
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ 54 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት እንክብካቤና የማገገም ሥራ እንደሚፈልግ ተገለጸ፡፡ 11 ሚሊዮን ሄክታሩ ቶሎ ካልታከመ ወደ በረሃማነት ሊቀየር እንደሚችልም ጥናቱ አመልክቷል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ የኢትዮጵያ ግማሽ ያህሉ የቆዳ ስፋት ያለው መሬት መልሶ እንዲያገግም ዛፍን ማዕከል ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚፈልግ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶክተር አደፍርስ ገለጻ፤ ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነ የአፍሪካ ቢሮ በኢትዮጵያ “ዎርልድ ሪሶሰርስ ኢንስቲትዩት” (WRI) የሚባል ትልቅ የምርምር ተቋም ቀደም ሲል የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከሚባለው መስሪያ ቤት ጋር ባጠናው ጥናት፤ ወደ 54 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት መታከም ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ዛፍን መሠረት ያደረገ የተጎዳ መሬትን መልሶ የማገገም ሥራ ላይ ትኩረት መስጠት አዋጭ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በዛፍና አረንጓዴ ልማት ማገገም የሚፈልገው መሬት የአገሪቷን የቆዳ ሽፋን ግማሽ ያህሉን እንደሚሸፍን የጠቀሱት ዶክተር አደፍርስ፤ ከዚህ ውስጥም 11 ሚሊዮኑ ቶሎ ካልታከመ ወደ በረሃማነት ሊቀየር እንደሚችል ጥናቱን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል፡፡ 18 ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ በመካከለኛ (ከ10 እስከ 15 ዓመታት ባለው ጊዜ) ውስጥ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች የማይሰራለት ከሆነ ወደ በረሃማነት ሊቀየር እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ሀብትና ቴክኖሎጂ የሌላት አገር እንደመሆኗ ዛፍን መሠረት ያደረገ የመሬት እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የአፈር መከላት ጎርፍና ድርቅ በተደጋጋሚ በመከሰታቸው ብዙ የተጎዱ መሬቶች አሉ፤ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባትም የአረንጓዴ ልማትን በሰፊው ለማከናወን እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡ ያልተፈቱ ተግዳሮቶችን በመያዝና በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተሞክሮ መሬቶችን የማከሙ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ለሥራው መሳካት በተለይ በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የማህበረሰቡ ምላሽ፤ የመንግስት ተቋማት ሥራውን የያዙበትና የመሩበት አግባብ ጥሩ ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አተገባበር ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የሚያስችል ተሞክሮና ልምድ ስላገኘን ፤ ይህንን ሥራ አጠንክረነው ነው መቀጠል ያለብን፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጋዴ አሻራ መርሀ ግብር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባስቀመጡት አቅጣጫ ነው ወደ ሥራ የተገባው” ብለዋል፡፡
ችግኝ ተክለን ሰፊ የደን መሬት ከመፍጠር ባለፈ ሥራው የባህላችን አካል እንዲሆን፤ ከአፈር መሸርሽር ጋር ተያይዞ ወንዞች ንጹህ ሆነው መፍሰስ እንዲችሉ የሚረዳ ማህበረሰብ መፍጠር፣ የተተከሉ ችግኞች አዘንብለው ሲያገኝ መልሶ የሚያቃና አረም ሲይዛቸው የሚኮተኩትና የሚያሳድግ ማህበረሰብ እንዲሆን፤ በተለይ ወጣቱ ማህበረሰብ አገሩን የሚወድና ለአገሩ ዘላቂ ልማት የሚቆረቆር ዜጋ ለመሆን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጭምር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር አደፍርስ አስታውቀዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም