበላቸው መስሪያ ቤቶች መካከልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት ቢሮ፣ የወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፤ እንዲሁም፣ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተጠቃሽ ናቸው።
አቤቱታ አቅራቢዎችም «ቤቱ ሲሠራ ቦታውን በስጦታ ከባለርስቶች ወስደን በራሳችን የገንዘብና የጉልበት ወጪ ቤት ገንብተን እያለ፤ መብራትና ውሃም በራሳችን ከፍለን አስገብተን እያለ መመሪያውንና አሠራሩን ተከትሎ ቦታው ወደ ግል ይዞታ መቀየር አለበት እንጂ እንዴት በኪራይ እንዲተዳደር የኪራይ ተመን ይጣልበታል?» የሚል ጥያቄ ይዘው ነበር ሲከራከሩ የነበሩት።
ይሁን እንጂ የኪራይ ተመኑ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጸድቆ ለወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ለወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፤ እንዲሁም፣ ለመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ወደ ኪራይ እንዲገቡ የሚያዝዝ ደብዳቤ ተጽፎ ስለነበር ጉዳዩ አቤቱታ አቅራቢዎች በፈለጉት መልክ ሊፈታ አልቻለም። አቤቱታ አቅራቢዎቹ ችግራቸው ሳይፈታ በእንጥልጥል እስከዛሬ ድረስ ሊቆዩ ተገደዋል።
የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ፍላጎት የመሬት ባለይዞታነት መብት እንዲፈጠርላቸው ሲሆን፣ የወረዳውና የክፍለ ከተማው ቤቶች ፍላጎት ግን የወጣውን የኪራይ ተመን መሠረት አድርጎ ለማከራየት ነበር። ይሁንና የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ የመሬት ባለይዞታነት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ በመሆኑ የቤቶች አስተዳደር መሬት መስጠት እንደማይችል ገልጾ፤ የመሬት ባለይዞታነት ጥያቄአቸው ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከፈለጉ ጉዳዩን ለቤቶች አስተዳደር ሳይሆን ለመሬት አስተዳደር ማቅረብ እንደሚገባቸው ምክረ ሃሳብ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
ዛሬም ቢሆን የመሬት ባለይዞታነት ጥያቄ የሚመለሰው በመሬት አስተዳደር እንጂ በቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት አለመሆኑን የገለጹት አቶ ዳኛቸው፤ የሰዎች ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ዘንድ የቤቶች አስተዳደር የራሱን ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። በቅርቡም የቤቶች አስተዳደር የሚደርስበትን ቁርጥ ያለ ውሳኔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።
የቤቶች አስተዳደር ከመሬት ተነስቶ የቤት ኪራይ ግምት ይሰጣል ወይ? ይህንን አሠራርስ ሕጋዊ የሚያደርግ መመሪያ ወይም አሠራር አለ ወይ? ተብለው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተጠየቁት አቶ ዳኛቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል። የተለያዩ መመሪያዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ መጥተዋል። እኔ የማውቃቸው መመሪያዎች አንደኛው መመሪያ ቁጥር 4፣ 2009 ሲሆን፤ መመሪያ ቁጥር 5፣ 2011 ሁለተኛው፤ አሁን በቅርቡ የወጣው መመሪያ ቁጥር 6፤ 2015 ደግሞ ሦስተኛው ነው። በተዋረድ እነኚህ መመሪያዎች በየዕለቱ እየተለወጡ የመጡበት ሁኔታ አለ። ግን በአጋጣሚ ሆኖ እነኚህ ሁሉም መመሪያዎች ከኪራይ ተመን አወጣጥና ከቤት ቁጥር አሰጣጥ አኳያ ሲታይ በማንኛውም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ወይም በግለሰብ የተሠሩ ቤቶች ወደ መንግሥት አስተዳደር ይግቡ ተብሎ ከታች፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማው በአስተዳደሩ ሲወሰንና ወደ መንግሥት ቤትነት ሲቀየሩ የቤት ቁጥር የመስጠት፤ የኪራይ ተመን የማውጣት የቤቶች አስተዳደር ሥራ ይሆናል።
ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ የቤቶች አስተዳደር ከመሬት ተነስቶ የኪራይ ተመን ማውጣት አይችልም። እዚህ ላይ የአስተዳደሩ ውሳኔ የሚለውን በአጽኖት ማየት ይገባል። ነገር ግን፣ በማንኛውም ሁኔታ የበላይ መስሪያ ቤትም ቢሆን የቤቶችን ተመን አውጥቶ ወደ ኪራይ አስገቡት የማለት ሥልጣን የለውም። ለምሳሌ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ ለአንድ ለተወሰነ ፕሮጀክት፣ በአንድ አካባቢ ቤት ቢሠራና ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ቤቶቹን ለመንግሥት አስረክቦ ሊሄድ ይችላል። ለመንግሥት አስረክቦ ሲሄድ በመንግሥት በኩል የተረከበው አካል ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ሲታሰብ የኪራይ ተመን ይወጣለታል።
