እንደ መግቢያ
ከአዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል ወደ ቦሌ ቡልቡላ በሚወስደው መንገድ ላይ ነኝ።200 ሜትር ዘቅዘቅ እንዳልኩኝ በረባዳው ሥፍራ የከተሙ ወጣቶች አገኘሁ።እነዚህ ወጣቶች ሁሉ ነገራቸው ትናንት እና ዛሬ በተለየ የንጽጽር መነፅር በልባቸው ውስጥ ስለማኖራቸውና ስለነገ ሕይወታቸው በሰፊው እያሰቡ ስለመሆናቸው ተግባራቸው ይመሰክራል። በእርግጥ ያለፈ ሕይወታቸውን ለማደስ፤ የባከነ ጊዜ ለማካካስ ማሰባቸው ላያስገርም ይችላል። እነርሱ ዛሬ ላይ ሆነው ትናንትን የኋሊት ሲያስታውሱ ብዙ ነገሮች በቁጭት የተሞሉ ሆነው ያገኟቸዋል። እናም ከነገ ጋር ለመሽቀዳደምና የባከነውን ጊዜ ለማካካስ እየተጉ ነው።
እነዚህ ወጣቶች ከአንድ ዓመት በፊት በሱስ ውስጥ ተደብቀው ለራሳቸውም ለአካባቢያቸውም ስጋት ተደርገው ይታዩ ነበር። ይሁንና ይህ ድግግሞሽ የተሞላበትና በሰዎች ዘንድ በጥላቻ ስሜት የተሞላ ሕይወት ሠላም ሊሰጣቸው አልቻለም። እናም ከዕለታት አንድ ቀን በሱስ ደንዝዘን ዕድሜያችንን ከምንጨርሰው እስኪ ሥራ እንሞክር ብለው ተነሳሱ። ምን እንስራ ሲባል ግን የሥራ ባህላቸው ደካማና የሱስ ቅጥረኛ ስለሆኑ አዲስ ሥራ ላይ ማማተሩ አልሆነላቸውም።
ሰፋፊ ፈጠራዎችን ስለማሰብም አልቻሉም። ግን በቅርበታቸው ሲታዘቡ እና ሲመለከቱ ከነበረው አንዳች ነገር ውል አለባቸው። በቃ በቅርበታቸው ያለው ቆሻሻ ለእነርሱ አንዳች የሕይወት መስመር እንደሚሰጣቸው አስበዋል። እናም ሕይወታቸውም ቢዝነሳቸውም ከዚህ ቆሻሻ ይጀምር ዘንድ ወሰኑ። የዚህ ሃሳብ ጠንሳሾች በሰላሳዎቹ የሚቆጠሩ ቢሆንም ወደ ተግባር የቀየሩት 17 ሆነው ነው። ከሱስ ተላቀው ዛሬ በርካቶችን ቀልብ የሚስብ ሥራ እየሰሩ ነው።
አብነቶች
ወጣት ነስሩ ሻፊ ቦሌ ሚካኤል 110 በሚባለው ስፍራ ነው የኑሮ መሰረቱ። በሙያ የታደለ እጅ አለው። የሎደር፤ ክሬቼር ኦፕሬተር ነበር። ሹፍርናም ሞክሯል። ሁሉ ነገር አልፎ ሕይወቱ ክፉኛ ተፈትኗል። ስደትን ሞክሯል። ወደ የመን ለማቅናት ሲል ሶማሊያ ቦሳሶ ላይ አደጋ ደርሶ ሕይወቱን በተዓምር ተርፋለች። ግን ‹‹ሃብቴ ጉልበቴ ነው›› የሚለው ነስሩ ዛሬ ምንም ሥራ አይንቅም፤ተስፋ አይቆርጥም።
ለበርካታ ዓመታት በሱስ ውስጥ ቆይቷል። ሱሰኛ ሆኜ በምቀመጥበት ወቅት እኔም አካባቢዬም ቆሽሸን ነበር ይላል። ይህ የእርሱ ብቻ ሳይሆን የጓደኞቹም ሃሳብ ነው። በአሁኑ ወቅት ውብ ያደረጉት ሥፍራ ሰዎች ሊቆሙበት ቀርቶ ለማለፍም በጣም አስፈሪ እንደነበርም ይናገራል።
