
– የሦስት ቢሊዮን ችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቋል
አሰላ:– በክልሉ ከተዘጋጁት አምሥት ቢሊዮን ችግኞች 4 ነጥብ 5 ቢሊዮኑ ዘንድሮ እንደሚተከሉ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የግብርና ዘርፍ ባለሥልጣናት የአርሲ ዞን የችግኝ ልማትን በትናንትናው ዕለት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደተናገሩት፤ ይህ ሥራ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተጣምሮ ሲሠራ ነው። በመሆኑም ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት ከታቀደው በላይ ችግኝ በክልል ደረጃ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ዘንድሮ አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ችግኝ ለማልማት ታቅዶ አምሥት ቢሊዮን ችግኝ መልማቱንም አስረድተዋል።
ክልሉ ከዚህ በፊት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሀገር ደረጃ ከተተከለው አብዛኛውን እንደሸፈነ ጠቁመው፤ በተያዘው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተዘጋጁት አምሥት ቢሊዮን ችግኞች አራት ነጥብ አምሥት ቢሊዮን ያህሉ ይተከላሉ ብለ ዋል።
ለዚህም ቀደም ብሎ እንቅስቃሴ መጀመሩንና ሦስት ቢሊዮን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። ቁፋሮው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም ገልፀዋል።
የክልሉ ሕዝብ በተፋሰስ ሥራው ላይ ያሳየውን ተነሳሽነት እና የእኔነት ስሜት በአረንጓዴ አሻራው ላይ እንደሚደግመው እንጠብቃለንም ነው ያሉት።
በተጎበኙት የአርሲ ዞን ጢዮ እና ኤጦሳ ወረዳዎች በተለየ ሁኔታ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ከዕቅድ በላይ ችግኞች መተከላቸውን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከችግኝ ዝግጅት አልፎ ተከላ መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ጌቱ፤ በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ቦጋለ በበኩላቸው፤ የተጎበኙት ችግኞች በቁጥር ከዕቅድ በላይ የተሳኩ መሆናቸውን ገልፀው በተገቢው የዕድገት ደረጃ ላይ መገኘታቸው የፅድቀት መጠናቸው ከፍ እንዲል ያደርገዋል ብለዋል።
የምርምር ኢንስቲትዩቱ በርካታ የግብርና ምርምሮችን እየለቀቀ መሆኑን አስረድተው የተጎበኙት ዓይነት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች አርሶ አደሩን ከሳይንስ የምርምር ውጤቶች ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015