አቤቱታ ካቀረቡት ሰዎች መካከል ለተወሰኑ ሰዎች ተለይቶ ካርታ ተሰጥቷቸዋል፤ ግማሾቹ ደግሞ የአፈር ግብር እየከፈሉ ይገኛሉ። ስለዚህ ምን ትላላችሁ ብለን የጠየቅናቸው አቶ ዳኛቸው ይህን ጉዳይ ለመሬት ማኔጅመንት እንዳቀረቡትና መሬት ማኔጅመንት ደግሞ ምንም ዓይነት ካርታ እንዳልሰጠ በደብዳቤ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
የእናንተ መስሪያ ቤት ስለቤቶቹ ለማጣራት ለባለ አደራ ቦርድ እና ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ለደብዳቤአችሁ ምላሽ የሰጡት ከላይ የተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች ስለቤቶቹ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ መረጃ ካላገኛችሁ ቤቶቹን የእኛ ናቸው ማለት ትችላላችሁ ወይ? ስንል አቶ ዳኛቸውን ጠይቀን ነበር። ከላይ የተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች ውዝግብ የተነሳባቸውን ቤቶች የቤቶች አስተዳደር መሆናቸውን ከገለጹ ውዝግብ የተነሳባቸው የቤቶች አስተዳደር ናቸው ሊባሉ እንደማይችሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። አሁንም ቢሆን ከቤቶች ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር ሊፈታ የሚችለው በክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር ነው ያሉት አቶ ዳኛቸው፤ ችግሩ መፍትሄ እስከሚገኝለት ድረስ መመሪያና አሠራርን ተከትለው ተባባሪ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት እና የክፍለ ከተማው ዋና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምላሽ
ባለፈው በነበረው የምርመራ ሂደት የቤቶች አስተዳደር ጉዳዩን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር መጨረስ ይችላል ብላችሁን ነበር:: ይህን ተከትሎ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር በመሄድ ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ በወረዳው ፋይል ተደራጅቶ ይስተናገዱ ተባለ:: በዚህም ነዋሪዎቹ ፋይል ማደራጀት ጀመሩ:: ነገር ግን ጉዳዩ በሂደት ላይ እያለ ፋይል መደራጀቱ እንዲቆም ተደረገ:: ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ኃላፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጌ ተዋበ ባለፈው ጉዳዩ በየአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ማለቅ እንደሚችል ነግራችሁን ነበር? ስንል:: ሲል ጥያቄ አቀረብንላቸው:: የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኃላፊም “መሬት አስተዳደር ይጨርሰው አላልኩም” ሲሉ ቀደም ብሎ የተናገሩትን ካዱ::
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር መጨረስ ይችላል ብለው የተናገሩት በቪዲዮም በድምጽም መረጃውን ይዘነዋል:: ሁለቱንም ለህዝብ እናሳያለን፤ አንድ እድል እንስጣችሁ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ጉዳዩን መጨረስ ይችላል ብለዋል ወይስ አላሉም? ብለን ጠየቅን:: በቪዲዮ እና በድምጽ መረጃው እንዳለን የተረዱት አቶ አንዳርጌ ስለጉዳዩ ምንም ማለት ሳይችሉ ቀሩ::
ከዚህ ቀጥሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ቤቶች ከየት ተነስተው ወደየት እንደመጡ በሚያሳያው ታሪክ ባለፈው በነበረው ምርመራ ሂደት መግባባት ተችሎ ነበር:: በዚህም የቤቶች የቀደመ ታሪካቸው ጋር ተስማምተን ጨርሰን ነበር:: እዚህ ላይ ምን ይላሉ? ስንል የክፍለ ከተማውን የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊውን ጠየቅን:: የክፍለ ከተማው የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊውም ባለፈው የጨረስነውን ጉዳይ ላለማመን በመፈለግ “ተስማምተን ጨረስን የሚባል ነገር የለም” ሲሉ መለሱ::
