
አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ችግር ለመፍታትና አገልግሎቱን ለማዘመን 26 ቢሊዮን ብር ተበጅቶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በኤሌክትሪክ አገልግሎት የታየውን የመቆራረጥ ችግርና በአገልግሎት አሰጣጡ የሚነሱ የተለያዩ የማህበረሰብ ቅሬታዎችን ለመፍታት 26 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የተሳለጠ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማደረግ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት፣ የማደስ፣ ተቋማዊ አቅምን የማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የመቆራረጥ ችግር እየተከሰተ ያለው በዝርጋታ ችግር፣ በመሰረተ ልማት ጉድለት እና በኤሌክትሪክ ግብአቶች ላይ በሚደርስ ስርቆትና ዝርፊያ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ሽፈራው፤ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ከቀን ወደ ቀን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተጠቃሚ ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በሚፈለገው ልክ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ የማዘመን ስራም እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በሀገሪቱ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ በአምስት ከተሞች አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ስራ ተሰርቷል፤ ተጠናክሮም የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡
ኢንጂነር ሽፈራው አክለውም፤ ከማህበረሰቡ በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥና ከቢል ንባብ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች ዲጂታል ቴክኖሎጂም ተቀብሎ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ከቢል ንባብ ጋር አያይዘው የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት 45 ሺህ ስማርት ሜትሮች ለኢንዱስትሪዎች እየተዘረጉላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ስማርት ሜትሮችም መዘርጋታቸው ኢንዱስትሪዎች ከርቀት ሆነው ቅሬታዎችን በቀጥታ ወደ ማዕከሉ በመላክ ምላሽ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በኤሌክትሪክ መስመሮች፣ በትራንስፎርመሮችና በመሰረተ ልማቶች ላይ ብልሽት በሚደርስባቸው ጊዜ በዲጅታል ሪሞት በመታገዝ በትክክል ጥገና እየተደረገላቸው መሆኑንና አለመሆኑን በቀጥታ ለመከታተል የሚያስችል ቴክኖሎጂ የማበልፀግና የመተግበር ስራ በፕሮጀክት ተይዞ እየተሰራበት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚሰጡ መሰረተ ልማቶችና በተለያዩ ግብአቶች ላይ የሚደረገውን ውድመት፣ ስርቆትና ዝርፊያ ህብረተሰቡ ሊከላከል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም