
በትምህርት ዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የተወሰነ አካል ትጋት ብቻ የሚጠይቅ ሳይሆን የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የወላጆችና የአስተዳደር ሠራተኞች ድምር ትጋት መሆኑ የማያጠራጥር ሐቅ ነው።
ከዚህም የተነሳ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች፣ የትምህርት የአስተዳደር አካላት በጋራ በመሆን በትምህርት ዘርፉ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ብሎም ብቁ ዜጋ ለመቅረጽ የተለያዩ የመማር ማስተማር ሥነ- ዘዴን ይጠቀማሉ።
ከእነዚህ ሥነ ዘዴዎች መካከል የጥያቄና መልስ ውድድር፣ የተለያዩ አጋዥ መጽሐፎችን የመረጃ ምንጮች መጠቀም፤ ከተመደበው የሥራ ሰዓት ውጪ ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት መስጠት እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።
በትምህርት የበቃ ዜጋ ለማፍራት ቆየት ያለውና የተለመደውን የመማር ማስተማር ሥነ-ዘዴ ብቻ መጠቀም ውጤታማ እንደማያደርግ የበርካታ ሀገራት ልምድ ያሳያል።
በተጨማሪም ለተማሪው በየጊዜው የሚዘጋጅላቸው ሀገር አቀፍ ፈተና በብቃት እንዲሻገር ተግባር ተኮር ትምህርትና ለተማሪው ማነቃቂያ የሚሆኑ ምዘናዎችና የጥያቄና መልስ ውድድሮችን ማዘጋጀት ጠቃሚ መሆኑን ተማሪዎች ይናገራሉ።
እንደሀገር በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለውን የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርቶች የሚዘጋጀው ውድድር ለመጪው የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ለማሻሻል እንደሚረዳ ትምህርት ሚኒስቴርም ይገልጻል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከኦልማርት ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በ2015 የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የእንግሊዘኛና በሒሳብ ትምህርቶች የጥያቄና መልስ ውድድር አዘጋጅቷል።
በማጠቃለያው መርሐ ግብር ላይ የጥያቄና መልስ ውድድሩ ተማሪዎች ለፈተና በማዘጋጀት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የገለጹት በትምህርት ሚኒስቴር የሒሳብ ሳይንስና ሥነ-ጥበብ ማበልጸጊያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ ተሬሳ ናቸው።
ውድድሩ በሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርቶች መደረጉ በተለይ ተማሪዎች በዋና ዋና ትምህርቶች ላይ የዳበረ ዕውቀት እንዲኖራቸው ያስችላል የሚሉት አቶ ታደሰ፤ በርካታ ተማሪዎችን በተመሳሳይ የጥያቄና መልስ ውድድሮች በማሳተፍ ለፈተና ብቁ ሆነው እንዲዘጋጁ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣በዘርፉ ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ ከኦልማርት ፋውንዴሽን ጋር በትብብር ሲሠራ መቆየቱንና የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ እንደሀገር ያሽቆለቆለውን የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ እንዲያንሰራራ የሚያግዝ እንደሆነ ያብራራሉ።
በትምህርት የበቃ ዜጋን ማፍራት ለተወሰነ ተቋም ወይም ግለሰብ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም በትብብር መሥራት ይኖርበታል ሲሉ ያስረዳሉ።
በጥያቄና መልስ ውድድሩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀችው ተማሪ ሙፈሪያት ታደሰ በበኩሏ፤ ውድድሩ አዝናኝና አስተማሪ መሆኑን በመግለጽ፤ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተማሪዎች ለምናደርገው ዝግጅት ወሳኝ ግብዓቶችን ያገኘንበት ነው ብላለች።
ተማሪው በግሉ ከሚያደርገው ዝግጅት ባለፈ ተመሳሳይ ውድድሮችን ላይ በመሳተፍና በመከታተል ለፈተና የሚያዘጋጁ ጥያቄዎችን መሥራት ከቻለ ሀገር አቀፍ ፈተናው ላይ የተሻለ ውጤት የማያመጣበት ምክንያት አይኖርም ስትል ሃሳቧን ሰጥታለች።
በውድድሩ ሁለተኛ የወጣው ተማሪ አብርሃም ሓፍቶም ደግሞ የጥያቄና መልስ ውድድሮችን በየትምህርት ቤቶችና በሀገር አቀፍ ደረጃ ማዘጋጀት ተማሪው ለፈተና ብቁ እንዲሆን ከሚያግዙ መንገዶች አንዱ መሆኑን ነው የተናገረው።
በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ጠንክሮ መማር ያስፈልጋል ያለው ተማሪ አብርሃም፤ ከጥናትና ጊዜ አጠቃቀም ባለፈ ወሳኝ ጥያቄዎች የተካተቱባቸው የጥያቄና መልስ ውድድሮችን ለፈተና ዝግጅት እንደማንቂያ አድርጎ መጠቀም እንደሚቻል ያስረዳል።
ውድድሩን ያዘጋጀው የኦልማርት ፋውንዴሽን መሥራችና የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ኑርሁሴን ሐሰን በበኩላቸው፤ ፋውንዴሽኑ በማኅበራዊ ጉዳዮች በተለይ በትምህርት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ውድድር ለማኅበራዊም ሆነ ለተፈጥሮ ሳይንስ መሠረት በሆኑ ሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መከናወኑን አስረድተዋል።
ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሽቆለቆለውን የዩኒቨርስቲ የመግቢያ ፈተና ውጤት እንዲያንሰራራ ከማገዝ ባለፈ ተማሪዎች ያላቸውን ዕውቀት እንዲያጎለብቱና ትምህርታቸው ላይ ይበልጥ እንዲያተኩሩ የሚረዳ በመሆኑ በቀጣይነትም ይሠራበታል ሲሉ ተናግረዋል።
ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የትምህርት ሥርዓቱን ማዘመንና በዘርፉ ብቁ ዜጋ ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ በትምህርት ዘርፉ ላይ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015