– አራት ሺህ ሜትሪክ ቶን የማገዶ እንጨት መቀነስ ተችሏል
አዲስ አበባ፡- በጅማ ዞን በአራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጭ ባዮ ጋዝ በመጀመሩ አራት ሺህ ሜትሪክ ቶን የማገዶ እንጨት መቀነስ መቻሉን የዞኑ የውሃ ሃብት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ገለጸ። ወደ ተፋሰስ የሚለቀቀውን የቡና እጣቢ 85 በመቶ መቀነስ ተችሏል።
በጅማ ዞን የውሃ ሃብት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀበል አባፊጣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዞኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ ነው። 200 ለሚሆኑ አባወራዎች በአራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ ባዮ ጋዝ እንዲያመርቱ በተደረገው ጥረት አራት ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚሆን የማገዶ እንጨትን በማስቀረት የደን መመናመንን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
የደን አካላት መመናመን የውሃ አካላት ላይ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአጋር አካላት ጋር በጥምረት እንደሚሠሩ አሳውቀዋል። ከደን ልማት፣ ከግብርና ቢሮ እና ከአከባቢ ጥበቃ ጋር የጋራ ኮሚቴ በማቋቋምና የጋራ እቅድ በማቀድ እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት።
“የውሃ ሃብት ልማቱን ለማረጋገጥ የከርሰ ምድሩን ውሃ ሊቀንሱ የሚችሉ ተክሎችን በማስወገድ በአዲስ እና ውሃውን
ሊጠብቁ የሚችሉ ዕፅዋት የመተካት ሥራ ተጀምሯል፤ በዚህም በዞኑ የውሃ ግፊት መጠን ጨምሯል” ሲሉ አብራርተዋል።
ከደንና ውሃ ሀብቶች ጥበቃው ጎን ለጎን የተለቀመ ቡናን አጥበው ፍሳሹን ወደ ተፋሰስ አካላት የሚጨምሩ የቡና አምራች ድርጅቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እያስተማሩ እና እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ በዞኑ ስድስት ሺህ የሚሆኑ የቡና አምራች ድርጅቶች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ወደ ውሃ አካላት እንዳይለቁ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
የቡና ፋብሪካ ያላቸው ባለሃብቶች ፍቃድ ከማውጣታቸው በፊት ገለባውን የሚጥሉበት የራሳቸው የቆሻሻ ማስወገጃ ገንዳ እንዲያዘጋጁ ተደርጓል። የቡናው ገለባ ላይ ተጨማሪ እሴቶችን በመጨመር ወደ ማዳበሪያነት ለመቀየርም እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል ሲሉም አክለዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015