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በቀደመው ምርመራ ተወያይተንባቸው የነበሩ ሃሳቦችን በማንሳት እዚህ ላይ ልዩነትዎ ምንድን ነው? ሲል ጠየቀ:: ማስተባበል ያልቻሉት ኃላፊም “አሁንም በታሪኩ ልዩነት የለኝም” ሲሉ እንደገና ሌላ ሃሳብ ሰጡ:: እዚህ ላይ ፍርዱን ለእናንተ ለአንባቢያን ትቻለሁ::
የዛሬውን ምርመራ በምንሰራበት ወቅት የቤቶች አስተዳደር ኃላፊው “ቤቶቹ ባለቤት አልባ ናቸው” ሲሉ ተናገሩ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በቤቶቹ ውስጥ ከ60 ዓመታት በላይ የነበሩ ነዋሪዎች እያሉ ስለምን ቤቶቹ ባለቤት አልባ ይላሉ? ሲል ኃላፊውን ጠየቀ:: ኃላፊውም “ባለቤት አልባ ያልኩት ቤቶቹን የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሰርቶ የሰጣቸው ስለሆኑ ነው” ሲሉ መለሱ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በምን መነሻ ነው ቤቶቹን የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የሰራቸው ናቸው ለማለት የቻሉት? ሲል ጥያቄ ሰነዘረ:: ኃላፊውም በንዴትና በማን አለብኝነት “አዎ ቤቶቹን አዋሽ ቆዳ ነው የሰራቸው!” ሲሉ መለሱ::
ዝግጅት ክፍሉም አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የሰራቸው ናቸው ካሉ የአዋሽ ፋብሪካ ስለመስራቱ የሚያሳይ አንድ ሰነድ ሊያሳዩኝ ይችላሉ? ሲል ኃለፊውን ጠየቀ:: ኃላፊውም ምንም ሰነድ ማቅረብ ሳይችሉ ቀሩ:: የዝግጅት ክፍሉም በኃላፊነት ደረጃ ተቀምጠው የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ያስፈጽማሉ ተብለው ሳለ ስለምን ያለምንም ማስረጃ ኃላፊነት የጎደለው መረጃ ለህዝብ ይሰጣሉ? ሲል ጠየቃቸው:: ለዚህም ጥያቄ ምንም መልስ አልነበራቸውም:: እዚህ ላይ ፍርዱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትቸዋለሁ::
ያለመረጃ እንደፈለጉ የሚናገሩት የቤቶች ኃላፊ፣ “አቤቱታ አቅራቢዎች ቤታቸውን የሰሩት በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ከሚገኝ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ መሬት ላይ ነው” ሲሉ ሃሳብ ሰጡ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ‹‹አቤቱታ አቅራቢዎቹ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ መሬት ላይ ቤት ስለመስራታቸው ማስረጃ ማቅረብ ይችላሉ?›› ሲል ጠየቃቸው:: አሁንም ለተጠየቁት ጥያቄ ምንም ምላሽ አልነበራቸውም::
ይህን ተከትሎ ክርክሩን ሲታደሙ የነበሩት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ አህመድ በክርክሩ ጣልቃ ገቡ:: ለተፈጠረው ችግር መልስ ሊያስገኝ የሚችል የመፍትሄ ሃሳብም አቀረቡ:: የመፍትሄ ሃሳቡም የሚከተለው ነው::
አቤቱታ አቅራቢዎቹ የቤት ባለቤትነት የሚያስገኝ መብት ካላቸው መብት ያጣሉ የሚል አቋም የለንም:: በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ያሉ ሰራተኞች በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሰራተኞች ስለነበሩ ቤቶቹን የሰራው አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ነው የሚሉ አንዳንድ ያልተረጋገጡ መረጃ ይደርሰናል:: በትክክል አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሰርቶ ለሰራተኞቹ ሰርቶ ሰጥቷል ወይስ የሚለውን በደንብ መመርመር ያስፈልጋል::
አቶ መሀመድ ዘለግ ያለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በመጨረሻም ለጉዳዩ መፍትሄ ለማበጀት አቤቱታ አቅራቢዎች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት እና መሬት ልማት አስተዳደር ያካተተ ኮሚቴ በማዋቀር በአጭር ቀናት ውስጥ ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል::
የጋዜጠኛው ትዝብት ፡- የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ አህመድ ችግሩን የተረዱበትና ችግሩን ለመፍታት የሄዱበትን የአመራር ጥብብ እጅግ በጣም አደንቃለሁ:: ከወጣት አመራሮች ይህን ያህል ብስለት የተሞላበት የአመራር ጥብብ ማስተዋሌ ወደፊት አገራችን ብዙ ተስፋዎች እንዳሏት መገንዘብ አስችሎኛል:: እንደዚህ አይነት በሳል አመራሮችን ያብዛልን መልእክቴ ነው::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2015