
አዲስ አበባ፡- በመኸር ግብርና ስራዎች ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የግብርና ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው እንደገለጹት፤ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው።
እንደ ዶክተር ኃይለማርያም ገለጻ፤ በመኸር ግብርናው ክልሉ በስፋት የሚመረቱ 10 ዋና ዋና ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጓል። ጤፍ፣ ስንዴ፣ አኩሪ አተር፣ ሩዝ፣ በቆሎና ማሽላ በመኸር ግብርና ልማት ትኩረት ከተሰጣቸው ምርቶች መካከል ናቸው።
አኩሪ አተር እንደ አገር ከሚመረተው 85 በመቶ ድርሻ ከክልሉ ልማት የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በአዊ፣ በምዕራብ ጎጃምና ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደርና ወልቃይት አካባቢ በስፋት ለማምረት መታቀዱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪ ከውጪ ይገባ የነበረውን የምግብ ዘይት ምርት ጥሬ ዕቃን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። በተለይም ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ሱፍና ሌሎች የቅባት እህሎች በስፋት እንዲመረቱ የሚረዳ ዝግጅት ማከናወኑንና የባለሙያ ድጋፍ የማቅረብ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚሰራው የግብርናው ዘርፍ እንቅስቃሴ ለአገር ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ በመወጣት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር ኃይለማርያም፤ በተለይም መካናይዜሽን ከ700 በላይ ትራክተሮች፣ 20 ሺህ የውሃ መሳቢያዎችን እንዲሁም ኮምባይነሮችና መውቂያ ማሽኖች በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል መቻሉን አመላክተዋል።
በዚህም በዘንድሮ ዓመት የሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ በሄክታር በአማካይ 24 ነጥብ 5 ኩንታል የነበረውን ወደ 29 ነጥብ 5 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል። በዘንድሮ የምርት ዘመን መስኖና የኩታ ገጠም የአስተራረስ ሥርዓት በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል። በዚህም ከአራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ በተለያዩ ሰብሎች ከ140 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።
በክልሉ ጤፍ ከ900 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማልማት ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ተመርቷል ያሉት ኃላፊው፤ በመኸር ግብርና ከ832 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኖ ከ33 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት መቻሉን ገልጸዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2015