ነስሩ እና ጓደኞቹ ስማቸውን ለማደስ ሲሉ ልጅ ሆነው የሚቸግራቸውን ለማስታወስ ተገደዱ፡ ነስሩ 37 ዓመት ደፍኗል። ከልጅነቱ ጀምሮ የሚዝናኑበት አካባቢ አልነበረም። እና ይህ ትውልድ በዚህ መንገድ መሄድ አለበት ወይ የሚለው ጥያቄ ፈጠረባቸው። ስለዚህ እኛም ከሱስ እንፅዳ ከዚያም አካባቢያችን ይጽዳ ብለው ተነሱ።እኛ በሱስ ውስጥ ቆይተን አዲስ ትውልድ ከሱስ የሚርቅበት መንገድ መጀመር አለብን አሉ። በመቃም እና በማጨስ የሚባክነው ጊዜ መደገም እንደሌለበት ተስማሙ። እናም ሁሉንም ነገር ከራሳቸው ጀምረው ማስተካከል ጀመሩ።
አሁን እነርሱ ቆሻሻ ብለው የሚጥሉት ነገር የለም። የቤት ፍርስራሽ፣ የውሃ እና ለስላሳ ፕላስቲኮች፣ ፌስታሎች፣ የግንባታ ፍርስራሾች፣ የሲሚንቶ ማሸጊያ ከረጢቶችና ወረቀቶችን፣ ለወለል ንጣፍ የሚሆኑ ስብርባሪ ጌጠኛ ድንጋዮች፣ ቆርኪ፣ ብሎኬቶችን ይገዛሉ። ነገሩን ላለማጋነን ቆሻሻ ተብሎ የማይገዙት ነገር የለም።
አንድም የሚቃጠል ነገር በአካባቢያቸው የለም። የሚበሰብስ ቆሻሻ ከሆነ መሬት ውስጥ ይቀብሩታል። ከዚያ ይህ ዛሬ ቆሻሻ ቢሆንም ነገ ለም አፈር ነው። እና መሬቱን ዛሬ ቢያቆሽሽም ነገ ወደ ለም አፈር ሲቀየር መልሶ አረንጓዴ ሳር ያበቅላል፤ ትውልድም ይጠቀምበታል።
ነስሩ አሁን ባለው ሁኔታ ዋንኛ ሃብት ብር አይደለም ይላል። የእኛ ዋንኛ ገቢያችን፤ ፍቅርና መሰብሰባችን ነው።እንደ ዱሮው ሸራ አንጥፈን በአጥር ጥግ ስንተኛ መዋል እና ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ልንሰራ እንችል ይሆናል። ግን ደግሞ ይህ ነገር እስከ መቼ የሚለው የዘወትር ጥያቄያቸው ነበር።
ነስሩና ጓደኞቹ በሚውሉበት አካባቢ ቆሻሻ በብዛት የሚደፋበት ሥፍራ ነበር። ቆሻሻ መጣሉ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ ጫና መፍጠሩም አሳሰባቸው። ከዚያም ያንን ቆሻሻ እየለቃቀሙ ጥቅም ላይ ማዋል ጀመሩ። በተለይም የውሃ ፕላስቲኮችን በተለያዩ ቅርፆች እየሰጧቸው ለአጥር፣ በርና አካባቢውን ማስዋቢያ አደረጉት። የተሽከርካሪ ጎማ ለወንበር መስሪያ ተጠቀሙበት።
ጠማማ ዕንጨቶችን አቃንተው ጠቃሚ ቁሳቁስ ሠሩበት። ብቻ በእነርሱ ዘንድ ቆሻሻ ተብሎ ጥቅም ላይ የማይውል ነገር የለም። ይህ ሥራቸው የሰዎችን ቀልብ እየገዛ መምጣቱን ነው የሚናገሩት። አልፎ አልፎ ቀድሞ የሚያውቋቸው ሰዎች ዛሬ ተለውጠው ሲመለከቷቸው፤ በርቱ ይሏቸዋል። አቅም ያለው ደግሞ ከቤት ጠርቶ ምሳ ይጋብዛቸዋል፤ አለፍ ሲል ደግሞ በገንዘብም የሚደግፋቸው ሰው አለ። ቀድሞ በአካባቢው ያልነበረ ውበት ጥለው፤ የሰዎችን ቀልብ ገዝተዋል።
