በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ የስፖርቱ ዘርፍ ቀስበቀስ ከመንግሥት በጀት በመላቀቅ የራሱን ቋሚ ሀብት ማመንጨት እንዳለበት ያስቀምጣል። ስፖርቱ ቋሚ ሀብት ለማመንጨት ዘርፉን መደገፍ የሚችሉ ባለሀብቶችን በስፋት ማሳተፍ እና ህዝባዊ መሰረት ማስያዝ እንደሚገባም በፖሊሲው ተቀምጧል። በሌላው ዓለም ያለው የስፖርት ዘርፍ እድገት በዚህ መንገድ የተቃኘ ነው።
በኢትዮጵያ የስፖርቱን ዘርፍ ከመንግሥት የበጀት ጥገኝነት አላቆ ራሱን እንዲችልና ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ጥረቶች ቢደረጉም እምብዛም ውጤት ማምጣት አልተቻለም፡፡ ይህም ስፖርቱ የመንግሥትን እጅ ጠባቂ ሆኖ እንዲጓዝ አስገድዶታል። በዚህም ዘርፉ ህዝባዊ መሰረት አጥቶ በርካታ ክለቦች እንዲፈርሱ ያደረገ ሲሆን፣ የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖችም በገንዘብ እጥረት ውድድሮችን ለማዘጋጀት እንዲቸገሩ አድርጓል።
ከመንግሥት በጀት ተላቀው ራሳቸውን ለመቻል ጥረት እያደረጉ ከሚገኙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አንዱ የቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን ተጠቃሽ ነው። የቦክስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ስፖርት ፖሊሲው እቅድ ስራ ላይ እንዲውል እና ስፖርቱን ከመንግሥት ድጎማ ለማላቀቅ እንዲሁም ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በ2015 ዓ.ም ትልቁ እቅዱ የቦክስ ስፖርትን ከመንግስት በጀት አላቆ በራሱ ፋይናንስ የሚመራበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የቦክስ ፌዴሬሽን እንደ አትሌቲክስና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ ባስቀመጠው እቅድ መሰረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ስራው ሂደትን የሚጠይቅ እንደመሆኑም በሚቀጥሉት ዓመታት ፌዴሬሽኑ እራሱን በፋይናንስና የሰው ኃይል የሚያደራጅበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
በአገር ውስጥ የሚካሄዱ የቦክስ ውድድሮች በዚሁ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት በበቂ ሁኔታ መደረግ ያልቻሉ ሲሆን፣ ስፖርቱን ከመንግሥት በማላቀቅ የራሱን ሀብት አመንጭቶ ውድድሮችን ለማስፋት ጥረት መጀመሩን ጠቁሟል። ስፖርቱ በፋይናንስ ረገድ በሁለት እግሩ ቆሞ በቂ የአገር ውስጥ ውድድሮች መዘጋጀታቸው ለቦክስ ስፖርት እድገት የጎላ ሚናን ይጫወታል። ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት ጥሩ ታሪክ ቢኖራትም በፋይናንስና በሌሎች ችግሮች ተገቢው ስራ ባለመሰራቱ ለመቀዛቀዙ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡
በዓለም ላይ ለሚካሄድ አንድ የቡጢ ፍልሚያ ለአሸናፊዎች ብቻ በሽልማት መልክ በሚሊዮን ዶላሮች ይበረከታል፡፡ ይህ የሚያሳየው ስፖርቱ ምንያህል እንዳደገና የበርካቶችን ትኩረት መያዝ እንደሚችል ነው። ስፖርቱ ማደጉ በርካታ ደጋፊ አካላትን እና ባለሀብቶችን ከጎኑ እንዲሰለፉ ያደርጋል፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ጠንካራ ሕዝባዊ መሰረት ይዞ ቋሚ የሀብት ምንጭ ያፈራል፡፡
ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ከሚያካሄዳቸው ውድድሮች መካከል የክለቦች ቻምፒዮና አንዱ ሲሆን እስከ አሁን በተደረጉ ሁለት ዙሮች ውድድሮቹን ለሚያዘጋጁና ለሚደግፉ አካላት በመሸጥ ሀብት ለማመንጨት ተሞክሯል፡፡ በመጀመርያ ዙር ክለቦች ቦክስ ቻምፒዮና ውድደሩን ለሲሳይ አድሬሴ ሁነት አዘጋጅ እና የሁለተኛ ዙር ውድድርን ደግሞ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለማካሄድ ተችሏል፡፡
በመጪው ሰኔ 2015 ዓ.ም የሚካሄደውን ሶስተኛውንና የማጠቃለያውን ውድድርም ለመሸጥ እና ስፖንሰር ማድረግ ለሚችሉ አካላት ለመስጠት በመሰራት ላይ ነው፡፡ ይሄ ስራ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት በጀት እና ድጎማ ወጥቶ የራሱን ገንዘብ በማመንጨት የተሻለ ተጠቃሚ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱ እንደሚሆን የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ይናገራሉ። ይህም የኢትዮጵያ ቦክስ የፌዴሬሽን ከመንግሥት ድጎማ ተላቆ ህዝባዊ መሰረት እንዲያዝ የሚደረገው ጥረት ማሳያ መሆኑን ያብራራሉ።
“ባለሙያውና አትሌቱ እንዳለ ሆኖ የስፖርቱ የጀርባ አጥንት ገንዘብ ነው” ያሉት የፅህፈት ቤት ሃላፊው የበጀት ችግርን ለመቅረፍና ፌዴሬሽኑ እራሱን ችሎ ከመንግሥት በጀት እንዲላቀቅ የተጀመረው ጥረት አበረታች ውጤት እያሳየ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በዚህ እራስን በመቻል ጥረት ውስጥ ውድድሮችን መሸጥ፣ ስፖንሰር ማምጣትና ባለሀብቱ ስፖርቱን የሚደግፍበትን መንገድ ማመቻቸት ትልቁ ስራ እንደሆነም አክለዋል። ቀደም ሲል ይህን ጥረት ለማሳካት እንቅፋት የሆኑ የአሰራር ሥርዓቶች ቢኖሩም አሁን ግን ፌዴሬሽኑ ስራዎችን በራሱ በመስራቱ እራሱንና ደጋፊ አካላትን መጥቀም እንደቻለ አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ እራሱን በገቢ ለመቻል በሚያደርገው ጥረት የተለያዩ የገቢ ማመንጫ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ስፖርቱን ህዝባዊ የማድረጉንም ስራ እየተለማመደ ነው፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ቀጣይ በፋይናንስ እራሱን በቻለ ቁጥር በስፖርቱ ውስጥ ያሉ አካላት ከመጠቀማቸውም በላይ ስፖርቱ ለማደግ እንደማይቸገር አቶ ስንታየሁ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015