በዚህም ብቻ አላበቁም። በአካባቢው ያሉ ጎዳና ተዳዳሪዎችም ሲለምኑ መመልከትን አልፈቀዱም። ይልቁንም እነዚህ ልጆች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ቆሻሻ ለቅመው መጥተው እንዲሸጡላቸው ነገሯቸው። ከዚያም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠርም በተጨማሪ ከረሃብ ታደጓቸው።
ነብዩ ገደፋው ለረጅም ዓመታት ጫት ሲቅም ነበር። በከንቱ ጊዜውን አሳልፏል። እርሱንም ጨምሮ በአብዛኛው ጓደኞቹ ከ5 እስከ 7 ዓመታት በማረሚያ ቤት ቆይቷል። በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ መታሰሩን የሚያስታውሰው ነብዩ ዛሬ ያ ሕይወት አለፈ፤ ነገ ሌላ ቀን ነው ይላል። ከማህበረሰቡ የተገለልንበት ዓመታትም ከዕድሜያችን የተቀነሱ ያክል ይሰመኛል ይላል።
ነብዩ ለዓመታት ጫት ቅሟል፤ በሌላ ሱስ ውስጥም ተዘፍቆ ነበር። በዚያን ወቅት ቤተሰቡ ጋር የተናጋ አኗኗር ነበረው። ዛሬ ግን ታሪኩ ተቀይሮ ታዛዥና ቤተሰባዊ ህይወትን በምክክር ይመራል። አሁን እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን፤ ነፃ ሰዎችም ነን ይላል። በተለይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪ በራሳችን ተነሳሽነት እንድንሠራ አድርጎናል ባይ ነው።
ገዛኸኝ አዳነ፤ የማህበሩ አባል ነው። ከማረሚያ ቤት ጋርም ይተዋወቃል። ለአንድ ዓመት ሜታል ፋብራሽን እውቀት አምባ ተምሯል። ግን ሱስ ተጫጭኖት፤ ኑሮም ከብዶት ትምህርቱን አቋረጠ። አሁን ሙሉ ለሙሉ ከሱስ ባይወጣም ሥራ ላይ በሆነ ጊዜ ግን ምንም ትዝ አይለውም። እናም እርሱም እንደ ጓደኞቹ በሥራ ተጠምዶ ስለ ነገ አማትሮ ይመለከታል።
የትሩፋቱ ተቋዳሽ
ተማሪዎች ከተማሪ ቤት ሲመለሱ በስፍራው መጥተው እንዲዝናኑ ይፈልጋሉ። ነዋሪችም ከዚህ ስፍራ እየመጡ ንጹህ አየር እንዲቀበሉ ይመክራሉ። ለዚህም አንዳችም ክፍያ አይፈልጉም። ዋናው ነገር ሰው አዕምሮዊ ሠላም ካገኘ ብዙ ነገር ሠርቶ፤ ታሪክ ይለውጣል ብለው ያስባሉ። ይህንንም ራሳቸው ተምረው እየተመለከቱ ስለሆነ ምስክር መቁጠር አስፈላጊ አይደለም። ቆሻሻ ወደ ጥቅም ቀይረው አካባቢውን ውብ አድርገዋል፤መጥፎ ሽታ አስወግደዋል፤የራሳቸውን መጥፎ ስም እያደሱ፤ማህበረሰቡንም እየካሱ ነው።
የገቢ ምንጭ
የቆሸሸውን ስፍራ አፅድተው ሻይ እና ቡና ጀምረዋል። ይህን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ።ከዚህ በዘለለ ቆሻሻ እየገዙ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋሉ። ለአብነት አንድ ኪሎ የውሃ መያዣ ጠርሙስ በአራት ብር ገዝተው መርካቶ በስድስት ብር ይሸጣሉ። ፌስታሎችን ኪሎ በ20 ብር ገዝተው መልሰው ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ፋብሪካዎች አትርፈው ይሸጣሉ።
የተሰባበሩ ብረታ ብረቶችን ወደ ጥቅም የሚቀየርበት ሥፍራ ይደፋሉ። ከህንፃ ግንባታ ስፍራ የሚወጣ አፈር ገዝተው አፈር ለሚፈለግ ሌላ አካል ይሸጣሉ። እንዲሁም በአፈሩ ላይ አበባ ይተክሉበታል፤ ጉድጓድም ይደፍኑበታል። ከህንፃ ግንባታ የተረፉ እና የተሰባበሩ ተረፈ ምርቶችን የራሳቸውን ግቢ እየተጠቀሙበት ከወጪ ይድናሉ። እንዲህ እያሉም የቁጠባ ባህል ተላምደዋል። አንድ ቀን ብንታመም አሊያም ደግሞ ማህበራዊ ሕይወታችን ላይ ችግር ቢገጥመን 30ሺ ብር እንዳለን እወቁ ይላሉ።
ፍልስፍና
ወደዚህ ስፍራ ለመግባት የውጭው በር ዝቅ ማለት ግድ ነው። በሩ በውሃ ጠርሙሶች የተሰራ ሲሆን እጅግ ለመሬት የቀረበ ነው። ‹‹ሰዎች ቆሻሻ ብለው ይሳደባሉ። እኛ ግን ጥቅሙን ስናይ ክብር ይገባዋል ብለን እናምናለን። ስለዚህ ሰዎች ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከዚህ በር ላይ ዝቅ ብለው መግባታቸው ቆሻሻ የሚናቅ ብቻ ሳይሆን የሚከበር ስለመሆኑ አስበን ነው›› ይላሉ።
በፕላስቲኮቹ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች ተሰርተዋል።የፕላስቲክ ቆሻሻ የውሃ ቱቦ መዝጋቱ፤ ለረጅም ጊዜ ያለመበስበሱ ያናድዳቸዋል። እናም ይህንን ነገር በቁጭት ብቻ ሳይሆን በአቅማቸው ወደ ጥቅም ተቀይሮ ንጹህ አካባቢ መፍጠሩ ‹‹ቆሻሻ ቆሻሻ አይደለም›› ለማለት ደፍረዋል።
አሁን የጀበና እያሉ መቃም ሳይሆን፤ የጀበና ቡና እያፈሉ ገንዘብ መስራት ነው ዓላማቸው። ቃጢራ እየቃሙ በአንድ ቦታ መቀመጥ ሳይሆን፤ ብር ለማግኘት በቀጠሮ የሚኳትኑበት ወቅት ነው። ችግርን በሙሉ አይተዋል። ከአሁን በኋላ ምን ቀረን ሲሉም እራሳቸውን ጠይቀዋል።አልሚ ልማታዊ ማህበር ብለው ለራሳቸው ስያሜ ሰጥተዋል።
ዛሬ እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሰው ያግዛሉ። በሙዳይ ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ወላጅ አልባ የሆኑ 10 ልጆች ያግዛሉ። በየወሩ አምስት ሺህ ብር ገቢ ያደርጋሉ በልጆቹ ስም። ሲመቻቸው ሄደው ልጆቹን አዝናንተው፤ ፎቶ ተነስተው ተጨዋውተው ይመጣሉ። ሁሉንም ነገር ስላዩት ወደ ኋላ ተመልሰው የሰው እጅ ማየት ሳይሆን የሌሎችን ሕይወት ለመቀየር ይተጋሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በ ክፍለዮሐንስ አንበርብር